
አዲስ አበባ፡- በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመመገብ የደረሱ ጎመን፣ ድንች፣ ሽንኩርት፣ ቆስጣ፣ካሮት ቀይስር፣ፎሶሊያና ሌሎች የጓሮ አትክልቶች በመስመር ተሰድረዋል።ቅጥር ግቢ ውስጥ በመስመር በመስመር ተተክለው የሚታዩት የጓሮ አትክልቶች አካባቢውን መናፈሻ አስመስለውታል። እነዚህ አትክልቶችና እንደ ቡና፣አቮካዶ፣ኮክ ያሉ ፍራፍሬዎች የግቢውን ውበት ማራኪና ሳቢ አድርገውታል ። በግቢው ውስጥ ትርፍ የሚባል ቦታ የለም።ግድግዳዎች እንኳ በሀይላንድ ዕቃ በተተከሉ የጓሮ አትክልቶች በመስመር ተሰድረውበታል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለምፀሐይ ጳውሎስ እንደገለጹት፤” ምግባችን በጓሯችን” በተሰኘው የጓሮ ግብርና እንቅስቃሴ በጠቅላይ ሚኒስትር ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚለሙ የጓሮ አትክልቶችን በማስጎብኘት እንዴት በአነስተኛ ቦታና ጠባብ ግቢ እንደ ቆስጣ፣ሰላጣና ጎመን ያሉ አትክልቶችን ማልማት እንደሚቻል ልምድ ማካፈል ተችሏል። በጉብኝቱና የልምድ ልውውጡ ላይ የተካፈሉ እናቶችም ይህን ልምድ ወስደው አትክልቶችን በትንሽ ቦታ ተክለውና ተንከባክበው በማሳደግ መጠቀም እንዲችሉ ያግዛል ።
ያለውን ትርፍ ቦታ ሁሉ ለከተማ ግብርና እናውል በሚል የተጀመረው ተግባር በአንድ ወር ከ15 ቀናት ውስጥ ፍሬ አፍርቶ አትክልቶቹ ለምግብ ደርሰዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤አትክልቶቹ ለዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቢሰጡ በሚኖሩበት ስፍራ በትንሽ ቦታ ማልማት መጠቀም እንደሚቻል ተሞክሮ እንዲወስዱ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ለተሳተፉ 55 እናቶችም በግቢው ውስጥ ለምተው የደረሱ አትክልቶችን እንዲጋሩ መደረጉንም ወይዘሮ አለምጸሐይ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያለንን ተካፍለን እርስ በእርስ ተሳስበን እንኑር ያሉትን ጥሪ ተከትሎ ጽሕፈት ቤቱ በግቢው ውስጥ ያለማቸውን የተለያዩ አትክልቶች ለእናቶች ማጋራቱንና ችግኞችን መስጠቱንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።
ወይዘሮ መቅደስ በቀለ ከወረዳ 10 ጨርቆስ አካባቢ ነዋሪ ናቸው።በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ያዩት አትክልቶችና ፍራፍሬዎች በግቢው ውስጥ እንዲህ ማልማት ይቻላል እንዴ ያሚያስብሉ ናቸው ይላሉ።
ቅጥር ግቢው ውስጥ ትርፍ የሚባል ቦታ የለም።ግድግዳዎችና ግቢው ውስጥ የሚገኙ ባዶ ቦታዎች በአትክልቶችና በፍራፍሬዎች ለምተዋል የሚሉት ወይዘሮ መቅደስ፤ እኛም ከዚህ ትምህርት ወስደን በየግቢያችን እንተክላለን።እኔ የምኖርበት ብዙም ትርፍ ቦታ ስለሌለ በግድግዳዎች ላይ ሀይላንድ ዕቃ አትክልቶችን በመትከል ቢያንስ የአትክልት ፍጆታችንን ለመሸፈን እንሠራለን ብላለች።
የደረሱ አትክልቶችን ማካፈላችን ፍቅርን ማካፈል ነው ያሉት ወይዘሮ አለምጸሐይ፤ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በመኖሪያ አካባቢው አትክልቶችን እያለማ የምግብ ፍጆታውን መሸፈን እንዲችል ለማበረታታትና ልምድ ለማካፈል ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም