
አዲስ አበባ፡- በየእምነት ተቋማቱ ያሉ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች የቆየውን የሕዝቡን ተቻችሎ የመኖር እሴት ለማስቀጠል ተቀራርበው መነጋገርና ለሀገር ሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ሙሺድ አስማማው አህመድ አስታወቀ።
ሙሺድ አስማማው አህመድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቀው፤ በየእምነት ተቋማቱ እየተፈጠረ ያለውን አለመግባባት ለመቅረፍ እንዲሁም እየጠፋ ያለውን የመከባበርና የመቻቻል እሴት ቀድሞ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ያስችል ዘንድ ሁሉም የሃይማኖት መሪዎችና አባቶች ተቀራርበው መነጋገርና በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
‹‹በተለይ አሁን ያለንበት ወቅት ብዙ ነገሮች የተበላሹበት ነው›› ያለው ሙሺድ አስማማው፤ ከዚህ ቀደም ግን የእምነት ተቋማቱ የታጣሉ ሰዎችን ለማስታረቅ ወይም ደግሞ ነገሮች ሲበላሹ እንዲያስተካክሉ የእምነት አባቶች ሚና የጎላ እንደነበር አመልክቷል። አሁን ግን ፖሊስ ሄዶ የሚያደራድረው የእምነት ተቋማት መሪዎችን እንደሆነ አንስቶ ይህም ለትውልዱ መልካም አርዓያነት እንዳያሳጣ ስጋቱን ገልጿል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም የሀገርን ወይም የሕዝብን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ የራሱን ፍላጎት ለማሳካት የሚሯሯጥ መሆኑ፤ እንዲሁም የፖለቲከኞቹ ተፅዕኖ እየጎላ በመምጣቱ እንደሆነ አብራርቷል።
‹‹አሁን እየሄድንበት ያለው መንገድ ስህተት ነው። በየቦታው ዘርን መሰረት ተደርጎ ጭፍጨፋ ተካሂዷል፤ መስጅድና ቤተክርስቲያት ተቃጥለዋል ፤ ወድመዋል፤ የእምነት ሰዎች ተገድለዋል፤ ይሁንና ቅዱስ ቁርዓንም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዙት ሁሉም በፍቅርና በመቻቻል እንዲኖር ነው›› ብለዋል። በመሆኑም የእምነት መሪዎቹ ከሁሉ በላይ የፈጣሪን ትዕዛዝ ለማስከበር ከቆሙት የስህተት መንገድ ሊመለሱና ህዝቡን ሊታደጉ እንደሚገባ ሙሺድ አስማማው አስገንዝቧል።
አክሎም ‹‹ከሁሉ በላይ ግን እምነታችን እንደሚያዘው በሰላምና በፍቅር ከሁሉ ጋር ተስማምተን ለመኖር ፍቃደኛ መሆንና ልባችንን ማዘጋጀት አለብን። በተለይ የእምነት አባቶች ስጋዊ ፍላጎታቸውን አሸንፈው ለሰላምና ለፍቅር መኖርን በህይወታቸው ተርጉመው ሊያሳዩ ይገባል›› በማለት ተናግሯል። ምዕመኑ የሚከተለውና የሚያምነው እነሱን በመሆኑ በሁሉም የእምነት ተቋም ያሉ መሪዎች አሁን ከያዙት አቋም ተመልሰው ህዝቡን ማድመጥ እንደሚገባቸውም አመልክቷል።
እንደ ሙሺድ አስማማው ገለጻ፤ አሁን ላይ በየእምነት ተቋሙ የፀጥታ አካል ካልቆመ አስተማኝ ሰላም ስለመኖሩ አጠራጣሪ ሆኗል። በተለያየ እምነት ተቋማት ብቻ ሳይሆን በአንድ ሃይማኖት ውስጥ እርስ በርስ ግጭት እየተፈጠረ አንዱ ሌላውን ለማሳሰር ሲሯሯትም ይስተዋላል። በየቀኑ የሚፈጠረው ህገወጥ ተግባር እየተለመደ ከመምጣቱ የተነሳም የበርካታ አማኞች አመለካከት ተቀይሯል። ፈጣሪ ለሰው ልጅ የሰጠው ክብርም ተረስቷል።
በመሆኑም ሁሉም የእምነት መሪ እንዲህ አይነቱ የሞራል ዝቅጠት ውስጥ እንዴት እንደገባ ራሱን መፈተሽ እንደሚገባው ሙሺድ አፅንኦት ሰጥቶ ተናግሯል። ‹‹ በዋናነት ከዚህ የስህተት መንገድ ህዝቡን መመለስ የሚችሉት እነዚህ የእምነት አባቶች በመሆናቸው ራሳቸውን በመጀመሪያ መፈተሽንና ወደ ትክክለኛው ሃይማኖታዊ ልምምድ መግባት አለባቸው›› በማለት አስገንዝቧል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም