የ2013/2014 የመኸር የምርት ዘመን ፣ ቀጥሎ የተከናወነው የመስኖና የበልግ የልማት ሥራ ተጠናቅቆ ለ2014/2015ዓ.ም የመኸር ግብርና ሥራ ከወዲሁ ዝግጅት በሚደረገበት ጊዜ ላይ እንገኛለን:: በተከታታይ የተከናወኑት የግብርና ሥራዎች ከፊታችን ለሚጠብቀን የመኸር የግብርና ሥራ ተሞክሮና ግንዛቤ የሚገኝባቸው እንደሆነ ይታመናል:: በዚህ ወቅት የሰብሉን፣የአትክልትና ፍራፍሬውን፣የእንስሳት ልማቱን ሁሉ አካቶ የሚከናወነው የግብርና ሥራ ይጠበቃል:: እንደሀገርም በግብርና ላይ የተመሰረተውን ኢኮኖሚ ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚቻለው ሁሉም በየአካባቢው በግብርና ሥራው የሚጠበቅበትን መወጣት ሲችል ነው:: ከዚህ አንጻር የኦሮሚያ ክልል ቡኖበደሌ ዞንን የግብርና ሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ከዞኑ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ጅፋር ጋር ቃለምልልስ አድርገናል::
አዲስዘመን፦ የግብርና ሥራ ከፍ ያለ ሀገራዊ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲኖረው በማድረግ የቡኖበደሌ ዞን በዘርፉ እያከናወነ ስላለው ተግባር ቢገልጹልን ?
አቶ ዳዊት፦ በዞኑ ሁለገብ የግብርና ሥራ ነው የሚከናወነው:: በቡና፣ በአዝርዕት ልማትና በሌሎችም ሰፊ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው:: በቅርቡ በተከናወነው የበጋ ወይንም የቆላ መስኖ ስንዴ ልማት በዞኑ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል:: በመስኖ ወደ ስምንት ሺህ ሰባ(8070)ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር ለመሸፍን ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፣የተከናወነው ግን ከእቅድ በላይ ነው:: 16ሺ ሄክታር መሬት ታርሶ በዘር ተሸፍኗል:: በዘር ከሚሸፈነው መሬትም ከ520ሺ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ በቅድመ ትንበያ ተይዟል:: እስካሁን በተከናወነው የምርት መሰብሰብ ሥራ ከአምስት መቶ ሺ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል:: ያለፉ የሥራ ተሞክሮዎች መልካም ውጤት ያስገኙ መሆናቸውም በግምገማ ተለይቷል:: አሁን በክረምት ለመኸር የግብርና ሥራ ዝግጅት እያደረግን ነው:: የዝግጅት ሥራው በስልጠና የታገዘ ሲሆን፣ አርሶ አደሩ ቀድሞ ዝግጅት እንዲያደርግ የዞኑ ግብርና ቢሮ በባለሙያዎቹ የክህሎት ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል:: ጎን ለጎንም የንቅናቄ ሥራ እየተከናወነ ነው:: ስልጠናው ባለሙያዎችንም ያካትታል:: የአሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት ባለሙያውንም የማብቃት ሥራ ይከናወናል:: በዚህ መልኩ የተያዘው ዕቅድ ከተከናወነ በኃላ ሙሉ ለሙሉ ወደ ግብርና ሥራው ይገባል:: የሚታረሰው መሬትም ከወዲሁ እንዲለይ ተደርጓል:: ወደ174ሺ ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል ለመሸፈን ነው በእቅድ የተያዘው:: አሁን ያለው ወቅታዊ የአየርፀባይ በተለይም ዝናቡ ለእርሻ ዝግጅት ተስማሚ ነው:: ቀድመው የማሳ ዝግጅት የጀመሩ አርሶአደሮችም ይገኛሉ::
አዲስዘመን፦ከቆላ የበጋ ስንዴ ልማት ጎን ለጎን በመስኖ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም ሲከናወን እንደቆየ ይታወቃል:: በዚህ ረገድ በቡኖበደሌ ዞን የተከናወነውን ልማት እንዴት ይገለፃል?
