የያዘነው ወር ከአጋማሹ በኋላ የሚያስተናግዳቸው ጥቂት ሀይማኖታዊና ህዝባዊ በአላት አሉ። እነዚህ በአላት ሲከበሩ የኖሩ ናቸው፤ ወደፊትም ሲከበሩ የሚቀጥሉ ይሆናል። ሚያዚያ አስራ አራት የስቅለት በአል፣ በአስራ ስድስት ትንሳኤ በሀያ ሶስት አለም አቀፍ የላብ አደሮች ቀን፤ በሀያ አራት ኢድ-አልፈጥር፣ ሀያ ሰባት ደግሞ የአርበኞች መታሰቢያ ናቸው። በእነዚህ ቀናት ደግሞ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ብዙዎቻችን በህብረት ለመገናኘት እድሉ አለን። እስካሁንም በአብዛኛው ቀናቶቹን የምናሳልፈው በተለመደ የአብሮነትና አንድነት መንፈስ ነው።
ለዛሬው ጉዳይ የነገሬ ማጠንጠኛ ወዲህ ነው። በእነዚህ በዓላት ወቅት ቀን ቆጥረን ከምናደርጋቸው የአብሮነት ከበራ እና የዘመቻ ክንውን በወጣ መልኩ ሰፊው ህዝብ በቀን ያልተገደበ፤ በሁኔታዎች ያልታጠረ የመተሳሰብና የመረዳዳት ብቻ ሳይሆን፤ ሰዎችን ለችግር የማይዳርግ ተግባር በመፈጸም፣ ቢያንስ ለሙታን የሚሰጠውን ፍቅርና እንክብካቤ ለሕያዋን በመስጠት የሕዝብ አንዱ የታሪክ ገጽ ሊሆን ይገባል። በእርግጥ በርካታ ታሪኮች ስንሰማና ስናነብ እንደምንረዳው ሰፊው ህዝብ ታሪክ ተቀባይ እንጂ ታሪክ ሰሪ አይደለም። ታሪክ የሚሰራው ተሸናፊዎች ብልጣ ብልጥ የሚሏቸው በእኔ እይታ ደግሞ ጎበዝና ጀግኖች በሆኑ ግለሰቦች ነው።
ሰፊው ህዝብ ታሪክ የመስራት አጋጣሚ አግኝቶ ቢሆን እንኳ ታሪኩን የሚነግርለት አልያም የሚጽፍለት አይኖርም፤ ምን አልባት ጓደኞቹ ቤተሰቡና ታሪክ ሲፈጽም ያዩት ብቻ ደጋግመው ሊያወሩለት ይችሉ ይሆናል እንጂ። ይህ ደግሞ አንድ ትውልድ የመሻገር እድሉ ጠባብ ነው። ቢሻገር እንኳን ሌላ ማስረጃ አስካልተገኘ ድረስ አፈታሪክን እንደ ሙሉ ታሪክ መቀበል ያዳግታል ወይንም ታሪክ ለማለት አያስደፍርም። ይህም ሆኖ ግን እኔ ህዝቤ እንዲሰራልኝ ለምመኘው ታሪክ ብቁ ነው ብዬ አምናለሁ። ብቻ ህዝቤ ታሪኬ በተናጠል ይመዝገብልኝ እንዳይለኝ እንጂ በቡድን ተጠቅሎ በዘመን ተለይቶ ሊከተብለት ይችላል።
እንደሚታወቀው የሰው ልጅ አንደማንኛው ፍጡር ከመሰሉ ጋር በማህበር ኖሮ በተናጠል የሚሞት ነው። እድል ልበለውና አድለኛ ከሆነ በአንዳንድ አጋጣሚዎች የኔ የሚላቸውን ጨምሮ ከብዙዎች ጋር ሊሞት ይችላል። ካልሆነ «ሞትና ሞሰብ የግል ጣጣ» ነው አንደሚባለው ከትልቁ የዘመን ስብሰባ ቀናችንን እየጠበቅን ብቻችንን ሹልክ እያልን እንሄዳለን። ተሰባስበን ስንኖር ብዙ የማያስማሙን ነገሮች እንዳሉ ያደባባይ ሚስጥር ነው። እንጣላለን፣ እንገፋፋለን ከፋ ሲል እንጫረሳለን። ስንሞት ግን ሁሉም ያዝንልናል ሰማይ ቤት አለ የሚባለው ቦታ ስንሄድም በምህረት የሚቀበለን እንዳለና ሁሉን ነገር እሱ እንደሚያዘጋጀው ይመሰክርልናል። እውነታውን ግን አይቶ የመጣ ስለሌለ ማረጋገጥ የሚቻል አይመስለኝም። እናም… እናም ዘመድ አዝማድ ተሰብስቦ በጥልቅ ሀዘን እየተቀባበለ በመሸከም ወደሰማይ ሄደ ከሚባለው ከማናውቀው ካላየነውና መቼም ከማናየው ነፍስ ተብያችን ለይቶ በጽኑ ፍቅር ይሸኛናል። ይሸኘናል ያልኩት ራቅ አድርጎ ይቀብረናል ላለማለት ነው።
በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ብዙዎቻችን የማናስተውለው አንድ ክስተት በተደጋጋሚ ሲከወን ይታያል። አድልዎ ያለበት የስም ለውጥ። ይህ የስም ለውጥ ደግሞ በፍርድ ቤት ሳይቀር ተቀባይነት ያለው ነው። ጾታ አይለይም፤ እድሜ አይቆጥርም፤ ዘር.. ብሄር ሀይማኖት አይመለከተውም። ብቻ መሞቱ ከተረጋገጠ ማንም በስሙ አይጠራም ሬሳው አልያም አስከሬኑ እየተባለ ይጠራል። ማታ ታሞ ሲጠይቀው እከሌ… እከሊት እዝጌር ይማርህ… እግዜር ይማርሽ ያለ ሁሉ ወደማይቀርበት መሄዱን ሲሰማ አስከሬኑ መጣ? ማለት ይጀምራል። ይቺ አንድ ቀን ሁላችንም በክብር የምንጠራባት የማትቀር የማእረግ ስማችን ናት። በቃ ሁሌም ይሄው ነው የሚሆነው ጠቢባኑ እንደሚሉት «ህይወት በገንፎ ተጀምራ በንፍሮ ትጠናቀቃለች» መወለድ ካለ መሞት የማይቀር እጣ ፈንታ ነው።
ስለዚህ መወለድ ወይንም መሞት የማይቀር የተፈጥሮ ሂደት እንጂ የታሪክ አካል አይመስለኝም። በሁለቱ ኩነቶች መካከል የሚኖረን ግዜ ግን በወለዱንና በእንክብካቤ በሚያሳድጉን ወይንም በጥሩ እንክብካቤ በመጎናጸፊያ አሳምረው ተንከባክበው በሚቀብሩን አይወሰነም። እንደየቆየንበት ዘመን ከተጠቀምንበት ክፉውንም ደጉንም ለማድረግ እድሉ አለን። በአብዛኛው የደግነት ታሪካችን ትዝ የሚለን ከላይ በተቀመጡት ሀይማኖታዊና ህዝባዊ በአላት ነው። በእነዚህ ቀናት መደጋገፉ መተባበሩ መጠያየቁ መረዳዳቱ ለጉድ ነው።
ሌላ ቀን አይራቡ፣ ሌላ ቀን አይታረዙ ይመስል በችግር ውስጥ ያሉ ለበአል እንዳይጎድልባቸው የማንቆፍረው ድንጋይ የለም። አንዳንዶቻችን ሌሎቹ ቀናት ተመርጠው ለግፍና ለሀጢያት የተቀመጡ ይመስል በእነዚህ ቀናት የተከሰተውን አውግዘን ሌላውን ቀለል አድርገን እናየዋለን። በበአላት ፍቅርን ለመስጠት ከምጣደፈው ባላነሰ በአዘቦቱ ከክፉ ስራችን አንቦዝንም። በዚህም የተነሳ ካሉብን ችግሮች አብዛኛዎቹ በራሳችን የተፈጠሩ ወይንም በዝምታችን እዚህ የደረሱ ሆነው እናገኛቸዋለን።
ባእድ ያልናቸው ክፉ አድራጊ ወራርያን አገራችንን ለቀውን ከሄዱ ድፍን ሰማኒያ አመት ሞላን። የሚገርመው ሰሞኑን ከሚከበሩት አንዱ በአል ይህን የምናዘክርበት ነው። ታዲያ የአንድንትን በዓል በልዩነት ውስጥ ሆነ ማክበር እንዴት ይሆናል?! እኛ ግን እስካሁን እንደ እብድ ውሻ ዘመን እየለየን በረባ ባረባው እንናከሳለን። ለክፉ ስራችን ደግሞ ግዜና ጉልበት ብቻ ሳይሆን ምክንያትም አናጣለትም፤ እንደ ባለሙያ ሴት እርሾ ትንሽ ትንሽ እያስቀረን ቀሪውን ለማቡካት እንጠቀምበታለን። አዲስ እህል አዲስ ውሃ ቢዘጋጅም እርሾው የከረመ ነው። ይኸው ዛሬ ብለን ብለን በኮመጠጠ እርሾ የመረረ ትውልድ ለመፍጠር በቅተናል።
ወደእኛ አገር ጉዳይ ስመጣ ግን ፍቅር የሚለው ነገር በሌላ ቢተረጎም ደስ ይለኛል። አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየን ከአብዛኞቻችን የሚጠበቀው ደግ መሆን ወይንም ጥሩ መስራትና ፍቅር መስጠት አይደለም። ይህን ጥቂቶች ብቻ ቢያደርጉት ይበቃል። ከብዙዎቻችን የሚጠበቀው ክፉ አለመሆን ነው።
ሰውን ማዳን ለህክምና ባለሙያዎች እንተው፤ እኛ ይህን ልንሰራ አይጠበቅብንም፤ ቢያንስ ግን መግደል እናቁም። መጠለያ ለመስራት ከመሯሯጣችን በፊት ማፈናቀላችንን እናቁም። በየሰፈሩ የተቸገረ ለመርዳት ብለን ገንዘብ ከምናወጣ ከቤት ኪራይ ጀምሮ አላግባብ የሚጨምረውን ዋጋ እንተው። የታመመ ለማሳከም ከመሮጥ ይልቅ ሰው ላለማሳመም እንትጋ። ይሄ ደግሞ በግዜ አይወሰንም፤ በቀን የሚገደብም አይለይም።
በተፈጥሮ ችግር አልያም በአጋጣሚ አደጋ የተጎዱትን ለመታደግ ጥቂት ልበቀናዎች ይበቃሉ። በቃ ይህው ነው። ሌላ ምንም አዲስ ነገር የለም። ይህን ማድረግ ትልቅ ታሪክ መስራት ነው ብዩ አምናለሁ። እናም ሰፊው ህዝብ ማን ይጽፍልኛል? ማን ያወራልኛል? አልያም ማን ይዘግበዋል? ሳይል «ለሬሳ» የሚሰጠውን ፍቅር ለህያዋን በማድረግ ደማቅ ታሪክ እንዲሰራ እፈልጋለሁ። በቀን በግዜ በቦታና በሁኔታ ያልተገደበ ፍቅር። ምን አልባት ከተሳካልኝ እኔም ለመጀመር አቅድ አለኝ። ደግ በመስራት ብቻ ሳይሆን ክፉ ባለመስራት ፍቅርን መስጠት።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 17 /2014