ነጋዴዎች በትንሽ ድካም ብዙ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ የሚፈጽሟቸው አሻጥሮች በአገሪቱ ውስጥ ለሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት፣ የመሠረታዊ የእቃና አገልግሎት ዋጋ ንረት እና እጥረት፣ የውጪ ምንዛሪ እጥረት፣ የኑሮ ውድነት እና የመሳሰሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንዱ መንስኤ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ። በነጋዴዎች ከሚፈጸሙ አሻጥሮች መካከል ምግብና ምግብ ነክ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር ቀላቅሎ መሸጥ አንዱ ነው።
ምግብን እና ምግብ ነክ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር በመደባለቅ ነጋዴዎች ትርፍ ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት በእኛ ዘመን የተጀመረ እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ከጥንት ስልጣኔዎች ዘመን ጀምሮ ወይንን ከውሃ፣ እንዲሁም ወተትን ከውሃ ጋር በመቀላቀል ነጋዴዎች በትንሽ ወጪ ብዙ ትርፍ ለማግኘት ጥረት ያደርጉ እንደነበር መዛግብት ያስረዳሉ።
በእርግጥ በጥንት ዘመን ነጋዴዎች ትርፍን ለማግኘት በምግብ እና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የሚቀላቅሏቸው ነገሮች ነጋዴዎቹ ትርፍ እንዲያገኙ ከማስቻል በዘለለ በዘመናችን እንደሚስተዋለው በሸማቾች ጤና ላይ ቀውስ የማስከተል እድላቸው አነስተኛ ነው።
በአገራችን በዋናነት የምርት ክለሳ ወይም ለጤና ጠንቅ የሆኑ ባዕድ ነገሮች መቀላቀል የሚታይባቸው ምርቶች ቅቤ፣ በርበሬ፣ ወተት፣ አይብ፣ ማር፣ ዱቄት፣ ቡና፣ ዘይት እና እንጀራ መሆናቸው በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ካወጣቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል።
እንጀራ ከጀሶ፣ ቅቤ ከሙዝ፣ ማር ከሞላሰስ ወይም ከስኳር፣ በርበሬ ከሸክላ አፈር እና ከቀለም፣ ጤፍን ከአሸዋ፣ ቡናን ከዋንዛ ፍሬ ጋር የሚቀላቅሉ ነጋዴዎችን አስመልክቶ የአገራችንን ሚዲያዎች ዘገባ መስማት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለመደ ዘገባ ሆኗል።
ምግብ እና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ባዕድ ነገሮችን መቀላቀል በኢኮኖሚ ላይ ከሚፈጥረው ችግር ባሻገር የዜጎች ጤና ላይ ከባድ ችግር ሊያስከትል የሚችል መሆኑ ከሌሎች የኢኮኖሚ አሻጥሮች በላይ እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል። ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ ምግቦች እንደ ካንሰር፣ ኮሌስትሮል፣ ኩላሊት፣ ደም ግፊትና የመሳሰሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች መንስኤ እየሆነ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። ለዚህም ነው በምግብ ላይ ባዕድ ነገሮችን የመቀላቀል ወንጀሎችን ለመከላከል የተለየ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው።
እንደዚህ አይነት ምግብ እና ምግብ ነክ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር ቀላቅሎ መሸጥ በተለይም በበዓላት ወቅት የመባባስ ሁኔታ ሊኖር ይችላል። የበዓል ወቅት ምርቶች በገፍ ወደ ገበያ የሚቀርቡበት ወቅት እንደመሆኑ ለመንግሥት አካላት ለቁጥጥር አዳጋች ስለሚሆን እኩይ ዓላማ አንግበው ለሚንቀሳቀሱት የበለጠ በር ሊከፍት ይችላል።
ይህ ከሕግ አንጻርም ሆነ ከሞራል አንጻር ትክክል ያልሆነ ተግባር እንደመሆኑ ማንም ሳያስገድዳቸው ነጋዴዎች ከእንደዚህ አይነት ተግባር ሊቆጠቡ ይገባል። የዜጎችን ጤና የሚጎዳ ተግባር በመፈጸም የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ዘላቂ ትርፍ ሊሆን አይችልም። ወንድምና እና እህት ኢትዮጵያውያንን ጤና በማወክ የሚገኘውን የትኛውንም አይነት ትርፍ ሊጠየፉ ይገባል።
ሁሉም ነጋዴ በሕግ እና በሞራል ላይመራ ይችላል። ሕግና ሞራል የማይገዛቸው ነጋዴዎችን ሕዝቡ ሊያጋልጣቸው ይገባል። ምግብ የሚመስሉ ነገር ግን የምግብነት ይዘት የሌላቸው ምርቶች ከምግብ ጋር መቀላቀል ለሰው ልጆች የጤና እክል ከማስከተላቸው ባሻገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መዘዛቸው የከፋ እንደመሆኑ ይህንን ችግር ለመከላከል ሕዝቡ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በቅርበት መሥራት አለበት። ለሕግ አካላት እና ለሸማች ማኅበራት ጥቆማ በመስጠት ምርቱ እንዲወገድ ወይም አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድበት ሊሠራ ይገባል።
ሕዝቡ የሚያቀርባቸውን ጥቆማዎች በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል። ምግብ እና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ባዕድ ነገሮችን መቀላቀልን ለመከላከል ከዚህ ቀደም የወጡ የተለያዩ አዋጆች አሉ። እነዚህን አዋጆች በሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል።
ከዚህም ባለፈ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉ አዋጆች እና ሕጎችን መፈተሽ ያስፈልጋል። አዋጆቹና ሕጎቹ ክፍተት ካለባቸው ክፍተቶቹን መሙላት ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባል። በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ ካሉ አዋጆች ባሻገር በዚህ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችሉ ተጨማሪ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ባዕድ ነገሮች የተቀላቀለባቸው ምርቶችን ለመለየት የሚያስችሉ ላቦራቶሪዎችን ማጠናከር ልዩ ትኩረት የሚያሻው ነው። ለዚህ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ይህንን ተግባር እየሠራ ያለው የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አቅም ማጠናከር ወሳኝነት አለው።
ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከሚደረጉ ጥረቶች ባሻገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ችግሩን ለመቀነስ ፖሊስ በትኩረት ሊሠራ ይገባል። ምግቦች ከባዕድ ነገሮች ጋር ሲደባለቁ በቀጥተኛ እማኝ ሊሆኑ የሚችሉ የሰዎችና ሌሎች ማስረጃዎችን ለማግኘት የሚያስችሉ ፖሊሳዊ ኦፕሬሽኖችን መሥራት ይገባል። በመሰል እኩል ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ አካላት ላይ ሕጋዊና አስተማሪ እርምጃዎች ሊወሰድባቸው ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 18 /2014