
አዲስ አበባ፡- ጽንፈኝነትን በየትኛውም መልክ፣ ቅርጽና መጠን ሁሉም እኩል መጠየፍ ይገባዋል ሲሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ጽንፈኝነትን በየትኛውም መልክ፣ ቅርጽና መጠን ሁሉም እኩል መጠየፍ ይገባል።
‹‹በሃይማኖትም፣ በፖለቲካም፣ በየትኛውም ቁመና የጽንፈኝነት ቅዱስ የለውም፤ ይህንን በአጽንኦት ማመን መቻል አለብን። በኔ ስም እንዲህ እንድታደርግ አልፈቅድልህም ብሎ መጀመሪያ ማውገዝ ያለበት የሃይማኖት ተቋማት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ናቸው›› ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት የምርምር ተቋማት መሆን መቻል አለባቸው። የምንሰማው እንደምናስተውለውና እንደምንኖረው ሁሉም ሃይማኖቶች ሠላምን፣ በጎነትን፣ ቻይነትንና ትህትናን የሚያስተምሩ ናቸው። ሁከትና ብጥብጥን የሚያበረታታን ትውልድ የሃይማኖት አባቶች በስማችን አትነግዱ ብለው ማውገዝ አለባቸው። በሃይማኖት ተቋማት ስም የሚሠራ ወንጀል ካለ የእምነት አባቶች አልፈቅድልህም ማለት አለባቸው። ከሠላም እንጂ ከጠብ የሚያተርፍ ማንም የለም። ለመጾም፣ ለመስገድ፣ ለማምለክ ሠላም ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ እንደ አገር በእስልምናም በክርስትና ሃይማኖትም በበጎ የምትነሳ አገር ናት። በጎ ታሪካችንን በጥላቻ እያጠፋነው ነው። ይሄ መቆም አለበት። ሲሉም መክረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲ የተመሠረተው ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር እንጂ ጥላቻ በመዝራት ግጭትን በመጥመቅ አሁን ካለንበት አስከፊ ሁኔታ ወደ ባሰ ሁኔታ ለማስገባት አይደለም ያሉት አቶ ክርስቲያን ግጭትን ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ማዋልን ሊያቆሙ ይገባል ብለዋል።
ዛሬ በግጭት ስልጣን ብንይዝ ነገ በግጭት እንወርዳለን ያሉት አቶ ክርስቲያን፤ ፖለቲካችን ሥር መሠረት እንዲይዝ፤ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህልና ምህዳር እንዲሁም የዴሞክራሲ ተግባራት እንዲኖሩ ሠላም ያስፈልገናል ሲሉ ገልጸዋል። ለዚህም የሕግ የበላይነት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። በተለይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የማይወዱትና እንዲቀየር የሚፈልጉት ሕግ እንኳን ቢሆን የማክበር ግዴታ አለባቸው ብለዋል። ነገ መንግሥት ሲሆኑ የሚያወጡት ሕግ ሊከበርላቸው በሚፈልጉት ልክ አሁን ላይ ያለውን ሕግ ጭምር የማክበር ግዴታ አለባቸው ሲሉም ገልጸዋል።
እንደ አቶ ክርስቲያን ገለጻ፤ ለዴሞክራሲ እታገላለሁ የሚሉ፤ የዴሞክራሲ ኃይል ነን ብለው ራሳቸውን የሰየሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግጭትን ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈጸሚያ ማዋልን ማቆም መቻል አለባቸው። ጨቋኝ ነው ብለው የፈረጁት አካል ሕግ እንዲያከብርም ምሳሌ መሆን መቻል አለባቸው። ሕግን እየጣሱ መንግሥት ሕግ እንዲያከብር መጠየቅ ግን ግብዝነት ይሆናል ሲሉም አመልክተዋል።
አቶ ክርስቲያን እንዳሉት፤ የጥላቻ አበጋዞች ፖለቲካን፣ ብሔርን፣ ሃይማኖትን እንደ ምሽግ እንዳይጠቀሙ መዝጋት ያስፈልጋል። እነዚህ ባዶ ሜዳ ላይ መጋለጥ መቻል አለባቸው። ይህ ሲሆን የጸጥታና የፍትሕ አካላትም ርምጃ ለመውሰድ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል። ማኅበረሰቡ እነዚህን የጥላቻ አበጋዞችን ተው ብሎ መምከር፣ ለሕግና ለፍትሕ ማቅረብ መቻል አለበት።
አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ዐውድ ከበፊቱ የተለየ በመሆኑ፤ ሕዝቡም ሆነ የመንግሥትን ኃላፊነት የወሰዱ ሰዎች ይህንን ማወቅ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል። ዛሬ ላይ “እስኪ እንየው” ተብለው የሚታለፉ ጉዳዮች የከፋ መከፋፈል እንዳያመጡ መጠንቀቅ እንደሚያፈልግም ጠቁመዋል። በዚህ ረገድ መንግሥት ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ መቻል እንዳለበትም ጠቅሰዋል።
በተለይ የጸጥታና ፍትሕ አካላትን የሚመሩ አካላት ቁርጥ ያለ ውሳኔ መወሰን መቻል እንዳለባቸውና የኢትዮጵያ አንድነትና የሕዝብ ደህንነት ቀይ መስመር መሆናቸውን በሚገባ ማመን እንደሚገባ አመላክተዋል። ሕጎች የሚወጡት ለመተግበር ስለሆነ የሕግ መተላለፍ ካለ መንግሥት የማስተግበር ግዴታ አለበት፤ ዜጎች ደግሞ በመንግሥት የሚወሰዱ ጸጥታን የማስከበርና ሠላምን የማስጠበቅ ርምጃዎች የማግኘት መብት እንዳላቸው ጠቁመዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም