በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተፈናቅሎ በተለያየ ችግር ውስጥ ይገኛል። መንግስትና መጽዋች አካላት የዕለት ዕርዳታና ድጋፍ ቢያደርጉም ችግሩን በቋሚነት በመፍታት ረገድ ግን ዳገት ሆኗል። የዜጎችም የሰቆቃ ህይወት ቀጥሏል።
ይህ ደግሞ መሆን አልነበረበትም፤ መቀጠልም የለበትም። በዚህ ረገድ እነዚህን ዜጎች መልሶ ለማቋቋምና ወደቀደመ ህይወታቸው ለመመለስ መደረግ ስለሚገባው ጉዳይ ምሁራንና ባለሙያዎች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
ፖለቲከኛና የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር መረራ ጉዲና፤ የፖለቲካ ሀይሎች በጊዜያዊ የጥቅም ስሌት ዜጎችን በማፈናቀል ዋጋ እየተከፈለ ነው። ከዚህ ወጥተው አገራዊ ጥቅም የሚያመጣ የቤት ስራቸውን መስራት አለባቸው።
ዜጎችን ማፈናቀል እግዚአብሄርም ሆነ በዓለማዊ ህግ ተጠያቂነትን ያመጣል። በዜጎች ስቃይ የሚመጣ ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ውሎ አድሮ ኪሳራው የከፋ መሆኑን ያስጠነቅቃሉ።
ፖለቲከኛና ምሁሩ እንደሚሉት፤ ዜጎችን በማቋቋም ሂደት መንግስት ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሩን መክፈት አለበት። ከፖለቲካዊ ጥቅም ይልቅ የዜጎችን ሰብዓዊ ጉዳት ለማስቀረት ሁላችንም መስራት አለብን። በኦሮሚያ ክልል የነበረውን መፈናቀል ለማገዝ በቂ ባይሆን
ተሳትፈናል። በአገር አቀፍ ያለውን መፈናቀል ወጥነት ባለው መልኩ በታቀደና ውጤት በሚያመጣ አካሄድ ሁሉንም የሚያሳትፍ አካሄድ በመዘርጋት በጋራ መስራት አለብን።
መፈናቀል ብሄራዊ መግባባት በመጥፋቱ በኢትዮጵያ ላይ የመጣ ችግር ነው። ይህን ችግር በጋራ እንጂ፤ በተናጠልና በእየራሱ መንገድ በመሮጥ አይፈታም። አዋጭም አይደለም። ችግሩ የሁላችንም በመሆኑ ሁላችንም ለሁላችን መቆም አለብን። የሰብዓዊነት ጉዳይ የድጋፍና የመፎካካሪያ የማድረጉ አዝማሚያ አደገኛና ብሄራዊ መግባባትን የሚሸረሽር መሆኑንም ያስጠነቅቃሉ።
የላይፍ አማካሪ ድርጅት ባለቤትና ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዳምጠው ወልዴ፤ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም በክልሎችና በተለያዩ አካላት የሚደረገው ጥረት ፈር ቀዳጅና የሚያስመሰግን ነው። ሆኖም ለሁሉም ዜጎች በፍትሃዊነትና በሰብዓዊነት ድጋፍ ለማድረግ በፌዴራል ደረጃ ወጥ በሆነ መንገድ በማዕከል የዕርዳታ ማሰባሰቡ ሥራ የሚመራ አካል አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታሉ።
የገጠመው መፈናቀል መጥፎ ቢሆንም በማቋቋሙ ሂደት ወደ መልካም አጋጣሚ መቀየር ይቻላል። ተበታትነው የሚኖሩ ዜጎችን በጥናት ላይ ተመስርቶ የጤና፤ የትምህርት፤ የውሃ፤ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና ሌሎች አገልግሎቶችን በዘመናዊ መንገድ ማደራጀት ይቻላል። በዚህ መንገድ ማቋቋሙ የእርሻን መሬት በአግባቡ ለመጠቀምና ተፈናቃዮቹ ከኋላቀር አኗኗር ወደተሻለ የህይወት ስልት እንዲሻገሩና ማስተማሪያም ማድረግ እንደሚቻል እንጂነሩ ይመክራሉ።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማራነው አካላት የተፈናቀሉ ዜጎችን በማቋቋም ሂደት እንደዜጋ የምንችለውን የማድረግ ኃላፊነት አለብን የሚሉት ኢንጂነሩ፤ ተቋራጮችና አማካሪዎች በተለይም የሚሰሩ ቤቶችንና አሰፋፈሩን በተመለከተ መለስተኛ ጥናት በማድረግ፤ ዲዛይን በመስራት፤ ግንባታውንም በመደገፍ፤ ከዚያም ሲያልፍ ያለትርፍ በዝቅተኛ ክፍያ በስራው ላይ በመሳተፍ መደገፍ እንችላለን። ማህበራትና መንግስት ተቀራርበው መስራት ከቻሉ ተቋራጮችና አማካሪዎች ይህን ለማድረግ አቅም እንዳላቸው ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የስነ ምግብ ተመራማሪው አቶ ክፍሌ ሀብቴ በበኩላቸው፤ ዜጎችን በቋሚነት ለማቋቋም የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልት ነድፎ መስራት ይገባል። በአጭር ጊዜ ዜጎች በህይወት ለመኖር የሚያስችል፤ ፕሮቲን፤ ስብና ካርቦሃይድሬት ያላቸውን ምግቦች በማቅረብ ስነ ምግብ ማሟላት ያስፈልጋል።
የረሀብ ጉዳት የደረሰባቸውን በልዩ ሁኔታ እንዲያገግሙ ወደ መደበኛ አካላዊ አቅማቸው እንዲመለሱ መስራት፤ በቋሚነት እስኪቋቋሙ ቢያንስ በቀን 2000 ካሎሪ እንዲሟላላቸው መስራትም አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።
ዜጎችን በማቋቋም ሂደት ከጤናው ዘርፍ ጋር በመቀናጀት የተመጣጠነ ምግብ ስርዓት መዘርጋት፤ ለዚህም የሚቋቋሙ ዜጎችን እንዳሉበት የስነ ምግብ ደረጃ በዝርዝር መለየት ያስፈልጋል። ለተለዩት ዜጎች የአመጋገብና የጤንነት አጠባበቅ ስራ መስራት ያስፈልጋል። የማቋቋም ሂደቱ የተለያዩ አካላት ድምር ውጤት በመሆኑ ሁሉም በጋራና በተናጠል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባም ያብራራሉ።
ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉ አንድ የየካቲት ሆስፒታል የጤና ባለሙያ በሰጡት ማብራሪያ፤ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም በጊዜያዊነት ወረርሽኝ፤ ውሃ ወለድ፤ የምግብ እጥረትና ሌሎች በሽታዎች እንዳይከሰቱ ተፈናቃዮች ባሉበት ጥንቃቄ ማድረግ፤ በተንቀሳቃሽ ጤና ኬላ፤ በጤና ጣቢያዎችና እንደየበሽታው ሁኔታ በሆስፒታሎች ህክምና መስጠት የሚያስችል አቅም ማደራጀት ያስፈልጋል።
በቋሚነት በማቋቋም ሂደቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ ጤና ቢሮዎችና የበጎ አድርጎት ድርጅቶች፤ የሰራተኛና ማህበራዊ ተቋማትና ሌሎች አካላትን በማሳተፍ ሰፊ ስራ መስራት ይገባል።
በሂደቱም ከሌሎቹ መደበኛ የህክምና አካሄድ በተለየ ክትትል ማድረግም ያስፈልጋል። በምግብ ዕጥረትና በተለያዩ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች እስኪያገግሙ ማድረግ ይገባል። ክትትሉ ሳይቆራረጥ ወደ መደበኛ ህይወት እስከሚገቡ ድረስ መሰራት እንዳለበትም ያመላክታሉ።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ትምህርት መምህሩ አቶ አስናቀው ታደለ፤ የተፈናቃይ ማህበረሰብ ተማሪዎችን ወደማስተማር ስራ ከመገባቱ በፊት የችግሩን ጥልቀት ማጥናት አስፈላጊ ነው። ተፈናቅለው ያሉ ዜጎች ከደረሰባቸው አካላዊና ቁሳዊ ጉዳት በላይ ስነልቦናዊ ጉዳቱ የከፋ ነው። በተለይም ደግሞ ምግብ፤ መጠለያና አልባሳት ከላገኙ ትምህርት ይከታተላሉ ማለት አይቻልም።
በመሆኑም ከትምህርት ሚኒስቴር እስከ ታችኛው መዋቅር ያሉ አካላት ይህን ከግንዛቤ አስገብተው መስራት አለባቸው። የቅድሚያ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት መሰረታዊ ፍላጎትን በማሟላት ጉዳይ ላይ ሊሆን ይገባል። ከስነልቦና ጫና እንዲወጡም መስራት ያስፈልጋል። በተለይም፤ ቤተሰቦቻቸው በዚህ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ መስራት አስፈላጊ ነው። ወላጆች ልጆቻቸው ከችግሩ እንዲወጡና ወደፊት ብሩህ ተስፋ እንዳለ ማመላከት፤ አቅሙ ካላቸው በትምህርታቸው ማገዝ አለባቸው።
በዚህ ደረጃ ርዳታ አድርገው ጫናው ከባድ ከሆነ በተለይም ልጆቹ የስምንተኛ፤ የአስረኛና የመሰናዶ ብሔራዊ ፈተና ተፈታኞች ከሆኑ ተፈትነዋል ብሎ ሪፖርት ለማድረግ ብቻ መፈተን የለባቸውም። በቀጣይም በውጤታቸው ላይ ጫና ስለሚያደርስባቸው ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ይጠቁማሉ። ለተፈናቀሉ ተማሪዎችና ለትምህርቱ ስራ ሁሉም የትምህርት ዘርፍ ተቋማትና አደረጃጀቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራት አለባቸው ይላሉ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2011
በአጎናፍር ገዛኽኝ