ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር የሚደረገው ጦርነት ጋብ ብሎ ቆይቷል፤ እንዲያውም ነገሮች በሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መልኩ ሊቋጩ እንደሚችሉ የሚያሳዩ አንዳንድ ምልክቶችም እየታዩ ይመስላል፡፡ እነዚህ ጥቃቅን ብልጭታዎች ግን በእርግጥ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች ናቸውን? ብለን ስንጠይቅ፤ በድፍረት አፍን ሞልቶ አዎ ለማስባል የሚበቁ ሆነው አናገኛቸውም፡፡ ከነዚህ በጎ ብልጭታዎች በተቃራኒው ስጋት የሚፈጥሩ ምልክቶች አሁንም በስፋት እየታዩ ነው፡፡
ለዚህ ማሳያነት የተወሰኑ ምሳሌዎችን እንመልከት፤- በዚህ ሳምንት የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘገባ እንዳመለከተው፤ ወደ ትግራይ እንዲገባ የተደረገውን የእርዳታ እህል ሕወሓት ለሕዝቡ ሳይሆን ለካድሬዎቹ እያደለ ስለመሆኑ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ ተናግረዋል፡፡ እርግጥ ይህ ሕወሓት የኖረበት ባህሪ ስለሆነ ባያስደንቅም ቅሉ የሚያመለክተው ግን ሕወሓት አሁንም ቁጭ አድርጎ የሚቀልበው ኃይል እንዳለ ነው፡፡ ይሄ አሳሳቢ ነው፡፡
በመድኃኒት በኩልም ተመሳሳይ ሁኔታ
ይታያል፡፡ አሸባሪ ቡድኑ በወረራ ይዞት ከነበረው የአማራ ክልል ለብዙ ጊዜ የሚበቃ መድኃኒት እንደዘረፈ ይነገራል፤ ከዚህ በተጨማሪ የዓለም ጤና ድርጅት መድኃኒት እያጋዘለት ይገኛል፡፡ ሆኖም ዛሬም በክልሉ ያሉ ሆስፒታሎች መድኃኒት አልባ መሆናቸውን ነው እማኞች የሚናገሩት፡፡ ይህም የሚያመለክተን ቡድኑ መድኃኒቱን ከሕዝቡ ነፍጎ ለታጣቂዎቹ እያከማቸና ለሌላ ዘመቻ የሚፈልገው መሆኑን ነው፡፡ በዚህም ሌላ ሴራ እየጠነሰሰ መሆኑን የሚያስረዳ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ማሰቡ የተሻለ ይሆናል፡፡
ምክንያቱም በዚህኛው ጦርነት ብቻ አንድ ትውልድ ለጦርነት የማገደው የሕወሓት አመራር፤ የቀሩትን የትግራይ ልጆች ለመጨመር ይገደዋል ተብሎ ሊታሰብ አይችልም፡፡ ከሳምንት በፊት የሕወሓቱ መሪ ዶ/ር ደብረጽዮን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ነገሮች እነሱ በሚፈልጉት መልኩ ካልሄዱ አሁንም አጎራባች ክልሎችን ለመውረር እንደሚሞክሩ መግለጻቸውም የሚታወስ ነው፡፡ የሽብር ቡድኑ መሪ ዶክተር ደብረጽዮን፣ የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክትም በተመሳሳይ ስለ ሰላም ምንም የማያወራ በተቃራኒው አይዟችሁ ገና እንዋጋለን የሚል መንፈስ የታየበት ነበር፡፡
የትግራይ ቴሌቪዥን የየቀኑ ዘገባ የሚያመለክተውም፣ አሁንም ቢሆን የፖለቲካ አመራሩ ከጦርነት ስካር እንዳልወጣ ነው፡፡ ከያለበት ምሽግ ሆኖ ሌላ የትግራይ ትውልድ ወደ ጦርሜዳ ለመግፋት እንዳቀደ የሚያመላክቱ መረጃዎች እየወጡ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው በየዋሻው የተደበቀው የሕወሓት አመራር ከጦርነት ውጪ ሌላ አማራጭ ያለው አይመስልም፡፡ ለዚህም ቢያንስ አንድ ውስጣዊ እና ሌላ አንድ ውጫዊ ምክንያት ማቅረብ ይቻላል፡፡
ውስጣዊው ምክንያት፣ በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ ከሚነገረው በላይ ስር የሰደደ እንደመሆኑ ፖለቲካዊ ችግር አስከትሎ በአመራሩ እና በሕዝቡ ዘንድ አተካሮን አስነስቷል፡፡ እናም ሰላም ከወረደ ሕዝብ ወሳኝ የሆኑ ጥያቄዎችን ማንሳት ስለሚጀምር፤ ያኔ ሁሉም ትግራዋይ ከየትኛውም ጠላት ከሚለው ኃይል በበለጠ ዋነኛ ጠላቱ ሕወሓት እንደሆነ ይገነዘባል፡፡ ስለዚህም ለሕወሓት ይህ አስፈሪ ወቅት እንዳይወጣ ያለው አማራጭ በቋሚነት ጠላት ፈጥሮ በመደበኛነት እየተዋጉ መቀጠል ነው፡፡
አንዳንዶች ይህን ጥያቄ ገና ከአሁኑ ማንሳት ቢጀምሩም፣ ዝም በሉ እየተባሉ ነገሩን ለማዳፈን እየተሞከረ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሕወሓት ኢመደበኛ ቃል አቀባይ ከሆኑት ሰዎች አንዱ የሆነው ፍጹም ብርሀነ ሰሞኑን በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ «ጠላት (ኢትዮጵያውያን) እንዳይደርስበት ብለን ዝም ስንል መሪዎቻችን ያንቀላፋሉ። ችግሮቹን በአካል ተገኝተን ብንናገርም የሚሰማን አካል የለም። እዚህ መጥተን (FACEBOOK ላይ) ብንናገር ለጠላት አሳልፋችሁ ሰጣችሁን ይባልና እንደ ጠላት ተቆጥረን ይዘመትብናል። ታዲያ ዝም ይሻላል?» ሲል አስፍሯል፡፡
ይህ የሚያመለክተው የሕወሓት አመራር ምንም ዓይነት ስልጣኑን የሚጋፋ ሀሳብ ላለመቀበል እና ግፋ እያለ ወጣት እየማገደ ለመዝለቅ መሞከሩን
ያስገንዝባል፡፡ አሁን ላይ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ባለው ሰብአዊ ቀውስ የተነሳ የወሲብ ንግድ፤ ሕገወጥ የሰው እና የገንዘብ ዝውውር፤ እና ሌሎችም ችግሮች ተስፋፍተዋል፡፡ እንደ ዶ/ር ደብረጽዮን እና አቶ ጌታቸው እንዲሁም ጄነራል ጻድቃን ያሉት መሪዎችም ይህን አሰቃቂ ሁኔታ በማስቀጠልና ጦርነት በየጊዜው በመጀመር እስከ መጨረሻው ስልጣን ላይ መቆየት ይፈልጋሉ፡፡
ውጫዊው ምክንያት ደግሞ በውጭ ሀገራት የሚኖረው በተለይም በሕወሓት ከለላ ከሀገር የወጣው እና በስደት የሚኖረው ኃይል ሕወሓት በጦርነቱ የደረሰበትን ሽንፈት መቀበል አለመፈለጉ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ጦርነቱን በዝና እንጂ በአካል ስላላየ አሁንም ቢሆን መዋጋት እንደሚችል ያስባል፡፡ ለዚህም ያለውን የኢኮኖሚ አቅም በሙሉ እየተጠቀመ በሀገር ቤት ያለውን ሰላማዊ ተጋሩ እየተጫነ ነው፡፡ ይሄ ጦርነትን ያላየ የፌስቡክ አርበኛ የሕወሓት ደጋፊ ሰልፍ በማድረግ፤ ዝመት እና ሙት የሚል የቀረርቶ ሙዚቃ በመሥራት እና ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ጀግና ለመምሰል በመሞከር ጊዜውን የሚፈጅ ኃላፊነት የማይሰማው ኃይል
ነው፡፡ ሀገር ቤት ያለው ተጋሩ ጦርነቱን አቁሙልን፤ ሰላም ይውረድልን ብሎ ሲናገር ቁጣ እና ጩኸቱ የሚያይለውም ከዚህ ኃይል ነው፡፡
እነዚህ ውስጣዊ እና ውጫዊ ሁኔታዎች ባሉበት ሁኔታ ሕወሓት ሙሉ ለሙሉ ለሰላማዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሄ ዕድል ሰጥቶ አርፎ ይቀመጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት እና አደገኛ መዘናጋት ነው፡፡ ስለዚህም ለሰላማዊ አካሄዶች ዕድል መስጠቱ እንዳለ ሆኖ ጥንቃቄ ግን
ያስፈልጋል፡፡ ሕወሓት አሁንም ችግር ፈጣሪ ለመሆን በቂ አቅም እንዳለው ግንዛቤ መውሰድ ይገባል፡፡ የመጀመሪያውንም ጦርነት የተዋጋው ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የሕዝብ ጎርፍ በመፍጠር ነበር፤ አሁንም ቢሆን ይህን ለመድገም ችግር የለበትም፡፡ ካለፈው ጦርነት የተረፈውን፤ ባለፈው ያልዘመተውን፤ ከትግራይ መውጫ አጥቶ ታንቆ የቆየውን እና ተስፋ የቆረጠውን ወጣት፤ በጥቅሉ ከሕፃን እስከ አዛውንት ሰብስቦ ለማሰለፍ እንደሚችል የሚታመን ሀቅ ነው፡፡
አንዳንድ ጭምጭምታዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነም፤ ሕወሓት የክረምቱን ወቅት ተጠቅሞና ጉም ተገን አድርጎ፤ አንድ ተጨማሪ ሙከራ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጭምጭምታዎችን ሙሉ ለሙሉ እውነት ነው ብሎ ለመቀበል ቢያስቸግርም፣ አይሆንምን ሳይሆን ይሆናልን አስቦ ጥንቃቄ ማድረግ ግን የበለጠ ይጠቅማል፡፡ ወቅታዊው ጸጥታ እንዲቀጥል ከፈለግን ከዝምታው ጀርባ ያለውን እንቅስቃሴም መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2014 ዓ.ም