አዲስ አበባ፡- በቲቢ በሽታ ላይ በየዓመቱ የሚሠሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የበሽታውን ስርጭት በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ቢሆንም ኢትዮጵያ አሁንም ከፍተኛ የቲቢ በሽታ ጫና እንዳለባት የብሄራዊ ቲቢ ምርምር አማካሪ ኮሚቴ አስታወቀ።
የኮሚቴው ሠብሳቢ ዶክተር ጌትነት ይመር በተለይም ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በየዓመቱ በሚካሄደው የቲቢ ምርምር ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ የምርምር ሥራዎች አብዛኛዎቹ የቲቢ በሽታን በመከላከል ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ይሁንና ኢትዮጵያ አሁንም ከፍተኛ የቲቢ ጫና ካለባቸው ሰላሳ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
እንደ ሰብሳቢው ገለፃ፤ የቲቢ በሽታን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን ለማወቅና አዳዲስ አሰራሮችንም ለማምጣት የምርምር ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ወሳኝ ነው። በኢትዮጵያም በቲቢ ላይ የተለያዩ የምርምር ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፤ በሽታንውን በመከላከል ረገድም የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
ቀደም ሲል በሀገሪቱ የነበረው የቲቢ ስርጭት ከፍተኛ የነበረ መሆኑን ሠብሳቢው ያስታወሱ ሲሆን፤ ሆኖም በተሠሩ አበረታች የምርምር ሥራዎች የበሽታው ስርጭት እየቀነሰ መምጣቱን ገልፀዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ በቲቢ ኤች አይ ቪ እና መድኃኒቱን በተላመደ ቲቢ ከፍተኛ ጫና ካለባቸው ሰላሳ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗንም ሥራ አስኪያጁ ጠቅሰው፤ ቲቢን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ካልተሠሩ በሽታው አሁንም የህብረተሰብ ጤና ችግር ሆኖ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
ዘንድሮው በ14ኛው የቲቢ ምርምር ጉባኤ መድኃኒትን ከመላመድም በላይ የሆኑ የቲቢ በሽታዎች፣ መድኃኒትን የተላመደን ቲቢ የህክምናው ጊዜ ማሳጠርና በአፍ በሚዋጥ መድኃኒት ብቻ መድኃኒቱን ከተላመደ የቲቢ በሽታ መዳን እንደሚቻል የሚያሳዩ በሀገር ውስጥ የተሠሩ የምርምር ሥራዎች ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዚሁ ሳምንት መጨረሻ መጋቢት 14 እና 15 ቀን 2011 ዓ.ም በሚካሄደው በዚሁ ጉባኤ የውጭና የሀገር ውስጥ ተመራማሪዎች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ዘጠና የሚጠጉ የምርምር ሥራዎችም ይቀርባሉ ተብሎ ይታሰባል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2011
በአስናቀ ፀጋዬ !�E_�UF�9�a%K