በመጽሐፍ ቅዱስ ዘፍጥረት ላይ የአብረሀምንና የሎጥን ታሪክ እናገኘለን:: አብረሀም የእግዚአብሄር ልጅነትን ከሚገልጽባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ወንድማማችነት ነው..እኛ ወንድማማቾች ነን ሲል፤ አብረሀም የሰውን ልጅ ሁሉ የሚወድ፣ የሚያቀርብ ወንድሜ ብሎ የሚጠራ ሰው ነበር:: አብረሀም ሎጥን ከመውደዱ የተነሳ እግዚአብሄር ለክብር ብቻውን ሲጠራው ብቻዬን አልከብርም ብሎ ያልተጠራውን ሎጥን ይዞት እንደወጣ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል:: ይሄ ብቻ አይደለም በእግዚአብሄር ጥሪ ወደ ከንዓን ሲሄዱ በመንገድ ላይ ያልተጠበቀ ሀብት ያገኛሉ:: በዚህም ድንገተኛ ሀብት በመካከላቸው ቅራኔ ገባ:: የሎጥ ልብ ሻከረ፣ በተገኘው ድንገተኛ ሀብት ወንድሜ ነህ ካለው ከአብረሀም ጋር ቅራኔ ውስጥ ገባ:: አብረሀምም አለ… “እኔና አንተ ወንድማማቾች ነን ልንጣላና ልንቀያየም አይገባም:: መፋቀር ከቻልን ያገኘንው ሀብት ከእኔና ከአንተ አልፎ ለሌሎች ይተርፋል..ተው ወንድማማቾች ነን” ሲለው ሎጥ ግን እሺ አላለም::
ባገኙት ድንገተኛ ሀብት አብሮ መሄድ፣ አብሮ መቆም ለሎጥ የማይቻል ሆነበት:: በዚህ ጊዜ አብረሀም አንድ ነገር አሰበ…ወንድሙ ሎጥ እንዳይከፋ ሲል ‹አንተ ቀድመህ ምረጥ፣ የፈለከውን ውሰድ እኔ ከአንተ ከተረፈው እጠቀማለሁ› አለው:: ይሄን ትህትና..ይሄን ሰውነት፣ ይሄን ወንድምነት በምን ትገልጹታላችሁ? አብረሀም እንዲህ ነበረ:: ሎጥም በአብረሀም ምርጫ ተስማምቶ ጥሩ ያለውን ነገር ለራሱ ወስዶ ጥሩ ያላለውን ለአብረሀም ትቶ በሻከረ ልብ ከወንድሙ ተለይቶ ሄደ:: በዚህ ሁሉ ውስጥ አብረሀም ስለሎጥ ያስብ ነበር:: በተለያዩባቸው ጊዜያቶች ውስጥ ወንድሙ እንዴት እንደሆነ፣ ምን እንደገጠመው በመጨነቅ በየእለቱ ሰዎችን ሲያገኝ ይጠይቅ ነበር::
ከእለታት አንድ ቀን ግን ስለ ወንድሙ ሎጥ ክፉ ነገር ሰማ:: ሎጥ ወደሚኖርበት ሰዶም ከተማ አምስት ንጉሶች ወርደው ሎጥንና ከብቶቹን ወስደው ሄዱ› የሚል:: በዚህ ጊዜ አብረሀም አልተደሰተም…የራሱ ጉዳይ፣ እሰይ እንኳንም ዘረፉት አላለም:: ወንድሙን ለማገዝ ተነሳ እንጂ:: በቤቱ ያሉ ወዳጆቹን አሰልፎ ስለ ወንድሙ ስለ ሎጥ ተንገላታ:: ንብረቱንም አስመለሰለት:: አብረሀም የዘመተው ወንድሙ ሎጥ አግዘኝ ብሎት አልነበረም፤ ውስጡ ባለው ፍቅርና ወንድማዊ ስሜት እንጂ:: የአብረሀም ልብ ይገርማል…በዚያ ሰዓት የገፋውን ሎጥን ወንድሜ ለማለት አልተቸገረም ነበር:: ሰው መሆን ማለት እንደዚህ ነው:: በልባችን ውስጥ ብዙ ፍቅር፣ ብዙ መውደድ ሲኖር እንደ አብረሀም ነው የምንሆነው:: ጊዜ እየጠበቅን አንወድም፣ ጊዜ እየጠበቅን አንጠላም::
ዓላማችን ከዛሬ ያለፈ ነገን ማየት ከሆነ በመልካምነታችን የሰዎችን ክፋት፣ የሰዎችን ጥላቻ ማሸነፍ የሚችል ሰውነት ልንገነባ ያስፈልገናል:: አሁን ላይ እንደ ሃገር ችግር እየፈጠሩብን ካሉና ከሌሉን ነገሮች ውስጥ አንዱ ይሄ በጥሩነት ሌሎችን ማሸነፍ አለመቻላችን ነው:: በሀሳብ ካልተግባባን መለያየትን ምርጫ ያደረግን ሕዝቦች ነን:: ሊያግባቡን የሚችሉ ብዙ ነገሮች እያሉ ለመለያየት ምክንያት የምንፈጥር ነን:: በመተው ማሸነፍ፣ በይቅርታ መርታት ዋጋው ምን ያህል እንደሆነ ገና አልደረስንበትም:: የወንድማማችነት መንፈስ በየትኛው ሁኔታ ውስጥ የማሸነፍ መንፈስ ነው:: ራሳችንን ለፍቅርና ለአብሮነት ስናስገዛ ወንድማማችነት በውስጣችን ይለመልማል ይሄ መሆኑ ተነጋግረን ባንግባባ እንኳን ላለመለያየት ዋስትና ይሰጠናል::
በሎጥ መቀየር የአብረሀም ልብ አልተቀየረም:: በሎጥ መሸነፍ አብረሀም አልተሸነፈም:: በሎጥ ክፉ ሀሳብ የአብረሀም ሀሳብ አልተበረዘም:: የሎጥ ሀሳብ የወንድማማችነት ሀሳብ አልነበረም፣ የአብረሀም ሀሳብ ግን የአንድነት ሀሳብ ነበር:: በልባችን ውስጥ ሰውነት ሲኖር ሌሎችን ከቁስና ከንብረት በላይ እናደርጋቸዋለን:: ሰው ስንሆን፣ ሰብዓዊነት ሲገባን እያቀያየሙን ያሉ ነገሮች የማይረቡ እንደሆኑ እንደርስባቸዋለን:: እውነትና ፍትሕን ስንረዳ እስከዛሬ የተራመድንባቸው ጎዳናዎች ምን ያክል ጎርባጣ እንደሆኑ እንደርስባቸዋለን:: እግዚአብሄርን ስንፈራ፣ ሚዛናዊነትን ስናውቅ የሰውን ልጅ በቁስና በገንዘብ መመዘን እናቆማለን:: በአብረሀምና በሎጥ መካከል የሆነው ይሄ ነበር:: አብረሀም ለወንድማማችነታቸው ሲል ብዙ ነገር ትቷል:: እኛ እኮ ወንድማማቾች ነን እነዚህ ነገሮች ሊያጣሉን አይገባም ሲል ሎጥን ነግሮታል::
ሎጥ ግን እንደ አብረሀም በእውነትና በፍትሕ፣ በሚዛናዊነትና በተፈጥሮ መካከል አልነበረም:: በጊዜያዊ ጥቅም ታውሮ ከሁሉ የሚበልጠውን ወንድማማችነታቸውን ሽሯል:: ከሁሉም የሚደንቀው ደግሞ ከዚህ በኋላ የሆነው ነው..አብረሀም ሎጥን እስከመጨረሻው ተከትሎታል..የከዳውን ወዳጁ በጠላቶቹ እንዳይሸነፍ ተዋግቶ ንብረቱነም አስመልስሎታል..ይሄ ሰውነት ዛሬ በእኔና በእናንተ ላይ እንዲገለጥ እሻለሁ:: እንደ አብረሀም ሰው እስካልሆንን ድረስ ያጣናቸውን ማስመለስ አንችልም:: እንደ አብረሀም ወንድማማችነትን እስካላስቀደምን ድረስ የምንገነባው ሃገርና ሕዝብ የለም:: ሃገራችን ኢትዮጵያ ለወንድማማችነት ቅድሚያ የሚሰጡ ሀሳቦች፣ ውይይቶች ያስፈልጓታል:: ዛሬ ላይ እየረበሹን ያሉ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮቻችን ወንድማማችነት ያልጎበኛቸው የራስ ወዳድነት ውጤቶች ናቸው::
እኚህ ችግሮቻችን ተነጋግረን ሳንግባባ፣ ተወያይተን ሳንስማማ አለያይተውን ሰንብተዋል:: ይህ ጊዜ እኚህን ችግሮቻችንን በወንድማዊ ስሜት ለመፍታት ጥሩ ጊዜ ነው:: ሃገራችን ለሰላም ቅድሚያ የሰጠችበት ሰሞን ላይ ነን፣ በሃገራዊ ምክክር ለዘላቂ ሰላም ሥራ እየሠራን ያለንበት ጊዜ ላይ ነን፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ በእርቅና በወንድማማችነት ስሜት ወደ ፊት ለመሄድ የተሰናዳንበት ማለዳ ላይ ነን:: ችግሮቻችን እንደ አብረሀም አይነት ልብና መንፈስ ይሻሉ:: አብሮ ለመኖር፣ አብሮ ሃገር ለመገንባት የጋራ የሆኑ ማኅበራዊ እሴቶች ሊኖሩን ይችላሉ::
እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከቀረው ዓለም በተለየ መልኩ ሊያግባቡንና ሊያቀራርቡን የሚችሉ ብዙ ነገሮች ያሉን ሕዝቦች ነን:: ትህትና አጣን እንጂ፣ ይቅር ባይነትን ሸሸግን እንጂ እንደ ድርና ማግ፣ እንደ ራስና ጸጉር የተሸመኑ በርካታ የአንድነት ቀለማት ነበሩን:: አሁን ላይ የጠፋን የአንድነት ታሪክ፣ የአንድነት አሻራ ሳይሆን የአንድነት ሀሳብ ነው:: አሁን ላይ ያጣነው የጋራ ባህል፣ የጋራ ሥርዓት ሳይሆን የጋራ እውነት ነው:: እዚች ሃገር ላይ ሎጥን የሆንን ብዙ ሰዎች አለን..እንደ አብረሀም ይቅር ስንል፣ ስንወድና ስናፈቅር የኖርንም አለን:: ከሁለቱ የትኛው ዋጋ እንዳለው መመዘን ይኖርብናል:: ራሳችንን ሚዛን ላይ አስቀምጠን ወይ አብረሀምን አሊያም ሎጥን መሆን ምርጫችን ነው:: ሃገር የሚወዱ ሁሉ፣ በጎ ትውልድ የሚናፍቁ ሁሉ በአብረሀም የወንድማማችነት መንፈስ ውስጥ መኖር እንደሚሹ አልጠራጠርም:: አሁን ላይ ለሃገራችን የሚያስፈልጋት እሱ ነውና::
‹ወንድሙን ታግሎ የጣለ ጀግና አይባልም…› በዚህ ማኅበራዊ አባባል ውስጥ ለዘመናት ኖረናል:: ግን ደግሞ ወንድሞቻችንን ታግለን ሳንጥል የኖርነው ጊዜ የለም:: በወንድሞቻችን ላይ የበላይ ሳንሆን ወይም ደግሞ ለመሆን ሳንሞክር የቀረንበት ጊዜ የለም:: ደስታዎቻችንን የምንፈልገው በወንድማችን መውደቅ ውስጥ፣ በወንድማችን ሀዘን ውስጥ ነው:: እንደ አብረሀም የሆነ ምንም የለንም:: ትላንትም ዛሬም እርስ በርስ የምንገዳደል፣ እርስ በርስ ጦርነት የከፈትን፣ እርስ በርስ የተገፋፋን ነን:: ለዚህም ነው እኛ ወንድማማቾች ነን ስል የተነሳሁት:: መበርታት ካለብን በድህነት ላይ እንበርታ፣ መዝመት ካለብን ለዘመናት ጠፍንጎ በያዘን ኋላ ቀርነት ላይ እንዝመት:: በድህነትና በኋላ ቀርነት እየኖርን በወንድማችን ላይ የምንነሳበት ምንም ምክንያት አይኖርም:: በአንድነት በመቆም የምናስተካክላቸው ብዙ ሃገራዊ ጉዳዮች አሉብን:: ጊዜአችንን፣ ገንዘባችንን፣ እውቀታችንን ለሁላችንም ጠላት በሆኑ ማኅበራዊ ችግሮቻችን ላይ ማድረግ አለብን::
ይሄኛው ትውልድ ስለ ሃገሩ ሲል ወንድማማችነትን በሚገባ ማቀንቀን አለበት:: ተለያይተን ያጣናቸውን በአንድነት በመቆም ማስመለስ አለብን:: ለዚህ ትውልድ አብረሀም ማነው? ሎጥስ እንዴት ይገለጻል? የአብረሀም ልብ እንደ ሎጥ ልብ በራስ ወዳድነት የቆሸሸች ብትሆን ኖሮ በመካከላቸው ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስባችሁታል? በአብረሀም ትዕግስት፣ በአብረሀም አርቆ ማሰብ ብዙ ነገሮች ተስተካክለዋል:: እኛም እንደ አብረሀም ያለ ሰውነት ያስፈልገናል:: እንደ አብረሀም ያለ ትዕግስት፣ እንደ አብረሀም ያለ ተስፋ ግድ ይለናል:: ስንሞቅ የሚያበርዱን፣ ስንቆጣ የሚያረጋጉን ፍቅር ለበስ ነፍሶች ያስፈልጉናል:: በአንድ አይነት እሳታዊ ስሜት ሃገር አትቆምም፣ ቤንዚል ላይ ክብሪት በሚጭሩ አይነት ሰይጣናዊ አስተሳሰቦች ትውልድ አይፈጠርም::
እኛ ወንድማማቾች ነን የሚል ዘመን ተሻጋሪ እሳቤ ያስፈልገናል:: ከዛሬ ወደ ነገ፣ ከነገም ወደ ከነገ ወዲያ የሚሻገር አብረሀማዊ ነፍስና ስጋ ያስፈልገናል:: ጥላቻዎቻችንን በፍቅር፣ መለያየቶቻችን በአንድነት ማሸነፍ ይኖርብናል:: ወንድማማችነት ከአንድ እናትና አባት መወለድ አይደለም፤ የሰው ልጅ በፈጠረው በአምላኩ በኩል ወንድማማች ነው:: ልባችንን ከጥላቻ ማጽዳት ከቻልን ወንድማማቾች እንደሆንን እንደርስበታለን:: በመካከላችን ያለውን ተፈጥሮአዊ ፍቅር፣ ተፈጥሮአዊ አንድነት፣ ተፈጥሮአዊ ወንድማማችነትን የሻረው ጥላቻችን ነው:: ሰው ማፍቀር ሲጀምር ፍጽምናን ይለምዳል:: ሰው መውደድ ሲጀምር የፈጣሪን ስውር ጥበብ ይደርስበታል:: ሰው አጠገቡ ያለውን ሌላ ሰው ወንድሜ ብሎ ሲጠራ ወደ ተወው ድንቅ ተፈጥሮው ይመለሳል፤ ኃይል ይጎበኘዋል:: ዛሬ ላይ በአንድ ሃገር፣ በአንድ ታሪክ ላይ ቆመን መግባባትና መስማማት ያቃተን ለመውደድ የተሠራ ልባችንን በጥላቻ ስለሞላነው ነው:: ፍቅር ተፈጥሮአዊ ነው…ጥላቻ ደግሞ ተምረን የምናገኘው ሰው ሠራሽ እሳቤ ነው:: ወንድማማችነት የፈጣሪ ስጦታ ነው፣ ጥላቻ ግን እኛ ፈጥረን፣ እኛ መግበን እኛው ያሳደግነው የክፉ ሀሳብ ልጅ ነው:: አሁን ላይ እየገዛን ያለው ኃይል ተፈጥሮአዊ ኃይል ሳይሆን በልምድ ያመጣነው፣ እኛው ወልደን ያሳደግነው የጥላቻ ኃይል ነው:: አሁን ላይ ተነጋግረን መግባባት፣ ተግባብቶ በአንድ መቆም ያቃተን በዚህ የጥላቻ ኃይል ውስጥ ስለቆምን ነው:: በፍቅር ወደ ተበጀው የአንድነት ሰውነት እንመለስ::
በተፈጥሮ አንድ አይነቶች ነን፣ ፍቅርን ለብሰን፣ አምላክነትን ተጎናጽፈን ነው የተወለድንው:: እውነትን፣ በጎነትን፣ ርህራሄን ተቀብተን ነው ሰው የሆንው:: በሂደት ግን ይሄን ልዕልና አጥተናል:: አንተ ውስጥ ያለችው ነፍስ እኔ ውስጥ ያለችው ናት:: አንተ ውስጥ ያለው ልብ እና አንተ ውስጥ ያለው አእምሮ እኔ ውስጥና ሌላው ሰው ጋ ያለ አእምሮና ልብ ነው:: ተፈጥሮ ጥላቻን እንዳናውቅ አድርጎ እንዲህ ነበር የቀመረን:: አሁናዊ ልብና አዕምሯችን ግን እንደትላንት አይደለም በሰማንው፣ በተነገረን፣ በተማርነው፣ ባየነው የጥላቻ መንፈስ ተሞልተን ያን የጥንቱን አምላካዊ ኃይላችንን አጥተናል:: በአሉባልታ፣ በትችት፣ መሠረት በሌለው ወሬ በነዚህ ሁሉ እየተገፋፋን ነው:: ሰው ከፍቅር ሲርቅ፣ ነፍስ ከመውደድ ስትሸሽ ለመኖር አቅም አያገኝም:: አሁን ላይ እየሞትን ያለነው፣ እየባከንን ያለነው ከፍቅር ከሸሸ፣ ከሰብዓዊነት በራቀ ልብና አእምሮ ነው:: ወደ ተፈጥሮ እንመለስ፤ ወደ አንድነታችን፣ ወደ ጥንቱ ወንድማማችነታችን እንመልከት::
ሰውነት ከሀብት፣ ከቁስ በላይ ነው:: ጊዜያዊ ጥቅማጥቅም ሊያጠፉት አይገባም:: በተለያዩ ነገሮች ላይ ላንግባባ እንችል ይሆናል፤ ወንድማማችነታችን አብሮን ካለ ግን በጭራሽ ወደ መለያየት አንሄድም:: የምንለያየው፣ ተነጋግረን የማንግባባው በመካከላችን የአንድነትና፣ የወንድማማችነት መንፈስ ሲጎድል ነው:: ይህ ሲሆን ደግሞ ኢትዮጵያ ታሳዝነኛለች፤ አንድነት ርቆን፣ ወንድም በወንድሙ ላይ እየተነሳ ለለውጥ መትጋታችን ትርጉም ያጣብኛል:: ጠመንጃ ታጥቀን፣ ጎራዴ ስለን በጠላትነት እየተያየን ወደ ፊት ለመሄድ መነሳታችን ያስነባኛል:: በመጨረሻም እንዲህ አልኩ፡- በነገር ቁርሾ የቆሸሹ፣ በአሉባልታ ትርክት የወየቡ ኢትዮጵያዊ ታሪኮቻችን ይታደሱ ዘንድ ወንድማማችነት ግድ ይለናል!፤ ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም