
ሰላም መቼም ቢሆን ከምንም በላይ አስፈላጊና ወሳኝ ጉዳይ ነው። ያለ ሰላም ምንም መሆን አይቻልም። ዕቅድ የሚታቀደው ፣ ምኞትና ተስፋ ማለም የሚቻለው ሰላም ሲኖር ብቻ ነው ። በጥቅሉ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚቻለው ሀገር ሰላም ሲሆን ነው። ስለዚህ የሰላም ጉዳይ ጊዜ የሚሰጠው ሳይሆን፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን አለበት።
መንግሥት በሀገር ላይ ሰላምን የማስከበር ፣የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነትም ግዴታም አለበት። ይሄንን ኃላፊነቱን በሚገባ ሊወጣ ይገባል። እስካሁን ባለው ሁኔታ በሀገራችን በተለያዩ ምክንያቶች የሰላም መደፍረስ ታይቷል። ብዙዎች ከውስጥም ከውጭም ተቀናጅተው የሀገርን ሰላም ለማናጋት ተንቀሳቅሰዋል። አንዴ በብሄር ፣ሌላ ጊዜ በሃይማኖት ለእያንዳንዱ ግጭት ስም በመስጠት የህዝብን ሰላም የሚያደፈርሱ ችግሮችን አስተናግደናል። ሀገር ተረጋግቶ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ ብዙ መሰናክሎች ተደቅነው አልፈዋል። በሂደቱም የዜጎች ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፤ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ይሄ አሳዛኝ ክስተት አሁንም ቀጥሏል። መንግሥትም አንዴ ጠንከር ሌላ ጊዜ ለስለስ በማለት ችግሮችን በሰከነና በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት ሞክሯል። መሰናክሎችን በትዕግስት በማለፍ ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ደርሷል።
ይሁን እንጂ የጸብ ደጋሾች ድግስ አሁንም አልተገታም። በጠላቶች ሴራና በውስጥ ባንዳዎች ተባባሪነት ኢትዮጵያን የማተራመስ እንቅስቃሴው ቀጥሏል። ሰሞኑንም አንዱን ሃይማኖት በሌላው ላይ ለማነሳሳት የሚደረገውን ሴራ ህዝብ በሚገባ ሊያውቀው ይገባል። ሃይማኖቴ ተነካ ፣ መስጊድ ወይም ቤተክርስቲያናት ሊያፈርሱ ነው ከሚለው የቅድመ ቃላት ዘመቻ ጀርባ ማን ምን እያደረገ ነው የሚለውንም ጠንቅቆ መረዳት ይገባል። ህዝብን ለእልቂት የሚዳርግ የሴራ ጥንስስ ነው ብሎ ቆም ብሎ ማሰብ ይገባል። እያንዳንዱ ድምጽ ባሰማ ቁጥር አብሮ ‹‹ሆ›› ብሎ የሆያሆዬው አካል ከመሆን ይልቅ ረጋ ብሎ ማሰብ ይገባል። ሰላም የሚገኘው በሆታ ሳይሆን ከመንግሥትና ከህዝብ ጋር በመነጋገርና በመወያየት የሆያሆዬውን ምንነት ለመረዳት በመሞከርና ለሆታው ተገዢ ባለመሆን ብቻ ነው።
ዛሬ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሀገር ለማፍረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አይኖርም። በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች እየፎከሩና አንድነታችንን በመሸርሸር ሀገርን ለማተራመስ እንደሚሰሩ ሲገልጹም ተደምጠዋል። ታሪካዊ ጠላቶቻችን እርስ በእርስ ስንታመስ መግቢያ በር እንደሚያገኙ ያስባሉ። የታሰበው ልማት ሁሉ አፈር ከድሜ እንደሚገባ ያውቃሉ። ከፍተኛ ወጪ ወጥቶባቸው ጉልበትና ጊዜ ፈሶባቸው የተሰሩት ልማቶች ሁሉ እንደሚፈርሱ ያውቃሉ። በዚህ መካከል ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማሰብ በሁሉም የእምነት ተቋማት መካከል ቅጥረኞችን በማደራጀት፣ ህዝብ ከህዝብ ፣ ህዝብን ከመንግሥት ጋር ለማጋጨት አበክረው ይሰራሉ።
አሁን እያየን ያለው የሃይማኖት ግጭት የሚመስል የሰላም መደፍረስ የዚሁ ዕቅድ አንዱ አካል ስለመሆኑ እማኝ ማቅረብ አይጠይቅም። በእስካሁኑ ሂደቶች የተረጋገጡት እውነታዎች ለዚህ እማኝ ናቸው። ህዝቡም ይሄንን በሚገባ ማወቅ አለበት። የዚህ ሴራ ሰለባ ላለመሆን ደግሞ ከሆታ ይልቅ በሰከነ መንፈስና በእርጋታ ነገሮችን አጢኖ ራሱን ከችግር ተባባሪነት ማውጣት አለበት። ለጥፋት ሳይሆን ለሰላም መሰለፍ ይገባል።
ሕዝብ ይሄን ከተወጣ፣ መንግሥትም ሀገርን እና ህዝብን በሚያተራምሱና ሰላም በሚነሱ አካላትና ተላላኪዎች ላይ ጠንከር ያለና የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ ይገባል። እስካሁን ብዙ ነገሮች በሆደ ሰፊነትና በትዕግስት ታልፏል። ሆኖም ትዕግስቱን በልኩ የሚገነዘብ ባለመኖሩ ችግሩ ሲብስ እንጂ ሲሻሻል አልታየም። በመሆኑም ትዕግስት ፍራቻ መስሎ ለሚሰማቸው አካላት ትዕግስትም ልክአለው መባል አለባቸው። መላው ህዝብም አሁን በሀገራችን እያየንና እየሰማናቸውና እያየናቸው ያሉትን የሰላም መደፍረሶች የታሪካዊ ጠላቶቻችን እቅድ መሆናቸውን በሚገባ በመገንዘብ ወደግባቸው ለመሄድ የሚያደርጉትን ጉዞ ከወዲሁ መግታት ይገባል።
ኢትዮጵያ የአንድ ብሄር ወይም የአንድ ሃይማኖት ሀገር አይደለችም። የሃይማኖትና የብሄር ብዝሀነት የምታስተናግድ አንዱ ከሌላው ወገኑ ጋር ልዩነቱን አምኖ፣ ተከባብሮና ተፋቅሮ የሚኖርባት ሀገር ናት። አንዱ ላንዱ ስጋት ሳይሆን ስጋው ሆኖ የኖረበትና አሁንም የሚኖርበት ሀገር ናት። አሁንም ማስቀጠል ያለብን ይሄንኑ አንድነታችንን ነው። ወደፊትም ማስቀጠል ያለብን በብዝሀነትና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ወንድማማችነትን ነው። ሀገር እንደሀገር እንድትቀጥል በቅድሚያ ከጠላቶቻችን ወጥመድ መውጣት መቻል አለብን። ከዚህ ወጥመድ መውጣት የምንችለው ደግሞ የሀገራችንን ሰላም ማክበርና ማስከበር ስንችል ነው ። መንግሥትም ትዕግስትም ልክ አለው ብሎ ሰላምን ለማስከበር በአጥፊዎቹ ላይ ያልተቆጠበ ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ሲችል ነው። የሚፈለገው ሁሉን አቀፍ ብልጽግናን ለማረጋገጥም ቢሆን ሰላምን ማስከበር የግድነውና ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ሥራው ጊዜ ሊሰጠው አይገባም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 /2014