የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፣‹‹የአስተሳሰብ ልዩነት፣ ፉክክርና የሚጋጭ ፍላጎት (Conflicting Interest) ባለባቸው አገራት ውስጥ ችግሮች በአንድ ፓርቲ፣ በአንድ ቡድን ወይንም በጥቂት ሰዎች አይፈቱም። ጥቂቶች በር ዘግተው ቢጨነቁና ቢጠበቡም መፍትሄ ሊሆኑና ሊያመጡም ፈፅሞ አይቻላቸውም። በመሆኑም ልዩነቶችን ለማጥበብም ሆነ ለማስታረቅ፣ ከተናጠል ይልቅ የጋራ ውይይት ባህልና ልምድ የግድ ነው›› ይላሉ።
ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተፈጠሩና ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የመጡ ያልተቋጩ ሃሳቦች፣ በይደር የቆዩ አለመግባባቶች እንዲሁም አገር ትቀጥል ዘንድ ቅድሚያ ተነስቷቸው የቆዩ የማያግባቡ አጀንዳዎች የተሸከመች አገር ናት። አገሪቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት የቆየ ባህል ቢኖራትም እነዚህን ባህሎች በአግባቡ የመጠቀም ልምዱ ቀስ በቀስ እየጠፋ መጥቷል። ይህ ደግሞ ችግሮች በቀላሉ ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙ፣ ውስጥ ውስጡን እንዲብላሉና ከትላንት እስከ ዛሬ እንዲከተላት ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል። ይሑንና ከህልውና ባሻገር ስለ መፅናትና መቀጠል እንዲሁም ስለ ሁለንተናዊ እድገት ሲታሰብ እነዚህን ልዩነቶች አጀንዳዎች መፍትሄ መስጠት የግድ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ከትናንት ሲንከባለሉ የመጡና በአገር ግንባታ ሂደቱ ላይ የራሳቸውን እክል የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በምክክርና ውይይት ለመፍታት ከፍ ያለ ሥራ ጀምራለች። አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሕግ በማቋቋምና ኮሚሽነሮችን በመሰየም ወደ ሥራ ተገብቷል። ዋናውን የምክክር ሂደት ለመጀመር የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትም በመከናወን ላይ ናቸው።
አካታች አገራዊ ምክክሩን በተመለከተም መገናኛ ብዙኃን ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ሚዛናዊና ወቅታዊ መረጃዎችን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ የማይተካ ሚና አላቸው። ሁነትን ከመዘገብ የዘለለ ለውጤታማነቱ ከፍ ያለ ሚና እንዳለባቸው ይታመናል።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኝ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጅን፣ የምክክርን ጽንሰ ሀሳብና አስፈላጊነት በህትመት፣ በቴሌቪዥን፣ በራዲዮና በማህበራዊ ሚዲያ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል። ኮሚሽኑ ከቀናት በፊትም ከመገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎችና ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።
በዚሁ መድረክ ላይም የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ መገናኛ ብዙሃን ሚዲያ እውቀትን፣ እውነትን፣ ፍቅርን፣ ሠላምን፣ እድገትንና መተባበርን በቀላሉ በአፍ መፍቻ ቋንቋው በተዓማኒነት ለህዝብ የሚያደርስ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ትክክለኛውን የውይይት ጽንሰ ሀሳብ፣ የአጀንዳ ቀረጻ አካሄድ፣ የውይይት ሂደትና ትግበራ፣ በየቋንቋዎቻቸው ለሕዝቡ በየወቅቱ ተደራሽ በማድረግ የኮሚሽኑ አጋር እንዲሆኑና ለምክክሩ ስኬታማነት እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
አዲስ ዘመን መገናኛ ብዙኃን ስለ አገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማነት ሚናቸው እንዴት ይቃኛል፣ ከወዲሁ ምን፣ እንዴትና በምን አግባብ መሥራትስ አለባቸው፣ የዲጂታል ሚዲው በምክክሩ ላይ የሚኖረውን ጫና ለመቋቋም ምን ሊደረግ ይገባል፣ የሚሉ ጥያቄ በማንሳት ምሁራንን አነጋግሯል።
አስተያየት ሰጪዎቹም አካታች አገራዊ ምክክር ጥያቄ ውስጥ የማይገባ አስፈላጊ ጉዳይ ስለመሆኑ ይስማሙበታል። ይሑንና ደግሞ ምክክሩ የታሰበው ውጤት እንዲገኝ በቂ ጥንቃቄና ቅድመ ዝግጅት ማድረግና ከወዲሁ መሰራት ያለባቸው የቤት ስራዎች ማከናወን እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሳምሶን መኮንን፣ ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራዊ ምክክር በማድረግ የተሳካላቸው አገራት እንዳሉ ሁሉ ምክክሩ ሳይሳካላቸው የቀሩ አሉ። ለዚህ ደግሞ ሚዲያው እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀስ ነው››ይላሉ።
‹‹በኢትዮጵያ ሊደረግ በታሰበው አገራዊ ምክክር የሚዲያው ሚና ጉልህ ነው›› የሚሉት ዶከተር ሳምሶን፣ በማህበረሰብ ደረጃ የሚደረግ ውይይት በማህበረሰባዊ ስነ-ተግባቦት የሚቃኝ ስለሆነ ሚዲያው ይህን ተግባቦት በማቀላጠፍ ረገድ የሚጫወተው አዎንታዊ ሚና ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊወጣ እንደሚችልም ይጠቁማሉ።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት መምህርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ፍሬዘር እጅጉ፣ መገናኛ ብዙሃን የተሻለ አገር እንዲፈጠር የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፣ ይሕንም በተለያየ አስተዋፅኦቸው ያስመለክታሉ ››ይላሉ።
አካታች አገራዊ ምክክሩ አገራዊ እንደመሆኑ መጠን በተሻለና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲከናወን ሂደቱን ከመዘገብ፣ መረጃ ከመስጠትና የተለያዩ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ መደላድል መፍጠርን ጨምሮ የመሪነት ሚናን እንደሚጫወቱም ያስረዳሉ።
ምሁራኑ፣ በአገራዊ ምክክሩ የመገናኛ ብዙሃን ሚና የጎላ መሆኑን ከማስገንዘብ ባሻገር ምክክሩ የታሰበው ውጤት እንዲገኝ በቂ ጥንቃቄና ቅድመ ዝግጅት ማድረግና ከወዲሁ መሰራት ያለባቸው የቤት ስራዎች ማከናወን እንደሚያስፈልግ አፅእኖት ይሰጡታል።
ለአገራዊ ውይይቱ ሁለንተናዊ ስኬት መገናኛ ብዙሃንና ሙያተኞች ሙያዊ ስነምግባር ላይ ብቻ በማተኮር ይዘታቸውን አገራዊ ጥቅምና ሰላም ላይ ማድረግ እንዳለባቸው የሚያሳስቡት ዶክተር ሳምሶንም፣ ሚዲያው የሁሉንም ፍላጎትና ሃሳቦች ማንሸራሸር እንዳለበትም አጽእኖት ይሰጡታል።
ሚዲያውና ሙያተኛው ሙያዊ ስነ ምግባርን ማዕከል በማድረግ የአገራዊ ምክክር ሂደቶችን የሚተች፣ መንገድ የሚያሳይ፣ የታፈኑ ሃሳቦች እንዲወጡ የሚያደርግ፣ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀት እንዲሁም በምክክሩ ጉዳዮች ዙሪያ ሽፋኖችን በመስጠት ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር ተናቦ ሊሰራ እንደፈሚገባም ያስረዳሉ።
ሙያዊ ነጻነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መገናኛ ብዙሃን የአገራዊ ምክክሩ አስፈላጊነትና ታላቅነትና ክስተትነት አምነውና ለችግሮችን መፍትሄ ይሆናል የሚለውን ሃሳብ ታሳቢ አድርገው ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚጠበቅባቸው የሚያስገነዝቡት አቶ ፍሬዘር በበኩላቸው፣ ሁነቱን ከመዘገብና የተለያዩ ሃሳቦችን ከማስተናገድ ባሻገርም አስፈላጊ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው በሚል አጀንዳ ቀርፀው ማቅረብ እንዳለባቸውም ይስማሙበታል።
ይሑንና በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ዋቢ የሚያደርጉ አስተያየት ሰጪዎች በአገራዊ ውይይቱ ላይ መገናኛ ብዙሃኑ በባለቤትነት እንደያዛቸው አካልና ሌላም ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ዘርን፣ አካባቢን፣ ሃይማኖትን ወይም ሌላ ቡድናዊ እሳቤን ተከትሎ የመንጎድ አዝማሚያዎች ሊያስመለክቱ፣ ለአብነትም፣ የክልል መገናኛ ብዙኃንን፤ አጀንዳዎችን ከሚገኙበት ክልል እሳቤ ጋር ብቻ ማቆራኘት ሊታይባቸው ይችላል የሚል ስጋት ያነሳሉ።
ይሕ ስጋት የሚጋሩት ዶክተር ሳምሶንም፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋሉ የሚዲያ ሁኔታዎች ሲቃኙ አገራዊ ፍላጎቶችን ከማንፀባረቅ ይልቅ የራሳቸውን ቡድናዊ ፍላጎቶች ማራመድ ላይ የተጠመዱ በመሆናቸው በአገራዊ ምክክሩ ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችል ያመላክታሉ።
በመሆኑም ‹‹እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ውስጥ የሚደረግ አገራዊ ምክክር ምን አይነት የሚዲያ ሞዴል ሊተገበር ይገባል ተብሎ ከወዲሁ ሊጤን ይገባል›› የሚሉት ዶክተር ሳምሶን፣ ይህ ሲባል ግን የሚዲያ ነፃነት መጋፋት ማለት እንዳልሆነና ይልቁንም አገራዊ ጥቅሞችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑ ሊዘነጋ እንደማይገባም ያሰምሩበታል። አገራዊ ምክክሩ ሁለንተናዊ ስኬት መገናኛ ብዙሃኑ የሚመራበት ዝርዝር መመሪያ ሰነድ ሊዘጋጅለት እንደሚገባም ይጠቁማሉ።
አቶ ፍሬዘር በበኩላቸው፣ ‹‹መገናኛ ብዙሃን የየራሳቸው አላማ፣ አሰራር አቋምና እይታ ሊኖራቸው ይችላል። ይሑንና ሁሉም በአንድና በዚህ ማእቀፍ ብቻ መንቀሳቀስ አለባቸው የሚል አስገዳጅ ማእቀፍ ማስቀመጥም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል›› ይላሉ።
በአገርም ሆነ በክልል ደረጃ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ከሁሉ በላይ የሙያውን መርህ እና ስነምግባርን ባከበረ መልኩ ሃላፊነታቸውን ጠብቀው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አፅእኖት የሚሰጡት አቶ ፍሬዘር፣ ሁነቱን በመዘገብ ሂደት ከተለያየ የፖለቲካ፣ የሃይማኖትም ሆነ የብሄር ተጽእኖ ራሳቸውን ነፃ ማድረግ አለባቸውም›› ይላሉ።
ምሁራኑ እንደሚገልጹት ከሆነም፣ አገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ መገናኛ ብዙሃን ከቡድንና አካባቢያዊ ልሳንነት ይልቅ የሁሉም ድምጽ ሆነው፤ የጎጥ ጥቅምን ለማስጠበቅ መሣሪያ ከመሆን ወጥተው አገርን አስቀድመው ስለ አገር ክብርና ከፍታ እያሰቡ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ሥራቸው ደግሞ ራሳቸውን ገለልተኛ ማድረግና ለየትኛውም ቡድን ፍላጎት መሳካት ከሚደረግ ጥረት ነጻ ማውጣት ይኖርባቸዋል።
ይሑንና አሁን ባለው ሁኔታ ይሕን በቀላሉ ማድረግ ይቻላል ወይ ተብሎ መጠየቁ አይቀሬ ነው። ለዚህ ምላሽ የሚሠጡት አቶ ፍሬዘር፣ በመገናኛ ብዙሃንና በጋዜጠኝነት ሙያ አንዱ መሰረታዊ ጉዳይ የህግ ማእቀፍ ስለመሆኑ ይጠቁማሉ።
በዚህ ሂደት አሁን ያለው የህግ ማእቀፍ ክልል መገናኛ ብዙሃን በነጻነት ከፖለቲካ ፓርቲ ከልሎች ጣልቃ ገብ አካላት ገለልተኛ ሆነው መስራት የሚችሉበትን አግባብ ለመፍጠርም አዋጆች፣ ህጎችና አደረጃጀታቸው መፈተሽ በተለይም ከፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ተፅእኖ ነጻ የሆነ አደረጃጀት እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል›› ይላሉ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ፤ መገናኛ ብዙሃን የምክክር መድረኩ ውጤታማ እንዲሆን በባለቤትነት መንፈስ ሊሰሩ እንደሚገባ አጽኖት ይሰጡታል። መገናኛ ብዙሃን በሌሎች አገራዊ ጉዳይ ላይ ያሳዩትን ወገንተኝነት በአገራዊ ምክክሩ ላይም መድገም በተለይም ለጉዳዩ ሰፊ ሽፋንና ከመስጠት ጀምሮ ተግባቦት ላይ ጠንካራ ሥራ መሥራት እንዳለባቸውም ያስገነዝባሉ።
‹‹አገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃ አሰጣጥ የግድ ነው››የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ መገናኛ ብዙኃን የሂደቱን ከሚያደናቅፍ መንገድ ተቆጥበው መሥራት እንዳለባቸው አፅእኖት ይሰጡታል።
‹‹በምክክር ሂደቱ ወቅት በሚካሄዱ ውይይቶች ላይ የሚነሱ ሃሳቦችን ለማንቋሸሽና ለመግፋት ከሚደረጉ ጥረቶች፤ በጽንፈኝነት የሚወጡ ሃሳቦችን ሌሎች ላይ ከማራገፍ እንዲሁም የአንድን አካል ሃሳብ ባልተገባ መንገድ ከመጠቀም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸውም›› ይላሉ።
የምክክር ኮሚሽኑም ለመገናኛ ብዙኃን ወቅቱን የጠበቀ መረጃ በአስፈላጊው ሰዓት በማቅረብ ተደራሽ የመሆን ግዴታ እንዳለበት ጠቁመው፣ መገናኛ ብዙኃኑ ህብረተሰቡን በውስጥ ሃሳብ ከማጠርና አስተሳሰቡን ከመገደብ መቆጠብ፣ ብዝሃነትን የሚቀበሉና ጽንፈኝነትን የማያራግቡ ሆነው ምክክሩን በአግባቡ ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል›› ነው ያሉት።
በአገራዊ ምክክር ሂደቱ መገናኛ ብዙሃኑም በጽኑ ዲሲፕሊን የራሳቸው አጀንዳ ከመስጠትና አላስፈላጊ ጥብቅ መቆጠብ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ተቋማቸውም በአገራዊ ምክክሩ ላይ የሚተላለፉ ዘገባዎችን መሰረት በማድረግ በመገናኛ ብዙኃኑ አሰራር ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ በየጊዜው ግብረ መልስ እንደሚሰጥ ነው ያስታወቁት።
ከመደበኛ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች ባሻገር በተለይ የዲጂታል ሚዲያው ለአገራዊ ውይይቱ ከባድ ራስ ምታት እንደሚሆን የሚጠቁሙና ከወዲሁም መፍትሄ ሊፈለግለት ይገባል የሚል አቋም ያላቸውም በርካቶች ናቸው።
አቶ ፍሬዘር እጅጉም፣‹‹በመደበኛው መገናኛ ብዙሃን መፈፀም የማይቻሉ ተግባራት በዲጂታል ሚዲያ ሊፈፀሙ ይችላሉ። ሀሰተኛ እንዲሁም ፀብ ቀስቃሽ የሆኑና በጥላቻ የተሞሉ መረጃዎችን በስፋት የሚሰራጭባቸው መድረኮችም ሲሆኑ ይስተዋላል›› ይላሉ።
ይሕ ደግሞ ለአገራዊ ውይይቱ ፈተና እንደሚሆን ይስማሙበታል። እንደ መደበኛው ሚዲያ እነዚህን በቀላሉ መቆጣጠር እንደማይቻል የሚጠቁሙት አቶ ፍሬዘር፣ ሁነኛ መፍትሄውም መደበኛውን መገናኛ ብዙሃን ማጠናከር መሆኑን ያስገነዝባሉ።
እንደ አቶ ፍሬዘር ገለጻ፣ መደበኛው መገናኛ ብዙሃን ጠንካራ ሆነው መውጣትና እውነተኛ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ በቻሉ ቁጥር በዲጂታል ሚዲያው የሚሠራጨው ሃሰተኛ መረጃ ይዳከማል። መደበኛ መገናኛ ብዙሃን እንዲጠናከሩና እንዲስፋፉ ለማድረግ ደግሞ የማትጊያ ስልቶችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከሁሉ በላይ መደበኛ መገናኛ ብዙሃን መረጃ የማግኘት መብትን በእጅጉ ቀላልና ቀልጣፍ ማድረግ የግድ እንደሚል የሚያስገነዝቡት አቶ ፍሬዘር፣ ማህበራዊ ሚዲያውን ከመቆጣጠር ባሻገር ዜጎች መረጃ በሚመለከት አስተዋይ፣ ጠንቃቃና ፈታሽ እንዲሆኑና በተሳሳተ አረዳድ፤ ያልተፈለገ ተግባር እንዳይፈፅሙ በተለይም የመገናኛ ብዙሃን መሰረታዊ እውቀት ወይንም ሚዲያ ሊትሬሲን ማጎልበት ናስልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።
ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ይግዛውም ዲጂታል ሚዲያው ወቅታዊ የአገር ፈተና መሆኑን ይስማሙበታል። ‹‹ባለፉት 30 ዓመታት የተሠሩ የፖለቲካ ትርክቶችና የተሠሩ ሥራዎች ለማኅበራዊ ትሥሥር ገፆች ትልቅ ግብዓት ወደ መሆን አዝማሚያ ሄደዋል። ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም አሸባሪው ሕወሓትን ጨምሮ በአገር ውስጥና ከአገር ወጪ ያሉ የኢትዮጵያን መልካም ነገር የማይፈልጉ አካላት በዲጂታል መንገድም ሆነ በአካላዊ ጦርነት ኢትዮጵያን ለማጥቃት ያላሰለሰ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉም›› ይላሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻም፣ ዲጂታል ሕወሓት የዲጂታል ጦርነቱን በተለያየ መንገድ እየተገበረ ነው። ለአብነትም ኦሮሞ ሳይሆኑ የኦሮሞ ሥም ገፆችን በመክፈት፤ አማራ ሳይሆኑ የአማራ ሥም የያዘ ገፅ በመክፈት የብሔር ጉዳዮችን አንስቶ በመሳደብና ተቆርቋሪ በመምሰል በሐሰተኛ ገፅ ተጠቅመው ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ማዛባት ጦርነት እያካሄዱ ነው።
በተጨማሪም በአርቲስቶች፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና በሌሎች ታዋቂ ሰዎች ሥም በርካታ ሐሰተኛ የትሥሥር ገፆች ተከፍተው ሲሠሩ በክትትል ተደርሶባቸው በሕግ የተጠየቁና ውሳኔ የተላለፈባቸው አሉ። ቁጥራቸው በርከት ያለ የሐሰተኛ መረጃ አሰራጮችና የሐሰተኛ ገፅ ተጠቃሚዎች በክስ ሂደት ላይ ይገኛሉ።
ሐሰተኛ የትሥሥር ገፆች ብቻ ሳይሆኑ ትክክለኛ አካውንቶች ሆነው ጭምር ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎችን የሚያሠራጩ እንዳሉ የሚገለጹት ዶክተር ሹመቴ፤ ዲጂታል ሚዲያዎችን በአግባቡ የመጠቀም ግንዛቤ በማኅበረሰቡ ዘንድ እምብዛም መሆኑ ለሚነሳው ሐሰተኛ መረጃ ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረለት ይጠቁማሉ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የራሱ የሆነ መሥፈርት አውጥቶ ሰፊ ክትትል እያደረገ እንደሆነና በሕግ የማስጠየቅ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው፣ ዋናው ነገር ግን ከገበያ የተገኘ ሁሉ እንደማይገዛ እንዲሁ መረጃዎች ሁሉ አይገበዩም፤ ህብረተሰቡ ምንጫቸው መጣራት ይኖርበታል። ይህ ሲደረግ የሐሰተኛ መረጃዎች ሥርጭት እና የሚያደርሱት ጉዳት እንዲቀንስ ይሆናል ነው››ያሉት። ፡
‹‹ከማህበራዊ ሚዲያ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ጠንካራ ቁጥጥር ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ›› የሚሉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ በበኩላቸው። እንደ ተቋም እነዚህን የመገናኛ ብዙኃንና የማህበራዊ ሚዲያዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ ጉዳዩ ለሚመለከተው የፍትህ ሚኒስቴር መቅረቡንና ሲፀድቅም ተግባራዊ እንደሚደረግ አመላክተዋል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም