
በቅርቡ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንትነት ምክትላቸውን በመተካት ሥልጣናቸውን ያስረከቡት አቶ ጌታቸው ረዳ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ቆይታ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ የፕሪቶሪያ ስምምነት መርሆዎችን ተከትለው ክልሉን ወደ መረጋጋት እና ልማት የሚወስዱ ርምጃዎችን እንዳያከናውኑ ጥቂት በሙስና የተጨማለቁ ሰዎች እንቅፋት እንደሆኑባቸው ነግረውናል።
ተፈፀሙ ያሏቸውን የሌብነትና ዘረፋ ድርጊቶች አጋልጠዋል። በተለይ በሕወሓት ውስጥ በአንድነትና በሕዝብ ደህንነት ስም የመሸጉ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች መኖራቸውን በማስረጃ ጠቅሰዋል። በዚህ ምክንያት በሥልጣን ዘመናቸው የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር እንዳልቻሉ ነግረውናል። የትግራይ ሕዝብ ህልውና በእነዚህ ጥቂት ኃይሎች ምክንያት ስጋት ውስጥ እንደሚገኝም ዘርዝረዋል።
የቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ያቀረቡት ክስ በሕወሓት ኃይሎች ውድቅ የተደረገ ቢሆንም ‹‹እሳት በሌለበት ጭስ አይታይም›› ነውና ነገሩ የዚህ የሌብነት ሰንሰለት ሊቆረጥ እንደሚገባ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያምናል።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነት፣ የትግራይ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ የፕሪቶሪያ ስምምነት ሥጋ ለብሶ መሬት ላይ ሊወርድ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ለተፈፃሚነቱ እንቅፋት የሆኑ ኃይሎች ‹‹ሀይ›› ሊባሉ ይገባል። ይህንን ኃላፊነት የክልሉ ነዋሪዎች መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። በመሀከላቸው የተንሰራፋውን የሌብነት ጅራት ቆርጠው ሊጥሉት ይገባል።
የትግራይ ሕዝብ ልክ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብዙ ፈተናዎችን እየተጋፈጠ ይገኛል። ፅናት፣ ፍትህ ናፋቂነት እና ቁርጠኝነት አሁንም የማህበረሰቡ መገለጫ መሆኑን አምናለሁ። እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ ያሉ አመራሮች በቅርቡ ይፋ ያደረጉት በክልሉ እየተካሄዱ ያሉ ብልሹ አሠራሮች የተጠያቂነት አስፈላጊነት፣ የሙስና አደጋዎች እና የእውነተኛ አንድነት አስፈላጊነትን ያመላክታሉ።
የአቶ ጌታቸው ረዳ በመረጃ ላይ የተመሠረቱ ክሶች ያለፈውን ስህተት ለመፍታት ብቻ ሳይሆን የወደፊት ሰላምና ክብር የሰፈነበት ለመገንባት በር ከፋች መሆናቸውን ልናውቅ ይገባል። ይህንን ስል ያለ ምክንያት አይደለም። አንድን ችግር ለመፍታት በቅድሚያ ችግሩን የፈጠረውን ምክንያት መገንዘብ ይኖርብናል። ቀሪው ‹‹እዳው ገብስ ነው›› ለዚህ አቶ ጌታቸው ረዳ በቂ የሆነ ምክንያት ሰጥተውናል።
ከልሉን ወደ ሰላም እና ልማት ለመመለስ በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጨማለቁ ጥቂት ግለሰቦች እንቅፋት ከሆኑ መፍትሔው ደግሞ ተጠያቂነትና የዘላቂ ሰላም ማስፈን ነው። አቶ ጌታቸው በግጭቶች ወቅት በተለይም በትግራይ የተፈፀሙ ወንጀሎች በጥልቀት ሊመረመሩ ይገባል ብለዋል። ይህንን ማድረግ ሲቻል የተዘረጋው የሌብነት ሰንሰለት ጫፍ ይገኛል።
ተጠያቂዎች መሪዎችም ሆኑ ግለሰቦች ማህበረሰቡ ፍትህ ሊያገኝ ይገባል። ይህንን የምለው ስለበቀል ሳይሆን ስለሰላም፣ ስለፍትህ እና ስለወደፊት የተረጋገጠ አንድነት ነው። የትግራይ ሕዝብ የደረሱበት የብዝበዛ ወንጀሎቸ፤ በስሙ የተነገደው ሸቀጥ እና ሌሎች ስህተቶች ታርመው እና ተጠያቂዎች የእጃቸውን አግኝተው ፍትህ ሲሰፍን ዳግም መተማመን መገንባት ይጀም ራል።
በአንድነትና በሰላም ስም ወንጀሎችን ችላ ማለት ወይም የእነዚህን ወንበዴዎች ያለመከሰስ መብትን መፍቀድ አሁን የተገኘውንም አንፃራዊ ሰላም አደጋ ውስጥ እንደሚከተ ሊታሰብበት ይገባል። ለዚህ ነው በክልሉ የተደረጉ ከባድ ወንጀሎችን መሠረት አድርጎ እውነተኛ ተጠያቂነት ማስፈን ማንም ሰው ከሕግ በላይ አለመሆኑን ያረጋግጣል የምለው።
አቶ ጌታቸው በትግራይ ሕዝብ አንድነት ስም እየተቆመረ መሆኑን በይፋ በአንደበታቸው ነግረውናል። አንድነትን እንደ ምክንያት በማድረግ የሀገሪቱን ሀብት ከውጭ ኃይሎች ጋር ተባብረው እየዘረፉ መሆኑን በሰነድ አረጋግጠው አቤት ብለዋል። ይህ የሚያሳየው የማኅበረሰቡን ስስ ጎን እነዚሀ ኃይሎች እንዴት እየተጠቀሙበት እንደሆነ ነው።
ርግጥ ነው በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ አንድነት ብዙ ጊዜ እንደ ጥንካሬ ይወደሳል፤ ነገር ግን እውነት ላይ መመሥረት አለበት። በግልፅ እያየናቸው ያሉ ኢፍትሃዊ ድርጊቶችን እልባት ሳያገኙ የአንድነት ጥሪዎች ትርጉም የለሾች ናቸው። ወንጀሎችን ለመሸሸግ ሕዝብ ስሱ ልብ ባለው የአንድነት ስም መማል ስልታዊና አደገኛ የወንጀል ሴራ ነው።
አቶ ጌታቸው ረዳ ስም ጠርተው በማስረጃ የከሰሷቸው ቡድኖች ሕዝቡን በሌብነት ተጨማልቀው ሲበዘብዙና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ደግሞ አንድነትን እንደ መሳሪያ ሊጠቀሙበት እየሞከሩ ነው። ይህ ዓይነቱ ለሀገርም ሆነ ለትግራይ ሕዝብ የማይጠቅም ‹‹የውሸት አንድነት›› ሊጋለጥ ይገባል። እውነተኛ አንድነት የሚመነጨው ከኢትዮጵያዊነትና እርሱን ለማፅናት ተግባራዊ ከሚደረግ የጋራ ዓላማ ውስጥ ነው።
ለዚህ ደግሞ ፍትህ፣ እኩልነት እና መከባበር ያስፈልጋል። ጥቂቶች ሕግንና ሕዝብን ተገን አድርገው እንዳሻቸው በወርቅ ሰሀን እጃቸውን ሊታጠቡ አይገባም። የትግራይ ሕዝብ ፍትህን በኛ አረጋገጥ ሂደት ውስጥ ከአንድ ሁልጊዜው አስደናቂ አጋርነቱን ማሳየት አለበት። የመደራጀት እና መብቱን በፈለገው አደረጃጀት ውስጥ ሆኖ ማስከበር መቻል አለበት።
አደገኛ የሙስና እና የሀብት ብዝበዛ የሀገር ህልውናን አደጋ ውስጥ ይጥላል። በቅርብ ጉዳዩን ይከታተሉ ከነበሩ አመራር አቶ ጌታቸው ረዳ የሰማነው ወንጀል ይህንን የሚያረጋግጥ ነው። በክልሉ ከፍተኛ የወርቅ ኮንትሮባንድ መኖሩን የቀድሞ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት በሥልጣን ቆይታቸው ባደረጉት ጥናት ማረጋገጣቸውን ነግረውናል።
የወርቅ ኮንትሮባንድ የመሰሉ ሕገ ወጥ ተግባራት ለልማት የታሰቡ ግቦችን ያሰናክላሉ። የሕዝብን ተስፋ ያጨልማሉ። ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅም የሚያስቀድሙ መሪዎች ሕዝባቸውን መክዳታቸውን እጅግ አሳሳቢ ነው። ወጣቶች ለእነዚህ ቡድኖች የግል ጥቅም ሲባል ውዱን ሕይወታቸውን ሲሰው ባለሥልጣናቱ በወርቅ ንግድ አቅላቸውን መሳታቸው በጣም አሳሳቢ ነው። እንዲህ ያለውን የተደራጀ ሌብነት ለመግታት እና ወንጀለኞችን ለማጋለጥ ግልጽነትና ድፍረት ይጠይቃል።
አቶ ጌታቸው በዚህ ረገድ ትልቁን ኃላፊነት ወስደዋል፤ ሕዝቡ ራሱን አደራጅቶ ቀጣይ ርምጃዎችን ለመውሰድ የቤት ሥራ አለበት። እነዚህ ቡድኖች የሕዝቡን ህልውና የሚጠብቁ ሳይሆን በሕገወጥ የወርቅ ንግድ ለመክበር የሚንቀሳቀሱ ተራ ወንበዴዎች መሆናቸውን የትግራይ ሕዝብ መገንዘብ አለበት።
በተለይ ሕዝቡ የተሰረቀውን ሀብቶቹን መልሶ ማግኘት እና ወደ ልማት ፊቱን ማዞር ይኖርበታል። ይህንን ሃሳብ ሲያራምድ ‹‹የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን ለመጣስ እየተሠራ ነው›› የሚል ተራ ፕሮፓጋንዳ ከዚህ የወንጀል ሰንሰለት መሪዎች ሊያጋጥመው ይችላል። ሆኖም በቀጥታ መጋፈት ይኖርበታል።
የትግራይ ወጣቶች ልዩ እውቅና ይገባቸዋል። ብዙዎች ሕይወታቸውን፣ ተስፋቸውን እና የወደፊት እጣ ፈንታቸውን ለአመኑበት ጉዳይ መስዋዕትነት አድርገዋል። ሆኖም መስዋዕትነቱ በሌቦቸ እና በጥቂት ወንጀለኞች የተጠለፈ መሆኑ ያስቆጫል። ለዚህ ነው እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ ዓይነት የክልሉ አመራሮች ወጣቶች አላስፈላጊ በሆኑ፣ አንድነትን በሚሸረሽሩ፣ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ውስጥ በሚከቱ በግጭቶች ወይም በኢኮኖሚያዊ አሻጥሮች እንዳይበዘበዙ መከላከል የሚኖርባቸው። የክልሉ ሕዝብ ሰላም አግኝቶ፣ ወንጀለኞች እና የሌብነት ሰንሰለት የዘረጉ ቡድኖች ተቀጥተው፤ በትምህርት፣ በሥራ እድሎች ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል።
በክልሉ የሕግ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስፈላጊ ነው። በተለይ ዜጎች በፈለጉት የፖለቲካ አደረጃጀት ውስጥ በነፃነት መሳተፍ እንዲችሉ ማድረግ ይገባል። በትግራይ ሕዝብ ህልውና እና አንድነት ስም የግል ጥቅማቸውን የሚያስከብሩ ወንበዴዎችን ሀይ ማለት ይገባል። ለዚህ ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕዝቡ የሚቀነቀኑ አዳዲስ የፖለቲካ ባሕሎች ሊበረታታ የሚገባው።
በተለይ ተቋማትን ማጠናከር ሁሉም ሰው በእኩል (ባለሥልጣን ይሁን ማንኛውም ግለሰብ) እጁን ሌብነትና ብልሹ አሠራር ውስጥ ከከተተ ተጠያቂ እንዲሆን ያስችላል። ገለልተኛ ፍርድ ቤቶች፣ ግልጽ አስተዳደር እና የዜጎች ቁጥጥር በክልሉ ሊሰፍን ይገባል።
በቅርቡ በወርቅ ኮንትሮባንድ ላይ ባለሥልጣናትን ተጠያቂ ለማድረግ በአቶ ጌታቸው ተነሳሽነት የተደረገው ግፊት አዎንታዊ ርምጃ ነው። እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች የሚያሳዩት ለውጥ የሚመጣው አዲስ የፖለቲካ ባሕል፣ ቁርጠኝነት እና የሕዝብ መንቃት ሲኖር ነው።
ማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ፍትህ ማግኘት አለበት። ብዙ የትግራይ ተወላጆች የክልሉ ሀብት ቢኖርም በድህነት ውስጥ ይኖራሉ። አብዛኛው ወጣት ሥራ አጥ ነው። ወጣቱ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እና የመሬት ተጠቃሚነት መሠረታዊ መብቶቹ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየሰማናቸው የሚገኙ እንደ መሬት ነጠቃ ያሉ ወይም ሕገ ወጥ የኮንትሮባንድ ንግዶች ሊቆሙ ይገባል።
ለዚህ የፌዴራል መንግሥት ሚና ወሳኝ ነው። የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈፃሚ እንዲሆን ግፊት ማድረግ ይገባዋል። በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያሉ አዳዲስ የትግራይ ክልል መሪዎች በእውነተኛ ለውጦች ላይ ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውን ደጋግመው ማረጋገጥ ይገባቸዋል። የፌዴራል መሠረተ ልማቶችን መጠበቅ፣ የጤና አጠባበቅ እና የትምህርት ሥርዓትን መልሶ ለመገንባት የሚደረግ የጋራ ጥረት ለአንድነት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ሃሳቤን ከማጠቃለል በፊት ይህንን ለማለት እወድዳለሁ። የትግራይ ቀጣይ መንገድ ግልፅ መሆን አለበት። ተጠያቂነት፣ እውነተኛ አንድነት እና ሰላምን ማስከበር ይገባዋል። ይህ ኃላፊነት የሕዝቡ፣ የምሁራኑ እና የተራማጅ ፖለቲከኞች የጋራ ዓላማ መሆን ይገባዋል።
ሌብነትን መግታት፣ ወጣቶችን በፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማብቃት እና አንድነትን ማጎልበት ይገባል። በቅርብ ጊዜ ውስጥ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶችን ወደ እድሎች ለመለወጥ ሕዝቡ ሊተባበር ይገባል። ርግጥ ነው የትግራይ ሕዝብ ለለውጥ ዝግጁ መሆኑን አሳይቷል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣ የአካባቢ መሪዎች፣ የፌዴራል ባለሥልጣናት እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከጎኑ የሚቆሙበት ጊዜ አሁን ነው። ሆኖም ግን የሌብነቱን ሰንሰለት ሕዝቡ እራሱ ሊቆርጠው ይገባል። የትግራይ ሕዝብ ለከንቱ የጥቂት ግለሰቦች ምቾት ለማስጠበቅ ሲሆን ብቻ መስዋዕት መሆን የለበትም። ሰላም!!
ሰው መሆን
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም