ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና የባህል መናገሻ ነች። ህዝቦቿ በብዙ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ተከብበውና ተዋድደው የሚኖሩ የፍቅርና የመከባበር ተምሳሌቶች ናቸው። አገሪቱ የራሷ የዘመን መቁጠሪያና ፊደል ያላት፤ በሌላው ዓለማት በማይገኙና ተወዳጅ በሆኑ በዓላት፣ አልባሳትና የአመጋገብ ስርዓት የምትታወቅም ነች።
ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ከመሆኗ አንፃር የዚያኑ ያህል እጅግ ብዙና ህብርን የተላበሱ እሴቶችና የጋራ ማንነቶችም አሏት። ዜጎች ከሃይማኖታቸው ከሚቀዳ የበዓል ስርዓቶች የተገነባ ውብ ማንነት ከመላበሱም ባሻገር፤ በመቻቻል ለዘመናት አብሮ በመኖር ባዳበረው እሴት የተነሳ ሁሉም የሚጋራው ባህልና ኢትዮጵያዊ ቀለም እንዲሁ መገለጫው ነው።
ከዓመቱ መጀመሪያ አንስቶ አዲስ ዘመን የዘመን መለወጫ እስኪበሰር ድረስ “ከመስከረም እስከ መስከረም” አያሌ ተወዳጅና በጉጉት የሚጠበቁ ክብረ በዓላት፤ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስነ ስርዓቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄዳሉ። ከዘመን መለወጫ “እንቁጣጣሽ” እስከ “መስቀል”፣ ኢሬቻ፣ ጨምበላላ፣ ጥምቀት፣ ጊፋታ እና ሌሎችም በርካታ የማህበረሰቡን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓቶች የሚያሳዩ ተወዳጅ እሴቶች በድምቀት ይከበራሉ። ከውጪ ሆኖ ለሚመለከታቸው የሚያስቀኑና “የኔ በሆኑ” በሚያሰኙ ኢትዮጵያዊ ህብር ማንነቶች የደመቀችና የተወደደች ምድርም ነች።
የያዝነው የታህሳስ ወርም እንዲሁ በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችና በእስልምና አማኞች ዘንድ “የፋሲካ” እና “የረመዳን” ታላላቅ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች የሚከናወኑበት ነው። ይህን ተከትሎም ባህላዊ ስርዓቶችና ኢትዮጵያዊ ባህላዊ እሴቶች በድምቀት ይታይበታል። በኢትዮጵያ አብዛኛው ባህላዊ ስርዓቶች በከፍተኛ ሁኔታ ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ጋር ትስስር ያላቸው ናቸው። የአመጋገብ፣ አለባበስ፣ መረዳዳት፣ ቤተሰባዊ አብሮነትና ፍቅር ከሃይማኖታዊ በዓላት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው።
ለምሳሌ ያህል በዛሬው እለት እየተከበረ በሚገኘው የክርስትና እምነት ተከታዮች “የፋሲካ በዓል” ጋር የሚገናኙ አያሌ ባህላዊ ስርዓቶች አሉ። በተለይ ይህ ክብረ በዓል ከመድረሱ አስቀድሞ የሃይማኖቱ ተከታዮች በእለቱ በድምቀት ለሚከወነው ስርዓት የሚያደርጉት ዝግጅት በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ልዩ ባህላዊ ውበትና ድምቀትን የሚፈጥር ነው። የበዓል ወቅት የገበያ ስርዓቱ ከምግብ፣ ባህላዊ መጠጥ ዝግጅት አለባበስና መሰል ጉድጉዶች ጋር ተሰናኝቶ የበዓሉ ድምቀት ብቻ ሳይሆኑ ለዘመናት ትውልድን ተሻግረው የመጣ ባህላዊ እሴት የሆነ ሃብት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን አብሮነትና ፍቅር በልዩ ሁኔታ ስፍራ አግኝተውና ከመቼውም ግዜ በተለየ ደምቀው የሚታዩት “ፋሲካን” በመሰሉ በዓላት ወቅት ነው። ለዚህ ዋናው ማሳያው ምንም እንኳን የእምነቱ ተከታዮች ባይሆኑም አብረው በመኖር ጉርብትና የሚፈጥሩት ህብረትና የመቻቻል ተምሳሌት ፈክተው የሚወጡት ልክ በዛሬዋ ቀን ተከብሮ እንደሚውለው “የፋሲካ” በዓል ላይ ነው።
መስከረም ሲጠባ “የእንቁጣጣሽ” ባህላዊ ጭፈራው፤ ጥምቀት ሲመጣ የልጃገረዶች የማጨት “የሎሚ” ውርወራውና ጨዋታው እንደሚደራው ሁሉ በፋሲካ ወቅትም እራሱን የቻለ ባህላዊ ጨዋታዎች በየቦታው ይታያል። ዛሬ የክርስትና እምነት ተከታዮች ልዩ “የፋሲካ” በዓል የሚከበርበት ቀን በመሆኑም በዚህ ወቅት ላይ ስለሚካሄዱ ባህላዊ ክንውኖች ልናወራችሁ ወድደናል።
በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙት ሸካዎች በቋንቋቸው ‹‹ማዲካም›› ሲሉ ፋሲካ መጣ ገበታው ቀና አለ ለማለት ነው። በየዓመቱ የሚከበረው የፋሲካ በዓል ሲመጣላቸው በስፋት ያነሱታል። ሜዲካም ቀጥተኛ ትርጉሙ ቀና ያለ ገበቴ ማለት ሲሆን በጾሙ ወቅት ተከድነውና ተሰቅለው የቆዩ የምግብ ዕቃዎች ታጥበውና ፀድተው ለምግብ የሚዘጋጁበት “ፋሲካ መጣ ገበታው ቀና አለ” ማለት እንደሆነ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ድርሳን ያመለክታል። ለዛሬ ደግሞ በዋናነትም “ሚሻ ሚሾ” ተብሎ የሚታወቀው የታዳጊዎች ባህላዊ ጨዋታ ላይ ልዩ ትኩረታችንን አድርገን የተወሰኑ ነገሮች እንጨዋወት።
ሚሻ ሚሾ-የፋሲካ ጨዋታ
በፋሲካ ወቅት ከሚከበሩ ባህላዊ ስርዓቶች መካከል በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የምናገኘው “የሚሻ ሚሾ” በዓል ነው። ይህ ስርዓት ልዩ ልዩ መገለጫዎች እና ትርጉሞች ያሉት ሲሆን በጉዳዩ ላይ ጠለቅ ያለ እውቀት ያላቸው ምሁራን በመፃህፋቸው ላይ ያሰፈሩትን ዳሰሳ ተመልክተን ይበልጥ ለመረዳት እንሞክር።
የዘንድሮው ፋሲካ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዳግማይ ትንሣኤ እየተከበረ ይቆያል። የበዓሉ መንደርደርያ ጸሎተ ሐሙስ ሆኖ ማዕከሉን በተለይ በዓለ ስቅለትን ያደርጋል። ከበዓለ ስቅለት ባህላዊ መገለጫዎች አንዱ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚዘወተረው ‹‹ሚሻ ሙሾ›› ነው።
ስለዚህ ባህላዊና ትውፊታዊ ሥርዓት ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ መታፈሪያ ‹‹መዝገበ በረከት ዘሰሙን ቅድስት›› በተሰኘውና መሰንበቻውን ለንባብ በበቃው መጽሐፋቸው ዘርዘር አድርገው ማስረጃዎች እያጣቀሱ አቅርበውታል።
በደራሲው አገላለጽ፣ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ወንዶች ሕፃናት ደግሞ ‹‹ሚሻ ሚሾ›› እያሉ እየዘመሩ በየቤቱ እየዞሩ ዱቄት ይለምናሉ። በዓሉ በቂጣ ስለሚከበር የአይሁድ የቂጣ በዓልን ይመስላል። አለቃ ታየ ገብረ ማርያም በ1902 ዓ.ም. በታተመው የትብብር ሥራቸው ‹‹ሚሻ ሚሾ›› የሚለው ስያሜ የት መጣ ‹‹ውሾ ውሾ›› ከሚል እንደሆነ ያስረዳሉ።
ሊቀ ሥልጣናት አባ ሀብተ ማርያም ወርቅነህ ‹‹ማኅበራዊ ኑሮ በኢትዮጵያ›› ብለው በሰየሙት መጽሐፋቸው፣ ይህም አይሁድን ለመስደብ የተሰነዘረ እንደሚመስል ይገልጻሉ። በሌላ መልኩ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ደግሞ ‹‹ሚሻ ሚሾ›› ወዲያ ወዲህ፣ ከዚያ ከዚህ ማለት ነው። ይህም ከየቤቱ ዱቄቱ የሚሰበሰብ መሆኑን ለማመልከት ነው በማለት ያስረዳሉ። በተጨማሪም የትውፊቱ ትክክለኛ መጠሪያ ‹‹ሙሾ ሙሾ›› የክርስቶስን ሕማም ለመግለጽ የተሰጠ መሆኑን፣ በጊዜ ሒደት ተለውጦ ‹‹ሚሻ ምሾ›› መባሉንም ይገልጻሉ።
አለቃ ደስታ ተክለ ወልድም የቃሉን ፍች ‹‹ሙሾ (ምሾ) የለቅሶ ዜማ፣ የለቅሶ ቅንቀና፣ ግጥም፣ ዜማ፣ ቁዘማ፣ እንጉርጎሮ፣ ረገዳ፣ ጭብጨባ ያለበት›› በማለት ያስረዳሉ። ይኼኛው ሐተታ ከክዋኔው ጋር ቀጥታ ቁርኝት አለው። ሕፃናቱ በየቤቱ መሄዳቸው አይሁድ ሐሙስ ሌሊት ከሐና ወደ ቀያፋ፣ ከቀያፋ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት መዞራቸውን ለመዘከር ነው። ሕፃናት ይህን ዕለት እንዲያስታውሱት በየዓመቱ እንዲዘክሩ በማድረግ ይቻል ዘንድ ሊቃውንት ይህንን ሥርዓት እንደሠሩ ይናገራሉ።
‹‹ሕፃናት ከምሴተ ሐሙስ ጀምረው እስከ በዓለ ስቅለት ምሽት የሚሻ ሙሾን ዝማሬ እያሰሙ በየቤቱ በመዞር ዱቄት የሚያሰባስቡት ትውፊታዊ ክዋኔ አለው። ሕፃናቱ በየቤቱ ዱቄት ለመሰብሰብ ሲዞሩ በቀለማት ወይም በእሳት ተለብልቦ የተዥጎረጎረ ቀጭን ዘንግ ይይዛሉ። መሬቱን በዘንግ በመምታት ዱቄት እስኪሰጣቸው ድረስ በተለያዩ ግጥሞች የታጀበ ዝማሬ ያሰማሉ። ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዘንግ መመታቱን ለመዘከር ነው።
በዝማሬያቸው
‹‹ሙሻ ሙሾ ስለ ስቅለቱ
አይንፈጉኝ ከዱቄቱ።
ሚሻ ምሾ፣ ሆ ሚሻ ሙሾ
ሳይጋገር መሸ፣
እሜቴ ይውጡ ይውጡ ይበላዋል አይጡ፣
እሜቴ ይነሱ ፣ ይንበሳበሱ፣
ከቆምንበት፤ ቁንጫው ፈላበት፣
ስለ አቦ፤ ያደረ ዳቦ፣
ስለ ስቅለቱ ፤ ዛቅ አድርገው ከዱቄቱ፤›› በማለት ይዘምራሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በርካታ ግጥሞችና የጨዋታ አይነቶችም ታዳጊዎቹ አሏቸው። ለምሳሌ የሚከተለው ይገኝበታል፤
«ሚሻ ሚሾ »ሚሻ ሚሾ -ሚሻሚሾ
እመይቴ ይነሱ – ይንቦሳቦሱ
ካደረው ዱቄት – ትንሽ ይፈሱ፤
እመይቴ – በቁልቢጡ
ነጭ ከዳቦ – ዱቄቱን ያምጡ።
ተልባና ኑጉን – ሱፉን ጨምረው
እማማ አደራ – ይዝከሩኝ አብረው።
ለስግደቱ – ለወገቤ
እመይቴ – ትንሽ ቅቤ፤
እማ ሆይ ይነሱ – ይንቦሳቦሱ፤
ማባያ ‘የሚሆን – ከጨው ድቁሱ።
መዋጫ – መሰልቀጫ፤
ከቅመሙ – ማጣፈጫ፤
እመይቴ ይነሱ – ይንደፋደፉ፤
ዘመራ ጠላ – ወይ ከድፍድፉ።
እመይቴ ይነሱ – ሳንርቅ ከደጁ፤
ከማር ወለላው – ይስጡን ከጠጁ።…»
ሕፃናት ሚሻ ሙሾ ብለው አንድ ቤት ሲጨፍሩ ከቤቱ ዱቄት፣ አዋዜ፣ ቅባኑግ ወይም ጨው ሊሰጣቸው ይችላል። ይኼንን ሲያገኙ ‹‹ዕድሜ የማቱሳላን፣ ጽድቅ የላሊበላን ይስጥልን፤›› ብለው መርቀው ይሄዳሉ። ለምነው ምንም ነገር ሳይሰጣቸው ከቀረ ‹‹እንደ ሰፌድ ይዘርጋሽ፣ እንደ ማጭድ ይቆልምሽ፣ ቁመት ያውራ ዶሮ፣ መልክ የዝንጀሮ፣ ግማት የፋሮ ይስጥሽ፤›› ብለው ይራገማሉ። ሕፃናቱም በዚህ ክዋኔ ታላቅ ምርቃት እንደሚሰጣቸው አለቃ ታየ ትውፊቱን አስቀምጠዋል። ሕፃናቱ በልመና ባገኙት ዱቄት ቂጣ ጋግረው ቅዳሜ ምሽት በጋራ ይመገቡታል።
እንደ መውጫ
በመግቢያችን ላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከወኑ የማህበረሰቡ መገለጫ የሆኑ እሴቶች በሙሉ የጋራ ሃብቶች ናቸው። ከሃይማኖታዊ ፋይዳቸው የዘለለ ባህላዊ እሴቶችና የሚጎላባቸው አያሌ ክብረ በእላትም እንዲሁ ተዋደውና ተከባብረው በሚኖሩ ማህበረሰቦች መካከል ይገኛሉ። የዚህ ጥቅል ድምር ኢትዮጵያ የሚል አንድ የጋራ ማንነትን የፈጠረም ነው።
በዓላት በመጡ ቁጥር የሃይማኖቱ ተከታዮች ያልሆኑም ጭምር የስነ ስርዓቱ ታዳሚዎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል በዛሬው የፋሲካ በዓል ላይ አብሮነትና ፍቅራቸውን የሚያሳዩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከክርስቲያን እህት ወንድሞቻቸው ጋር ያከብራሉ። ይሄ ከሃይማኖታዊ ፋይዳው በዘለለ የአብሮነት እሴትን የሚያጎላ ነው። በተመሳሳይ የክርስትና እምነት ተከታዮች ረመዳንን ተከትሎ በሚደረገው አፍጥር ስርዓት ላይ በተመሳሳይ ፍቅራቸውንና ለጎረቤቶቻቸው ያላቸውን አክብሮት በስርዓቱ ላይ ያሳያሉ።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ ውስጥ በዓልና ባህል ልዩ መስተጋብር አላቸው። ለዚያም ነው አገራችን ኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት የአገረ መንግስት ታሪክ፣ ውብ ባህልና ማንነት ያላቸው ብሄረሰቦች በጋራ ተዋደውና በአንድነት ተጋምደው የሚኖሩባት አገር መሆኗ በገሃድ የሚታይ ሃቅ ነው የምንለው። ህዝቦቿ እንደ “ሚሻ ሚሾ” አይነት ለጆሮ ማራኪ፣ አይን ገብና ተወዳጅ የሆኑ እሴቶች ባለቤት ፤ ባህልና ወጋቸው ለባዳው የሚያስቀና ለወዳጅ ሃሴትን የሚፈጥር ጭምር መሆኑን አፋችንን ሞልተን የምንናገረው። ጠላትን በአንድነት መክተው ድባቅ የሚመቱ ለሉአላዊነታቸው መከበር በጋራ ዘብ የሚቆሙም ብቻ ሳይሆኑ በደስታቸውም ግዜ አብረው የሚበሉ፣ የሚረዳዱና የሚከባበሩም ናቸው።
ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያዊነትን ሳይለቁና የመጡበትን ማህበረሰብ ባህልና ማንነት ሳይሸራርፉ አብረው የመኖር የሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤትም ናቸው። ለዚህ የፋሲካና ረመዳን በዓላት ምሳሌ መሆን ይችላሉ። በተለያዩ ግዜያት የነዚህን ህዝቦች አንድነት የሚፈታተኑ አያሌ አጋጣሚዎች ነበሩ። ይሁንና በጠንካራው አብሮነትና የተጋድሎ ወኔ ችግሮቹን በጣጥሰው በማለፍ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። በድምቀትም ክብረ በዓላችን “ሚሻ ሚሾ” ብለው አክብረው “ረመዳን ከሪም” ተባብለው ተመራርቀው አንድነታቸውን አጠንክረው የሚኖሩት። መልካም የፋሲካ በዓል ለሁላችንም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም