ሁሌም እንደሚባለው አካል ጉዳተኝነት ተፈጥሯዊ አይደለም። ድንገት መጥ እንጂ ለአንድ ሰው፣ በተለይ አካል ጉዳተኛ ይሆን ዘንድ የተሰጠው ችግር አይደለም። በዓለም አቀፍ ከአንድ ቢሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች፣ በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከተለያየ ዓይነት የአካል ጉዳት ጋር የመኖራቸው ምስጢር ይኸው እንጂ ሌላ አይደለም። ለዚህም ነው የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ከትናንት በስቲያ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ ችግሩን በ«ማንኛውም ሰው ላይ ከውልደት እስከ ዕለተ ሞት ድረስ በማይክሮ ሰከንዶች ውስጥ የአካል ጉዳት ሊከሰት ይችላል። ክስተቱ በሰከንዶች ሊፈጠር የሚችል በመሆኑ ጉዳዩን የጋራ አድርጎ ከልብ መሥራት ያስፈልጋል፤ ጉዳዩ ለአካል ጉዳተኞች ብቻ ሊተውና ሊገፋ አይገባም» በማለት የገለፁት። ስለዚህ ምን ይደረግ?
በዓለማችን አንድን የሚገፋ የማይመስልን ችግር ከስሩ ፈንቅሎ ለመጣል ብቸኛው በሚመስል ደረጃ መፍትሄው መደራጀት ሆኖ ከተገኘ ሰንብቷል። በአገራችንም ከአንድ ብርቱ ሁለት መዳኒቱ የሚለው አባባልም የሚያሳየን ይህንኑ የመደራጀት አስፈላጊነትን ነው። በ25ኛው የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሸን የምሥረታ ክብረ በዓል ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬም ይህንኑ በሚያጠናክር መልኩ ነው የመደራጀትን አስፈላጊነት የተናገሩት።
እንደ ሚኒስትሯ አገላለፅ አካል ጉዳተኞች በተደራጀ መንገድ የሚያካሂዱት ትግል አድልዎ እና መገለልን እያስወገደ መጥቷል፤ በአካል ጉዳተኞች ላይ ሲደርሱ የነበሩት የመገለልና አድልዎ ተግባራት ስፍራቸውን ለእኩል ዕድል እየለቀቁ ይገኛሉ። ለዚህ ውጤት መገኘት አካል ጉዳተኞች በተደራጀ መንገድ መንቀሳቀሳቸው በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው። ተግባሩም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።
ሌላውና ሊቀረፍ የሚገባው ችግር የአካታችነት ችግር ነው። እስካሁን ባለው አሠራርም ሆነ አተያይ በዓለማችን የአካታችነት ችግር በብዛት ይስተዋላል።
የአካል ጉዳተኞችም ድምፅ «አልተካተትንምና ልንካተት ይገባዋል» የሚል ነው። ይህንን በተመለከተም በተደጋጋሚ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ሲዘጋጁ ቢታዩም ተግባራዊነት ላይ ግን ችግር መኖሩ አልቀረም። ወይም፣ የአፈፃፀም ችግር አለ። በዚሁ፣ «ጉዟችን ይቀጥላል» በሚል መሪ ሐሳብ በተከበረው በ25ኛው የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን የምሥረታ ክብረ በዓል ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንደሚሉት ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ የሚሰጥ አካታችነት ያለው አሠራርም በየተቋማቱ ጎልቶ ሊወጣ፤ የአካል ጉዳተኞች መብት፣ ጥቅምና ተሳትፎ እንዲከበር የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል።
አካል ጉዳተኞች ለዘመናት ከተሳትፎና ተጠቃሚነት ተገፍተው ሊኖሩ እንደማይገባ፤ መብትና ጥቅሞቻቸውን ለማክበርም መንግሥታት፣ የአካል ጉዳተኛ ማኅበራትና አካል ጉዳተኞች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ማኅበረሰቡ እየተሻሻሉ የመጡ ሕጎችን እየተገበሩ እንደሚገኙት ሁሉ ይህንንም አጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆኑን፤ በጎጂ ልማድ፣ በተዛባ አመለካከት፣ በአግላይ ሕግጋትና በመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳም አካል ጉዳተኞች ተጋፍጠውት የነበረው ችግር ውስብስብና ለዘመናት ትውልድ የተቀባበለው ዘርፈ ብዙ መከራ እየገፉ እዚህ ስለ መድረሳቸው፤ ይህ አስከፊ ገጽታ እንዲቀየርም በመንግሥታት፣ በአካል ጉዳተኛ ማኅበራትና በአካል ጉዳተኞች፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና በአጠቃላይም በማኅበረሰቡ በኩል እየተደረገ ባለው ጥረት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጨባጭ ለውጥ ማሳየት መጀመሩን እና የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል።
ተሳትፎና አካታችነትን በተመለከተ አንድ ማሳያ ሊሆን የሚችል ተቋም መጥቀስ ይቻላል።
በበላይ ዘለቀ ቁ.2 ትምህርት ቤት ተገኝተን እንደተመለከትነው አካቶ ፕሮግራምን የያዘ በመሆኑ ለየት ብሎ አግኝተነው እንደ ነበር በስፋት የተነጋገርንበት ጉዳይ ነው። ከትምህርት ቤቱ ካገኘነው መረጃም መረዳት የቻልነው ትምህርት ቤቱ ከሙአለ ሕፃናት ጀምሮ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ፣ በሦስት ሳይክል የሚያስተምር ሲሆን፤ ለየት የሚያደርገው ከእነዚህ ሳይክሎች (ደረጃዎች?) በተጨማሪ «አካቶ»ንና ልዩ ፍላጎት ፕሮግራምን አካቶ የሚገኝ መሆኑን ነው።
እዚህ ላይ በላይ ዘለቀ ቁጥር 2ን እንደ ማሳያ እንጥቀስ እንጂ ሌሎች ትምህርት ቤቶች አይሰጡም እያልን አይደለም። እንደ አገር ካየነው ግን «አለ» ለማለት ያስቸግራል።
ይህ ፀሐፊ አሁን ያለበትን ሁኔታ ባያውቅም ባለፈው አመት «ኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲሴቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት (ኢሲዲዲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው የተባለ እና ለአካል ጉዳተኞች መረጃ የሚሰጥ 6768 የነፃ ጥሪ ማዕከል» ማቋቋሙን፤ «የዚህ የመረጃ ማዕከል ዋና አላማ ከአካል ጉዳት ጋራ የተያያዙ አስፈላጊ በድምጽ የተዘጋጁ መረጃዎችን ለአካል ጉዳተኛው እና ለተቀረው ማኅበረሰብ ማቅረብ» መሆኑን፤ «አካል ጉዳተኞች ጥያቄ ቢኖራቸው ወይንም ማካፈል የሚፈልጉት ልምድ ካለ ድምጻቸውን ቀርፀው መላክ እንደሚችሉ»፤ «ከአገልግሎቶቹ መካከልም ስለ አካል ጉዳተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለን አዲስ መረጃ መግለጽ፣ ስለ አካል ጉዳተኛነት ጠቅላላ መረጃ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ አካል ጉዳተኞች ያሉ ሕጎች፣ አካል ጉዳተኝነት ምን ማለት እንደሆነ፣ ከአካል ጉዳተኞች ጋር የሚሠሩ ምን ዓይነት ቋንቋ መጠቀም እንዳለባቸው የሚያስረዱ መረጃዎች መያዙ»፤ «ስለ አካቶ ጤና፣ ተደራሽ ስለሆኑ የጤና ተቋማት እና ስለ ጾታዊ ጥቃት፣ ስለ አካቶ ትምህርት፣ ስለ አካቶ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ ስለ ሥራ እና ሥራ ገበያ፣ የሥራ ዕድሎች መረጃ» መስጠት የሚችል መሆኑ ወዘተ በድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች ተገልፆ እንደነበር ያስታውሳል።
ይህንን እዚህ መጥቀስ ያስፈለገበት አቢይ ምክንያት ይህንን መሰል ተቋማት በየዘርፉ ሊገነቡና ሊስፋፉ የሚገቡ መሆናቸውን ለመግለፅና አካል ጉዳተኞችም እንደማንኛውም ዜጋ ተጠቃሚ መሆን ያለባቸው መሆኑን ለመጠቆም ሲሆን፤ እንደ «የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል» በመባል የሚታወቀው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም”ና የመሳሰሉትንም ሳንረሳ፤ የአካል ጉዳተኞች መብት ጉዳይ የሌላ ሳይሆን የመሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ መሆኑንም በማስታወስ ነው።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 20 /2014