ሴቶች የኅብረተሰቡ ግማሽ አካል ናቸው እየተባለ በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል:: በተወራው ልክ ግን ሴቶች ለበርካታ አመታት በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከወንዶች እኩል ተጠቃሚ ሲሆኑ አልታየም:: በተለይ ደግሞ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያን ያህል አልነበረም::
በጊዜ ሂደት የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም አሁንም ብዙ እንደሚቀረው ብዙዎችን ያስማማል:: በርግጥ ሴቶች ተቀጥሮ ከመሥራት ጀምሮ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው እንዲሠሩ በመንግሥት በኩል በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል:: ወደ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተሸጋግረው እንዲሠሩም ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል::
ሆኖም በእነዚህ ዘርፎች ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት በመንግሥት በኩል ሲደረግ የነበረው ጥረት አርኪ ሆኖ አልተገኘም:: በተለይ ደግሞ ለሴቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ ይስተዋላል:: ከዚህ አንፃር የግሉ ዘርፍ ሚና የጎላ ቢሆንም ከሚሸከመው የሥራ ዕድል ጋር ሲነፃፀር ብዙ አልተሠራበትም::
የግሉ ዘርፍ ግዙፍ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነውና የሚጠበቅበትን ያህል ከሠራ፤ በተለይ ደግሞ በትብብርና አጋርነት የመሥራትን ሂደት ከተላመደ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ይችላል:: በዚሁ የሥራ ዕድል ፈጠራ ታዲያ ሴቶችም ተጠቃሚ ይሆናሉ:: በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆን በተለይ ሴቶችን እንዴት በሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ከሰሞኑ በሁለት የግል ተቋማት መካከል የተደረገው ስምምነት ጥሩ ማሳያ ነው::
‹‹እናት ባንክ›› በኢትዮጵያ በአስራ አንድ ባለ ራዕይ ሴቶች ሃሳብ አመንጪነት የተቋቋመ የመጀመሪያው የሴቶች ባንክ ሲሆን ላለፉት ዘጠኝ አመታት የተሟላ የባንክ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል:: ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የባንክ አገልግሎት ከመስጠት በዘለለ በተለይ ሴቶችን በኢኮኖሚ የማብቃት ተልዕኮ ይዞ በመንቀሳቀስም ይታወቃል::
ባንኩ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳካት የሴቶች ባንክ አገልግሎት መምሪያ ያዘጋጀ ሲሆን ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ብድር የሚያገኙበትን አሠራርም አመቻችቷል:: በተለያዩ ዘርፎችና ጊዜያት እናቶችና እህቶች ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና ለመስጠትና ለተተኪው ትውልድ አርአያ እንዲሆኑ በማሰብም በአዲስ አበባ የሚከፍታቸው ቅርንጫፎች በእነዚሁ ሴት የአገር ባለውለታዎች ስም እንዲሰየም አድርጓል::
ከዚህም ባሻገር በተለያየ መልኩ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች የማቆያና ድጋፍ ከሚሰጡ ድርጅቶች ጋር ትብብር በመፍጠር በባንኩ ውስጥ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣም ይገኛል:: በየአመቱ ከሚያገኘው ትርፍ 5 ከመቶ ያህሉን ሥራ መፍጠር ለሚችሉ፤ ነገር ግን ማስያዢያ ማቅረብ ለማይችሉ ይህ ትርፍ እንደማስያዣ እንዲውል በማድረግ ብድር በማበደር በርካታ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑም አስችሏል::
የሁሉንም ኅብረተሰብ ክፍሎች ፍላጎት በሚያሟላና የሴቶችን የፋይናንስ አካታችነት በሚያጎለብት መልኩ የተለያዩ አሠራሮችን በመከተል የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎቶችን እየሰጠም ነው::
የሚሰጠውን አገልግሎት ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ከማብዛት ጎን ለጎን የቴክኖሎጂ መሠረትና ሰፊ ተደራሽነት ካላቸው ተቋማት ጋር በትብብር እየሠራ ይገኛል:: ባንኩ ከሃይብሪድ ዲዛይን -ራይድ ጋር በስትራቴጂያዊ አጋርነት በትብብር አብሮ ለመስራት ከሰሞኑ ያደረገው ስምምነትም የዚሁ ትብብር አንዱ ማሳያ ነው::
በተመሳሳይ ሃይብሪድ ዲዛይን-ራይድም በሴት የተመሠረተና በቴክኖሎጂ የታገዘ አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት እያቀረበ ያለ ተቋም ሲሆን የጥሪ ማዕከልን ጨምሮ ለአጠቃቀም አመቺ የሆኑ መተግበሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ማህበረሰቡ ፈጣን፣ ደህንቱ የተጠበቀና አስደሳች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ እያደረገ ይገኛል::
በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዋነኛ አላማም የእናት ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ከሃይብሪድ ዲዛይን ቴክኖሎጂና ቴክኒካዊ ትብብር ጋር ጥምረት በመፍጠር ጥራት ያለው የባንክና የፋይናንስ ምክር ለማቅረብ፣ ለራይድ ትራንስፖርት አቅራቢ አሽከርካሪዎች የብድር አገልግሎት ለመስጠት፣ ተሳፋሪዎች በባንኩ ሞባይል ባንኪንግ ተጠቅመው ክፍያ እንዲከፍሉ እንዲሁም የራይድ አሽከርካሪዎች ለሃይብሪድ ዲዛይን የሚከፍሉትን ኮሚሽን /ክሬዲት/ ክፍያ በባንኩ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት እንዲከፍሉ ለማድረግ ነው::
ከእነዚህ አላማዎች በዘለለ ታዲያ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረገው በትብብር አብሮ የመስራት ስምምነት ለሴቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ እሴት የጨመረ እንደሆነም ተነግሮለታል::
አቶ ኤርሚያስ አንዳርጌ የእናት ባንክ ፕሬዚዳንት ናቸው:: እርሳቸው እንደሚሉት በእናት ባንክና በሃይብሪድ ዲዛይን ራይድ መካከል የተደረገው አብሮ የመሥራት ስምምነት በሥራ ዕድል ፈጠራ ለሴቶች የተለየ ዕድል ይዞ መጥቷል:: ባንኩ ከራይድ ጋር ሲሠራ ሴቶች ሆነው በአሽከርካሪነት የሚሠሩና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች በመኖራቸው የዚሁ ስምምነት ተጠቃሚ ይሆናሉ::
ባንኩ በዚሁ ስምምነት መሠረት በዋናነት ለመሥራት ያቀደው ወደእዚሁ የራይድ ቢዝነስ መግባት የሚፈልጉ ሴቶች ካሉ ቁጠባ በማስተማር ገንዘብ በባንኩ ቆጥበው ወደ ሥራ ገብተው ገቢ እንዲያገኙ ነው:: ይሄ እንደመንደረደሪያ ቢቆጠርም ባንኩ በቀጣይ ሌሎች ብዛት ያላቸው የሥራ ዕድሎችን ለሴቶች ለመፍጠር የሚሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ:: በቀጣይም ባንኩ ከራይድ ጋር የሚሠራቸው ሌሎች ሥራዎች አሉ:: እነዚህም ሥራዎች ትኩረታቸው በሴቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ነው:: ባንኩ የተቋቋመበት ዋነኛ አላማም ሴቶችን የማገዝና የማብቃት ሥራን መሥራት ነው:: ይህንንም ባንኩ በአግባቡ ለመሥራት ቁርጠኛ ነው:: ሆኖም ባንኩ ለሁሉም ዕድል የሚሰጥ ባንክ በመሆኑ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች የባንኩ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ::
እናት ባንክ ሴቶች በአብዛኛው በኢኮኖሚ የተጎዱ መሆናቸውን ስለሚያምን ሴቶችን በኢኮኖሚ ቢያበቃ በርካቶችን መጥቀም ይችላል:: አንድ እናት ሥራ አገኘች ማለት ደግሞ ቤተሰቧን ደጎመች ማለት ነው:: ልጆቿም አይራቡም::
ባንኩ በቀጣይ በሴቶች ላይ ተመሳሳይ ሥራዎችን ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: በተለይ ደግሞ ባንኩ ሴቶችን በፋይናንስ ተጠቃሚ የሚያደርግ ክፍል አደራጅቷል:: የዚህ ክፍል ዋና ሥራው ለሴቶች እንዴት የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል የሚያጠና ክፍል ነው::
ይህን ስምምነት መነሻ በማድረግም ከዚህ በኋላ ባንኩ ለሴቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርና ሴቶች ሥራ አገኝተው ሕይወታቸውን እንዲያሻሻሉ በርካታ ሥራዎች ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል::
የሃይብሪድ ዲዛይን-ራይድ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሳምራዊት ፍቅሩ በበኩላቸው እንደሚሉት ራይድና እናት ባንክ ባደረጉት በጋራ የመስራት ስምምነት መሠረት ራይድን መቀላቀል ለሚፈልጉ አዳዲስ ሴት አሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ ባለንብረቶች እንዲሁም ለወንዶችም ጭምር የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ::
የራይድ አገልግሎት ፈጣን ገንዘብ የሚገኝበት ከመሆኑ አኳያም በተለይ ራእይ ላላቸው ሴቶችና ወጣቶች ገንዘባቸውን በሌሎች ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለማዋል ያግዛቸዋል:: ከዚህ አኳያ አዳዲስ ለሚገቡ ሴቶችና ወጣቶች ሃይብሪድ ዲዛይን-ራይድ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ይገኛል::
በዋናነት ደግሞ ከእናት ባንክ ጋር የተደረገው ስምምነት ሴት አሽከርካሪዎች ከባንኩ ብድር ሲወስዱ በአነስተኛ ወለድ ብድራቸውን እንዲከፍሉ ያስችላቸዋል:: ወደ ባንኩ ሲመጡና የራይድ ኮሚሽን /ክሬዲት/ ክፍያ ሲፈፅሙም የተወሰነ ቅናሽ ያገኛሉ:: በተለይ ደግሞ የሌላ ሰው ተሽከርካሪ ይዘው የራይድ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሴቶች የራሳቸው ተሽከርካሪ እንዲኖራቸው ሁኔታዎች ተመቻችቶላቸዋል::
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገለፃ ሃይብሪድ ዲዛይን-ራይድ ራዕዩን ለብዙ ባንኮች የተናገረ ቢሆንም እናት ባንክ ያለምንም ማንገራገር ራዕዩን ተቀብሎ ስምምነት ፈፅሟል:: ባንኩ ይህን ራዕይ ተቀብሎ አብሮ ለመስራት የተስማማውም ራይድ እየሠራ ያለውን ሥራ በማየትና የወደፊቱንም እድገት በመመልከት ነው:: በምላሹ ሃይብሪድ ዲዛይን- ራይድ እናት ባንክ በተለይ ሴቶች በኢኮኖሚ ብቁ እንዲሆኑ ስለሚያበረታታ በጋራ ለመሥራት ተስማምቷል::
በዚሁ ስምምነት መሠረት ‹‹በእናት ራእይ›› የእናት ባንክ የቁጠባ ፕሮግራም አሽከርካሪዎች ለአንድ ዓመት በመቆጠብ ባንኩ በሚያመቻችላቸው ብድር ተሽከርካሪዎቻቸውን መቀየር ይችላሉ::
‹‹እናት እፎይታ›› በተሰኘው የባንኩ የቁጠባ ፕሮግራምም አሽከርካሪዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ገንዘብ ሲያጥራቸው ባንኩ የብድር አገልግሎት አመቻችቶላቸዋል:: ‹‹በእናት ደራሽ›› ፕሮግራም ደግሞ አዳዲስ አሽከርካሪዎች ወደ ራይድ ገብተው ሥራ የሚጀምሩበትን ብድር ያመቻቻል::
በቀጣይም ሃይብሪድ ዲዛይን-ራይድ በተለይ በሴቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት እቅድ ይዟል:: አሽከርካሪዎችን በስልክ የማናገር ሥራዎች እየተሠሩም ይገኛሉ:: ይህም ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም ጭምር ያካትታል::
ራይድ ለሴቶች ትኩረት አድርጎ እየሠራ ያለ ቢሆንም በዋናነት የሚያየው ግን የፆታውን ጉዳይ ሳይሆን የወጣት ሴቶችንም ሆነ ወንዶችን ራዕይ ነው:: ራዕያቸውን ለማሳካትና መድረስ የሚፈልጉበት ቦታ እንዲደርሱም ይደግፋል:: ከዚህ አንፃር ራይድ የሴትና ወንድ ወጣቶች የራእያቸው ጉዞ አጋር ነው::
በእናት ባንክና በሃይብሪድ ዲዛይን-ራይድ መካከል አብሮ ለመሥራት የተደረገው ስምምነት ተግባራዊ መሆን ሲጀምር ለራይድ አሽከርካሪዎች፣ ለሃይብሪድ ዲዛይን፣ ለባንኩ ብሎም ለሰፊው ማህበረሰብ የትራንስፖርት አገልግሎት ጥራት ከመጨመር፣ የአከፋፈል ሥርዓትን ከማዘመንና የጋራ ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አንፃር የሚኖረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሚሆን በብዙዎች ዘንድ ተነግሮለታል::
ከዚህ ባለፈ ስምምነቱ ሌሎች የግል ተቋማት በጋራ አብረው ለመሥራት የሚያነሳሳና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ዜጎችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚያድረጉ ሥራዎችን በጋራ ለማከናወን የሚንቀሳቀስ እንደሆነም ተጠቁሟል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 /2014