ከሮማዊያን ዘመን ጀምሮ ለብዙ ሺህ ዓመታት ለሮኬት ሳይንስ መሰረት የሆኑ ምርምሮችና ሙከራዎች ሲደረግ ቢቆይም ለዘመናዊ ሮኬት ሳይንስ መሰረት የተጣለው በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ድርሳናት ያስረዳሉ። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ለዘመናዊ ሮኬቶች ሳይንሳዊ መሰረት የተጣለው በታላቁ እንግሊዛዊ ሳይንቲስት ሰር አይዛክ ኒውተን (1642-1727) ነው። ኒውተን ስለ አካላዊ እንቅስቃሴ ያለውን ግንዛቤ በሦስት ሳይንሳዊ ሕጎች አደራጅቷል። ሕጎቹ ሮኬቶች እንዴት እንደሚሠሩ እና ለምን በውጫዊ ክፍተት ውስጥ መሥራት እንደሚችሉ ያብራራሉ።
የኒውተን ህጎች ብዙም ሳይቆይ በሮኬቶች ዲዛይን ላይ ተግባራዊ ተጽእኖ ማሳደር ጀመሩ። በ1720 አካባቢ አንድ ሆላንዳዊ ፕሮፌሰር ቪለም ግራቬሳንዴ በእንፋሎት አውሮፕላኖች የሚንቀሳቀሱ ሞዴል መኪናዎችን ሠሩ። በጀርመን እና ሩሲያ ውስጥ የነበሩ የሮኬት ሞካሪዎች ከ45 ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ያላቸው ሮኬቶችን መስራት ጀመሩ። ከእነዚህ ሮኬቶች መካከል አንዳንዶቹ በጣም ኃይለኛ ከመሆናቸው የተነሳ ሮኬቶቹ ገና ከመነሳታቸው በፊት በጭስ ማውጫው የሚንበለበሉ ነበልባሎች በመሬት ውስጥ ጥልቅ ጉድጓዶችን የሚቆፍሩ ነበሩ።
በ18 ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሮኬቶች እንደ የጦር መሳሪያ ደግም ጥቅም ላይ መዋል ጀመሩ:: እ.ኤ.አ. በ 1792 እና በ 1799 በብሪታንያ ላይ የተተኮሰው የህንድ ሮኬቶች ስኬታማ መሆናቸው የመድፍ ኤክስፐርቶች ፍላጎት መሳብ ቻለ። በተለይም የእንግሊዛዊውን የመድፍ ኤክስፐርት ኮሎኔል ዊልያም ኮንግሬቭን ፍላጎት ሳበ። ኮንግሬቭ ለብሪቲሽ ወታደሮች የሚውል ሮኬቶችን ለመንደፍ ተነሳ።
የኮንግሬቭ ሮኬቶች በውጊያው ከፍተኛ ስኬት ነበራቸው። በዘመኑ የነበሩ ሮኬቶች በተለይም በከበባ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች በጠላት ላይ በመተኮስ ከበባውን ለመስበር ጥቅም ላይ ይውል ነበር። . ከዚያን ወቅት ጀምሮ በመላው ዓለም የሮኬት ተመራማሪዎች የሮኬቶችን ትክክለኛነትን ለማሻሻል ጥረት አድርገዋል። እንግሊዛዊ ዊልያም ሄል የሮኬቶችን እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያ ዘዴ ፈጥሮ ነበር።
ሮኬቶች ከዚያ በኋላ በመላው አውሮፓ አህጉር በሚደረጉ ጦርነቶች በተሳካ ሁኔታ መጠቀማቸውን ቀጥለውም ነበር። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ሮኬቶች ለጦርነት ብቻ ሳይሆን ለሰላማዊ ተግባራትም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደርገዋል። እ.ኤ.አ. በ 1898 አንድ የሩሲያ ትምህርት ቤት መምህር የነበረው ኮንስታንቲን ፂዮልኮቭስኪ (1857-1935) በሮኬት የጠፈር አሰሳ ሀሳብ አቀረበ። ሮኬቶችን ለጠፈር አሰሳ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚረዱ የተለያዩ ሀሳቦችንም ማቅረብ ችሎ ነበር። ፂልኮቩስኪ ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ በማበርከቱ የዘመናዊ የጠፈር ምርምር አባት ተብሎ እስከመጠራት ደርሷል።
የሮኬት ሳይንስን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት በ20ኛው ክፍለ ዘመንም ተጠናክሮ ቀጥሎ እንደነበር ናሳ ባሳተመው መጣጥፍ ላይ አመላክቷል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ አሜሪካዊው ሮበርት ኤች ጎዳርድ (1882-1945) ተግባራዊ ሙከራዎችን አድርጓል። ችግሮች ቢያጋጥሙትም ጎድዳርድ የመጀመሪያውን የተሳካ በረራ መጋቢት 16 ቀን 1926 አሳካ። በፈሳሽ ኦክሲጅንና ቤንዚን ተጭኖ ሮኬቱ ለሁለት ሰከንድ ተኩል ብቻ በመብረር 12.5 ሜትር ከፍታ በመውጣት 56 ሜትር ርቀት ላይ አረፈ። በዛሬው መመዘኛዎች፣ በረራው አስደናቂ አልነበረም፣ ነገር ግን በ1903 በራይት ወንድሞች እንዳከናወኑት እንደ መጀመሪያው የአውሮፕላን በረራ፣ የጎድዳርድ ቤንዚን ሮኬት በረራ የዘመኑ ፈር ቀዳጅ ስራ ነበር።
ሦስተኛው ታላቅ የጠፈር አቅኚ ኸርማን ኦበርት (1894-1989) በ1923 ስለ ሮኬት ወደ ጠፈር ጉዞ መጽሐፍ አሳተሞም ነበር። የእሱ ጽሑፎች ለዘርፉ እድገት እጅግ ጠቃሚ ነበሩ። በጽሁፎቹ ምክንያት በአለም ዙሪያ ብዙ የሮኬት ዘርፍ ተመራማሪዎች ተፈጥረዋል። በጀርመን ውስጥ የዚህ አይነት ማህበረሰብ ምስረታ የሆነው ቬሬይን ፉር ራምሺፋህርት (ማህበረሰብ ለስፔስ ቱሪስት) የ V-2 ሮኬት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ይህም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለንደን ላይ ጥቅም ላይ ውሏል። እ.ኤ.አ. በ 1937 የጀርመን መሐንዲሶች እና ሳይንቲስቶች ኦበርትን ጨምሮ በባልቲክ ባህር ዳርቻ ላይ በፔኔሙንድ ተሰበሰቡ። በዚያ በጊዜው እጅግ የላቀ ሮኬት በቨርንሄር ቮን ብራውን ዳይሬክተርነት ተገንብቶ ይበር ነበር።
ቪ-2 ሮኬት (በጀርመን A-4 ተብሎ የሚጠራው) ከዛሬዎቹ ሮኬቶች ጋር ሲነጻጸር ትንሽ ነበር። በየሰባት ሰከንድ አንድ ቶን በሚደርስ ፍጥነት የፈሳሽ ኦክሲጅን እና የአልኮሆል ቅልቅል የሚፈጅ ነው። አንዴ ከተከፈተ ቪ-2 መላውን የከተማ ብሎኮች ሊያወድም የሚችል አስፈሪ መሳሪያ ነበር።
እንደ እድል ሆኖ በወቅቱ አላይድ ፎርስ ተብሎ ይጠሩ የነበሩት እንግሊዝና አጋሮቹ V-2 ሮኬቶችን መጠቀም አልጀመሩም ነበር። ይህንን መሳሪያ መጠቀም የጀመሩት በጦርነቱ ማብቂያ ላይ ነው። በጦርነቱ ማብቂያ የጀርመን የሮኬት ሳይንቲስቶች እና መሐንዲሶች አትላንቲክ ውቅያኖስን በመሻገር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሊያርፉ የሚችሉ የተራቀቁ ሚሳኤሎች ዕቅድ አውጥተውም ነበር።
በጦርነቱ ጀርመን መሸነፏን ብሎም ለውድቀት መዳረጓን ተከትሎ፣ ብዙ ጥቅም ላይ ያልዋሉ V-2 ሮኬቶች እና አካላት በእነ እንግሊዝ በሚመራው አላይድ ሀይል እጅ ውስጥ ገብተዋል። ብዙ የጀርመን ሮኬት ሳይንቲስቶች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተሸገሩ። ሌሎች ደግሞ ወደ ሶቪየት ህብረት ሄዱ።
ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች የሶቪየት ኅብረት የሮኬቶችን አቅም እንደ ወታደራዊ መሣሪያ ተገንዝበው የተለያዩ የሙከራ ፕሮግራሞችን ጀመሩ። መጀመሪያ ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ከጎድደርድ ቀደምት ሃሳቦች ውስጥ አንዱ በሆነው ከፍታ በከባቢ አየር የሚነፋ ሮኬቶችን የያዘ ፕሮግራም ጀመረች። በኋላም የተለያዩ መካከለኛ እና ረጅም ርቀት አቋራጭ ሚሳኤሎች ተሰራ። እነዚህ የአሜሪካ የጠፈር ፕሮግራም መነሻ ሆኑ። እንደ ሬድስቶን፣ አትላስ እና ታይታን ያሉ ሚሳኤሎች በመጨረሻ ጠፈርተኞችን ወደ ህዋ ማጓጓዣ ሆኑ።
እ.ኤ.አ ኦክቶበር 4, 1957 በሶቭየት ኅብረት ምድርን የምትዞር ሰው ሰራሽ ሳተላይት በማምጠቅ ዓለምን አስደነቀች። ስፑትኒክ 1 እየተባለ የሚጠራው ሳተላይቱ በሁለቱ ልዕለ ኃያላን አገራት መካከል በተደረገው የኅዋ ውድድር ያስጀመረች የመጀመሪያዋ የተሳከ ሮኬት ነበረች። አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሶቪየቶች ላይካ የተባለ ውሻ የያዘች ሳተላይት ወደ ህዋ አመጠቁ። እሽቅድድሙ አልቆመም። ከጥቂት ወራት በኋላ አሜሪካኖች ሌላ ሮኬት አመጠቁ። ሮኬቱ የአሜሪካ መከላከያ ሀይል ነበር። በ1958 አሜሪካኖች የህዋ ፕሮግራም (ናሳን አቋቋሙ)። ናሳ ከወታደራዊ እሽቅድድም ይልቅ ለሰላማዊ ዓላማ ህዋና ማሰሻ ሆኖ ቀጠለ።
ናሳ ከተቋቋመ በኋላ በርካታ ሰዎች እና ማሽኖች ወደ ህዋ መጥቀዋል። የህዋ ተመራማሪዎች በጨረቃ ላይ እንዲያርፉ ተደርገዋል። ሮቦቶች ወደ ተለያዩ ፕላኔቶች ተጉዘዋል። ህዋ ለምርምርና ለንግድ ክፍት ሆኗል። ሳተላይቶች ሳይንቲስቶች ዓለማችንን እንዲያጠኑ፣ የአየር ሁኔታን እንዲተነብዩና በዓለም ዙሪያ ፈጣን ተግባቦት እንዲኖር አስችለዋል። ሳይንቲስቶች ዓለማችንን የበለጠ የመፈተሽ ፍላጎት እየጨመረ በመሆኑ አሁን ካሉት የበለጡ ሮኬቶችን መገንባት አስፈላጊ እየሆነ ነው። የሮኬት ቴክኖሎጂ ከተጀመረበት ከብዙ ሺህ ዓመታት ወዲህ የሮኬት ቴክኖሎጂ ከአነስተኛ ተተኳሽ ቴክኖሎጂ ወደ ስፔስ ትላልቅ ማሽኖችን ይዞ መንቀሳቀስ የሚችል ሆኗል። ሮኬቶች ዩኒቨርስን ለሰው ልጅ ክፍት አድርገዋል።
የአገራችን ፋና ወጊው ሮኬት የማስወንጨፍ ዜና
የሮኬት ሳይንስ በዓለም ላይ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቀ የመጣ ዘርፍ ቢሆን በኢትዮጵያ ግን እንደ ቅንጦት ይታያል። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከሚደረግ መጠነኛ እንቅስቃሴ ውጪ ይህ ነው የሚባል ስራ አልተሰራበትም። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ለተለያዩ ዓላማዎች የሚውሉ ሮኬቶችን የማስወንጨፍ ሙከራዎች እየተደረጉ ነው። አምና በባህር ዳር ከተማ የሚኖሩ ታዳጊዎች በተሳካ ሁኔታ ሮኬት ማስወንጨፋቸውን የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። እነዚህ ታዳጊዎች ያደረጉት የተሳከ ሙከራ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን የፈጠረ ነበር። በቅርቡ ደግሞ የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ በአጼ ቴዎድሮስ ስም የተሰየመ ሮኬት የማስወንጨፍ ሙከራ ማድረጉን በቅርቡ ይፋ አድርጓል። የማስወንጨፍ ሙከራውም የተሳከ እንደነበር ተዘግቧል። ይህን የአጼ ቴዎድሮስን 154ኛ የሰማዕትነት በዓል ምክንያት በማድረግ የተከናወነ ነው። በመጠን አነስ ያለ ሮኬት ደግሞ በልዑል ዓለማየሁ ስም መወንጨፉን ነው የተጠቆመው።
የዩኒቨርሲቲው ተግባር ለብዙዎች ኩራት እንድሰማቸው ያደረገ ነው። አገሬ በሮኬት ቴክኖሎጂ ወደፊት ከሌሎች ያደጉት አገራት ተርታ ልትሰለፍ ነው የሚል ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጓል። በቀጣይ በህዋ በሚደረገው እሽቅድድም ውስጥ አንዷ እንድትሆንም መሰረት የሚጥል ተደርጎ ተወስዷል። ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ አለም የደረሰችበት ቦታ ለመድረስ ዳዴ ማለቷ ይበል የሚያሰኝ ነው። የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተግባር ኢትዮጵያዊያን ኩራት እንዲሰማቸው ያደረገ ነው። አገሬ በሮኬት ቴክኖሎጂ ወደፊት ከሌሎች ያደጉት አገራት ተርታ ልትሰለፍ ነው የሚል ተስፋ እንዲሰንቅ አድርጓል። በቀጣይ በህዋ በሚደረገው እሽቅድድም ውስጥ አንዷ እንድትሆንም መሰረት የሚጥል ተደርጎ ተወስዷል።
የዩኒቨርሲቲው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ብርሃኑ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የዩኒቨርሲቲው የሮኬት ሳይንስ ማዕከል ጥናትና ምርምር አድርጎ ሮኬት የማስወንጨፍ ጥረት ሲያደርግ የዘንድሮው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። የዛሬ ዓመት ሙከራ አድርጎ ነበር። አምና በተለምዷዊ መንገድ ለማስወንጨፍ ጥረት አድርጓል። የአምናው ሙከራውም የተሳከ ነበር። የአምናው ወደ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ማስወንጨፍ የተቻለ ሲሆን በበይነ መረብ የታገዘ አልነበረም። በወቅቱ አገሪቱ ጦርነት ውስጥ ስለነበረች ስለሮኬቱ ማስወንጨፍ ብዙም አልተወራለትም። በብዙ ሰዎች ዘንድም አልታወቀም። በቦታው በነበሩ ሰዎች ግን መገረምን የፈጠረ ነበር።
እንደ አቶ ዳዊት ማብራሪያ፤ ዩኒቨርሲቲው እስከ 5 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል የተሳከ የሮኬት ማስወንጨፍ ሙከራ አድርጓል። ከአምናው የተሻለ ሁኔታ ስላለ ቦታ ተመርጦ፤ የደቡብ ጎንደር ዞን የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች፣ የሚዲያ አካላት እና የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች ባሉበት አሞራ ገደል የተሳከ የማስወንጨፍ ሙከራ ተደርጓል።
ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ ያደረገውን የተሳከ ሙከራ የዛሬ ዓመት ካደረገው ለየት የሚያደርገው የሮኬት ማስወንጨፍ ስርዓቱን ከበይነ መረብ ጋር የተገናኘ መሆኑ ነው። ይህንም በሁለት በኩል የሚታይ ነው። በአንድ በኩል ዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ የመጀመሪያው ኢንዱስትሪ ተጸንሶ የተወለደበት የጋፋት ኢንዱስትሪ አቅራቢያ የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ የአጼ ቴዎድሮስን የቴክኖሎጂ ጥማት ለመመለስ አንድ እርምጃ ወደ ፊት መሄዱን የሚያመላክት ነው።
ሌላኛው እንደ አገር ኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ አካሄድ ውስጥ ግንባር ቀደም እንድትሆን የሚያስችሉ አገር በቀል ልሂቃን መኖራቸውን የሚያመላክት ነው። ይህ ለአገሪቱ የሮኬት ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው። እንደ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ የሮኬት ሳይንስ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር መገለጥ መጀመራቸው በተለይም በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የሚደረገው የሮኬት ሳይንስ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ የወደፊት መጻኢ እድሏ የተሻለ እንዲሆን የሚረዳ ነው። የአገሪቱን የሮኬት ሳይንስ አቅምና የሮኬት ሳይንስ ጥበብ የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ እንደሚቻል አመላካች ነው ብለዋል።
ወደፊት ይፋ የሚሆኑ በርካታ ስራዎች አሉ። ዩኒቨርሲቲው ከሮቦቲክስ ጋር የተገናኙ ሌሎች ስራዎችንም እየሰራ ነው። ከሬዲዮ ጋር የተገናኙ ስራዎችም እየተሰሩ ነው። ከድሮን ጋር የተያያዙ ስራዎችም በሂደት ላይ ሲሆን በቅርቡ ይፋ እንደሚደረጉም ጠቁመዋል።
ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በመድፍ ፈጠራ እና በስኬታማው የሮኬት ማስወንጨፍ ሂደት ላይ ለተሳተፉ የቴክኖሎጂ ምሁራንና ተማሪዎች የእውቅና እና የምስጋና መርሀ ግብር በቅርቡ ያከናወነ ሲሆን። በመርሀ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው የእውቅና መርሀ ግብሩ የተዘጋጀው በሮኬት ሳይንስ ዘርፍ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ በተግባር ያሳዩትን ተመራማሪዎች፣ ምሁራን እና ተማሪዎችን በማበረታታት ለቀጣይ ስራ አቅጣጫዎችንም ማስቀመጣቸውን ዩኒቨርሲቲው በፌስቡክ ገጽ አስፍሯል።
“የቴክኖሎጂ ምሁራን እና ተማሪዎች 154ኛውን የአፄ ቴዎድሮስ ዝክረ-ሰማዕት መታሰቢያ በዓል አስመልክተው ባዘጋጁት ተጨባጭ የፈጠራ ሥራዎች ሙከራ ብዙ አካላት ተደንቀዋል” ያሉት ፕሬዚዳንቱ በተገኘው ውጤት ሳይዘናጉ የምርምር ሥራዎቻቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። አያይዘውም የሮኬት ሳይንስ ማዕከሉ ከተገኘው ውጤት በላይ በተሻለ አቅም እንዲንቀሳቀስ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አጽንኦት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የዩኒቨርሲቲው ሮኬት ሳይንስ ማዕከሉ ሰብሳቢ መምህር በለጠ ጌታቸው አሁን ያደረጉት የመድፍ ፈጠራ ሥራ እና የሮኬት ማስወንጨፍ ሙከራ ጅምር መሆኑን ጠቅሰው በቅርቡ ይፋ የሚደረጉ ሌሎች የፈጠራ ስራዎች በሂደት ላይ እንደሚገኙ አመላክተዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 25 ቀን 2014 ዓ.ም