የኢትዮጵያና የግሪክ ግንኙነት ረጅም ዓመት ያስቆጠረና ታሪካዊ የሚባል ነው፡፡ የንግድ ልውውጡ ግን የቆይታውን ያህል ውጤት አላስመዘገበም፡፡ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም የዘርፉ አመራሮች ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ይህንን ሁኔታ በመቀየርና በአገራቱ መካከል የተሻለ የንግድ ግንኙነት ለመፍጠር እየተሠራ ይገኛል፡፡
ሰሞኑን በግሪክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ ያደረገው ጉብኝትም ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ያለመ ነው፡፡ የንግድ ልውውጡን ለማሻሻልም በሁለቱ አገራት ንግድ ምክር ቤቶች መካከል ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ስምምነቱ በየአገራቱ ያሉ የንግድ ሁኔታዎችና የፖሊሲ ማትጊያዎች የመረጃ ልውውጥ ማድረግ፤ የንግድ ትርዒት፤ ሥልጠናዎችና የተለያዩ መርሀ ግብሮች በጋራ ማዘጋጀት፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ የሚያስችል መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ሙሉጌታ እንደሚሉት፤ የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነቱ በአገራቱ መካከል ተዋውቆና ተቀራርቦ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ያስችላል፡፡ በነጋዴዎች መካከል
የሚደረግ የእርስ በርስ ግንኙነት ደግሞ የበለጠ መተማመን ይፈጥራል፡፡ በመተማመን የሚደረግ ንግድም ውጤታማ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ስምምነቱ የሁለቱን አገራት የንግድ ግንኙነት በማስተሳሰር የበለጠ ለመሥራት ያስችላል፡፡
ባለሀብቶች እንዲገቡ መንግሥት የኢንቨስትመንቱን ማስፋፊያ ለማሻሻል የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስፋፋት የግብርና ምርት የማቀነባበር ሥራ እንዲተገበር ልዩ ትኩረት መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡ ግሪኮች በተለይም በምርት ላይ እሴት በመጨመር ረገድ ከፍተኛ አቅም ያላቸው በመሆኑ በጋራ ለመሥራት የተሻለ ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ግሪኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው የንግድ ትስስር አነስተኛ በሚባል ደረጃ ያለ መሆኑን በመጠቆምም፤ እ.ኤ.አ ከ2014 እስከ 2018 ላለፉት አምስት ዓመታት ወደ ግሪክ ምርት ተልኮ በአማካኝ 10 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ግሪኮች ወደ ኢትዮጵያ የላኩት 25 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህም ‹‹በአገራቱ መካከል ዝቅተኛ የንግድ ልውውጥ መኖሩን ያሳያል፡፡ የንግድ ሚዛኑም ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወደነርሱ ያመዝናል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ብዙ ባለሃብቶችን ለመሳብና ንግዱን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ አለባት›› ይላሉ፡፡
በገቢ ደረጃ ድርሻው ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፤ ከግሪክ የተለያዩ ማሽነሪዎች፤ ተሸከርካሪዎችና የመሳሰሉት ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡ የነዚህ መጠንም ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው ብለዋል።
ወደ ግሪክ በዋናነት የቅባት እህል፤ ቡና፤ ጥራጥሬ፣ የተፈጥሮ ሙጫና ዕጣን የሚላክ ሲሆን፤ እነዚህንም ከበፊቱ የበለጠ መጠን መላክ ይገባል ባይ ናቸው፡፡ በሌላ በኩልም፤ እሴት የተጨመረባቸውን ምርቶች መላክ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፤ ከእነርሱም በአንጻራዊነት መቀበል እንደሚያስፈልግና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ግሪኮች የተሻለ ቴክኖሎጂ ስላላቸው በኢንቨስትመንት ረገድ ግንኙነት መፍጠሩ ጠቃሚ መሆኑንም አውስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ምክትል ፀሐፊ አቶ ውቤ መንግስቱ፤ የንግድ ግንኙነቱ የተዘጋጀው በሁለቱ የንግድ ማህበረሰቦች መካከል ትስስሩን ለማጠናከር ታስቦ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በአገራቱ መካከል የነበረው የንግድ ግንኙነት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን በማመልከት፤ የግሪክ ኢኮኖሚ እየተነቃቃ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የሁለቱን አገሮች የንግድ ትስስር ለማሳደግ በሁለቱም አገራት መካከል ፍላጎት አለ፡፡ በኩባንያና በማህበራት መካከል ግንኙነት በመመስራት ፍላጎቱን ማስተሳሰር ቀጣይ ተግባር ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ውቤ ማብራሪያ፤ የንግዱ ሁኔታ መሻሻል ታይቶበታል፡፡ ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የሚመቹ ናቸው፡፡ ባለሀብቶች ወደአገር ውስጥ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንሠራለን፡፡ ስምምነት ያደረግንባቸውንም ጉዳዮች አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ምቹ ሁኔታዎችን በማስፈን ከሌሎች አገራት ጋርም የመግባቢያ ስምምነት እናደርጋለን፡፡
አቶ ኃይለ ገብርኤል አየለ ድርጅታቸው በኢትዮጵያና በአፍሪካ አገራት የግሪክ ኩባንያዎችን የሚወክል መሆኑን ይናገራሉ። ግሪኮች በኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና በሪል እስቴት ግንባታ ተሰማርተዋል፡፡ በቀጣይ በጋራ የእርሻ ሥራ ለመሥራት እየተነጋገሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡ ወደ ውጭ አገር መላክ ሳይሆን አገር ውስጥ ገብተው ልምዳቸውንና አሰራራቸውን እንዲያጋሯቸው እንደሚፈልጉም ይናገራሉ፡፡
እውቀታቸውን አጋርተውንና በአገር ውስጥ አስፈላጊ ግብአቶች አምርተን ወደ ውጭ የምንልክበትን ሁኔታ ለመፍጠር እያመቻቸን እንገኛለን የሚሉት አቶ ኃይለ ገብርኤል፤ በቀጣይም የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሊኖር ስለሚችል ከእነርሱ የንግድ ልዑካን ጋር ስንገናኝ አገር ውስጥ ገብተው ፋብሪካቸውን ተክለው በጋራ እንድንሠራ የሚያስችለንን መግባባት ለመፍጠር እንሠራለን ይላሉ፡፡
በኤልዲጄ የግሪክ ኩባንያ አማካሪው ዲዮኒ ማርዮ፤ ድርጅታቸው በዋናነት በኮንስትራክሽንና በፍሳሽ ማስወገጃ ሥራ መሰማራቱን ይጠቁማሉ፡፡ በቦሌ አራብሳ፤ በቱሉ ዲምቱና በኦሮሚያ ክልል በጋራ መኖሪያ ቤቶች ስኬታማ ሥራ መሥራታቸውንም ይናገራሉ፡፡ ኩባንያቸው የ50 ዓመት እድሜ ያስቆጠረ፤ የዳበረ ልምድ ያለውና በ100 የዓለም አገራት የሚሠራ በመሆኑ በኢትዮጵያ ለመሥራት ዕድል ማግኘቱ እንዳስደሰታቸው ይገልጻሉ፡፡
የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነት ለሁለቱም አገራት ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው የሚሉት አማካሪው ዲዮኒ ማርዮ፤ በኢትዮጵያ የግል ዘርፉ እንዲጠናከርና እንዲያድግ ያግዛል ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ተስፋ ሰጪ የልማት ሥራዎች የታዩባት አገር መሆኗ ኩባንያቸው እንዲገባ ምክንያት እንደሆነውም ይጠቁማሉ፡፡ ከ14 በላይ የግሪክ ኩባንያዎች በቱሪዝም፤ በማኑፋክቸሪንግ፤ በኃይልና በመሰረተ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2011
በዘላለም ግዛው