አዲስ አበባ፡- የመገናኛ ብዙሃኑ ትክክለኛ መረጃዎችን ለህዝብ በማድረስ ስራ ላይ እንዲጠመዱ በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ጥሪ አቀረቡ።
የመንግስት ረዳት ተጠሪ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ መገናኛ ብዙሃኑ በምክር ቤቱም ይሁን ከአስፈፃሚ አካላት የሚተላለፉ መረጃዎችን በትክክል ከምንጫቸው በማጥራትና ፈልፍሎ በማውጣት ለህዝብ የማድረስ ስራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ አምባሳደር መስፍን ገለጻ፤ መገናኛ ብዙሃኑ በህዝቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ያለማጋነንና ያለማሳነስ እንዲሁም ቦታው ድረስ በመሄድ በትክክለኛ መረጃዎች የታገዘ ስራ መስራት አለባቸው። ይህን በማድረጋቸው በአንድ በኩል መንግስት ስራውን በአግባቡ እንዲወጣ ከማገዙም በተጨማሪ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ኃላፊነቱን በማይወጣበት ጊዜ ህዝብ የመረጠው ምክር ቤት ተፅዕኖ እንዲፈጥር ያስችላል።
ረዳት ተጠሪው፣ ‹‹የማህበራዊ ሚዲያው አገራችን ባጋጠማት ችግር ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ አገሪቱ አንድነቷ እንዲጠናከር በሚያደርጉ መረጃዎች ላይ ማተኮር አለበት። በየቀኑ ህዝቡን የሚያጋጩ የተሳሳቱ መረጃዎች መተላለፍ የለባቸውም። የዜናዎቹና የመረጃዎቹ ምንጭ በአግባቡ መጣራት ይኖርባቸዋል›› ሲሉ ጠቅሰው፤ለሁሉም የመገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ ሚዲያ ላይ ላሉ አካላት መረጃ በጥራትና በወቅቱ እንዲሁም በትክክለኛ መንገድ ማስተላለፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
‹‹መገናኛ ብዙሃን ሰላማችንን ዘላቂ የሚያደርግ፣ የዴሞክራሲ ስርዓትን የሚያጎለብት፣ የአገሪቱን አንድነት የሚያጠናክርና በህዝቦች መካከል ያለውን የቆየ የባህል፣ የቋንቋና የታሪክ ትስስርና አንድነትን ይበልጥ ከፍ የሚያደርግ ስራ ላይ መጠመድ አለባቸው›› ያሉት አምባሳደር መስፍን፣ ልዩነትን ከሚሰብኩና ከሚያባብሱ ግለሰቦችና የፖለቲካ አቋም ካላቸው ጋር የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለአገር አይበጅም ሲሉ ገልጸዋል። ስለዚህ ሚዲያው በዚህ ላይ ትክክለኛ ስራ ቢሰራ ምክር ቤቱ ለሚያደርገው የለውጥ እንቅስቃሴው ሚናው የጎላ እንደሆነም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2011
በ አስቴር ኤልያስ