አባቶቻችን ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል የሚሉት ተረት አላቸው፡፡ ምክንያቱም፣ ወሬ ለማፍረስም ሆነ ለመገንባት ትልቅ አቅም ያለው በቀላሉ የማይታይ፤ ትንሹን ጉዳይ ትልቅ አድርጎ በማግዘፍ ትኩረት የመሳብ፤ የብዙዎቹን ኑሮና ሰላም የማናጋት እንዲሁም ትዳር ከማፍረስና ቤተሰብ ከመበተን አልፎ ተርፎ በሕዝቦች መካከል ጥላቻ በመዝራት፣ በቀል በማትረፍና ቂምና ስጋት በመቀስቀስም የሚወዳደረው የለም፡፡ አስፈላጊ ከሆነ አቅሙ የብዙዎችን ቤት ብቻ ሳይሆን ሃገርም ለማፍረስ የሚያንስ አለመሆኑን ብዙ ማስረጃዎችን ዋቢ አድርጎ ጥንካሬውን መናገር ይቻላል፡፡የሊቢያው መሪ ጋዳፊን መጠነ ሰፊ የሕዝብ አመጽ በማስነሳት ግብዓተ መሬታቸውን ለማፋጠን መብቃቱ፤ የሱዳን መሪ የነበሩትን አልበሽርን መንበረ ስልጣን ነቅንቆ ለሥር መዳረጉን እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል፡፡
ስለ ወሬ አቅምና ጉልበት ይሄን ካልኩ ዘንዳ፤ ለዛሬው ላነሳ ወደ ወደድሁት ጉዳይ ልመለስ፡፡ ለዛሬ አጀንዳ ማድረግ የፈለግኩት ወሬ ባሳለፍነው ትንሳኤ በዓል ገበያ ላይ ለመፍጠር ታስቦ የነበረውን ሳቦታጅ ነው፡፡ ሳቦታጁን መዝራት የጀመረው ገና የሁዳዴ ጾም ከመግባቱ አንስቶ ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ ጎመንን እንደ አንድ ማሳያ ብናነሳ፤ ጾሙ የገባ ሰሞን 10 ብር የነበረው ጎመን 20 ብር እንደገባ በሰፊው መወራት ጀመረ፡፡ ብዙ ሰዎች በዚህ ወሬ ተናጡ፡፡ ስጋት አድሮባቸው ጎመን ለመጠየቅም የፈሩ ነበሩ፡፡ ጎመን 20 ብር ሆነ እንዴ? ብለው ለመጠየቅ የደፈሩ ሰዎችም እራሳቸው በወሰኑት ዋጋ ብልጦች ነጋዴዎች ሆነ አዎን ብለው የ10 ብሩን ጎመን 20 ብር ሲሸጡላቸው ተስተውሏል፡፡
በወቅቱ የጎመን ዋጋ 20 ብር የሆነው በወሬ እንጂ በነጋዴው ውሳኔና አምራቹ ዋጋ በመጨመሩ አልነበረም፡፡ ይሄን የሁዳዴ ጾም የገባ ሰሞን በወሬ ደረጃ የተናፈሰውን ሰምቶ ሊገበይ በሄደው በራሱ በሸማቹ ውሳኔ በ20 ብር የተሸጠውን ጎመን፤ በተመሳሳይ መጠን ብዙ ጎመን ነጋዴዎች ዘንድ እንደቀድሞው የጎመን ዋጋ በ10 ብር ሲሸጥ እንደነበረም መግለጹ ተገቢነት አለው፡ ይህ የሚያሳየው ሁሉም የአፉንና የጆሮውን ፍሬ ማግኘቱን፤ በ20 ብር ሆነ ወሬ የተነዳው በ20 ብር ሲበላ፤ የወሬውን ረብ የለሽ የተገነዘበው ደግሞ በ10 ብር ሸምቶ መመገቡን ነው፡፡ ስለዚህ በወቅቱ የጎመን ዋጋ አንዳንድ ነጋዴዎች ዘንድ በእጥፍ በማደግ 20 ብር የገባው ‹‹በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ›› እንዲሉ፣ የሚናፈሰውን ወሬ ተከትሎ ጎመን ነጋዴ ጋር ሄዶ ጎመን 20 ብር መግባቱን በጠየቀ ጎመን ሸማች ውሳኔ ጭምር መሆኑን መታዘብ ችያለሁ፡፡
በጎመን የጀመረው የዋጋ ንረት የሁዳዴው ጾም እየገፋ ሲመጣ በዚሁ በወሬ እየተገፋ መጥቶ ቀድሞውንም ‹‹እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ›› እንዲሉ፣ በየጊዜው እየናረ የመጣውን የዘይት ዋጋ በፍጥነት የብዙዎቻችን የወር ደሞዝ የማይገዛውና የዕለት ምግብ ሳይሆን የቅንጦት ፍጆታ አድርጎት አረፈ፡፡ እኔ እንደታዘብኩት የዚህ የዘይት ዋጋም ቢሆን በፍጥነት ተመንድጎ እዚህ የቅንጦት ፍጆታዎች ደረጃ መድረስ የቻለው የምርቱ ዋጋ ከቦታው ሲመጣ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ጨምሮ ሳይሆን እንደተለመደውና እንደጎመኑ ሁሉ በወሬ ተገፍቶ
ነበር፡፡ ‹‹ማየት ማመን ነው›› እንዲሉ መነን አካባቢ 110 ብር ተብሎ የነበረ ለአንድ ሊትር ትንሽ ቅር የሚለው የሱፍ ዘይት አሥር ባልሞላ ደቂቃ ውስጥ 185 ብር ሲሸጥ መታዘብ ችያለሁ፡፡ በተመሳሳይ በዚሁ ደቂቃ ውስጥ 160 ብር ተብሎ የነበረ አንድ ሊትሩ የዚሁ የሱፍ ዘይት ዋጋ ደግሞ በወሬ ግፊት ብቻ 200 ብር መግባቱንም አይቻለሁ፡፡
በዚህ መልኩ በወሬ ሲገፋ የመጣ ዘይት ዋጋ ባሳለፍነው የትንሳኤ በዓል ዕድሜ ለወረኞችና ከ500 እስከ 700 ብር የነበረው ባለ አምስት ሊትር ዘይት ዋጋ እስከ 1ሺህ 200 ብር ለመሸጥ በቅቷል፡፡እንዲህም ሆኖ በወሬ ባልተሸነፉ ብዙዎቹ ባለመደብሮች ጋር ደግሞ 920 ብር ተሸጧል፡፡ ባለ አንዱ ሊትር የዚሁ የሱፍ ዘይት ከ195 ብር እስከ 250 ብር በመሸጡ ሕብረተሰቡ በወሬ እየተገፋ በተቆለለው የዘይትም ሆነ ሌሎች ምርቶች ዋጋ ምክንያት በዓልን ለማክበርም
ተገድዷል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ገበያውን ለማረጋጋት በተደረገው ጥረትና በተወሰኑ ሸቀጦች ላይ አቅርቦት እንዲጨምርና በማኅበራትና ሌሎች ባለድርሻዎች በኩል እንዲቀርብ መደረጉ በተወሰነ መልኩ ለበዓል ገበያው መረጋጋት ማበርከቱ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
ለዚሁ በዓል በዋንኛነት አስፈላጊ የሆኑ ሽንኩርት እና ዶሮም ከዚሁ ከገበያ የወሬ ሳቦታጅ ሰለባነት አልዳኑም ነበር፡፡ ሰሞነ ሕማማት ለመግባት ሳምንት ሲቀረው በወሬ እየተገፋ 40 ብር የገባው ቀይ ሽንኩርት ሰሞነ ሕማማት ሲገባ በፍጥነት እስከ 50 ብር መግባቱ ተሰማ፡፡ በተለይ ሃገር በቀል ዝርያ መሆኑ የሚነገርለት የሀበሻ ቀይ ሽንኩርት ዋጋ 70 ብር መድረሱም ተነገረ፡፡ ይሄም በዋጋ ንረት ብዛት የመግዛት አቅሙ እየተዳከመና የትንሳኤን በዓል የማክበር ተስፋው እየተሸረሸረ የመጣውን ኅብረተሰብ በስጋት ሲንጠው ቆየ፡፡ ነገር ግን እንደ ተፈራው የገበያ ሳቦታጅ ወሬ ሟርቱ ሳይዝለት ቀርቶ እስከ ትንሳኤ በዓል ዋዜማ የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ እስከ 35 ብር በማሽቆልቆል ወርዶ ኅብረተሰቡ ሽንኩርት ሸምቶ በዓሉን ማክበር ቻለ፡፡
የአንድ ዶሮ ዋጋ አንድ ሺህ ብር እና ከዛም በላይ የመግባቱ ወሬ መናፈስ የጀመረውም በሰሞነ ሕማማቱ ወቅት ነበር፡፡ወሬው በኅብረተሰቡ ዘንድ የዶሮ እጥረት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋትም ፈጥሮ ነበር፡፡ ሆኖም በዘንድሮ ትንሳኤ በዓል እንደ ዕድል ሆኖ የዚሁ የገበያ ሳቦታጅ ወሬ ሟርቱ ሳይዝለት ቀርቶ የሀበሻውም ሆነ የፈረንጁ ዶሮ ዋጋው በፍፁም እንደ ታሰበው ሊጋነን አልቻለም፡፡እስከ በዓሉ ዋዜማ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በየመኪናው ላይ የትኞቹም አካባቢዎች አንድ ዶሮ እስከ 400 ብር ሲሸጥ ውሏል፡፡ ታርዶ የተበለተውም ቢሆን በየሱፐር ማርኬቶቹ በተለይም አራት ኪሎ ባሉት ሱፐር ማርኬቶች በተመሳሳይ ዋጋና እንደ ልብ መሸጥ በመቻሉ የገበያ ሳቦታጅ ወሬው ሟርት ሳይዝ ቀርቷል፡፡
ይህ እውነት የሚያስረዳን ደግሞ በአገራችን ለሚስተዋለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ችግር እንደ ምክንያት ከሚነሱ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን፣ ከውጪ ምንዛሪ ችግር፣ ከደላላ፣ ከነጋዴ ሥነምግባር፣ ከገበያ ቁጥጥርና ክትትል መላላት፣ ከሕግ ማስከበርና ተያያዥ ጉዳዮች ባሻገር፤ በወሬ ደረጃ የሚነገረው የሸቀጦች ዋጋን አንሮ የመሳል አካሄድ አንድ መንስኤ መሆኑን ነው፡፡ ይህ በወሬ ላይ የተመሠረተ ዋጋን የማናር አካሄድም አሉባልታውን ለተከተለ የሚሠራ፤ ወሬን አጣርቶ ለሚራመድ የማይሠራ መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡ በትንሳኤው ገበያ የታየውም ይሄው
ነው፡፡ ሆኖም ወሬ አንዱ የዋጋ ንረት መፍጠሪያ ሳቦታጅ መሆኑን ተገንዝበን ልንጠነቀቅ፤ በሐሰት ወሬ ላይ ተመሥርቶ ከሚፈጠር የዋጋ ንረት ለመጠበቅም ሐሰትን በእውነት ልናከሽፍም ይገባል፡፡
ሰላማዊት ውቤ