ባለፉት አራት የለውጥ ዓመታት ሴቶች ከቀደሙት ስርዓቶች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ቦታ ላይ መቀመጥ ችለዋል። በ2011 ዓ.ም 20 አባላት ባሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚኒስትሮች ካቢኔ 10ሩን ሴት ሚኒስትሮች በማድረግ የጾታ ስብጥሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማመጣጠን ተችሎ የነበረ መሆኑ ሴቶች አሁን የደረሱበትን ደረጃ ያመለክታል። ቀስ በቀስ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው እየጨመረ፤ አቅማቸውም እየጎለበተ መምጣት ችሏል። በየተሰማሩበትም መስክ አያሌ ስኬቶችን ለማስመዝገብ በቅተዋል።
የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚናገሩት ሴቶችን ለስኬት ከሚያበቁት ዋንኛው በራሱ ለስኬት ሊበቁ የሚችሉበትን መስክ ማግኘት መቻላቸው ነው። ሌላው ሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነፃፀሩ ከወንዶች ይልቅ ጠንቃቃ መሆናቸው ነው። እንደ ስነ ልቦና ባለሙያዎቹ ምክረ-ሀሳብ በርግጥ ሴቶች በባህርያቸው ከወንዶች በተሻለ ጠንቃቃ ናቸው። ከነገሮች ጋርም ቢሆን ቶሎ የመላመድ ችሎታ አላቸው። አዳዲስ ነገሮችን ለማወቅና ለማግኘት ጉጉና ራሳቸውን በፍጥነት የሚያዘጋጁም መሆናቸውን የስነ ልቦና ባለሙያዎቹ ይናገሩላቸዋል። አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመቋቋም ተፎካካሪ መሆንን ይችሉበታልም ይሏቸዋል።
በአብዛኛው ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ፈጥነው ስኬት መጨበጥ የሚችሉት በነዚህ ዓይነቶቹ ወሳኝ ነጥቦች መሆኑንም የስነ ልቦና ባለሙያዎቹ ይመሰክሩላቸዋል። ዘመናዊና በቂ ዕውቀት ከተካበተ ልምድ ጋር መቅሰም ሴቶችን ፈጥኖ ለስኬት የሚያበቃ ተደማሪ ምስጢር መሆኑንም ባለሙያዎቹ ይጠቁማሉ። በዘንድሮ ዓመት መጀመርያዎቹ ወራቶች አካባቢ 100 የአፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶችን ለስኬት ያበቁት እነዚሁ ምስጢሮች አይደሉም ማለት አይቻልም።
መቀመጫውን በአህጉራችን አፍሪካ ያደረገውና አቫንሴ ሚዲያ የተሰኘው ድርጅት በዚሁ በዘንድሮ ዓመት ለእነኝህ ድንቅ ሴቶች ዕውቅና ሊሰጥባቸው ያስቻሉትም በተሰማሩበት ልዩ ልዩ የሥራ መስኮች ስኬትን ማጎናፀፍ ያስቻሉ የስኬት ምስጢሮች ናቸው። አቫንሴ ሚዲያ በተሰማሩበት ልዩ ልዩ የሥራ መስኮች ስኬትን መጎናጸፍ ለቻሉ አፍሪካዊያን ሴቶች በየዓመቱ ዕውቅና ይሰጣል፡፡ የሚሰጠውም በእነዚህ መስፈርቶች በማወዳደርም ነው። ሚዲያው ላለፉት ሶስት ተከታታይ ዓመታትም ዕውቅና የመስጠት ተግባሩን ሲያከናውን የቆየው በዚህ መልኩ ነው። አቫንሴ ሚዲያ እንደ አውሮውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ2021 በተመሳሳይ በተለይ የአመራርና አፈጻጸም ክህሎትን፣ በግል ያስመዘገቡት ስኬትና ዕውቀትን የማጋራት ቁርጠኝነት የተላበሱ፤ እንዲሁም የተለመደና ምቹ ያልሆነ አሰራር ስርዓት በመቀየር ረገድ ተቋማዊ ለውጥ ያመጡ በሚል ያስቀመጣቸውን እነዚህን ስድስት ብቃት አጎናፃፊ ምስጢሮች የተላበሱ ዝርዝር መስፈርቶች አሟልተው የተገኙበትና ከመላው አፍሪካ አገራት በእጩነት የቀረቡበት ምርጫ አካሂዶ ነበር።
ድርጅቱ በዚህም መሰረት ስኬታማና ውጤታማ የሆኑ 100 ተጽዕኖ ፈጣሪ አፍሪካዊ እንስቶችን በመለየት ስም ዝርዝራቸውን 100women.avancemedia.org በተሰኘ ይፋዊ ድረ-ገጹ አስታውቋል፡፡ አቫንሴ ሚዲያ ዘንድሮ ባካሄደው የምርጫ ሂደት አገራችንን ወክለው በእጩነት ከቀረቡት እንስት ኢትዮጵያውያን መካከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ርዕሰ-ብሔር ሳህለወቅር ዘውዴ፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ እንዲሁም የሶልሪቤል ጫማ ፋብሪካ መስራችና ስራ አስስኪያጅ ወይዘሮ ቤተልሔም ጥላሁን በዝርዝሩ ውስጥ ስማቸው መካተቱን ይፋ ያደረገበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህም አገራችንን በጎ ገጽታ እንድትላበስ የበኩሉን እገዛ አድርጓል፡፡ ከበጎ ገጽታው ባሻገርም ሌሎች የአገራችን ሴቶችን ለስኬት በማነሳሳትና በማብቃት አርአያ እንደሚሆንም አያጠያይቅም፡፡
ይሄን ካልን ዘንዳ በአቫንሴ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ተረጋግጦ ዕውቅናን ማግኘት ከቻሉት ሴቶች መካከል የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው አገርና ሕዝባቸውን እያገለገሉ ሥላሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የተወሰነ ልንነግራችሁ ወደድን፡፡ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ በወርሃ የካቲት 1942 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው የተወለዱት። የመጀመርያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምርታቸውን ያጠናቀቁት በሊሴ ገብረማርያም ትምርት ቤት ሲሆን፤ የፈረንሳዩ ሞንተፔለ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ምሩቅ ናቸው። አማርኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ እና እንግሊዘኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ። ቁጥር በሌላቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች በእነዚህ ቋንቋዎች ንግግር አድርገዋል፡፡ አምባሳደሯ ንግግር አዋቂና ብልህ ሴት በመሆናቸው ንግግር ባደረጉበት መድረክ ሁሉ ረጋ ብሎ አረፍተ ነገሮችን እያስረገጡ ጥዑመ ዜማ በመላበስ ጥርት ብሎ የሚንቆረቆረው ድምፃቸው ሳይሰለቹ እንዲደመጡና ንግግር ባደረጉ ተብለው እንዲናፈቁ ሲያደርጋቸው ቆይቷል፡፡ አሁንም እንደዛው።
አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ለኢትዮጵያ እንደ ውጪ አገር አገልግሎት ሰራተኛ እ.ኤ.አ ከ1989 እስከ 1993 ተቀማጭነታቸውን ሴኔጋል በማድረግ የማሊ፣ የኬፕ ቨርድ፣ የጊኒ ቢሳዎ፣ የጋምቢያና የጊኒ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል። እኤአ ከ1993 እስከ 2002 ደግሞ በጅቡቲ አምባሳደር ሆነው የሰሩ ሲሆን በወቅቱ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ቋሚ ተወካይም ነበሩ። እኤአ ከ2002 እስከ 2006 በፈረንሳይ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል፡፡ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም ተወካይ ሆነው ሰርተዋል። በተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ውስጥ የተቀናጀው የሰላም አስከባሪ ኃይል ተወካይ በመሆን በሴንትራል አፍሪካ (BINUCA) ኃላፊ በመሆንም ያገለገሉበት ዳጎስ ያለ ታሪክ አላቸው።
በአፍሪካ ሕብረት ውስጥና በተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ውስጥም የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ሆነው ማገልገላቸው ይነገራል፡፡ አምባሳደር ሳህለወርቅ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥም የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው ሰርተዋል። እ.ኤ.አ በ2011 የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀኃፊ የነበሩት ባን ኪሙንም በኬኒያ የተባበሩት መንግሥታት ዳይሬክተር ጄነራል አድርገው ሾመዋቸው ያገለገሉበት ሁኔታ መኖሩን ሰነዶች ያወሳሉ። በተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ በአፍሪካ ሕብረት ልዩ ተወካይ እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት የተባበሩት መንግሥታት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሾመዋል። አምባሳደር ሳህለወርቅ ጥቅምት ፩፭ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። በፕሬዚዳንትነት ሚና ለማገልገል የመጀመርያዋ ሴት መሆናቸውንም ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
አምባሳደር ሳህለወርቅ ሁለት የስድስት ዓመት ውል እንደሚያገለግሉ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ አምባሳደር ሳህለወርቅ ብቻ ናቸው ሴት የአገር መሪ። ከሳቸው በፊት ኢትዮጵያ የነበራት አንድ ሌላ ሴት የአገር መሪ ቢኖሩ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ልጅ ንግሥት ዘውዲቱ እንደነበሩ ሰነዶች ይጠቅሳሉ፡፡ ሳህለወርቅ በአቫንሴ ሚዲያ ዕውቅናውን ማግኘት የቻሉት በእነዚሁ አስተዋጾአቸው መሆኑን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት “አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ማን ናቸው?” ሲል በሰራው ዘገባ እንዳመለከተው፤ ፈረንሳይ በሚገኘው ሞንፔሌር ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ አማርኛ፣ ፈረንሳይኛና እንግሊዝኛ ቋንቋን አቀላጥፈው መናገር ይችላሉ፡፡ የበዛውን የሕይወት ጉዞና የሥራና የትምህርት እርምጃዎቻቸውን አጠቃልሎ ሲያቀርብም፤ አምባሳደር ሳህለወርቅ በአምባሳደርነትና በተለያዩ ኃላፊነቶች በታላላቅ አለማቀፋዊ ተቋማት አገልግለዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የኢፌዴሬ ፕሬዚዳንት ሆነው ከመሰየማቸው አስቀድሞ፤ በአፍሪካ ህብረት የተመድ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ልዩ ረዳት እና በአፍሪካ ህብረት የተባበሩት መንግስታት ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ነበር፡፡ ከዛም ቀደም ብለው ከ 1989 እስከ 1993 በሴኔጋል፣ ኬፕቨርዲ፣ ጊኒቢሳው፣ ጋምቢያና ጊኒ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገራቸውንና ሕዝባቸውን አገልግለዋል፡፡
በተመሳሳይ፣ ከ 1993 እስከ 2002 በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የኢጋድ ቋሚ መልዕክተኛ፣ ከ 2002 እስከ 2006 በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር፣ በዩኔስኮ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ እና የቱኒዝያና ሞሮኮ ተጠሪ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ የተባበሩት መንግስታት የተቀናጀ ሰላም ግንባታ ቢሮ ልዩ ተወካይና ኃላፊ ሆነውም ሰርተዋል፡፡
ፕሬዚዳንት፣ ሳህለወርቅ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ እንዲሁም በኢፌዲሪ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ጀነራል ዳይሬክተር በመሆን በከፍተኛ ኃላፊነት ሰርተዋል፡፡ በ2011 በናይሮቢ የተባበሩት መንግስታት ቢሮ ዳይሬክተር ጄኔራል በመሆን በወቅቱ የተመድ ዋና ፀሀፊ ባን ኪ ሙን ተሹመው ያገለገሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፤ በተመድ ከዋናና ምክትል ዋና ፀሀፊነት ቀጥሎ ያለውን ከፍተኛ የአመራር እርከን ያገኙ የመጀመሪያዋ ሰውም ናቸው፡፡
ይህ ከፍ ያለ የትምህርት ዝግጅታቸው እና የሥራ ልምድና ክህሎታቸው ታዲያ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሆነው እስከመሰየም አድርሷቸዋል፡፡ በዚህም ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በመፈጸም ለአገራቸው ሁለንተናው ከፍታና ብልጽግና እርሳቸው የሚጠበቀውን ሁሉ እያበረከቱ ያሉ ሲሆን፤ በተለይ ለሴት ልጆች ከፍታ በልዩ ትኩረት እየሰሩ ይገኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ፕሬዚዳንቷ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ ለአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር ለሴቶች ድምጽ ለመሆን ቃል ገብተው ሥራ የመጀመራቸው ምስጢር ስለመሆኑ ይነገራል፡፡
የፕሬዝዳንቷ መመረጥ ተከትሎም በኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶች ውክልና እየጨመረ መምጣቱን የሚናገሩም ጥቂት አይደሉም፡፡ ለታዳጊና ወጣት ሴቶች በስኬታማ ለሴቶች እንዲሰጥ አቅጣጫ ያስቀመጡበትና ሲተገበር የቆየውም ፕሬዚዳንታዊ ሜንተርሺፕም የዚሁ ሥራቸውና ለሴቶች ከፍ ያለ ቦታ መስጠታቸው ማሳያ ተደርጎም ይነገራል፡፡ ፎርብስ ባወጣው 100 የዓመቱ (2020) ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ሲያካትታቸውም እነዚህንና ሌሎች በርካታ የስኬት ጉዟቸው፤ የውጤት መንገዳቸውን ከግምት በማስገባት ነው፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም