የገንዘብ ሚኒስቴር እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ንረት ማረጋጋት እንዲቻልና መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች የሆኑት ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ የሕፃናት ወተት እና ሩዝ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፍቃድ (በፍራንኮ ቫሉታ) በጉምሩክ ኮሚሽን በኩል በቀጥታ እንዲገቡ መወሰኑን ከቀናት በፊት አሳውቋል።
ውሳኔውም በርካታ የውጭ አገር የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የራሳቸውን ሚና መጫወት እንዲችሉ የፍራንኮ ቫሉታ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከለትሎ የተላለፈ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ቀረጥና ታክስን በሚመለከት በገንዘብ ሚኒስቴር በ22/3/2013 ዓ.ም በቁጥር ማአ.30/7/51 በተጻፈው ደብዳቤ መሠረት እንዲፈጸም፤ አፈጻጸሙን በተመለከተ ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት በኩል ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግበትም አሳውቋል።
ፍራንኮ ቫሉታ ሕጋዊ ከሆነ ምንጭ የሚገኝ የውጭ ምንዛሪ ማለት ሲሆን፣ ይህም የባንክ ቤት ፈቃድ ሳያስፈልግ የሚገቡ ምርቶችን ወደ አገር ለማስገባት የሚያስችል የፈቃድ ዓይነት ማለት ነው። መብት ያላቸው አስመጪዎች ወደ አገር ውስጥ ለሚያስገቧቸው ምርቶች የውጭ ምንዛሬን በተመለከተ በብሔራዊ ባንክ የወጡ እና በንግድ ባንኮች የሚተገበሩ ጥብቅ መመሪያዎችን የማለፍ ግዴታ የለባቸውም።
ውሳኔው በተለይ ከ35 በመቶ በላይ ሆኗል የሚባለውን የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት ምን አበርክቶ ይኖረዋል፣ ከውሳኔ ጋር ተያይዞስ ምን ስጋቶች ይኖራሉ፣ ሊወሰዱ የሚገባቸው ጥንቃቄዎችስ ምን ሊሆኑ ይገባል በሚል ጥያቄዎችን በማንሳት አዲስ ዘመን ጋዜጣም የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን አነጋግረናል።
አስተያየታቸው ያጋሩን የምጣኔ ሀብት ምሁራንም፣ መንግሥት በከፍተኛ ወጪ በመግዛት በዝቅተኛ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ከሚያቀርባቸው መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች በተጨማሪ በሌሎች አካላት የሚገባውን በማከል አቅርቦቱ በከፍተኛ ደረጃ ይጨምር ዘንድ ያለውጭ ምንዛሪ ሸቀጦችን የማስገባት አሠራር መፈቀዱ፣ እየታየ ላለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ጊዜያዊ ማስተንፈሻ ጥሩ የመፍትሔ አማራጭ እንደሆነ ይስማሙበታል። ይሁንና ደግሞ የፍራንኮ ቫሉታው ትግበራው በሚፈለገው መንገድ መራመድ ካልቻለ አደጋው ከባድና እጅግ የከፋ ስለመሆኑም ያስገነዝባሉ።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸው ከጠየቅናቸው መካከል አንዱ የሆኑት በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ሞላ አለማየሁም፣ ያለምንም የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ ምርቶችን ማስገባት በተለይ የገቢ ንግድን ለማሻሻል እና ለማረጋጋት በተለያዩ ጊዜያት ሲፈቀድ ተመልሶም ሲከለከል ሲነሳ መቆየቱ ያስታውሳሉ።
ፍራንኮ ቫሉታ በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ በተለይ የአገር ኢኮኖሚ ሲንገጫገጭና ግሽበት ሲከሰት ዋጋን ከማረጋጋት አንፃር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውም የሚያመላክቱት ዶክተር ሞላ፣ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረጉም በተለይ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት ረገድ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ያሰምሩበታል። ‹‹መንግሥት ይህን ውሳኔ ያሳለፈው አቅርቦትና ፍላጎቱ መመጣጠን ባለመቻሉ እና የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት ነው›› ይላሉ፡
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱም፣ መንግሥት ፍራንኮ ቫሉታን መፍቀዱ የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስና የምርት አቅርቦትን ለመጨመር እንደሚረዳ ይገልፃሉ። የአገር ውስጥ ፍላጎትና አቅርቦትም አለመመ ጣጠንን በማስተካከል፤ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና የምርት እጥረትን ለመቅረፍ ጥሩ መፍትሄ ተደርጎ እንደሚታይም ይጠቁማሉ።
የውጭ ምንዛሬ ከዋነኞቹ የዋጋ ንረት ምክንያቶች የሚመደብ መሆኑን የሚያስረዱት ሌሎች የምጣኔ ሀብት ምሁራንም፣ አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ባለበት ጊዜ የውጭ አገራት ገንዘብ ሁሉ የግድ ከባንክ መወሰድ አለበት ብሎ ሙጥኝ ማለት ትክክል እንዳልሆነና የፍራንኮ ቫሉታ አማራጭም የግድ እንደሆነም ያሰምሩበታል።
‹‹ይሁንና የፍራኮ ቫሉታው ትግበራ ሌላ ችግር እንዳያመጣ መጠንቀቅ የግድ ነው›› ይላሉ። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ክቡር ገናም ይህን እሳቤ ይጋሩታል። ፍራንኮ ቫሉታ ያላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል መጠንቀቅ እንደሚገባ አጽእኖት የሚሠጡት አቶ ክቡር፣ የፈቃዱን ዓላማ ለማሳካት ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም ለማዳበር የሚፈልጉ ግለሰቦች ያላግባብ እንዳይጠቀሙበት ሂደቱ በጥብቅ ሥነ ምግባር እንዲመራ ማድረግ እንደሚገባም ያሰምሩበታል።
ዶክተር ሞላ አለማየሁም ቢሆን ‹‹ፍራንኮ ቫሎታ አመራጭ መፍትሄ ከመሆኑ ባሻገር የራሱ የሆኑ ፈተናዎችን ይዞ የሚመጣ ነው›› ይላሉ። የመንግሥትን ፖሊሲ በአግባቡ እንዳይሳለጥ የማድረግ አቅም እንዳለው በመጠቆም፣ በርካታ አገራት አማራጩን ተግባራዊ ከማድረግ የሚቆጠቡትም በዚህና በሌሎችም ምክንያቶች መሆኑንም ያስገነዝባሉ።
እንደ ዶክተር ሞላ ገለጻም፣ በፍራንኮ ቫሉታ ትግበራ ወቅት ከቁጥጥር ጋር በተያያዘ በሚስተዋሉ ድክመቶችና በሚፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባራት አገር የሚያስፈልጋትና ወደ አገር የሚገባው የተለያየ ሊሆንም ይችላል። ተጠቃሚዎቹ እንጂ አገር የምትፈልገው ላይገባ የሚችልበት ዕድልም ሰፊ ነው።
ተጠቃሚዎቹ ትርፍን ብቻ ታሳቢ በማድረግ የሚፈልጉትን ምርት ወደ አገር ውስጥ አስገቡ ማለት ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአገርን ኢኮኖሚ ይጎዳል። ገበያ ላይ ያሉ በተለይ በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉት ሳይቀር በዝቅተኛ ዋጋ የሚገቡ ከሆነ ደግሞ የአገር ውስጥ አምራቾችን ያደቃል። በማደግ ላይ ያሉ ፋብሪካዎችን ያቀጭጫል።
በጉዳዩ ላይ የተለያየ ምልከታቸው የሚያጋሩ ዓለምአቀፍ የምጣኔ ሀብት ምሁራንም፣ ፍራንኮ ቫሉታ፣ በተለይ የጥቁር ገበያን በማስፋፋት ረገድ ከባድ ተፅእኖ እንዳለው በመጠቆም፣ ችግሩ እንዳይከሰት አስቀድሞ መከላከል የሚቻልበትን መንገድ መቀየስ ካልተቻለም አደጋው ከባድ ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ።
‹‹ከሁሉ በላይ በወንጀል የተገኘ ገንዘብንም በእግረ መንገድ ሕጋዊ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል›› የሚሉት የምጣኔ ሀብት ምሁራኑ፣ አሠራሩ ጥንቃቄ ካልተደረገበት ግለሰቦች በትይዩ ገበያ ገዝተው ያስቀመጡትን ወይም ያጠራቀሙትን የውጭ ምንዛሪ የሚያጥቡበት ወይም ሕጋዊ የሚያደርጉበት ሁኔታን ሊያመቻች እንደሚችል ይጠቁማሉ።
በተለይ የትግበራው ዕድል ተጠቃሚ ግለሰቦች አጋጣሚውን በመጠቀም ከጥቁር ገበያ ዶላር እየገዙ የተፈቀዱትን ዕቃዎች በፍራንኮ ቫሉታ ስም በማስገባት እንደገና የጥቁር ገበያው ጡንቻ እንዲፈረጥም ያደርጋል የሚል ስጋታቸውንም ያስቀምጣሉ።
ዶክተር ሞላ አለማየሁም፣ ውሳኔውን ተከትሎ የጥቁር ገበያ ጉዳይ ዋነኛው አደጋ ስለመሆኑም ያሰምሩበታል። ውሳኔው ለጥቁር ገበያው (Black Market) መስፋፋት በተለይም ሕጋዊ ያልሆነን ገንዘብ ሕጋዊ የማድረጊያ አንዱ መንገድ ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም፣ ይህ እንዳይሆን በማድረግ ረገድም መንግሥትን ከባድ ቤት ሥራ እንዳለበት ያስገነዝባሉ። በፍራንኮ ቫሉታው ትግበራ ከሁሉ በላይ ጠንካራ ቁጥጥር እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑም አፅእኖት ይሰጡታል።
የፍራንኮ ቫሉታ መብት መፈቀድ ጥቁር ገበያን ለመቆጣጠር ሲባል በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ የወጡ የተሻሻሉ መመሪያዎችን የሚፃረር እንደሆነም የሚከራከሩ ባለሙያዎች አሉ። የተሻሻሉት መመሪያዎች ዋነኛ ግብ በጥቁር ገበያ የሚፈጸመውን ሕገወጥ ድርጊት ለመከላከል ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ፍራንኮ ቫሉታ ተፈቀደ ማለት ጥቁር ገበያን መደገፍ ሊሆን እንደሚችል ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚያቀርቡት አስተያየት ነው።
በፍራንኮ ቫሎታው ተጠቃሚ የሚሆኑ ግለሰቦች የውጭ ምንዛሪ ምንጭን ማሳወቅ እንደ ግዴታ መቀመጡ ተገቢ ቢሆንም፤ ብሔራዊ ባንክ ምንጩን የማረጋገጥ ግዴታ ተከታትሎ የማስፈጸም አቅሙ ደካማ ከሆነ መመሪያው አደገኛ መሣሪያ የመሆን ዕድል እንደሚኖረው የሚገልፁም በርካቶች ናቸው።
በፍራንኮ ቫሉታ ለሚገባው ዕቃ አስመጪው የሚያቀርበውን የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ብሔራዊ ባንክ እንደሚያረጋግጥ ቢታመንም፣ ብሔራዊ ባንክ የገንዘቡን ምንጭ እንዴት ያረጋግጣል? ለሚለው ጥያቄ እስካሁን የተሰጠ ማብራሪያ የለም።
ዶክተር ሞላ አለማየሁ፣ ለበጎ የታሰበው በፍራንኮ ቫሉታ ሸቀጦችን ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ውሳኔ ሌላ ችግር እንዳያመጣ መሠራት ስላለበትም የቤት ሥራ ሲጠቁሙም ከሁሉ በላይ ውጤቱን መገምገም የግድ እንደሆነም ያሰምሩበታል። ‹‹መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ያለ ውጭ ምንዛሪ
ፈቃድ በቀጥታ እየተፈቀደ ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በመወሰኑ ውጤቱ ታይቷል፤ ገበያውስ ተረጋግቷል ወይ የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ በየጊዜው መቃኘት ያስፈልጋል›› ይላሉ።
‹‹አፈፃፀሙን በየጊዜው መከታተል የግድ ይላል። የተፈለገውን ውጤቱን አምጥቷል አላመጣም፣ የሚለውም መገምገም አለበት። ከዚህም ከፍ ሲል ውጤቱ እየታየ ማሻሻያዎች ካስፈለጉም ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይላልም›› ነው ያሉት።
ችግሩ የአገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት ብሎም ግብይት ሊያናጋው ስለሚችል ከሁሉ በላይ በትግበራው ሂደት ጠንካራ ቁጥጥር እጅግ ወሳኝ ስለመሆኑም አፅእኖት የሚሠጡት ዶክተር ሞላ አለማየሁ፣ ለዚህ ደግሞ የተለየ ስልት መንደፍ እንደሚገባና ብሔራዊ ባንክም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት።
ከዚህ ባሻገር ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ምርቶች መንግሥት ፈቃድ የሰጣቸው ናቸው አይደሉም የሚለውን ይበልጥ መከታተል እንደሚያስፈልግም አፅእኖት የሚሠጡት ዶክተር ሞላ፣ ይህን ኃላፊነትም የጉምሩክ ኮሚሽንም ብሎም የንግድ ሚኒስቴር በከፍተኛ ኃላፊነት መወጣት እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት።
ከተዓማኒነት አንፃር የፍራንኮ ቫሉታ ዕድል እንዲጠቀሙ ፈቃድ የተሰጣቸው አካላት መረጃ ሊቀርብ ይገባል እና ፍራንኮ ቫሉታ አስታከው ሌሎች ግብዓቶች ማምጣት አለማምጣታቸው መፈተሽ ያስፈልጋል በሚለው ይስማሙበታል።
የፍራንኮ ቫሉታው ውሳኔ በተለይ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት የአጭር ጊዜ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ እንዳልሆነ የሚያስገነዝቡት የምጣኔ ሀብት ምሁራኑ፣ ይህ እንደመሆኑም ችግሩን ለመሻገር ተጨማሪ መፍትሔዎች ማስተዋወቅ የግድ እንደሚልም ያስገነዝባሉ።
የፍራንኮ ቫሉታ ተግባራዊነት አሁንም የዋጋ ንረቱን ሊያረጋጋው ወይም ላያረጋጋው እንደሚችል የሚያመላካቱት አቶ ክቡር ገና፣ ፍራንኮ ቫሉታ በተወሰነ ጊዜ የተወሰነ ችግር እንዲፈታ እንጂ፤ ለረጅም ጊዜ የሚሆን መፍትሄ እንዳልሆነም ይገልጻሉ።
በተለይም ከሰላምና ጸጥታ ጋር ተያይዞ የሚነሱት ችግሮች ፈጣን እልባት መስጠት እንዲሁም፣ አስፈላጊ ምርቶችን ለማምረት የሚጠቅሙ መሆኑን የገለጹት አቶ ክቡር፣ ከፖሊሲ ጀምሮ የምርት አቀራረብና የምርት እድገት፣ የምርት ጥራት፣ የገበያ አቅርቦት፣ ሎጂስቲክስና የመሳሰሉት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግም ነው ያብራሩት።
ፍራንኮ ቫሉታ ጊዜያዊና የአጭር ጊዜና ምላሽ መስጫ መፍትሄ ስለመሆኑ የሚስማሙበት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱም፣ ለመፍትሔውም በቋሚነት የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ እና ከውስጥ ፍላጎት አልፎም የውጭ ምንዛሬ ማስገባት የሚያስችሉ ዋና ዋና ምርቶችን በስፋት ማምረት ብሎም ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚጠቅም አመልክተዋል።
‹‹ፍራንኮ ቫሉታ ጊዜያዊና ችግሮቹ ይበልጥ እንዳይባባሱ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ለአጭር ጊዜ የሚሆን ማስተንፈሻ ነው።በተለይ ከዕለት ዕለት እየተባባሰ የመጣውን ዋጋ ግሽበት ፈር ለማስያዝ ዘላቂው መፍትሄ የአገሪቱን መዋቅራዊ ኢኮኖሚ ኡደት ማስተካከል ይገባል»የሚሉት ዶክተር ሞላ አለማየሁ በበኩላቸው፣ በተለይ ፍላጎትና አቅርቦት ምጥጥን ልዩነቱን ለማስተካከል አገር ውስጥ በተሻለ ማምረት የሚችልበትን መንገድ መቀየስና ለዚህ ተግባራዊነትም ሌት ተቀን መትጋት እንደሚያስፈልግ አፅእኖት ሰጥተውታል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 /2014