አቶ ዳዊት፦ ቀደም ብዬ እንዳነሳሁት በዞኑ ሁለገብ የግብርና ሥራ ነው የሚከናወነው:: በመሆኑም በማህበር የተደራጁ የአካባቢው ወጣቶች በአትክልትና ፍራፍሬ በተለይም በአቮካዶ ልማት ሰፊ ሥራ ተሰርቷል:: በአሁኑ ወቅትም ዘር የማዳቀል ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣በተለይም በዞኑ ሶስት ወረዳዎች ውስጥ የችግኝ ጣቢያዎች በማፍላት ጭምር ነው ሥራዎች የተከናወኑት:: በነዚህ ችግኝ ጣቢያዎች የሚፈላውን ወይንም የሚዘጋጀውን ችግኝ በ185ሺ ሄክታር መሬት ላይ የአቮካዶ ልማት ለማከናወን መሬቱ በክላስተር ተዘጋጅቷል:: የሙዝ ልማትም በተመሳሳይ ለማከናወን እንቅስቃሴ ተጀምሯል:: በክላስተር የአሰራር ዘዴ ወደ 85ሺ የሙዝ ችግኝ ለመትከል በእቅድ ተይዞ ወደ 60 ሺ ችግኞች ተተክለዋል:: በዘንድሮ አመት በልዩ የትኩረት አቅጣጫ ይዘን እየተንቀሳቀስን ያለው የከተማ ግብርናን ማስፋፋት ነው:: የከተማውን ነዋሪ የአትክልትና ፍራፍሬ ፍላጎት በማሟላት ደረጃ ብዙ ሥራዎች እንደሚጠበቁ ቀድመን በመገምገም የለየነው ሥራ በመሆኑ ትኩረት
ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን:: የልማት ሥራው ከመከናወኑ በፊትም መሰራት ስላለባቸው የልማት ሥራዎችና ልማቱም በእውቀት እንዲከናወን በስልጠና በማብቃት ነው ወደ ሥራ የተገባው:: በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና የከተማው ነዋሪ ባለው ክፍት ቦታ የተለያዩ አትክልቶችን በመትከል ቢያንስ እራሱን ለመመገብ የሚያስችለውን የከተማ ግብርና ሥራ እንዲያከናውን የሚረዳውን ክህሎት እንዲያገኝ ነው የተደረገው::
አዲስዘመን፦ በዞኑ ሁለገብ የግብርና ሥራ እንደመከናወኑ በእንስሳት ልማት በኩል ያለው እንቅስቃሴ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? በተለይም በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በድርቅ እንስሳት እየተጎዱ በመሆኑ መልሶ የመተካትም ሆነ በዘርፉ ሰፊ ሥራ ይጠበቃል:: ከዚህ አንጻር ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ዳዊት፦በእንስሳት ልማት በተለይ ከከተማ ግብርና ልማት ጋር ማያያዝ ይቻላል:: በመሆኑም አመርቂ በሚባል ደረጃ እየተሰራ ነው:: በአርቲፊሻል በማዳቀል ዘዴ እንስሳትን የማራባት ሥራ ተሰርቷል:: እንሰሳት የማራባቱ ሥራ መስፋቱ ለወተት ምርት መጨመር ወይንም ከፍ ማለት አስተዋጽኦ ያበረክታል:: በአሁኑ ጊዜ የከተማው ነዋሪ በከተማ ግብርና በተከናወነ የወተት ልማት ነው በመጠቀም ላይ የሚገኘው:: እዚህ ላይ አልሰራንም ወይንም ይቀረናል ብለን በግምገማ የለየነው በዞኑ በደሌ ከተማ ላይ የወተት ማዕከል በማቋቋም ሰፊ ሥራ መሥራት ይቻል እንደነበር ነው:: ምክንያቱም የእንስሳት ሀብቱና የምርት አቅርቦቱ አለ:: አቅርቦቱ በተበታተነ መልኩ ከሚከናወን የወተት ማዕከል ቢቋቋም ለአቅራቢውም ለተጠቀሚውም ምቹ ይሆናል:: ማእከሉ ቢቋቋም ወጣቶችን በማደራጀት እንዲሰሩ ማድረግ ይቻላል:: ልማቱ ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር አስተዋጽኦ ይኖረዋል:: በቢሮ ደረጃም እየተወያየንበት ነው:: ቀጣዩ ስራ በውይይት እንዳይቀር ማድረግ ነው::
ከድርቅ ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ ሀገራችን ከውስጥም ከውጪም በገጠማት የተለያየ ፈተና በብዙ ችግር ውስጥ እንደሆነች ይታወቃል:: ይህ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ እያጋጠመ ካለው ፈተና ለመውጣት ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው በዞናችን ግንዛቤ ተይዟል።በመሆኑም በዘመናዊ የአረባብ ዘዴ የእንስሳት ሀብትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው:: ዞኑ ለእንስሳት፣ለአሳ እርባታና ለንብ ማነብ ምቹ በመሆኑ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን ከግብርና ሥራ ጋር ተያያዥ በሆኑት ላይ ሥራዎች ይሰራሉ:: ሥራው ደግሞ ተጀመረ እንጂ ኢትዮጵያ ሀገራችን ከዘርፉ ከምትጠብቀው ውጤት አኳያና ዞኑም በግብርናው ዘርፍ በስፋት ሊከናወን የሚችል ካለው እምቅ ሀብት አኳያ የቤት ሥራ እንደሚጠብቀን እኛም በአመራር ደረጃ ተነጋግረንበት መግባባት ላይ ደርሰን የተሻለ ሥራ ሰርተን ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀስን ነው:: እንቅስቃሴው የተለያዩ የግብርና ውጤቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ አስተዋጽኦ ለማበርከት ነው:: በተለይም የእንስሳት ውጤቶችና የማር ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚቻልበት ዕድል አለ:: ከኛ የሚጠበቀው ልማቱን ማዘመን ነው::
አዲስዘመን፦ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር አንዱ መንገድ ቴክኖሎጂን መጠቀም ነው:: ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ደግሞ በተለያየ መንገድ ይገለጻል:: ከዚህ አንጻር ያለው ጥረት ምን ይመስላል?
አቶ ዳዊት፦የግብርና ሥራ በቴክኖሎጂ ሲታገዝ ምርትና ምርታማነት እንደሚያድግ ወይንም እንደሚጨምር ጥያቄ ውስጥ አይገባም:: ከቴክኖሎጂ ግብአቶች አንዱ የክላስተር ወይንም ኩታገጠም የግብርና ዘዴ ነው:: ይህ ዘዴ ምርጥዘር፣ ማዳበሪያ እንዲሁም በመስመር መዝራትና ሌሎች የግብርና ግብአቶችን አጠቃቀም አካቶ የያዘ በመሆኑ ይህን
ለመተግበር በትኩረት ይሰራል:: ባለፈው አመት በዚህ የክላስተር ዘዴ ወደ 58ሺ ሄክታር ነበር በክላስተር የተለያየ የሰብል ልማት የተከናወነው።በ2014/2015 የመኸር የምርት ዘመን ሄክታሩን በእጥፍ በማሳደግ በስምንት ሰብሎች ላይ በክላስተር ለማምረት አቅደን እየሰራን ነው:: ምርታማነትን ከመጨመር አንጻር አስተዋጽኦው ከፍ ያለ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶታል:: ለአርሶአደሩም ግንዛቤ እየተሰጠ ያለው በዚህ ደረጃ ነው::
አዲስዘመን፦ በዚህ ወቅት እንደተግዳሮት እየተነሳ ያለው የማዳበሪያ አቅርቦት ነው:: ዞኑ ይሄን በምን መልኩ ሊፈታው አስቧል?
አቶ ዳዊት፦ እንደሀገር ባጋጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የዓለም የማዳበሪያ ዋጋ መናር የተነሳ አቅርቦቱ ቀደም ሲል እንደበረው ሊሆን እንደማይችል ይጠበቃል:: በመሆኑም በጉዳዩ ላይ በክልል ደረጃ እንደ አቅጣጫ ተይዞ የተፈጥሮ ማዳበሪያ የማዘጋጀት ሥራ እንዲጠናከር ተደርጓል:: የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈር ለምነትን በማስተካከልና በመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው:: የማዳበሪያ አቅርቦትን ሙሉ ለሙሉ ይተካል የሚል እምነት ባይኖርም አማራጭ ዘዴ በመጠቀም ችግሩን መፍታት የግድ ነው:: የተፈጥሮ ማዳበሪያን ከማዘጋጀት ጎን ለጎን የማዳበሪያ አቅርቦትንም ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው። ዞኑ 135ሺ ኩንታል ማዳበሪየ እንዲቀርብ ለክልል ጥያቄ አቅርበናል:: ከቀረበው ጥያቄ ውስጥ ወደ 33ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ገብቷል:: ቀሪው መቅረብ ካልቻለ በተፈጥሮ ማዳበሪያ በማካካስ የግብርና ሥራው ይከናወናል:: ሌላው ተግዳሮት የበቆሎ ዘር እጥረት ነው:: በተለይም ፓይነር የሚባል የዘር አይነት ከጠየቅነው ዘር አንድ ሶስተኛ የሚሆነው እንኳን አልደረሰንም:: ሌሎች ምርጥ ዘሮች ላይ ችግር አልገጠመንም::
አዲስዘመን፦በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከፈተው ጦርነት ምክንያት በግብርና ሥራው ላይ የባከነ ጊዜ መኖሩ ይታወቃልና ይህንን በሚያካክስ ሥራ መሰራት አለበት:: ከዚህ አንጻር ያላችሁ ዝግጁነትስ ምን ይመስላል?
አቶ ዳዊት፦እውነት ነው ብዙ የባከኑ ጊዜዎች አሉ:: ስለዚህ የተለያየ አቅጣጫዎችን ይዞ ነው በግብርና ሥራው ላይ እየሰራን የምንገኘው:: ዞናችን የሰላም ዞን ነው:: እንደ አመራርም፣እንደ ባለሙያና አርሶአደር በተለያዩ አካባቢዎች በግብርና የባከኑትን የመሸፈን ተግባር ለማከናወን ነው ያቀድነው:: ድርብርብ ተልዕኮዎችንና ኃላፊነቶችን ይዘን እየተንቀሳቀስን መሆናችንን አርሶአደሩም ያውቃል:: በመሆኑም አመራሩና አርሶአደሩ እጅ ለእጅ ተያይዞ ለልማት ዕድገት ተነሳስቷል ማለት ይቻላል::
አዲስዘመን፦ዞኑ በሚያከናውነው የግብርና ሥራ ዋና ዋና ብሎ የሚለያቸው ምርቶች አሉ?
አቶ ዳዊት፦ ከዋና ዋና ምርቶቹ የቡና ምርት ይጠቀሳል:: በቆሎም ከሌላው ሰብል በስፋት ይመረታል:: በክላስተር የአመራረት ዘዴ የበቆሎ ምርት ከአንድ ሄክታር በአማካይ እስከ 50 ኩንታል፣ከፍ ሲል ደግሞ እስከ አንድ መቶ ኩንታል ምርት ይገኛል:: ከምርታማነት አንጻር በአንድ ሄክታር እስከ አምስት ኩንታል ነው የጨመረው:: ማሽላ፣ጤፍ፣ጥራጥሬና የቅባት እህሎች በቅደም ተከተል ይገለጻሉ:: በተጨማሪም አትክልትና ፍራፍሬ ናቸው::
አዲስዘመን፦ ምርትና ምርታማነትን ካደገ በኃላ ገበያ ላይ ወጥቶ አርሶአደሩን፣አካባቢውንና ሀገርን ተጠቃሚ ማድረግ ይኖርበታል:: የገበያ ትስስሩስ ምን ይመስላል?
አቶ ዳዊት፦አምራቹና ተጠቃሚው እንዳይገናኝ ትልቁን ችግር እየፈጠረ ያለው በመካከል ላይ ሆኖ የሚደልለው ነው:: በመሆኑም ችግሩ ሰው ሰራሽ ነው:: ይህን ለመቅረፍ የሰንበት ገበያ ተጀምሯል:: ይህ በመጠኑም ቢሆን ያቃልላል ተብሎ ይታመናል:: አርሶአደሩን ንግዱን ከሚመራ የመንግሥት ተቋማት ጋር በማስተሳሰር ከሸማቹ ጋር በቀጥታ እንዲገበያይ ጥረት እየተደረገ ነው:: በዞኑም ኤግዚቢሽንና ባዛር በሚል ሸማቹን ከአርሶአደሩ ጋር የሚያገናኝ ሥራ ተጀምሯል:: ጅምሩም ያበረታታል:: አጠናክረን በመቀጠል ለውጥ እንዲመጣ ጥረት እናደርጋለን::
አዲስ ዘመን፦ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን::
አቶ ዳዊት፦እኔም አመሰግናለሁ::