በዚህ አምድ በአገራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት ነው። በዛሬው አምዳችን ለበርካታ ዓመታት መንግስታዊ የሥራ ኃላፊነትን በአግባቡ ሲወጡ ከቆዩት በጠቅላይ አቃቤ ህግ ማዕረግ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና የህግ አማካሪ አቶ መርሐፅድቅ መኮንን ጋር ቆይታ አድርገናል። ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ በህግ ዓይን ቃኝተዋል፤ የመፍትሄ ሐሳቦችንም ሰንዝረዋል፤ እርቀ ሠላም ኮሚሽን በሥራ ስኬታማ እንዲሆን መከወን ስለሚገባቸው ጉዳዮች፣ በክልሎች መካከል የሚስተዋለው መስተጋብር እንዲሁም በቀጣይ አገሪቱ ሰላማዊ ሆና እንድትቀጥል ሊደረጉ ስለሚገቡ ጥንቃቄዎችን ጠቁመዋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ለሰብዓዊ ዕርዳታ እና የተረጋጋ መንፈስ ለመፍጠር ሲባል ወደ ትግራይ የሚወስዱ መንገዶች መከፈታቸውና የአየር በረራ መፈቀዱን በህግ ዓይን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ መርሐፅድቅ፡– ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በህግ ማስከበር ዘመቻው በአብዛኛው የአገር ውስጥ ጦርነት በመሆኑ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል። ከፍተኛ ንብረት ወድሟል፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ አዳክሟል፤ የህብረተሰቡን ኑሮ አመሰቃቅሏል። በተለይ ደግሞ ጦርነት ይካሄድባቸው የነበረባቸው አካባቢዎች ክፉኛ ተጎድተዋል። ምናልባት ባለበት ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ አገሪቱን ወደ ለየለት ከፍተኛ የመጠፋፋት ሁኔታ ይዞ እንደሚሄድና በማንኛውም ወጪ፤ ኪሳራ እና መሥዕዋትነት ሠላም መረጋጋጥ እንደሚገባ ይታመናል። ይህ እኛ ዜጎቿ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የውስጥ ለውስጥ ጦርነት ለረጅም ጊዜ መቀጠል እንደሌለበት ሲመከርበት የቆየ ነው። አሁንም ቢሆን ስስ የሆነ የግጭት መገታት ቢኖርም ይህም ቢሆን ትንሽ ተስፋ የሚሰጥ ስለሆነ ወደ ሰብዓዊ እርዳታ ማተኮር ይገባል የሚል ነው። በውስጣዊና ውጫዊ ጫና የተነሳ መንግስት ይህን አቋም ወስዷል። ነገር ግን ግን በአሸባሪ ሕወሓትና ፌደራል መንግስት መካከል የተደረገ ሥምምት ነው ለማለት ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ተደራድረው በጋራ ተኩስ ማቆም አለባቸው። ቀደም ሲል የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት ወስዶ የነበረው የፌደራል መንግስት ነው።
አሸባሪ ኃይል ግን ይህንን እንደ አጋጣሚ በመቁጠር ለመደራጀት እና ወደ መሐል አገር ገብቶ ከፍተኛ ጥፋት ለማድረስ ምክንያት ሆኗል። ጥቃቱ የደረሰባቸው ኃይሎችና የፌደራል መንግስት በመጨረሻ ወደ መጣበት እንዲመለስ አድርገውታል። ግን ግልጽ መደረግ ያለበት ጦርነት በግልጽ ቆሟል ብሎ አፍ ሞልቶ ለመናገር የሚያስችል ሥምምነት ተደርሷል ማለት አያስችልም። አሸባሪ ኃይሉ ግን በጉዳዩ የተስማማ መስሎ ቀርቧል፤ ተቋርጦ የነበረው ሰብዓዊ እርዳታም በአየርም በየብስም ወትሮ ከነበረው በተሻለ እንዲደርስ እየተደረገ ነው። ግን መታወቅ ያለበት በጦርነቱ የተጎዱ ሰዎችንና አካባቢዎችን ሙሉ ለሙሉ እያዳረሰ ነው ማለት አይቻልም። እነዚህን አካባቢዎችን በማለፍ ወደ ትግራይ እየተጓጓዘ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፍ ተቋማት ፕሮፓጋንዳ ብቻ ሳይሆን ዕርዳታ ጭምር ወደ ትግራይ ያደላ እንጂ የአማራና አፋር ክልል ጉዳትን ከግምት አላስገቡም። ይህ ከሞራል እና ከሰብዓዊነት ህግ አኳያ አግባብ ነው?
አቶ መርሐፅድቅ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው። ይህን ጉዳይ አንስተን ወደ ብያኔ ከመሄዳችን በፊት የትኩረቱ መነሻ ምንድን ነው ብለን ማየት አለብን። ሰፋ ያለው ድምጽ የሚሰማው በአብዛኛው የጦርነቱ መነሻ ትግራይ ነው በሚል በአብዛኛው ትግራይ ክልልን ማዕከል ያደረገ ነው። መላው የትግራይን ክፍል በከፍተኛ ደረጃ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ነው ብለው እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምክንያት አለ። የትግራይ ክልልን ሲመራ የነበረው ሕወሓት ነው። ከዚህም አልፎ በማዕከላዊ መንግስት ላይ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ከፍተኛውን ሥልጣን ይዞ ቆይቷል። በዚህ ወቅት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ወደ ተሳሳተ መንገድ የሚወስዱ ሰፋፊ የውሸት ትርክቶችን በመቅረጽ ራሱን በዲፕሎማሲ ያጎለበተ አንዳንድ ጊዜም በምዕራቡ አለም ላሉ ኃያላን አገራት ራሱን በማስገዛትና በቀጣናው በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ራሱን ወኪል በመመስል የአካባቢው ፖሊስ ሆኖ ለመቆየት ሲሠራ እንደነበር ይታወቃል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በመንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ የሰገሰጋቸው ኃይሎች አሉ። ይህ እንግዲህ የሰብዓዊ እርዳታ ተሟጋች ድርጅቶችን ጭምር ያካትታል። በዚህ የተነሳ ለዚህ ቡድን ያላቸው ልብ ስስ ነው። በተለይም ደግሞ በአሜሪካ አስተዳደር በተለይም በውጭ ጉዳይ ዲፓርትመንት በቀድሞ አስተዳደር ውስጥ ያሉ እንደ ሱዛን ራይዝ፣ ጃንዳይ የመሳሰሉት የሕወሓትን አይዶሎጂ የሚደግፉ እና በመስክ ድረስ ሄደው ጓደኛ ያደረጓቸው ሰዎች ያሉበት ነው። እንግዲህ ትግራይን ከኢትዮጵያ በራቀ መልኩ እንዲያውቁ እና የሕወሓትን የማጭበርበር ሥራ በከፍተኛ ደረጃ አቅፎ ያቆየ ኃይል ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ከፌደራሉ መንግስት ርቆ ክልሉን ማስተዳደር በጀመረበት እና ‹‹ዲፋክቶ ስቴት›› ለመመስረት ሙከራ አድርጎ በሚመራበት ወቅት የተበዳይነት ስሜትን ይዞ በመቅረብ ጉዳዩን የሚያጮሁለት ብዙ ነበሩ። በዚህም የተነሳ ትኩረት ለማግኘት ችሏል። በአሁኑ ወቅትም ሰብዓዊ ዕርዳታ አማራ እና አፋር ክልልን አልፎ ወደ ትግራይ ክልል እንዲሄድ መደረጉ ይህም ብቻ ሳይሆን አሸባሪው በአማራ እና አፋር ክልል የተወሰኑ ወረዳዎችን ተቆጣጥሮና ኮሪደሩን ዘግቶ ዕርዳታ አመላላሽ ተሽከርካሪዎችን እየወጋ እና እያስቆመ ባለበት ሁኔታ ብሎም ዕርዳታ በአየር ብቻ እንዲሄድለት ሙከራ እያደረገ ባለበት ሁኔታ ይህ ለምን ሆነ ከተባለ ከላይ ያልነው ምክንያት ዋንኛው ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ከሞራል፤ ህግ እና ከሰብዓዊነት አኳያ አግባብ ነው?
አቶ መርሐፅድቅ፡– ከህግ አኳያ ሠብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የሚመራባቸው ዓለም አቀፍ መርሆች አሉ። በዋነኝነት ይህ የአገር ውስጥ ግጭት በመሆኑ የሚፈናቀሉ ወገኖች በሚኖሩበት ወቅት ለእነዚህ ዜጎች ዕርዳታ የሚቀርብበት ሁኔታ አለ። በመጀመሪያ ለመሰል ችግር ቅድሚያ ኃላፊነት የሚወስዱት የአገር ውስጥ መንግስታት ናቸው። ነገር ግን ይህ ማድረግ ካቃታቸው ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ መጠየቅና መፈለግ የተለመደና የሚፈቀድ ነው። ይህ እንዴት ይፈቀዳል ከተባለ 1998 ዓ.ም እንደ ዓለም አቀፍ ባህል ህግ ወይንም ልምድ የሚወሰደው የወጣው የውስጥ መፈናቀልን ለማገዝ የወጣ መሪ መርሆች አሉ። በዚህ ውስጥ አንቀፅ 24 ላይ ማናቸውም ዓይነት የሚደረጉ ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ አራት መርሆችን መከተል አለበት ይላል።
የመጀመሪያው ሰብዓዊነት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ዕርዳታ ሲሰጥ ለየትኛውም መወገን የለበትም፤ ወይንም ዕርዳታ አቅራቢው ከየትኛውም ወገን ገለልተኛ መሆን አለበት። ሦስተኛው የዕርዳታ መመዘኛው ፍላጎት ነው። ነገር ግን አዛውንት፤ ሴቶች፤ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እያለ የፍላጎት ቅደም ተከተል ሊኖር ይችላል። አራተኛው ደግሞ አለማዳላት ነው። ይህ ለማንኛውም አካላት ማዳላት የለበትም የሚለውን መርህና ሐሳብ የያዘ ነው። ከዚህም በተጨማሪ መሰል ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ለወታደራዊ ድጋፎች እንዳይውሉ ጥንቃቄ መደረግ አለበት የሚል ነው።
በመሰረቱ የራሳችንን እቅድ አውጥተን ተፈናቃዮቻችን ማቋቋም ካልቻልን በመሰል እርዳታ መቀጠል አንችልም። የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አካል ነን። ዓለም አቀፉ ተቋማት ችግራችን ሊጋሩ ይገባል። ዞሮ ዞሮ መሰል ዕርዳታዎችን ለማድረግ ሲገባም አገሪቱን የሚከበሩ ህጎችና ግዴታዎች አሉ፤ አገሪቱን ከሚያስተዳድር መንግስት ጋር በመናበብ ነው።
አሁን የሚታየው ግን ከዚህ በተቃራኒ አይደለም። ጦርነቱ ትግራይ ተጀምሮ በትግራይ ላይ አልተጠናቀቀም። አሸባሪው ኃይል እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ መጥቶ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፤ የግለሰብ ቤቶችና ንብረቶች ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል፤ ሴቶችና ህፃናት በከፍተኛ ደረጃ ተጎሳቅለዋል፤ ተደፍረዋል። በአማራ እና አፋር ክልል ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ ተከስቷል። ከሞተው እና ከቆሰለው በተጨማሪ በርካቶች ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ውስጥ ናቸው። አንዳንዶች ደግሞ በባዶ ሜዳ ላይ ናቸው።
ለአብነት ዋግኽምራ አካባቢ ያለውን ማየት ይቻላል። የዓለም አቀፍ ተቋማት ማገዝ ነበረባቸው። ግን በየብስና በአየር በቂ በረራ የተፈቀው እርዳታ ይግባ የሚለውና ዓለም አቀፉ ተቋማት ጩኸታቸው ወደ ትግራይ ብቻ ያደላ ነው። ይህ ሁሉ ጫና መንግስት መሥራት ከሚገባው በላይ እንዲሰራ ጫና ውስጥ ወድቋል። ይህ ዓለም አቀፍ መርህን የሚጣረስ ነው።
በመርህ 25 ላይ እንደተቀመጠው ማንኛውም ሰብዓዊ ዕርዳታ ለጦርነት ዓላማ አለመዋሉን ማረጋገጥ አለበት የሚለው ተጥሷል። ወደ ትግራይ ክልል የሚጫኑ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ለህዝብ በትክክል መድረሳቸው አጠራጣሪ ነው። ትግራይ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችን ናቸው ሰብዓዊ እርዳታ ቢደርስ የሚከፋው ያለ አይመስለኝም። መከተል የሚገባቸውን መርሆች መከበር አለባቸው። ሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች መድሃኒቶችና ሌሎች ሰብዓዊ ቁሶች ለጦርነት ዓላማ እየዋሉ በቀጥታም ለሕወሓት ዓላማ ማስፈፀሚያ መሆናቸው ተረጋግጧል።
ለአብነትም የዓለም ምግብ ድርጅት የጫኑ በርካታ ተሽከርካሪዎችም ሳይመለሱ ቀርተዋል። ይህ ሁሉ የሚያሳያው ሰብዓዊ ዕርዳታ ሰብዓዊነት፤ አለማዳላት፣ ገለልተኝትን የሚሉ ዓለም አቀፍ መርሆችን የተቃረነ ነው። ዓለም አቀፍ ተቋማት በተለይም ደግሞ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚባሉትም የትግራይ ወራሪ ኃይሎች በአፋር እና አማራ ክልል ሴቶችን ሲደፍሩ፣ ትምህርት ቤቶችን ሲያቃጥሉ፣ ንብረት ሲያወድሙ፣ ህዝብ ሲያሰቃዩ፣ ህፃናትን ሲገድሉ፤ ተቋማትን በከፍተኛ ደረጃ ሲዘርፉ፣ በቡድኑ የደረሱ ከፍተኛ ሰብዓዊ ጥሰቶችን አስመልክተው መግለጫ ሲያወጡ ነበር። ነገር ግን በየጊዜው አቋማቸውን ሲቀያይሩ ነበር። በሰብዓዊነትም ሆነ በሰብዓዊ መብቶች የሚወሰዱት አቋም አስተማማኝ አይደለም። በመሆኑም በራስ አገዝ ፕሮጀክቶች ራሳችንን ማቋቋም ካልሞከርን በስተቀር በሠብዓዊ ዕርዳታ ሥም ሰፊ ችግሮች ይከተላሉ።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ቀደም ሲል የተናጠል ተኩስ አቁም ሥምምነት አድርጎ ከትግራይ ክልል ሲወጣ ወራሪ ቡድኑ ራሱን በማደራጀት አማራ እና አፋር ክልልን መልሶ ወሯል። አሁንም የፌደራል መንግስት ከአንድ ወገን ብቻ ኃላፊነት መወሰዱ ችግር አያመጣም?
አቶ መርሐፅድቅ፡– ጥያቄዎቹና ስጋቶቹ ትክክል ናቸው። መንግስት መሰል የተናጠል ዕርምጃ ሲወስድ በዘፈቀደ የሚወስድ አይመስለኝም። በመሰረቱ የመጀመሪያው የተናጠል ተኩስ ማቆም ሥምምነት ሲባል አይገባኝም። ሥምምነት የሁለት ወገኖች ድርድር የሚደረስበት ውል መሆኑን አምናለሁ። ይህ መባል ያለበት የተናጠል ተኩስ ማቆም እርምጃ ነው። መንግስት መሰል እርምጃዎችን የሚወስደው ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ቅድመ ሁኔታዎችን በመገምገም ነው። ምናልባት የፌደራል መንግስት ተቻኩሎ የወሰደው እርምጃ ነው የሚሉ አሉ። ግን ይህ በጥንቃቄ መታየት አለበት።
ጦርነቱ ረጅም ጊዜ ወስዷል። ማወቅ ያለብን ሕወሓት ጦርነቱን የጀመረው ለራሱ የገዘፈ ምስል በመስጠት ነው። መንግስት ጊዜ ሲሰጥ አሸባሪ ቡድን መልሶ ተደራጀ የሚለው አንደኛው ምክንያት ሊሆን ይችላል። መንግስት ግን የወሰደው እርምጃ በተጠና መንገድ እንደሆነ ዘርዘር ያለ ምክንያት ሊሰጥ ይችላል። መታወቅ ያለበት ትግራይ ክልል ያለውም ህዝብ የእኛው ህዝብ ነው። አሁንም የትግራይ ህዝብ ከሕወሓት አመራር ጋር ያለውን ሁኔታ ግንኙነት ለማወቅም ይረዳዋል የሚል እሳቤም ያግዛል። ነገር ግን መጨረሻ ላይ የታየው ይህ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ሰብዓዊ ዕርዳታ ሥም በአየርና በየብስ በገፍ እርዳታ ሲገባ አሸባሪውን ቡድን ለማገዝ የሚውሉ ቁሳዊና የሰነድ ድጋፎች የማድረግ ዕድል አይሰፋም?
አቶ መርሐጽቅ፡- ውስጥ ለውስጥ የሚካሄድ ጦርነት በጣም አስቸጋሪ ነው። በሁለት አገራት መካከል ቢሆን ከፍተኛ የሆነ የጎራ መደበላለቅ ይቀንሳል። ውስጣዊ ጦርነት ሚዛኑን ለመረዳት አስቸጋሪ ሁኔታዎች የመፈጠር ዕድል አላቸው። በጦርነት በመሬት ላይ ኃይል ሲገኝ በዲፕሎማሲውም ከፍተኛ የሆነ ዕድል ይገኛል። አሸባሪ ሕወሓት መሰሪ ነው። ሰላማዊ ድርድርና ውይይት እንዲህ በቀላሉ አይገባውም። ሕወሓት መሰሪ ድርጅት በመሆኑ በስልጣን ዘመኑ ቀብሮ ያቆያቸውን መሳሪያዎችንም ሲጠቀም ነበር። ለህዝብ የሚሰጥ ሰብዓዊ ድጋፍ እንኳ ሳይቀር የሕወሓት ታጣቂዎች ዘርፈው ሲጠቀሙ ነበር። ነገር ግን የፌደራል መንግስት የወሰደው የተኩስ አቁም እርምጃው የትግራይ ህዝብን ያሉበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚሆን ነው።
በእርግጥ አሸባሪው ሕወሓት ከሰሜን ሸዋ የተመለስኩት ፈልጌና አፈግፍጌ እንጂ ተሸንፌ አይደለም ሲል ይዋሻል። ዞሮ ዞሮ ግን የሕወሓት መሰሪነት ገና ብዙ መከራ ያመጣብናል። ከዚህ የምንማረው ነገር አለ። የጥምር ኃይሉ ሆነ የፌደራል መንግስት ከፍተኛ መሥዕዋትነት ከፍለዋል ለ17 ወራት የተካሄደ ጦርነት ነው። እስካሁን የደረሰውን ውድመት እንኳ ታሳቢ አድርገን ከአሁን በኋላ በእያንዳንዱ ሂደት የምንወስደው እርምጃ የከፋ ኪሳራ እንዳንከፍል ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል። ነገር ግን ምን ትርፍ ተገኘ ምንስ ጉዳት አስከተለ የሚለውን ግን በጥልቅ ጥናት የሚመለስ ነው። የሚወሰደው እርምጃ በብሄራዊ ሉዓላዊነት ጋር የተያያዘ መሆኑን ማሰብ አስፈላጊ ነው። ይህ ውስጣዊ ጦርነት በመሆኑም የተወሳሰበ በመሆኑ እያንዳንዱ የሚወሰደው እርምጃ ጥንቃቄ ይፈልጋል።
አሸባሪ ሕወሓትም ጦርነቱን ብቻውን የተዋጋው ሳይሆን ከውስጥና ከውጭ የሚደገፍ ነው። ሸኔ፣ ጉሙዝ ታጣቂ ቡድኖችንና የመሳሰሉትም በየፊናቸው የሚያግዙት ቡድን ነው። የፌደራል መንግስት የተወሰደው የተኩስ ማቆም እርምጃ መልካም ቢሆንም ከሕወሓት መሰሪ ባህሪ አኳያ ወደ ሠላም ይመጣል ወይ የሚለውን በሚገባ ማጤን ይገባል። በሌላ በኩል ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት አዕምሮ የሚገዛ ከሆነ እና ወደ ሠላም ከመጣ ህዝቡን ለሌላ ቀውስ እንዳይዳረግ ያግዛል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ጉዳይ በቀጣናው ላይም ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ ተጨማሪ ችግር ሳይኖር ችግሩን እንዴት ማቆም ይቻላል የሚሉ ኃይሎችም ተበራክተዋል። ጫናው ደግሞ የሚበዛው ፌደራል መንግስት ላይ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ጫናው የኢትዮጵያን ሠላም የማፈይልጉ እና በትርምስ ውስጥ እንድትኖር በሚፈልጉ ብሎም የቀጣናው ሠላም የሚጠቅማቸው ወዳጅ አገራት ጭምርም የሚሳተፉበት መሆኑንም ማጤን ያስፈልጋል። ከመሃል አገር ተነስተውም አሸባሪን ቡድን የሚደግፉ አሉ። ጦርነቱ ካልቆመ መተላለቁ ይቀጥላል። ሌላው ይህን ቡድን የሚያግዙ አካላትን በጥናት ላይ ተመስርቶ ዕርምጃ መውሰድ እና ከጨዋታው ውጭ ማድረግም ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- አገር በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ሆና ሰሞኑን አማራና ኦሮሚያ ክልል ብልጽግናዎች የሚያወጡት መግለጫ አግባብ ነውን? እንደአገራዊና በአንድ ርዕዮተ ዓለም ለሚመራ ፓርቲስ ይህ አካሄድ አደጋ የለውም?
አቶ መርሐፅድቅ መኮንን፡- እውነት ለመናገር አገር ከሚመራ አንድ የተደራጀ ፓርቲ አይጠበቅም። ብልፅግና ፓርቲ ከተባለ በኋላ የራሳቸው ምክንያት ሊኖር ይችላል ካዛ በኋላ የብልፅግና ፓርቲ አንድ ፓርቲ ከሆነ በየመንደሩስ ሲደርስ የሆነ ብሄር ጠርተህ መልሰህ ብልፅግና የምትልበት ምክንያት ሊኖር አይችልም። የብልፅግና ፓርቲ የአማራ፣ የሶማሌ፣ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ እያልክ የአገሪቱን የቆዳ ስፋት ተከትለህ የፓርቲውን መዋቅር ልታስፋፋ ትችላለህ። ይህን ማድረግ ሲገባ መልሶ ያንኑ ብሄር ወለድ የነበሩትን ተቋማት ፓርቲዎች ምንም እንኳን ህጋዊ ሰውነት የላቸውም ቢባልም አሁንም ህጋዊ ሰውነት ያላቸው በሚያስመስል መንገድ ነው ሲንቀሳቀሱ የምናያቸው። ይህ የመጀመሪያው ችግር ይመስለኛል።
ከዚህ ባሸገር ደግሞ ቢያንስ መሪዎች ናቸው። በተለያየ ደረጃ ኦሮሚያን የሚመሩትም ሆነ አማራን የሚመሩት ትልቅ ህዝብ እንመራለን ብለው በምርጫ ተወዳድረው አሸንፋችኋል ተብለው በቦርድ ተመስክሮላቸው መንግስታዊ ስልጣን የያዙና እንደፖሊት ቢሮ በጋራ አገር ለመምራት የሚገናኙ ኃይሎች ናቸው። ወደየመንደራቸው ሲመለሱ አንዲትን መንደር ወስደው ለምሳሌ ምንጃር ሸንኮራ ውስጥ ነው ያለችው ወይስ ፈንታሌ ናት የተባለችው መንደር አንደኛው አሞራ ቤት ናት ሲል ሌላኛው ቆርኬ ናት ይላል። ቦታዋ የተለያየ ሥም ሊኖራት ይችላል።
የብሄር ፖለቲካ እጅግ በጦዘበት በዚህ ወቅት ጠላቶች ከሚያጦዙት በላይ እርስበርስ በብሄር በመፏከት በትንሽ መሬት ይህ የኔ ነው ያ ደግሞ ያንተ ነው የሚለው አካሄድ ብዙ ለውጥ አያመጣም። ይህ ብቻ አይደለም በጣም ብዙ መታረም ያለብን ጉዳዮችም አሉ። በኢፌዴሪ ህገመንግስቱ አንቀፅ 40 ንቁስ አንቀፅ 3 ላይ የከተማም ሆነ የገጠር መሬት በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ሀብትና ንብረት እንደመሆኑ አይሸጥም አይለወጥም። ይህ ማለት መሬት የሁሉም ነው ማለት ነው።
ህገመንግስቱ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም ከነችግሩ መሬትና የተፈጥሮ ሃብቶችን የመላው ኢትዮጵያውያን ሃብት ነው የሚያደርገው። ኃላፊነት የሚገባቸው አካላት ይህን ጠንቅቀው የሚያውቁ ቢሆን ኖሮ የሰሞኑ ክስተት ባልተፈጠረ ነበር። ከዚህ አንፃር ሁለቱም ፓርቲዎች በይፋ ወጥተው ይቅርታ ማለት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- መሰል ችግሮችን ጨምሮ የእርቀ ሠላም ኮሚሽኑ በአገሪቱ የሚታዩ ግጭቶችን የማስቆምና የኢትዮጵያን ችግሮች የማቃለል ዕድሉ ምን ያህል ነው?
አቶ መርሐፅድቅ መኮንን፡- ይህ የፖለቲካ ፈቃደኝነት ጉዳይ ነው። ከዚህ በላይ ሌላ እድል ያለን አይመስለኝም። ወደውጪ እንኳን ብናንጋጥጥ እከሌ ይደግፈናል ወይም እነዚህ ግጭቶች ይዘን እንደአገርና መንግስት ለመቀጠል የሚያስችለን እድል ከባህር ማዶ ይመጣል ለማለት የሚያስችል አይደለም። ስለዚህ እኛ በመጋጨታችን በከፍተኛ ደረጃ እንጎዳለን እንጂ የሚያዳምጠን እንኳን የለም። ትልልቆቹ ግጭቶች በመጡ ቁጥር ከነጭራሹ ከታሪክ ገፅም ልንዘነጋ እንችላለን።
ያልፀዳ ብዙ ነገር አለ። በርካታ የፖለቲካ ቡድኖችም አሁን እየተካሄደ ያለውን ጥረትና አገራዊ ምክክሩን በሥራ ላይ ለማዋል እየተደረገ ያለው ጥረት ግልፅነት የለውም፤ የስልጣን ማስቀጠያ ነው መንግስት የራሱን ፕሮጀክት ነው እየሰራብን ያለው ብለው የሚያምኑ አሉ። ከዚህ አኳያ ምክንያታቸውን በደምብ ማዳመጥና ይህ ለምን እንደሆነና እንዳልሆነ ማየት ይገባል። በሠላማዊ መንገድ ማነጋገር፣ መወያየት መግባባትና ልዩነቶችን ማጥበብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር ሰላማዊ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ምን መሰራት አለበት?
አቶ መርሐፅድቅ፡- ተፈናቃይ እና ዕርዳታ ፈላጊ ዜጎቻችን ወደ 20 ሚሊዮን ደርሰዋል። ይህን ማቆምና መፍትሄ ማፈላለግ ይገባል። ይህን እንደ አገር የገጠመንን ችግር መፍታት አለብን። የሽግግር ፍትህ ያስፈልጋል። አገራዊ ምክክሩ ላይ በርካቶች የተለያየ እሳቤ አላቸው። አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ ከውጭ ማምጣት አንችልም። ትክክለኛው መፍትሄ መመካከር ነው። ጦርነቱን አብርዶ ለዘላቂ ሠላም መነጋገር ብቻ ሳይሆን የጦርነቱ ሰላባ የሆኑ ተጎጂዎች እውቅና መስጠትና ካሳ መስጠት ተገቢ ነው። ተጠያቂዎችም በዓደባባይ መለየት አለባቸው። ብሄራዊ ምክክር ውስጥ ጎልቶ ያልወጣው ይህ የሽግግር ፍትህ ነው። በዚህ ከታገዘ የአገሪቱ ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑ ዋና ዋና አካላት የሚጠየቁበትም ሥርዓት መኖር አለበት። ይህ ሳይሆን የይስሙላ ዕርቅ መካሄድ አለበት ከተባለ አጥጋቢ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ላደረጉት ቆይታ አመሰግናለሁ።
አቶ መርሐፅድቅ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 /2014