
አዲስ አበባ:- የኢትዮጵያ አንድነትና የሕዝብ ሰላም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ክርስቲያንም ሙስሊምም የሃይማኖት አባቶች እና ሰላም ሚኒስቴር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የታሪክ ተመራማሪና ጸሐፊ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ገለጹ፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር አደም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የሕዝብ አንድነትና የኢትዮጵያ ሰላም አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ክርስቲያንም ሙስሊምም የሃይማኖት መሪዎች እና ሰላም ሚኒስቴር ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡
የሕዝብ አንድነትና የአገር ሰላም እንዲጠበቅ የአገር መከላከያ ሠራዊትን ማጠናከር ይገባል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አደም፤ የሃይማኖት መሪዎችና ሰላም ሚኒስቴር የተሰጣቸውን ሰላምና የሕዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ካልቻሉ የአገር ደህንነት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባትም ያስቸግራል ብለዋል፡፡
ቀሳውስትም ሆኑ ሼኮች ከቤተ ክህነትና ከመስኪድ ወጥተው ወደ ሕዝቡ በመግባት የሕዝብ አንድነትን ማስተማር አለባቸው፡፡ አደጋውን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኅብረትና አንድነት እንዲኖር በቀዳሚነት በመታገል እና በማስተማር ኃላፊነታቸውን መወጣትም ይገባቸዋል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ኢስላምና ክርስቲያን ተቻችለው የኖሩባት አገር ናት፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች የሚሰብኩት ሰላምን እንደመሆኑ ክርስቲያኑም ሙስሊሙም ከእምነታቸው አንጻር ካስተማሩ ፈጣሪን የሚፈራ፣ ሕዝብን የሚያከብር ትውልድ ይፈጠራል፡፡
ባለፉት 30 ዓመታት እምነት አልባ እና አገር አልባ ትውልድ እንዲፈጠር መሠራቱን በማስታወስም፤ ትውልዱ አገሩን የሚወድ ፈጣሪውንም የሚፈራ አድርጎ የመቅረጽ የቤት ሥራ አለብን። ሥራ ፈጠራ ላይ ትኩረት ተደርጎ ካልተሰራ ኑሮ ውድነቱ ተባብሶ ይቀጥላል ሰላም፣ መረጋጋትና አንድነት ከተፈጠረ ኢትዮጵያን በፍጥነት ማሳደግ ይቻላል ብለዋል።
‹‹ሰላም ሚኒስቴር›› ስያሜው በጣም ቆንጆ ቢሆንም በተግባር ግን የሚጠበቅበትን ሚና ሊወጣ ይገባል።
በቅንነት ኢትዮጵያዊነት የሌለው ሰው በመንግሥት መዋቅርም ሆኖ ደባ ሊፈጽም ይችላል አሁን የሚታዩ አዝማሚያዎችን በጥንቃቄ መመልከት ያስፈልጋል። ሁሉም ለኢትዮጵያ በመታገል አብሮ ካልቆመ ሰላም ለማስፈን ያስቸግራል። በርካታ የቤት ሥራ ይቀረናል ሲሉም መክረዋል።
የዲፕሎማሲ ሥራ ላይ ለውጥ መምጣት አለበት። አረብኛ ቋንቋ የሚናገሩ አምባሳደሮች በመካከለኛው ምስራቅ ተመድበው ሁኔታውን መከታተል አለባቸው። የኢትዮጵያ እስልምና ጉባኤ በተጠናከረ መልኩ ተቋቁሞ ኢትዮጵያ በዓለም ሙስሊም ኅብረተሰብ ውስጥ ያላትን ከበሬታ ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወን ይጠበቅበታል።
ከሚታዩ ግጭቶች በስተጀርባ ማን ሊኖር ይችላል የሚለው ባግባቡ ሊጠና ይገባዋል። በዚህ ጉዳይ የታሪካዊ ጠላቶቻችን ሚና ምን እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል። ኢትዮጵያ የካርታ አቀማመጧን ብንመለከት ለመካከለኛው ምስራቅ ቅርበት ያላት ሆና እናገኛታለን ብለዋል።
ግብጾች ኢትዮጵያን ልክ እንደ ሶሪያና የመን ለማድረግ ቢሞክሩም ይከሽፍባቸዋል። አንድ ፋይል ሲዘጋባቸው ሌላ ፋይል ይከፍታሉ። ይህች አገር በሰላም እንድትኖር አይፈልጉም። በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ላይ የተቃጣው ጥቃት ዝም ብሎ የተፈጠረ ሳይሆን የእነርሱ እጅ ነበረበት።
ግብጾች በዓረብኛ የሚተላለፉ አራት ሺህ ሚዲያ አላቸው። 80 ሺ ምሑራኖች በዓለም አቀፍ ተሰራጭተው ይገኛሉ። የዓባይ ጉዳይ ለእነርሱ ትልቅ ቦታ አለው፤ አንድ ግብጻዊ ከሕጻንነቱ ጀምሮ ያለዓባይ ሕይወት እንደሌለው፣ ከሰማይ የተሰጠ ትሩፋት እንደሆነ ያስተምሩታል በዓባይ የመጣ በሕይወታቸው እንደመጣም ይቆጥራሉ ነው ያሉት።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 ቀን 2014 ዓ.ም