
ይህች ቀጣዩ መዳረሻዬ የምትሆነው ሀገር እኔ ካለሁበት አህጉር ምንም እንኳን በጂኦግራፊ አቀማመጧ ሩቅ ብትሆንም የጎረቤት ያህል አውቃታለሁ። ምክንያቱም በልጅነቴ አእምሮዬ በታሪክ መጻሕፍት ስለስርወ መንግስታቶቿ ተምሬአለሁ። ነፍስ ካወቅሁ በኋላም በገነባቻቸው መንገዶችና ድልድዮች ከዘመድ ወዳጆቼ ጋር ቅርበትን ፈጥሬአለሁ።
በአልባሳቶቿ አጊጫለሁ፤ በቁሳቁሶቿ ተገልግዬአለሁ። ስለዚህ አሁን በአካል ላያት ናፍቄአለሁ። ከዚህ በፊት መሬቷን ረግጬ አላውቅም። የቻይና ጉዞ የመጀመሪያዬ ስለሆነ የበረራዬን ቀን በጉጉት ስጠባበቅ ነበር። ማየት ማመን ነውና በአካል ላየው እየተቃረብኩ ስለሆነ ጉጉቴ ይበልጥ ጨመረ።
የጉዞዬ ዓላማ ቻይና ለእንግሊዝኛ ተናጋሪ ሀገራት ታዋቂ ጋዜጠኞች ያዘጋጀችውን የሦስት ሳምንታት ሴሚናር ለመካፈል ነው። እኩለ ሌሊት ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከባልደረቦቼ ጋር ሆነን በዕለቱ ወደ ቻይና የሚጓዘው የበረራ ቁጥር ET604 በሆነ አውሮፕላን መሬት ለቀን ተነሳን። አብረውን የሚጓዙት አብዛኞቹ ቻይናውያን ቢሆኑም የሌሎች አፍሪካ ሀገራት ዜጎችም ይታዩኛል።
ከአፍሪካ ወደ ቻይና በቀጥታ ከሚበሩ ጥቂት አየር መንገደኞች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንዱ ነው። በሀገር ልጆች የበረራ አስተናጋጆች “ጤና ይስጥልን! የስታር አሊያንስ አባል በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመብረር እንኳን በደህና መጡ” የሚል ልብን የሚያሞቅ ሰላምታ ቀረበልን። የአብራሪዎች የበረራ ልምድ፣ የበረራ ላይ መስተንግዶና የመዝናኛ አማራጮች በሙሉ በአየር መንገዳችን በትክክልም እንድንኮራ የሚያደርግ ነው።
የሚያነበው እያነበበ ገሚሱ በፊልም እየተዝናና እንቅልፍ የረታው እየተኛ ከ11 ሰዓት በረራ በኋላ ከቀኑ 10፡30 ቤጂንግ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደረሰን። አየር ላይ ሆነን የአውሮፕላን ማረፊያው ግዝፈት አደነቅን። አውሮፕላን እያረፈ ከስር በማሳለጫ መንገድ መኪኖች ሲያልፉ ይታያል። ከአውሮፕላን ስንወርድ ደግሞ ግዙፍ መሆኑን ይበልጥ ተረዳን።
ኤርፖርት ውስጥ ቀላል ባቡር ወደ ኤርፖርቱ የሚገቡና ከኤርፖርቱ የሚወጡ መንገደኞችን ያመላልሳል። ለመንገደኞች ምቹ የሆኑ አሳንሰሮች 2ኛ ፎቅ ወደ ምድር ቤት ከምድር ቤት ወደ ፎቅ ያደርሳሉ። ትላልቅ ስክሪኖች የበረራ መረጃዎችን ይሰጣሉ። በአጠቃላይ ኤርፖርቱ ልዩ ነው።
እንደተለመደው ከአውሮፕላን እንደ ወረድን የሻንጣ መረከቢያ ቦታ እንደርሳለን ብለን ስንጠብቅ ቀላል ባቡር ውስጥ ገባን። በባቡር መሄዳችን ካልቀረማ ሻንጣችንን ለመረከብ የተወሰኑ ደቂቃዎች መጠበቃችን አይቀርም የሚል ግምት አደረብን። የሚገርመው ግን ሻንጣችን በየት በኩል እንደተላከ ሳናውቅ ልክ ከባቡር እንደወረድን ተረከብን።
ከኤርፖርቱ በር ወጣ እንዳልን ስማችን እና የኢትዮጵያ ባንዲራ ያረፈበት ወረቀት ከፍ አድርገው ይዘው የሚጠብቁ ወጣቶችን አገኘን። አስተባባሪዎች ናቸው። በፈገግታ ተቀበሉን። የቡድኑ አባላት መሟላቱን ለማወቅ ቆጠሩን። የጎደለ ሰው አለመኖሩን ከአረጋገጡ በኋላ ወደ ተዘጋጀልን አነስተኛ አውቶቡስ ወሰዱን።
የአውሮፕላን ማረፊያው ከከተማ ወጣ ያለ ስለሆነ ቀጣዩ ጉዞአችን ወደ ተዘጋጀልን ሆቴል እንደሆነ በአስተባባሪዎቹ አማካኝነት ተነገረን። በጉዟችን ወቅት ከዚህ በፊት አይተናቸው የማናውቃቸው ረዣዥም ፎቆችና እንደ ክር የተጠላለፉ የማሳለጫ መንገዶችን እያየን ተደመምን። ከአንድ ሰዓት ጉዞ በኋላ በባሕር ውስጥ ምግብ የሚታወቅ “ሮያል ሊንክ ዚ ሊዩ” ተብሎ የሚጠራ ሆቴል ደረስን።
ሻንጣችንን ወደተመደብንበት ክፍል ካስገባን በኋላ የእራት ሰዓት ሲደርስ ወደ መመገቢያ ክፍል አቀናን። ገበታው ሙሉ ነው። ነገር ግን እኔና ባልደረቦቼ የምናውቀው የምግብ ዓይነት በጣት የሚቆጠር ነበር። ምክንያቱም የቀደመ የቻይና የጉዞ ታሪክ የለንም። ቻይናውያን ለሚወዱት እንግዳ የሚያቀርቡት ምግብ ዝርዝር ውስጥ አንዱም እንዳልተጓደለ ሲነገረን የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት በመጀመሪያው ቀን ተረዳን።
ቻይናውያን ከሹካ ይልቅ በቾፕ ስቲክ መመገብን ያዘወትራሉ። በቾፕ ስቲክ መመገብ ሲታይ ቀላል ቢመስልም ቅሉ ሲሞክሩት ግን ያደናግራል። “ከበሮ በሰው እጅ ሲያዩት ያምራል ሲይዙት ያደናግራል” እንደሚባለው ሀገራዊ አባባል። በቾፕ ስቲክ ለመብላት ሞክረን በቀላሉ ስላልተሳካልን እስከምንለምደው በሹካ መመገብን ተያያዝነው።
ከእራት በኋላ ቤጂንግ በምሽት ምን እንደምትመስል ለማየት ለእግር ጉዞ የሆቴሉን ግቢ ለቅቀን ወጣን። ድንገት ቦታ ከጠፋብን እንድንጠቀምበት የተሰጠን ባጅ እና የየት ሀገር ዜጋ እንደሆንን የሚመስክርልን ፓስፖርት ከእጃችን አልተለዩንም። ከተማዋ ምሽትን ቀን በሚያስመስሉ መብራቶች ተንቆጥቁጣለች።
ቤጂንግ የ3000 ዓመታት ታሪክ ያላት ጥንታዊ ከተማ ብትሆንም እርጅና አይታይባትም። በእድሜ ጠና ያሉ ሰዎች ውሻዎቻቸውን በገመድ እየጎተቱ የእግር ጉዞ ሲያደርጉ ይታያሉ። መልዕክት የሚያደርሱ ወጣቶች ዳር ላይ ስኩተሮቻቸው ላይ ቁጭ ብለው ትዕዛዝ ለመቀበል የእጅ ስልኮቻቸው ላይ አፍጥጠዋል።
ከየሕንፃዎቹ ስር በቀይ ቀለም ያሸበረቁ ምግብ ቤቶች ውስጥ የሚመገቡ ሰዎች በመስኮት በኩል ይታያሉ። በቻይናውያን ባሕል እራት በጊዜ ነው የሚበላው። በአብዛኛው ምሽት 12፡00 ላይ ነው። የእግር ጉዟችን ቀጥለን ባለኬብል የኤሌክትሪክ አውቶቡሶች፣ ስኩተሮችና ብስክሌቶች በብዛት በቤጂንግ ጎዳናዎች ላይ ይታያሉ። ከተማዋ “የብስክሌት ከተማ” አስመስሏታል። የፈለገ ሰው ኪው አራ ኮድ ስካን አድርጎ ከፍሎ ብስክሌት ይዞ ያሻው ቦታ ደርሶ መመለስ ይችላል።
ከሕንፃዎች ፊት ለፊት በሚገኙ ክፍት ቦታዎች ሰዎች ሰብሰብ ብለው ሙዚቃ ከፍተው የሰውነት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ማየት ሌላው የቻይና ውበት ነው። የሚከፈቱት የሩቅ ምስራቅ ሙዚቃዎች ልብን ይሰርቃሉ። ወደ ሆነ ዓለም ይወስዳሉ። ሰዎቹ ደስተኞች፣ ሰላምታና ሰው ወዳድ ናቸው።
“ኒያሁ” በቻይና ቆይታዬ ለመጀመሪያ ጊዜ የለመድኩት ቃል ነው። ትርጉሙ ሰላም ማለት ነው።
ከቻይናውያን ጋር በቋንቋ የሚለያይ ሰው እንኳን በስሜት፣ በሰብዓዊነትና በማህበራዊ መስተጋብር መግባባት አይከብደውም። እንግዳ ሲያዩ ፎቶ ተነስቶ ማስታወሻ ማስቀረትን ይወዳሉ። ፎቶ የሚያነሳቸው ሰው ሲያዩም ደስ ብሏቸው ለፎቶ ይዘጋጃሉ።
በቻይና ቆይታ ካስገረሙኝ ነገሮች መካከል ሃያ እና ሠላሳ ሚሊዮን ሕዝብ የሚኖርባቸው ከተሞች መንገዶቻቸው በሰው ሲጨናነቁ እምብዛም አይታዩም። የእግር ጉዞ ስናደርግ ብዙ ሰው መንገድ ላይ አይታይም። መንገድ ላይ የሚታየውም አንዳች ፋይዳ ያለው ነገር የሚከውን ነው።
በምሽት መንቀሳቀስ የሚፈጥረው ችግር ይኖር ይሆን ብለን አስተባባሪዎችን አስቀድመን ጠይቀን ነበር። ምንም የፀጥታ ስጋት እንደሌለ ነግረውናል። እውነትም የቻይና ከተሞች ሰላማዊ ናቸው። ሞባይል ቀማኛ የለ ኪስ አውላቂ የለ። ማን ነህ ከየት መጣህ የለ። ሁሉም የሚመለከተው ጉዳይ ላይ ነው የሚያተኩረው። እኛም ያለ ስጋት የባይተዋርነት ስሜት ሳይሰማን እስኪደክመን ድረስ በጎዳናዎች ላይ ተመላለስንበት። ከእግር ጉዞ በኋላ ወደ ሆቴላችን ተመልሰን አረፍ አልን።
ለቀጣዩ ቀን የገለፃ ፕሮግራም በጠዋት ተነስቼ መዘጋጀት ነበረብኝ። የድካም ስሜት ተሰምቶኝ ስለነበር ሳልነቃ ምሽቱን አገባደድኩት። ድንገት ከእንቅልፌ ስባንን በመስኮት በኩል ብርሃን ይታያል። ወይኔ! ገና በመጀመሪያ ቀን እንቅልፍ ጥሎኝ ፕሮግራሙ ላይ አርፍጄ ልገባ ነው የሚል ስጋት አደረብኝ። የእጅ ሰዓቴን ስመለከት 11፡00 ይላል። የሰዓቴን ትክክለኛነት ተጠራጠርኩ። ነገር ግን ሰዓቴ በትክክል ጊዜ መቁጠሩን አላቆመም ነበር። ለካ ቻይና እንደ ኢትዮጵያ አይደለም፡- ቶሎ ይነጋል። ተመልሼ ለመተኛት ሞከርኩ ግን እንቅልፍ በዓይኔ አልዞር አለ።
ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ላይ ቁርሳችንን በልተን ሰዓቱ ሲደርስ ገለፃ ወደሚደረግበት አዳራሽ ገባን። አዳራሹ ውስጥ ከኬንያ፣ ጋምቢያ፣ ዛምቢያና ዛንዚባር የመጡ ጋዜጠኞች ታድመዋል። በመጀመሪያው ቀን ገለፃ የጥንቷ ቻይና የአሁኗ ቻይና ታሪኮች ትውውቅ ጀመርን። ሀገሪቷን አንድ ስላደረጓት ስርወ መንግሥታትና የቅብብሎሽ ሥራዎች በተመለከተ ማብራሪያ ቀረበ።
ታላቁ ግንብን የገነቡበት የጽናት ታሪክ ሲነገረን በተመስጦ ተከታተልን። ከሌሎች ሀገራት ጋር ስላደረጉዋቸው ጦርነቶች እና ሌሎች የቻይና የፈተና ጊዜያቶች ገለፃ ተደረገልን። የፈተና ጊዜያቶች ታሪክ ብቻ አይደለም። ከፈተና እንዴት እንደወጡ ጭምር ተብራራልን። እ.አ.አ በ1949 የነበረው የቻይና የነፍስ ወከፍ ገቢ (ጂዲፒ ፐርካፒታል) አሁን ካለው ጋር በንፅፅር ሲቀርብ ለውጡ የሚያስደምም ነበር። ከ27 ዶላር ተነስቶ እንደ ሮኬት ተተኩሶ 2021 ላይ 12,359 ዶላር ላይ ነው የደረሰው። እዚህ ላይ ለመድረስ የመንግሥትና የሕዝብ ቁርጠኝነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደጠየቀ የተለያዩ ማሳያዎች ቀረበልን። በጠዋትና በከሰዓት ክፍለ ጊዜ በነበሩ ገለፃዎች ስለቻይና ፈጣን የልማት ጉዞ ብዙ ነገርን አስጨብጦናል። እነዚህን ወደ ሀገራችን ብንወስዳቸው ለውጥ እናመጣበት ነበር እያልን በቁጭት ስሜት እና በመደመም ውስጥ ሆነን ገለፃውን ተከታተልን።
በቀጣዮቹ ቀናትም የግማሽ ቀን ገለፃዎች ቀጠሉ። ገለፃው በዋናነት ሚዲያን ተጠቅሞ ሕዝብን እንዴት ለልማት ማነሳሳት ይቻላል የሚል ላይ ያተኮረ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊት የቤጂንግ ሰማይ በጭስ የተሸፈነ እና ሙስና የሀገሪቱ ፈተና ነበር። እነዚህን ሁኔታዎች ለመቀየር ሚዲያን በሚገባ እንደተጠቀሙበት ይናገራሉ።
ሜይንስትሪም ሚዲያውም ሆነ ማህበራዊ ሚዲያው በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ጭምር በሙስና ሲዘፈቁ መረጃዎችን ከኅብረተሰቡ ተቀብሎ ይታገላል። በሙስና የተዘፈቁ ግለሰቦችን ከፓርቲ ነጥሎ በማቅረብ ፓርቲው ውስጡን እንዲያጠራ ያግዛል። ሚዲያዎች የሕዝብን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ።
በ20 ቀናት የቻይና ቆይታችን ከአጫጭር ገለፃዎች በተጨማሪ ቤጂንግና ሌሎች ከተሞች የሚገኙ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ ሙዚየሞችን እንዲሁም ታሪካዊ ቦታዎችን የመጎብኘት ዕድል አግኝተናል። ከአዳራሽ ውጭ ቻይና ምን እንደምትመስልና ምን እየሠራች እንደሆነ ያስመለከቱን ተቋማት አሉ። ከእነዚህ ውስጥ የቻይና የግብርና ሳይንስ አካዳሚ አንዱ ነው።
አካዳሚው በሚያደርጋቸው ምርምሮች የአበባ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ ዕሴት የመጨመርና ምርታማነትን የማሳደግ ሥራ ይሠራል። በኢትዮጵያ ጽጌሬዳ አበባ ገናና ስም እንዳላት ሁሉ ቻይናዎች ለፒዮኒ አበባ ልዩ ስፍራ አላቸው። ከኮስሞቲክስ እስከ ምግብ ልዩ ልዩ ምርት ይዘጋጅበታል። አካዳሚው በዚህ የአበባ ዓይነት ያዘጋጃቸው የኮስሞቲክሶች፣ የሻይና ቢራ ምርቶች ለእይታ አቅርቧቸዋል። አካዳሚው ከአፍሪካ ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተማሪዎችን ተቀብሎ እያሰለጠነ ይገኛል።
ጉብኝታችን አይረሴ ካደረጉት መካከል በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡት ታላቁ ግንብና ቴምፕል ኦፍ ሄቨን ይገኙበታል። በእነዚህ ስፍራዎች በነበረን ቆይታ ቻይና ታሪክን ተንከባክቦ በማቆየት መልካም ልምዳቸውና በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ቁጥር ተገርመናል። ቻይናውያን ከአንደኛው ግዛት ወደ ሌላ ግዛት ተዘዋውረው ሀገራቸውን የመጎብኘት ልምድ እንዳላቸው የቱሪስት መዳረሻዎች የሚታየው የሕዝብ ማዕበል ይመሰክራል። በቴምፕል ኦፍ ሄቨን ቅርስ ዙሪያ 500 ዓመታትን ያስቆጠሩ ዛፎች በእንክብካቤ ተይዘዋል። ቻይና ሰውና ተፈጥሮን አስማምታ የምታኖር ሀገር ነች። ሌላው ስለቱሪስት መዳረሻዎቻቸው በአስጎብኚዎችና በጽሑፍ በተቀመጡ ማብራሪያዎች አማካኝነት በቂ መረጃ ይሰጣል። ከተደረጉልን ገለጻዎችና ከጎበኘናቸው ቅርሶች መረዳት እንደቻልነው የቻይና ታሪክ በቅብብሎሽ የተገነባ ነው። ሙዚየሞቻቸው በአስረጂ ቁሳቁሶች በሚገባ የተደራጁ ናቸው። በሰቭን ዲ እና በመሳሰሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ጎብኚዎች በቦታውና በጊዜው የተገኙ ያህል እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ናቸው።
ከቤጂንግ ውጭ ቀጥሎ ያቀናነው ከሁለት ሰዓታት በረራ በኋላ መዳረሻችን ወደ ሆነችው ሁናን ግዛት ነው። ይህች ግዛት በቅመማ ቅመም በተከሸኑ ምግቦች፣ ስቲንኪ ቶፉ እና ቦባ የሚል መጠሪያ ያለው ሻይ በወተት ትታወቃለች። በዚህ ግዛት የምትገኘው ሻንግሻ ከተማ ለሁለት ቀናት አድረን የተለያዩ ቦታዎችን ጎበኘን። ሻንግሻ ቀደም ሲል በባሕል ማዕከልነት የምትታወቅ ከተማ ብትሆንም አሁን አሁን የንግድ ማዕከል ጭምር እየሆነች ነው።
በዚህች ከተማ በተለያየ መንገድ ከቻይና ባሕል ጋር ትውውቅ አድርገናል፤ ደስ የሚል ጊዜ ከቻይና አፍሪካ ጓደኞቻችን ጋር አሳልፈናል። ባሕላዊ አልባሳት፣ ጌጣጌጦችና ሌሎች ቁሳቁሶች የሚገኙባቸው ጎዳናዎች ተዘዋውረን ለማስታወሻ ያሻንን ሸምተናል። በሁናን ግዛት ቆይታችን ዕድሜ ጠገብ ሙዚየሞችን ጎብኝተናል። ዩኢሉ አካዳሚ ከአንድ ሺህ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ እና በቻይና ጥንታዊ ከሚባሉ አራት አካዳሚዎች መካከል አንዱ ነው።
በአሁኑ ወቅት ሙዚየምም ሆኖ ተማሪዎችን ተቀብሎ ያስተምራል። ዕውቁ ፈላስፋ ኮንፊሺየስ በዚህ አካዳሚ ውስጥ ያስተምሩ ነበር። በቻይና ለውጥ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዙት ማኦ ዚዶንግ የተማሩበት ሲሆን ዶርመተሪያቸው ሳይቀር ለጎብኚዎች ክፍት ነው። ሀውልታቸው ወደ አካዳሚው መግቢያ በር ላይ በትልቁ በኩራት ቆሟል።
ከሁናን ግዛት ሳንወጣ ሻንግሻ ዲስትሪክት የምትገኝ ቶንጉዋን ተብላ የምትጠራ ጥንታዊ ከተማ ውስጥ ብዙ ሊነገርላት የሚገባ የታሪክ ሀብታም ነች። ይህች መንደር የሴራሚክ የትውልድ ቦታ ናት ተብሎ ይታመናል። ቶንጉዋን በቁፋሮ የተገኙ ቻይናውያን ከ1000 ዓመታት በፊት በታንግ ስርወ መንግሥት ዘመን ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የሴራሚክ መገልገያዎች ተሰብስበው እና በአግባቡ ተደራጅተው የሚታዩበት ሙዚየም በውስጧ የያዘች ከተማ ነች።
ታሪካዊ ከተማ በመሆኗ በቱሪስቶች በስፋት ትጎበኛለች። ለሴራሚክ መሥሪያ የሚውል አፈር በስፋት የሚገኝበት አካባቢ ነው። የአካባቢው ሰው ውብ የሴራሚክ መገልገያዎች የመሥራት ጥበብ ከጥንት ጀምሮ እየተላለፈ አሁንም በዚህ ሙያ የሚተዳደሩ በርካቶች ናቸው። ከተማውን በጎበኘንበት ወቅት አንድ የሴራሚክ ሥራ ባለሙያ ሲኒ በፍጥነት ሰርቶ ለጎብኚዎች ሲያሳይ ተመልክቼአለሁ። ይህ ብቻ አይደለም በዚህች ከተማ የሚገኙ ቤቶች የጥንት ቻይናውያን ዐሻራ ያረፈባቸው እና ታሪካዊ ክስተት ያስተናገዱ በመሆናቸው በቱሪስቶች ይጎበኛሉ።
ሶስተኛው መዳረሻችን የነበረችው ከተማ ዩያንግ ትሰኛለች። በዩያንግ ቆይታችንም ታሪካዊ ቦታዎች፣ ፓርኮችንና የቻይናና አፍሪካ የንግድ ትስስርን የሚያጠናክሩ ፕሮጀክቶችና ኢንቨስትመንቶችን ጎብኝተናል። በአብዛኛው ቻይናውያን የሚታወቀውና ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ዩያንግ ታወር የሚባል የቱሪስት መዳረሻን ጎብኝተናል። በሚንግ እና ታንግ ስርወ መንግሥታት የተገነቡ የቻይናን ባሕላዊ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የሚንጸባርቁ ባለ2 ፎቅ ሕንፃዎች በዚህ ስፍራ ይገኛሉ።
ታወሮቹ ከተማውን ከሚያቋርጠው ወንዝ አጠገብ የሚገኝ በመሆኑ የመርከቦችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ ሲውሉ ነበር። በዚህ ከተማ ቆይታችን ቻይና ከአካባቢ ጥበቃ ሰፊ ሥራ የሠራችበት ፕሮጀክት ተመልክተናል። ጁንሹሀን ፓርክ የለማው ታዋቂውን ያንግቲዝ የሚባለው ወንዝና በውስጡ የሚገኙ ዶሊፊኖችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ነው።
ከዩያንግ ከተማ ሳንወጣ የቻይናና አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የንግድ የሙከራ (ፓይለት) ዞን የጉብኝታችን አካል ነበር። ዞኑ ቻይና ከአፍሪካ ጋር የኢንዱስትሪ ትብብር ለማድረግ ዓላማ ሰንቃ ያቋቋመችው ነፃ የንግድ ቀጣና ነው። የአፍሪካና የቻይና ድርጅቶች ተጠቃሚ እንደሚያደርግና እ.አ.አ በ2027 ዓመታዊ ገቢው 10 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ ቀጣና ነው።
ሌላው በሁናን ግዛት የወጪ ንግድ የሚያሳልጥ ቺንግሊንግጂ ተብሎ የሚጠራ ቁልፍ ወደብ ከሕንፃ አናት ላይ ወጥተን ቁልቁል ተመልክተናል። ወደቡ የተገነባው ሺያንግ፣ ጂንግና ዩሃን የሚባሉ ሶስት ሶስት ወንዞች የሚገናኙበት ስፍራ ነው። ልክ ዓባይ በጣና ላይ ሲያልፍ እንደሚታየው የወንዞቹ የተለያየ ቀለም አንዱ በአንዱ ላይ ሲፈሱ ልዩ ትይንትን ይፈጥራሉ። ወደቡ ሰባት ክሬኖች ያሉትና 820 ሺህ መደበኛ ኮንቴነሮች የማስተናገድ አቅም ያለው ነው።
ሌላው የጉብኝታችን አካል ጂንጂንግ የተሰኘ የሻይ እርሻ ነው። የሻይ እርሻው በሁናን ግዛት ውስጥ ትልቁ ሲሆን ስፋቱም 10,000 ሄክታር ነው። በመንግሥት እና በግል ኢንተርፕራይዞች አጋርነት የሚሠራ ድርጅት ነው። የምሥረታ ታሪኩ የሚነሳው እ.ኤ.አ. ከ1958 ሲሆን በአረንጓዴ ሻይ ልማት ነው የሚታወቀው። የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በሻይ ቅጠል መሰብሰብ ሥራ እንድንሳተፍ ተጋብዘን ተሳትፈናል።
የሻይ አፈላል ሥነ ሥርዓት ጥበብ እንደሆነ አንዲት ቆንጆ ወጣት አስመለከተችን። ቻይና ለሻይ ትልቅ ቦታ እንደምትሰጥ ተረድተናል። ከተለመዱት የሻይ ዓይነቶች በተጨማሪ ነጭ ሻይን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሻይ ዓይነቶች በቻይና ይመረታል። ሻይ በፍቅር የሚጠጣበትና እንግዳ የሚሸኝበት ባሕላዊ መጠጥ ነው።
ማህበራዊ ግንኙነትን ለማጠናከር ይውላል፡- ልክ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለው የቡና ሥነ ሥርዓት። ተያያዥ በሆነ ጉብኝት ደግሞ ጂንጂንግ ኦብሰርቫቶሪ ማዕከል ፀሐይን በቅርበት እንድናይ አስቻለን። እግረ መንገዳችንም ቻይና ከጥንት ጊዜ የጨረቃን እንቅስቃሴ በማጥናት ለግብርና ሥራ ሲጠቀሙበት እንደነበር ተገንዝበናል።
ጉብኝታችን የቪዲዮና የፈጠራ ፓርክም ያካተተ ነበር። በእኛ ሀገር አምራቾችን እንደሚይዘው የኢንዱስትሪ ፓርክ የመዝናኛ ይዘቶች የሚያዘጋጁና የቴክኖሎጂ ተቋማት ያቀፈ ማሌንሻን የተሰኘ ፓርክ ጎብኝተናል። በዚህ ፓርክ ከፍተኛ አቅም ያላቸው ዘመናዊ ካሜራዎችና ስክሪን የሌለው ተች (እንደ ፕሮጀክተር ጨረር ብቻ ያለው) አዲስ ቴክኖሎጂ ተመልክተናል።
ጉብኝታችን በከተማ ብቻ የታጠረ አልነበረም። ከከተማ ወጣ ብለን መንደሩን ጭምር የማየት ዕድል አግኝተናል። ከዩያንግ ከተማ ተነስተን የሁለት ሰዓታት የመኪና ጉዞ አድርገን 500 ዓመታትን ያስቆጠረ ጃንጉይንግ መንደር ጎብኝተናል። መንደሩ በቻይና በቅርስነት የተመዘገበና በአሁኑ ወቅት ነዋሪዎች ያሉት ነው።
51 ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የቱሪስት መዳረሻ ነው። መንደሩ በርካታ ቤቶችን የያዘና የቤቶቹ ጣሪያ እርስ በርስ የተያያዙ ናቸው። ቤቶቹ የተያያዙበት ምክንያት ደግሞ በዚህ መንደር ይኖሩ የነበሩ ቀደምት ነዋሪዎች ዝምድና የሚያሳይ ነው። ግቢው ውስጥ ወደሚገኘው ወደ አንደኛው ቤት ስንገባ በእንጨት የተሠራ ረዥም በር ተከፈተልን። ይህ በር ብዙ ጊዜ እንደማይከፈት ተነገረን። ነገር ግን ለእኛ ለአፍሪካውያን እንግዶች ሲባል ተከፍቶ በዚሁ በር በኩል ወደ ውስጥ ገባን።
በቻይና በተለያዩ አካባቢዎች በነበረን ቆይታ ሕዝቡ በመልካም መስተንግዶና የእንግዳ አቀባበል እንዲሁም በፍቅር ተቀብሎ ቻይና እንደ ሁለተኛ ሀገራችን እንድንቆጥራት ነው ያደረገን። ከሁሉ የሚደንቀው ሀገሪቷ ከአፍሪካ ሩቅ ብትሆንም የሀገሬው ሰው ከእሱ የተለየ የቆዳ ቀለም ያለው ሰው ሲያይ የተለየ አመለካከት አያድርበትም። ፍቅሩንና እንክብካቤውን አያጓድልም። ቻይና ዘረኝነት ከቶ የማታውቅ ምርጥ የሩቅ ምስራቅ ሀገር ነች።
በመጨረሻም በ20 ቀናት የቻይና ቆይታዬ ሁሉም የሀገሬ ሰው ቻይና የደረሰችበት የዕድገት ደረጃና የሥራ ባሕል ቢያይ ብዬ እንድመኝ አድርጎኛል። ብዙ ትምህርቶችን የቀሰምኩበት አይረሴ ጊዜ ያሳለፍኩበትና ቻይናን ስመለከትበት የነበረው መነጽሬን እንዳስተካክል ያስገደደኝ ነው። በሕይወት ዘመኔ በሙሉ የሚከተለኝ ለቤተሰቦቼ፣ ለጓደኞቼና ለሥራ ባልደረቦቼ የማካፍላቸው ታሪኮችን ያገኘሁበት ጉዞ ነበር። ጥሩ ትዝታ ሆነው በልቤ ታትመው ይኖራሉ
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ጋሻው ታደሠ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 15 ቀን 2017 ዓ.ም