የተወለደው አዲስ አበባ ነው። ወቅቱም መጋቢት 27 ቀን 1975 ዓ.ም። ነጋዴ አባቱ እና የቤት እመቤት እናቱ ከወለዷቸው ልጆች መካከል አንዱ ነው።
ቤተሰቦቹ በሀይሉ ዋሴ የሚል ስም ሲሰጡት ወዳጆቹ ግን የሚያውቁት ዋጄ በሚለው መጠሪያው ነው። ብዙዎች ከጥቂት ጊዜያት በፊት በፋና ቴሌቪዥን ይተላለፍ በነበረው ተከታታይ ሲትኮም ምን ልታዘዝ ደራሲነት እና ዳይሬክተርነት ያወቁታል።
ሲኒማ የመግባት እድል ያላቸው ሰዎች ደግሞ የዋጄን ፊልሞች በይዘታቸው ጥንካሬ ያውቋቸዋል። ያ ልጅ፤ በልደቴ ቀን፤ ዩቶጵያ፤ በእናት መንገድ፤ አይራቅ እና ሰኔ 30 የዋጄ የጥበብ ጸጋ የተገለጠባቸው እና ብዙ ተመልካች አይቶ ያደነቃቸው ፊልሞች ናቸው።
በተለይም በእናት መንገድ በተሰኘው ፊልም በ5ተኛው ጉማ አዋርድ በምርጥ ፅሁፍ እና ዝግጅት ያሸነፈ ሲሆን በምን ልታዘዝ ድራማ ደግሞ በ8ተኛው ለዛ አዋርድ በምርጥ ቲቪ ድራማ አሸናፊ ሆኗል። ምን ልታዘዝ ሲትኮሙ ጋር በተያያዘም አልጀዚራ 25 ደቂቃ ርዝማኔ ያለው ዶክመንተሪ በሱ ላይ ሰርቷል። በዛሬው ጽሁፋችን ግን ከግላዊ ታሪኩ በበለጠ በበሀይሉ እሳቤዎች ዙሪያ እናጠነጥናለን።
በሀይሉ ፊልም ሰሪ ብቻ አይደለም፤ ጥልቅ አሳቢም ነው። ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ዲግሪ ቢኖረውም በውስጡ ያለው ራስን የመግለጽ ሀይለኛ ፍላጎት ግን ወደ ፊልም መራው። ይህ ራስን የመግለጽ ፍላጎት በጥቂት የፊልም ኮርሶች ታጅቦ ወደ ባለሙያነትም መራው።
ዋጄን የሚያውቁት ሰዎች ግን ይበልጥ የሚያውቁት በጥልቅ አሳቢነቱ ነው። ስለ አገር እና ስለ ኢትዮጵያዊነት በተለይ ጠለቅ ያለ እሳቤ አለው። በፊልሞቹ ውስጥም ይህ በግልጽ ይታያል። ”ማንበብ እወዳለሁ …… ታሪክ እወዳለሁ …ሀይማኖታዊ ነገር እወዳለሁ …ፖለቲካ እወዳለሁ” የሚለው በሀይሉ፣ የሚሰራቸው ፊልሞች የንባብ እና የሕይወት መንገዱ ውጤቶች እንደሆኑ ይናገራል።
የዋጄን አስተሳሰብ ለመረዳት ደግሞ የሚያነባቸውን መጻህፍት ማወቅ ያግዛል። የታላላቆቹ ጸሀፍት ዶ/ር እጓለ ገ/ዮሀንስ እና ተክለሀዋርያትን እንዲሁም ቀደምት ኢትዮጵያውያን ልሂቃንን መጻህፍት ነው የሚያነበው። እነዚህ ጸሀፍት ደግሞ በጥልቅ አሳቢነታቸው እና ከዘመናቸው የቀደሙ በመሆናቸው የሚታወቁ ናቸው። ለምሳሌ ዓለምን ዞረው የተማሩት ዶ/ር እጓለ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ የተሰኘ ታዋቂ መጽሐፍ አላቸው።
በዚህ መጽሐፋቸውም የኢትዮጵያ የትምህርት ስርአት በምን አይነት መንገድ መቀረጽ እንዳለበት በስፋት አተትዋል። ዋጄ የእኚህ ሊቅ እሳቤ ጥላ አጥልቶበታል። የምንማርበት ስርአተ ትምህርት በትክክል አልተቀረጸም ይላል። የተከተልነው ከምእራብ የተቀዳ ስርአተ ትምህርት ካለፈው አቆራርጦን ከመጪው ሳንሆን መሀል ላይ እንድንንሳፈፍ አድርጎናልም ይላል።
ዋጄ “በመንፈሳዊ ስልጣኔ እቀናለሁ” የሚልም ነው። በዘመናዊው ስልጣኔ ላይ ጥርጣሬ አለው። በፊልሞቹም ላይ ይህ ይስተዋላል። ለምሳሌ ያህል አይራቅ የተሰኘ ፊልሙ የሁለት ስልጣኔዎች ፍልሚያ የሚታይበት ፊልም ነው። “ስልጣኔን ዲፋይን ማድረግ አለብን” የሚል ሲሆን፣ አሁን “ስልጣኔ ብለን የምንረዳው ነገር ምእራባውያኑ ያቀበሉን ነው” ብሎም ያምናል።
ይህ የብያኔ (ዴፍኒሽን) ችግር ስልጣኔ ላይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ፊልም ላይም እንዳለ ይናገራል። ”እኔ የሆሊውድ ፊልሞችን እያየሁ ነው ያደግኩት። ስለዚህም የአሜሪካ ፊልም ሲባል ምን ማለት እንደሆነ አውቃለሁ፤ ሌላውም ሰው ያውቃል። ነገር ግን የኢትዮጵያ ፊልም ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንኳን ተመልካቹ ፊልም የሚሰራው ሰው ራሱ አያውቀውም” ይላል። ስለዚህም የኢትዮጵያ ፊልም ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ብያኔ መፍጠር አስፈላጊ ነው ይላል።
እሱ የሚለውን የፊልም ብያኔ ለማምጣትም ሆነ “የእውቀት ክፍተት” አለበት የሚለውን የኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ለመሙላት በፊልሙ ዙሪያ ያሉ ሰዎች መሰባስብ እና ለአንድ የጋራ ሀሳብ አገልጋይ መሆን አለባቸው ይላል። ኢንዱስትሪው የሀሳብ አለቃ እንደሚያስፈልገውም ያምናል።
ከዚህም ባለፈ ብዙ የሚነገር እሴት ባላት አገር ላይ የሚሰራው ፊልም የሀሳብ ድርቀት ያጠቃው እንዳይሆን መጠንቀቅ እና ማንበብ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል። ገና ሁለት አስርት ዓመታት እንኳ የሞላ ታሪክ በሌለው የኢትዮጵያ የፊልም ዘርፍ ውስጥ ስማቸውን በደማቅ ቀለም እየጻፉ ካሉ የኪነ ጥበብ ሰዎች መካከል ዋጄ ነው፤ ዋጄ ዘርፉ አሁንም የፋይናንስም ሆነ የእውቀት ክፍተት ቢኖርበትም በርካታ ጎበዝ ወጣት የፊልም ባለሙያዎች ብቅ ብቅ እያሉ መሆናቸው ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ያምናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፊልሙም ሆነ ጠቅላላው የጥብብ ዘርፍ ከፖለቲካ እና ፖለቲካኞች ጫና ነጻ መሆን እንዳለበት በከያኒያን ዘንድም አድርባይነት ፈጽሞ መታየት እንደሌለበት በጥብቅ ይሞግታል። በህብረተሰብ ደረጃም የባህል ለውጥ እንደሚያስፈልግ ይናገራል። በተለይም ልሂቃኑ እና ፊደል ቀመሱ ላይ ትችት ይሰነዝራል።
በሕዝብም ደረጃ ከሞራል አንጻር ብዙ ችግሮች እንደሚስተዋሉ እና የሃይማኖት ተቋማት በተለይ ትውልዱ የሞራል ሚዛኑ ያልተዛባ እንዲሆን ማስተማር አለባቸው ይላል። ኪነ ጥበብ የሕዝብን ቁስል ማሳየት እንዳለባት የሚናገረው ዋጄ፣ ከለውጡ በፊት በጀመረው ምን ልታዘዝ ድራማ ውስጥ ይህን የሕዝብ ስሜት በጥበባዊ መንገድ ለማሳየት ሞክሯል።
በሀይሉ ጸጥታ ያለበትን ሕይወት ይወዳል። ከስራ ውጭ ብዙ ጊዜውን በንባብ እንዲሁም ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ እንደሚያሳልፍ ይናገራል። “ቤተክርስቲያን መሄድ ወደ ቀልቤ እንድመለስ እና ከራሴ ጋር እንዳወራ እድል ይሰጠኛል” የሚለው በሀይሉ፣ ከዚህም በተጨማሪ በእረፍት ቀኑ ከጓደኞቹ ጋር በማሳለፍ እንዲሁም ሁኔታው ሲያመች ከከተማ ወጣ በማለት እንደሚዝናና ገልጾልናል። በመጨረሻ መልእክት እንዲያስተላልፍ እድል ሰጠነው። “ፈጣሪ መደማመጡን ያድለን። አሁን የምንጣላው ካለመደማመጥ በማይጨበጡ ሀሳቦች ነው” ብሎናል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም