ሰውነት በራሱ ያለው ለሌለው የሚያጋራበት በማዘንና መተዛዘን የተቃኘ ሰብዓዊነት ነው። ሰው በዚህ መንገድ በማሰቡ ከእንስሳ ይለያል። ይሄ ዓይነቱ ባሕርይ ደግሞ የትኛውም ዓይነት ጤናማ ሰው የሚገለፅበት ነው።
ነገር ግን የአሁኑ ዘመን ነጋዴ ባህርይ ከዚህ ዓይነቱ ወጣ ያለ ነው። የሚያሰላው ትርፉን ብቻ ስለሆነ አምስት ሊትር ዘይት ከአንድ ሺህ ብር በላይ ሲሸጥ የሸማቹ አቅም አያሳስበውም። አንድ ጆንያ ከሰል 1ሺህ 200 ብር መሸጡ ግድ አይሰጠውም። ኪሎ ሽንኩርት 46 ብር እና በላይ መሸጡም የደንበኛውን ኪስ የሚጎዳ አይመስለውም። እሱ ትልቅ ትርፍ እስካገኘበት ድረስ ደንበኛው ላይ ዋጋ መቆለል በፍፁም አያስጨንቀውም።
የዛሬ የትንሳኤ በዓል እንግዳችን፣ ማርና ጠጅን ጨምሮ በሀበሻ መጠጦች ምርትና የገበያ አቅርቦት ላይ የተሰማሩት አቶ ሙሉ ቀን ተካ ግን ከእነዚህ ዓይነቶቹ ነጋዴዎች የተለዩ ናቸው። ምንም እንኳን እሳቸውም ነጋዴ ቢሆኑም እንዲህ ዓይነቶቹን ነጋዴዎች ከመውቀስ አይመለሱም። የሚመለከተው አካል በእነዚህ ዓይነቶቹ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት የሚል አቋም አላቸው። ዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱ በደንበኞቻቸው አቅም ላይ የፈጠረውን ጫና ሲያስቡት ነጋዴ መሆናቸውን ፈጽሞ ይጠላሉ። እንደውም በዚህ ዓይነቱ ዘመን ሰው ሆነው መፈጠራቸውን እስከመጥላት አድርሷቸዋል። ፈጣሪያቸውን ለምን ፈጠርከኝ ብለውም ጠይቀዋል። በዘንድሮ ትንሳኤ በዓል እንዲህ ዓይነቶቹ ጨካኝ ነጋዴዎችና አምራቾች እያሉ፣ እያሉ የቆለሉትን ዋጋ ለደንበኞቻቸው ደፍረው ለመናገር ያፍሩና ይፈራሉ። ብዙ ጊዜ ሰራተኞቻቸው ጣልቃ እየገቡ ባይገስጿዋቸው ለደንበኞቻቸው አቅም በማዘን ይሉንታ ካመረቱበትና ካመጡበት በታች እስከ መሸጥ ለመድረስ አይመለሱም ተብለው ሲታሙም ሰምተናል። አቶ ሙሉ ቀንን ያገኘናቸው አራት ኪሎ የትንሳኤ ባዛር ተሳታፊ ኢንተርፕራይዞች መካከል በሽያጭ ላይ ነው። ቢዝነስ ካርድ ያሳተሙት 7ሺህ 500 ብር አውጥተው ነው። ካርዱ የምርትና የገበያ ቦታቸውን ከማስተዋወቅ ባሻገር ብዙ ደንበኞች ማፍራት እንደሚያስችላቸው ያምናሉ። ዕምነታቸው ከመሬት ሳይሆን የሳምንት ዕድሜ ባለው ባዛር ከ50 በላይ ቋሚ ደንበኞች ካፈሩበት ልምድ የተነሳ ነው።
ነጋዴው እንዳወጉን ተወልደው ያደጉት የማርና የቅቤ መገኛ በሆነው በምስራቅ ጎጃም ዞን ነው። ቢሆንም ዛሬ ላይ ታዋቂ ማርና ቅቤ አምራችና አቅራቢ ያደረጋቸው ብዙ ውጣ ውረዶች ያሳለፉበት የሕይወት ዕጣ ክፍላቸው ነው እንጂ በማርና ቅቤ አገር መወለድና ማደጋቸው አይደለም። ምርታቸው ጥራት ያለው ነው። በደንበኞቻቸው ተአማኒነትና ተወዳጅነትን አትርፎላቸዋል። ዋጋቸው ተመጣጣኝ መሆኑም በዋጋ ንረት የሚሸሹ ሸማቾችንን ማቅረብ አስችሏቸዋል። በተለይ እንዲህ እንደ ዛሬው ላለው የትንሳኤ በዓል ገበያ ውጤታማ አድርጓቸዋል። በመሆኑም የዕውቁን ማርና ቅቤ ነጋዴ የአቶ ሙሉ ቀን ተካን ሕይወትና ልምዳቸውን ተጋሩልን ስንል ጋብዘናችኋል።
ውልደትና ዕድገት ከትምህርት ሁኔታ ጋር
አቶ ሙሉ ቀን ተወልደው ያደጉት የማርና የቅቤ መገኛ በሆነው በምስራቅ ጎጃም ዞን ነው። የተወለዱበት ሥፍራ ለደብረማርቆስ ከተማ የቀረበ ሲሆን ልዩ ስሙ ጎዛመን ወረዳ ገራሞ ደንደራም ቀበሌ ገበሬ ማህበር ይሰኛል። በቀለም ትምህርት በኩል በተወለዱበት አካባቢ በነበረው በገራሞ ደንደራም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ስድስተኛ ክፍል ዘልቀዋል።
ሕይወት በአዲስ አበባ
አቶ ሙሉ ቀን ወደ አዲስ አበባ ከተማ የመጡት በታዳጊነት ዕድሜያቸው ነው። አመጣጣቸው የጦርነት ግዳጅ ሽሽት ቢሆንም የላኳቸው ከዚህ ቀደም የጦርነትን አስከፊነት የቀመሱት የሚሳሱላቸው ወላጅ አባታቸው ነበሩ። ለወላጆቻቸው የበኩር ልጅ የነበሩትና ከጊዜ ብዛት ለችግር የተዳረገውን ቤተሰባቸውን የመንከባከቡ ሃላፊነት ገና በታዳጊነት ዕድሜያቸው የተጫነባቸው ሙሉ ቀን የአዲስ አበባው የአክስታቸው ቤትም የሚያወላዳቸው ሆኖ አላገኙትም።
የሕይወት ውጣ ውረድ
ከአክስታቸው ቤት ወጥተው ጎዳና እስከ ማደር ደርሰዋል። የሆቴል ቤት የመስተንግዶ ሥራ አግኝተው እስከተላቀቁበት ጊዜ ድረስ ከጎዳና ለመውጣት እጅግ ዝቅተኛ እስከሆነው የጉልበት ሥራ ሰርተዋል። ጠጅ ቀጂም ነበሩ። በተለይ 22 አካባቢ የሚገኘው ጦቢያ ጠጅ ቤት የሰሩበት ጊዜን በፍፁም አይዘነጉትም። በሁሉም ሥራዎች ያሳለፉት ጊዜ በተለይም ጠጅ የመቅዳት ሥራቸው ከ18 ሰዓታት በላይ በማስፈጋት የታዳጊነት ጉልበታቸውን መብላቱ አሁን ላይ ሆነው ሲያስቡት ይጎረብጣቸዋል። ሆኖም በሱስ አጥምዶ መና ሳያስቀራቸው ለዛሬው የማርና ጠጅ አምራችና አቅራቢነታቸው መሰረት መጣል የሚያስችላቸው ልምድ እንዲያካብቱ ስላደረጋቸው እና ምክንያት ስለሆናቸው ደግሞ ይፅናናሉ።
ሙሉ ቀን የማር ጠጅ ኢንተርፕራይዝ ምስረታና አስተዋጽኦ
አቶ ሙሉ ቀን በዕድሜ ታዳጊ ቢሆኑም በተፈጥሮ አስተዋይ ናቸው። እንደ ልጅ ጨዋታም ሆነ ዋዛ ፈዛዛ አያታልላቸውም። በዚህ ላይ ሕይወት ጎትታ ጎዳና በማውጣት ሳይቀር ቀልድ እንደማታውቅ አስተምራቸው ነው ያለፈችው። በመሆኑም ከእንግዲህ እሷን ስኬታማ አድርገው ሕይወታቸውን ለመቀጠል የሚያባክኑት ጊዜ እንደሌላቸው አሳምረው ተረድተዋል። እናም ከጠጅ ቀጂነቱ ጀምሮ እስከ ብጥበጣውና ጠመቃው ያለውን የሙያ ሂደት በጽሞና ሲከታተሉ ቆዩ። ሥራውን እየወደዱትና ውስጣቸው እየሰረፀም መጣ። ለጠጅ ቤቱ ማር የሚያቀርቡት ነጋዴ አገር ቤት ያሉት ወላጆቻቸው ጎረቤት መሆናቸው ሥራውን የበለጠ እንዲወዱት አደረጋቸው። ሱሰኛና ጠጪ ባይሆኑም ጥሩ የማር ጠጅ ቃና መለየት የሚያስችላቸውን ያህል መቅመሳቸው ብቻ አገዛቸውና ሳይዘናጉ በእነዚሁ ምክንያቶች ወደ ማር ጠጅ ሥራ ገቡ። ዛሬ ሙሉ ቀን የማር ጠጅ ኢንተርፕራይዝ ባለቤትና መሥራች ሥራ አስኪያጅም ሆነዋል። ማርና የማር ውጤቶችን በማምረትና አቅርቦት ላይ ነው የተሰማሩት። በሥራው ለ20 ዓመት ያህል ቆይተዋል። ከራሳቸው አልፈው በበዓላት ወቅት ከ30 በላይ ለሆኑ ሰዎች፤ በቋሚነት ደግሞ ለስምንት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠርም ችለዋል። የእህትና ወንድሞቻቸውን ልጆች ጨምሮ ልጆቻቸውን በድምሩ 16 ቤተሰብ ለማስተዳደርም በቅተዋል። የዘንድሮን የትንሳኤ በዓል ጨምሮ አቅምና ገቢ የሌላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች እንቁላልና ዶሮ ገዝተው ከመስጠት ጀምሮ እጃቸውን በመዘርጋት የአቅማቸውን ይደግፋሉ። አገር ስትወረር፣ ሕዝብ ሲፈናቀልና ሲቸገርም ቀድመው በመድረስ ከሚያደርጉት እገዛ ባሻገር ለመከላከያ ሠራዊት ከ30ሺህ ብር በላይ ለግሰዋል።
የአቅርቦት ዓይነቶችና ምንጫቸው
አሁን ላይ ነጋዴው የማር ጠጅ ብቻ ሳይሆን ለምግብና ለጠጅ የሚውል ንፁህ ማር በማምረትና እንደ ጎጃም በረንዳ ላሉ ነጋዴዎች በማቅረብ ይታወቃሉ። በተጨማሪም የሀበሻ መጠጦችን ያቀርባሉ። ከሚያቀርቧቸውም መካከል ለደም ብዛት ዓይነተኛ መድሃኒት መሆኑ የሚነገርለትን የግብጦ አረቄ ጨምሮ የኮሶ፣ የቡና፣ የማር፣ የዳጉሳ አረቄዎች ይጠቀሳሉ። እነዚህ ደግሞ በዓውድ ዓመትም ሆነ ከአውድ ዓመት ውጭ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች ናቸው። ለሰርግና ለተለያዩ ድግሶችም ያስፈልጋሉ። ቢሆንም ዓመት በዓልን ተንተርሶ ባለው ወቅት የምርታቸው ፈላጊ ይጨምራል። ምርትና አቅርቦታቸውም የዚያኑ ያህል ከፍ ይላል። የሚያስገኙት ገቢም ቢሆን ዳጎስ ይላል። በአብዛኛው ከተለያዩ አካባቢዎች በትዕዛዝ ተዘጋጅተውና ተሰብስበው የሚመጡ ቢሆኑም በእሳቸው የሚመረቱበትም ሁኔታ አለ። ማር ከቴፒ፣ ከቦንጋና ከጎጃም ሲያመጡ፤ ቅቤ ደግሞ ከሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደብረ ብርሃን፣ ሸኖ ዙሪያ፣ ከሀሙሲት አርሶ አደሮች ይሰበስባሉ።
በበዓላት ወቅት ያለው የምርት ተፈላጊነት
የትንሳኤ በዓል በክርስትና ሃይማኖት ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ተወዳጅና ተናፋቂ በዓል ነው። 55 ቀን ሙሉ በጾምና ፀሎት ተቆይቶ በጾም ወቅት ወደ የሚከለከሉ ምግብና መጠጦች የሚገባበት ጊዜ በመሆኑ ሁሉም የእሳቸው ምርቶች በገበያ ይፈለጋሉ። ቅቤም ሆነ ማርና አረቄ ፈላጊያቸው ብዙ ነው። ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በዓሉን የሚያሳልፉት እነዚህን ምርቶች ሸምተው በመጠቀም ነው። አረቄ በራሱ ሥጋን ጨምሮ ቅባታማ ምግቦችን ለማንሸራሸር ስለሚጠቅም በብዙ ሰዎች ይሸመታል።
በዘንድሮ የትንሳኤ በዓል የምርት ዋጋ
በዘንድሮ ትንሳኤ በዓል በተሳተፉበት ቅድስተ ማርያም ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኘው የአራት ኪሎ ባዘር የክትፎ ለጋ ቅቤ ሲሸጡ የነበረው 500 ብር ነው። በሳል የወጥ ቅቤ ደግሞ 490 ብር ሲሸጡ ቆይተዋል።
የተጣራውን የቴፒ የጫካ ማር 500፤ ነጩን የዚሁ አካባቢ የተጣራ ማርም እንዲሁ በ500ብር ሲሸጡ ነው የዋሉት። ያልተጣራው የጎጃም ማር 300ብር ነበር። ያቀረቧቸው የግብጦ፣ የዳጉሳና የኮሶና ሌሎች አረቄዎች ዋጋቸው ከፊቱ አንፃር ሲታይ በዘንድሮ ትንሳኤ በዓል በእጅጉ ተወድዷል። አንድ ሊትሩን ሲሸጡ የሰነበቱት 180 ብር ነው። ከእሳቸው የሚረከቡ ደግሞ ከ250 ብር በላይ እንደሚሸጡት መታዘብ ችለዋል። የሁሉም የሀበሻ ምግብና መጠጥ አቅርቦት በዘንድሮው የትንሳኤ በዓል ቀንሷል። አሁን በተጨባጭ ካለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት አንጻር አራት ጀሪካን አረቄ ብቻ በትዕዛዝ አሰርተው ነው ያቀረቡት።
የኑሮ ውድነት፣ የዋጋ ንረትና አስተያየት
አቶ ሙሉ ቀን አሁን ባለው እጅግ የተጋነነ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት የተለየ አመለካከት አላቸው። ነጋዴ ቢሆኑም ነጋዴውን ይወቅሳሉ። የንግድ ስርዓቱን ፈር በማስያዙ ረገድ ትልቅ ሃላፊነት የተጣለበትን አካልንም ያነሳሉ። በተለይ ሰላም ማስፈኑ የንግድ ስርዓቱን ፈር በማስያዝና የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን በመቅረፍ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው መንግስት በዚህ በኩል ከልቡና በቁርጠኝነት እንዲሰራም ምክራቸውን ይለግሳሉ። ለዋጋ መናሩና ለኑሮ ውድነቱ ምክንያት ያሏቸውን ከእነዚሁ አካላት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችንም በዝርዝር ያስቀምጣሉ።
በንግዱ ሰንሰለት ውስጥ ካሉት በተለይ እሳቸው በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ የተከሰተውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት አስመልክተው ቀዳሚ ተጠያቂ የሚያደርጉት ገጠር ያለውን አርሶ አደር ነው። ዕድሜ ለቴክኖሎጂ አንዱ ክልል ሌላው ክልል ካለ የአርሶ አደር ነጋዴ ጋር በስልክ ተደዋውሎ ምርቱን ይይዘዋል። አያወጣውም። ይሄ በአንዴ ሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የሚደረግ በመሆኑ የምርት እጥረት ያለ ያስመስላል። እንደሳቸው ናፍታና ዘይት ከውጭ በመምጣታቸው ተወደዱ ቢባልም ጤፉ፣ ስንዴው፣ ገብሱ፣ ሽንኩርቱ፣ ቅቤው፣ ማሩ፣ በሬው፣ በጉ፣ ፍየሉ፣ ዶሮ እና እንቁላሉ እዚሁ አርሶ አደር ጋር ናቸው። ከውጭ የሚመጡ አይደሉም። ሆኖም በንግድ ሂደታቸው ወቅት እንደታዘቡት ምክንያቱም አርሶ አደሩ ከቅቤ በስተቀር ሌሎቹን ሁሉንም ምርቶች አያወጣቸው። ደብቋቸዋል። ሲቀመጥ ስለሚበላሽና ቃናው ስለሚቀየርበት የሚያወጣውን ቅቤም እጅግ በተጋነነ ውድ ዋጋ ነው የሚሸጥላቸው። እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ምርቱንና አቅርቦቱን ሲጀምሩ አዲስ አበባ ላይ አምጥተው አንድ ኪሎ ማር በ12ብር ነበር ይሸጡ የነበሩት። አንድ ኪሎ ቅቤ ደግሞ 18ብር ነበር ዋጋው። በዘንድሮ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ በዓል አንድ ኪሎ ማር 500 ብር ለመሸጥ ተገድደዋል። ይሁንና እሳቸው የሚያስረክባቸው ነጋዴዎች ጎጃም በረንዳ ላይ እስከ 630 ብር ሲሸጡት ታዝበዋል። እሳቸው 500 ብር የሚሸጡትን ቅቢያቸውን የሚያስረክባቸው የቤት ኪራዩንና ሌሎች ወጪዎቻቸውን ታሳቢ በማድረግ ቢሸጡትም የኑሮ ውድነቱ በዚህ ከቀጠለ ያስፈራል ባይ ናቸው።
የሚገርመው ደግሞ ከእነሱ የሚቀበሉት ሌሎች ነጋዴዎች ከእነሱ እጅግ በተጋነነ ዋጋ ጭማሪ አድርገው ምርቱን ለሕብረተሰቡ ማቅረባቸው ነው። ቅቤ ከመጣበት በላይ ተሸጧል። እሳቸው በሳሉን 490፤ ለክትፎ የሚውለውን ደግሞ 500ብር ብለው ለመናገር ራሱ በሚያፍሩበት ሁኔታ የብዙ ነጋዴዎች ዋጋ መጨመር ያሳዝናቸዋል። ነጋዴ መሆናቸውን አብዝተው እንዲጠሉም አድርጓቸዋል። እንደውም ዘመኑን ሰው ሆኜ መፈጠሬን ሁሉ የጠላሁበት ነው እስከማለትም አድርሳቸዋል። ከምሬታቸው መብዛት የተነሳ ፈጣሪያቸውን ለምን ፈጠርከኝ እስከ ማለት ሁሉ በቅተዋል።
የእነዚህ ነጋዴዎች ጭካኔ የተሞላበት የተጋነነ ጭማሪ በሸቀጣ ሸቀጥ ቢታይ ለሰው ልጆች ንጽሕናን ለመጠበቅ ሰርክ አስፈላጊ የሆነው ሳሙና አንዱ 40 ብር መግባቱን ሰምተዋል፤ አዝነዋልም።
ከላይ እንዳልነው፣ ለበዓል ስራ እስከ 30 ሰው የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። በቋሚነት ስምንት ሰራተኞች አሏቸው የሚያስተምሯቸው የእህታቸውን ልጆች ጨምሮ 16 ቤተሰብ ናቸው። አንድ የልብስ ሳሙና 40 ብር መግባቱ አሳስቧቸዋል። እሳቸው ደግሞ ከሥራቸው ፀባይ አንፃር ሳሙና በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። ጠጅ ሲበጠብጡ፣ ማርና ቅቤ ሲመዝኑ፣ ምርቶቹን ወደዚያ ወደዚህ ሲያደርጉ የሥራ ልብሳቸው ይቆሽሻል። ለዚህ በየቀኑ ከሁለት ሳሙና በላይ ይጠቀማሉ። አንድ ኩንታል ከሰል 1ሺህ 200 ብር ገብቷል። በሰሙነ ህማማት ሳምንት አምስት ሊትሩን ዘይት ያውም ባለቤታቸው ባለ መደብሩን ስለሚያውቁት ለምነው አንድ ሺህ 200 ብር ነው የገዙት። ዘይትን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን የሚደብቁ ነጋዴዎችም አሉ። መደበቁና በአንዳንዱ ምርት ላይ የሚደረገው ጭማሪ እንዲሁም የኑሮ ውድነቱ መባባስ በሙሉ በሕብረተሰቡ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን አይተውበታል። አንድ ኪሎ ቅቤ 20ብር ቢሸጥ ደንበኞቻቸው ዘይት ገዝተው እንደማይበሉ ይልቁኑም ቅቤ ገዝተው እንደሚበሉ ያስባሉ። በዘንድሮ ትንሳኤ 500ብር ቅቤ ገዝቶ የመብላት አቅም ያለው ደንበኛ በማጣታቸው ገበያቸው ተቀዛቅዟል።
ምርት የሚደብቁ ነጋዴዎች ስላሉ አቅርቦት የለም። ለዘንድሮው የትንሳኤ በዓል የአቅርቦት ዝግጅት ለማድረግ ከሁለት ወር በላይ ፈጅቶባቸዋል። ድርጊቱን ትራንስፖርቱ ወቅታዊ የአገሪቱን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ነው። የንግድ ሂደቱን በቁጥጥርና ክትትል ፈር የማስያዝ ሃላፊነት የተጣለበት አካል ‹‹አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› እንደሚባለው ተረት ዝም ብሎ እያየ ነው። በዚህ በኩል የዋጋ ንረቱንና ንረቱ ያመጣውን አጠቃላይ ሁኔታ ሰበብ ያደረገ የትራንስፖርት እጥረትም አለበት። አገራችን አሁን ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታም ሌላው እንቅፋት ነው። ሰው በተለይ እንደ እሳቸው ከቦታ ቦታ የሚዘዋወር ነጋዴ በሰላም ወጥቶ በሰላም የሚገባበት ሁኔታ የለም። በሰላም እጦት ምክንያት መንገድ ላይ ወድቆ እስከ ወዲያኛው የሚቀርበት ሁኔታ ብዙ ነው። ከዚህ ባሻገርም እንቅስቃሴው በሙሉ በጭንቅ የተሞላ ነው።
አሁን ላይ እጅግ በብርቱ የንግድ እንቅስቃሴውን እያስቸገረ ያለው ሁኔታ የፀጥታው ጉዳይ ነው። የቅቤውንም ሆነ የማሩንና ሌላውን ምርት በየክልሉ ካለው አርሶ አደር ሰብስቦ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ፈተና ሆኗል። በተለይ ዘንድሮ ሁኔታው እጅግ እየተባባሰ መጥቷል። የፀጥታ ችግር በመኖሩ ምክንያት በመኪና ሄደው በአውሮፕላን ለመመለስ የተገደዱበት ሁኔታ ሁሉ ገጥሟቸዋል።
ከገጠመኞቻቸው መካከል ከአንድ ወር በፊት ጎሃ ጽዮን ላይ የደረሰባቸው አንዱ ማሳያ ነው። ይሄም ጎሃ ጽዮን ላይ ነዋሪውን ጨምሮ በብዙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሕይወትና ንብረት መጥፋት አደጋ የደረሰው እሳቸው ባለፉ በ30 ደቂቃ ውስጥ መሆኑ ነው። በተመሳሳይ እንዲሁ ሌላ ክልል ደርሰው ሲመለሱ እሳቸው ሲያልፉ አደጋው ሲፈጠር አንድ የሆነበት ጊዜም ገጥሟቸዋል። እህቶቻቸውና ሙሽራዋ ከኋላ የመኖራቸው ሁኔታ ሰቆቃና ጭንቀታቸውን አባብሶባቸው አልፏል። በሰላሙ ዕጦት የተነሳ ሕይወት ጭንቀት ሆኖባቸዋል። ከዚህ አንፃር ወቅቱ ለስራ የሚያመች አይደለም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ቤተሰቦቻቸው በተለይም ልጆቻቸው በቃ ሥራው ይቅርብህ አትውጣ እስከ ማለት ደርሰዋል። ሆኖም አቶ ሙሉቀን ተካ ይሄ አልተዋጠላቸው። ካልሰሩ የእሳቸውንም ሆነ የቤተሰባቸውንና በሥራቸው ያሉትን ሠራተኞች ጉሮሮ ለመድፈን የሚያስችል ሌላ አማራጭ እንደሌላቸውም አሳምረው ያወቃሉ። በመሆኑም በድፍረት ሄደው ለትንሳኤ በዓል ለማቅረብ ያሰቡትን ምርት ሰብስበው ተመልሰዋል።
መንግሥት በሰላም ዙሪያ ሊኖረው ስለሚገባው ድርሻ
እንደ እንግዳችን አቶ ሙሉ ቀን ምክር መንግስት ሕዝቡን ከአስከፊ የኑሮ ውድነቱና ከዋጋ ንረቱ መታደግ ከፈለገ ቅቤና ማሩን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የንግዱን እንቅስቃሴ ወረድ ብሎ ማየት ይኖርበታል። የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ንረቱ የነፃ ገበያ መርህን የተከተለ ነው የሚባል ዓይነት ባይሆንም አጉል ነፃ ገበያና ዴሞክራሲ እያሉ በዝምታ ማለፉ አይታያቸውም። ‹ሕዝቡ ራብ ላይ ነው› ባይ ናቸው።
በራሳቸው ኑሮ ከብዷቸዋል። እግዚአብሔር ይመስገንና የራሳቸው መኖሪያ ቪላ ቢገነቡም የመሸጫ ሼድ (ክፍል) ስላልተሰጣቸው ለመጋዘንና ለሽያጭ የሱቅ ኪራይ በየወሩ የሚያወጡትን ከ40ሺህ ብር በላይ መክፈልም ሊያቅታቸው ተቃርቧል። ቤተሰባቸውን ፍፁም ማስተዳደር አልቻሉም። ሁሉም ቁርስ፣ ምሳና ራት ይፈልጋሉ። በሥራ የሚደክም ሰው መክሰስ ሻይና ቡና ሊያስፈልገው ይችላል። ይሄን ለመመገብ የሚያስፈልገው ወጪ አሁን ባለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ሲሰላ ቀላል አይደለም። በመሆኑም እሳቸው በራሳቸው ኑሮ በእጅጉ ከብዷቸዋል። 16 ያህል ቤተሰባቸውን ጨምሮ ቋሚ ሠራተኞቻቸውን ማስተዳደሩ እየተሳናቸው ነው። የበዛው የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ንረቱ ጫና ጊዜያዊ ሰራተኞቻቸውን የሚያሳድሩበት አቅማቸውም እየተመናመነ እንዲመጣ አስገድዶታል።
በጥቅሉ የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ንረቱ ያስጨንቃል። እሳቸውና እንደሳቸው ያለ ሰው ወጥቶና ወርዶና ተሯሩጦ ሰርቶ ጉሮሮውን ይሸፍናል። ሆኖም ለአቶ ሙሉ ቀን በተለይ ሁልጊዜ የሚያሳስባቸው ወርሃዊ ገቢ ያለው የሕብረተሰብ ክፍል ነው። አንድ ወይም ሁለት ልጅ ያለው እንዴት ሆኖ ኑሮውን እንደሚገፋ ሲያስቡት ያማቸዋል። በእጅጉም ያሳዝናቸዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በባህሪው ሁሉም ተደጋግፎ እንደመኖሩ ከራሱ አልፎ ተርፎ እናት አባቱን፤ ወንድሙንና እህቱን እንዲሁም ሌላውን ቤተሰቡን በመርዳት የሚኖር ነው። በዚህ ላይ ለመኖሪያና ለንግድ የቤቱ ኪራይ የሚከፍለው አለ። ይህ ሁሉ እያለ የኑሮ ውድነት ጫናውን እንዴት ሊቋቋመው እንደሚችል ሲያስቡት ያስፈራቸዋል። በመሆኑም መንግስት እዚህ የሚታየው አስከፊ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራ የተሻለ ስለ መሆኑ ይመክራሉ። የፀጥታው ጉዳይም ሌላው በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት የሚገባ ትልቅ ሥራ መሆኑንም ያመለክታሉ።
ነገር ግን መንግስት በዚህ በፀጥታ ጉዳይ ላይ መሥራት ለምን እንዳቃተውም ደጋግመው ይጠይቃሉ። እንደ አቶ ሙሉ ቀን ተካ ከመሬት ተነስቶ የጎበዝ አለቃና ሌላም ሌላም የሚሆነውን ሊያይና ሃይ ሊለው ይገባል። መንግስት ጉልበት የሚያጣው ሕዝብ ከጎኑ አልሆን ሲለው ነው። ነገር ግን አሁን ላይ እንደታዘቡት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎኑ ነው። ይሄ በተግባር ታይቷል። እሳቸውን ጨምሮ ሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ኢትዮጵያ በጁንታው በተወረረችበትም ሆነ የውጭ ጠላት በመጣባት ወቅት እንደ ንብ ነው ሆ ብሎ የተነሳው። የአዲስ አበባ ከተማ ወጣት በተለይ የአፋርና የአማራ ሕዝብ የሆነው ወገኑ በተወረረና በተጎዳበት ወቅት እንደ ንብ ሆ ብሎ ተነስቶ ግልብጥ ብሎ ወደ ጦርነት የሄደ እለት እሳቸው ብቻ ናቸው የሆኑትን የሚያውቁት። ግልብጥ ብሎ የሄደው ወደ ድግስ ሳይሆን ሕይወቱን ወደሚሰዋበት ወደ ሞት ግብ የሚሄድ በመሆኑ እሳቸው የደም እንባ አልቅሰዋል። ማልቀስ ብቻ ሳይሆን “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” ብለውም በግላቸው ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት 30ሺህ ብር ያህል የአቅማቸውን የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል። ይሄ የሚኖሩበት ወረዳ ሰባት የሚመሰክረው ጉዳይ ነው። ለወረዳው እለግሳለሁ ብለው የገቡት ቃል ሁለት ሺህ ብር ነበር። ሆኖም አገር እንዲህ እየሆነች፤ ሕዝብ እንዲህ እየተጎዳና እየተፈናቀለ የኔ ልፋትና መኖር ምንድነው ብለው በዕለቱ ወረዳ ላይ 10ሺህ ብር አስገብተዋል። ከዛ በኋላም ለመከላከያ ሠራዊቱ 30ሺህ ብር ሰጥተዋል።
እውነታው እንዲህ ሆኖ ሳለ አሁን ላይ “መንግስት ለምንድነው አቅም ያጣው?” የሚለው ጥያቄ በአእምሯቸው ማቃጨሉን አላቆመም። ሕዝቡ ለመንግስት ምን አጎደለበት፣ መቸስ “አልገዛም” ብሎ እንቢ አለ? ለዚህ ሆ ብሎ መነሳቱና ከጎኑ መሆኑ ማሳያ ነው። አሁን ላይ መንግስትን የጠላ ሕዝብ አለመኖሩን በተለያየ መንገድ ማረጋገጥም ይቻላል ባይ ናቸው። ግን ደግሞ ይህ ሕዝብ ለምን ለዋጋ ንረት እና ለኑሮ ውድነት እንደ ተዳረገ ግራ ይገባቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚከሰተው ሕዝብና መንግስት ሲለያዩ ብቻ ነው። ሕዝብና መንግስት አንድ ሆኖ መንግስት እንዴት የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ንረቱን መቆጣጠር አቃተው? ለምድነው ችግር ላይ የምንወድቀው? ብለውም በእጅጉ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።
ችግሩ የእሳቸው ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ነው። በመሆኑም መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ቢያስተካክለው ደስ ይላቸዋል። ውሳጣቸውን የሚያውቁት እሳቸው ብቻ ናቸው። ልጅ ማስተማርም ሆነ ቀለብ መሸመት አልቻሉም።
እሳቸው እየሰሩ የተቸገሩት፣ ደሞዝተኛውንና ምንም የገቢ ምንጭ የሌለውን ሲያስቡት የሚያማቸው ለዚህ ነው። ቤተክርስቲያን እና መስጂድ ያሉና ጎዳና ላይ የወደቁ እናቶችና አባቶች ከእሳቸውና እንደሳቸው ካለ የሕብረተሰብ ክፍል ነው የሚጠብቁት። እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ሲለምኑ አውጥቶ መስጠትም ሆነ መርዳት የሚቻለው ሲኖር ነው። ከሌለ እንኳን ከውጭ ያሉ ወገኖችን መደገፍ ቤት ውስጥ ያሉትን መሸከፍ አይቻልምና ከባድ ነው። ለምንድነው እንዲህ በዋጋ ንረት የምንሰቃየው? ሲሉ ራሳቸውን እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል። ሁሌ ምንድነው ከውጭ የ(ሚ)መጣው ብለው ያስባሉ። እንደእሳቸው ናፍጣ ላይ ችግር መኖሩ እውነትና ዓለም አቀፍ ችግር ነው። ዘይትም እንዲሁ ዓይነት ችግር ይሆናል። ፍላጎቱና አቅርቦቱ አለመመጣጠኑና የፋብሪካዎቹ ማነስ ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ሁለት ፍጆታዎች ሰበብ ይሄን ያህል የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት የመጣበት ምክንያት ምንም ሊያሳምናቸው አልቻለም።
ነጋዴውስ ለምንድነው እግዚአብሔርን የማይፈራው? ወገኑ እየተቸገረ እሱ የሚበለጽግበት ምን ዓይነት ህሊና ቢኖረው ነው? ሌላውን ርቃኑን እያስኬደ እሱ መልበሱ ምን ይጠቅመዋል? ስንት ዓመትስ የሚኖር ይመስለዋል? የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በእርሱ ተቻችሎ የሚኖር ነው። ሕዝቡ የሚከተለው ክርስትናም ሆነ እስልምና አምላኩን የሚፈራ ነው። በመሆኑም በዘንድሮው የትንሳኤ በዓል እንዳለፉት ዓመታት ሌሎች በዓላት ሁሉ ነጋዴውን የሕብረተሰብ ክፍል አብዝተው ለሕብረተሰቡ እንዲያስብ፤ እግዚአብሔርን በመፍራት የንግድ ሥራውን እንዲያከናውን ይለምኑታል። እንዲህ አይነቱን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት በመፍጠር እየተሰራ ያለው የፖለቲካ አሻጥር ነው። አሻጥሩ የተደረገው መንግስትን ለመጣል ታስቦ ከሆነ ትክክል አይደለም። መንግስት ቢሄድ መንግስት ይተካል። ነገር ግን “ለውጥ የሚመጣው ሕዝብ ለረሃብ እየተዳረገ፣ እየታረደና እየተቸገረ ነው ወይ?” በማለት ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በየቢሮ ያለውን ብሔርተኛ መፈተሸ ተገቢ እንደሆነም ይመክራሉ።
የኑሮ ውድነት ጫና በመንግሥት ላይ
እንደ እንግዳችን የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱ በሕብረተሰቡ ላይ ብቻ ሳይሆን መንግስትም ላይም ጫና ፈጥሯል። ባለፉት ሶስት ዓመታት መንግስት ባዛር ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ድጋፍ ሲያደርግላቸው ቆይቷል። በዘንድሮ የትንሳኤ በዓል ግን የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ንረቱ መንግስትም ላይ ጫና ስለፈጠረ እና በጀት ስለሌለው ባዛር ላይ የተሳተፉት ለድንኳን ኪራይና ጥበቃ፤ እንዲሁም፣ ምንም እንኳን ወቅቱ ሰሙነ-ህማማት በመሆኑና ዘፈን አላስፈላጊ በመሆኑ ባይጠቀሙም የዲጄ ወጪዎችን በራሳቸው ሸፍነው ነው። ይሄን ወጪ የሚሸፍን ሁለት ሺህ ብር መክፈል ያቃታቸው ነጋዴዎች በዘንድሮ የትንሳኤ በዓል አልተሳተፉም። ማርና ቅቤ አምራቹና አቅራቢው ሙሉ ቀን መንግስት ይሄን ወጪ መሸፈን ባለመቻሉ አልፈረዱም። ሌሎች አገሮች ኢንዱስትሪያቸውን እያስፋፉ ቢሆንም እኛ አገር በጀቱ እንደሚታየው ወንድም በወንድሙ ላይ ለሚከፍተው ጦርነት እየዋለ መሆኑን ዋቢ ያደርጋሉ። በዚህ ውስጥ ነጋዴው በጭካኔ በወገኑ ላይ የተጋነነ ዋጋ በመቆለሉ ያዝናሉ። በተለይ እንደ ትንሳኤ ያሉ ታላላቅ ኃይማኖታዊ በዓላት ከዕምነቱ አስተምህሮም አንፃር የሰው ልጅ እርስ በእርሱ የሚደጋገፍበት የፍቅር መገለጫ በመሆኑ መጨካከኑ ቢቀር ሲሉም ምክራቸውን በመለገስ ያካፈሉንን ተሞክሮ ይደመድማሉ። መልካም የትንሳኤ በዓል!!!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም