አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባን የውሃ አቅርቦት ለማሳደግ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ከውጪ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ መጓታቸውን የከተማዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ላፊ አቶ ስዩም ቶላ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በከተማዋ ለመጠጥ ውሃ አቅርቦትና ፍሳሽ ማስወገድ ሀምሳ ፕሮጀክቶች በስራ ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል የአዲስ አበባን የውሃ ችግር ይፈታሉ ተብለው የታሰቡት ትልልቅ የውሃ አቅርቦት ፕሮጀክቶች ከውጪ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ አልቻሉም።
68 ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ በቀን የማቅረብ አቅም ያለውና የምስራቅ አዲስ አበባን የውሃ ችግር ይፈታል ተብሎ የተጀመረው የሳውዝ አያት ኖርዝ ፋንታ የ21 የጥልቅ ጉድጓድ ውሃ ቁፋሮ ፕሮጀክት አንዱ ነው። ፕሮጀክቱ ከሁለት ዓመት በፊት በአንድ ዓመት ለማጠናቀቅ የግንባታ ስምምነቱ ተፈርሞ ስራው ቢጀመርም የማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታ ከተጠናቀቁ በኋላ ከውጪ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ የቧንቧና ፓንፕ ግዥ ማከናወን ባለመቻሉ ለዓመት ያህል ለመቆም ተገዷል። በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ገንዘቡ ተለቆ የቧንቧና ፓምፕ ግዥ ተፈጽሞ ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ላይ በመሆናቸው በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ወራት አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ተናግረዋል።
ሁለተኛው በከተማዋ ሰሜንና ሰሜን ምስራቅ ያለውን የውሃ አቅርቦት ችግር ይፈታል ተብሎ የታሰበው እና 86 ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ በቀን የሚሰጠው የለገዳዲ ምዕራፍ ሁለት ነው። ፕሮጀክቱ በ2008 ዓ.ም 20 ጉድጓዶች የተቆፈሩ ቢሆንም ለዝርጋታ ጥናት ተሰርቶ በ2009 ዓ.ም ጨረታ ወጥቶ መረጣ ከተካሄደ በኋላ የውጪ ምንዛሬ እጥረትና የዶላር መጨመር በመከሰቱ ጨረታውን ያሸነፉት ድርጅቶች ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች አቅርበው ስራውን አቁመውታል። የማረጋገጫና የዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግ በመጠየቃቸው በ2010 ዓ.ም ጨረታው ተሰርዞ በ2011 ዓ.ም ጥቅምት ወር አዲስ ጨረታ ወጥቶ በሂደት ላይ ይገኛል። ወደስራ ከተገባ ፕሮጀክቱ የሚወስደው ጊዜ 18 ወራት ብቻ ነው። በከተማዋ የተለያዩ ኪስ ቦታዎች ዘንድሮ የአስር ጉድጓዶች ቁፋሮ የተጠናቀቀ ሲሆን አራቱ ወደ ስራ ገብተዋል። ሌሎቹ የሙከራ ስርጭት ላይ ናቸው። ከእነዚህም በቀን ከአምስት እስከ ስድስት ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚገኝ አቶ ስዩም ገልፀዋል።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ ጉድጓድ በመቆፈር የአዲስ አበባን የውሃ ችግር በአጭር ጊዜ መፍታት አይቻልም። በመሆኑም በቅርብ ያሉ የገፀምድር ውሃዎችን እያጣሩ ማቅረብ የሚጠበቅ በመሆኑ በቀጣይ ለመስራት እቅድ ተይዟል።
ኃላፊው፣ ለረጅም ጊዜ እቅድ የተያዙትን የግድብ ግንባታ ፕሮጀክቶች ሲጠቁሙም፤ የገፈርሳን ወንዝ በማልማት በቀን 70 ሺ ሜትር ኪዩብ፤ በሱልልታ አካባቢ ሲብሉ ወንዝን በማልማት 500 ሺ ሜትር ኪዩብ፣ የአለልቱና ጅዳ ወንዞችን በማልማት 600 ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ በየቀኑ ለማምረት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አዲስ አበባ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ በቀን የሚያስፈልጋት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት እየቀረበላት ያለው ግን 520 ሺ ብቻ ነው። ይህም የፍላጎቱን 54 በመቶ ማለት ነው። የከተማዋ የውሃ ችግር ግን የእጥረት ብቻ ሳይሆን በውሃ መገኛ አካባቢ ያሉት 24 ሰዓት የሚያገኙ ሲሆን፣ ከውሃ መገኛው የሚርቁት ደግሞ በፈረቃ በሳምንት አንድ ቀን ብቻም የሚያገኙ እንዳሉ በመጠቆም ፕሮጀክቶቹ ይህንን ለመቅረፍ እንደሚረዱም ሃላፊው ጨምረው ተናግረዋል
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