በበዓል ሰሞን ላይ እንደመገኘታችን ዛሬ ስለመስጠት እናወራለን። መስጠት በሕይወት ውስጥ እጅግ ሀይል ካላቸው ነፍሳዊ ፍሰሀዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። በእያንዳንዳችን ህላዊ ውስጥ የደመቁ ሕይወቶች፣ የፈኩ ትላትናዎች በመስጠት የተዋቡ ናቸው። እግዜር ሲስቅ ያየው አለ? እግዜር ሲስቅ ማየት ካሻችሁ እጆቻችሁ ለመስጠት ዘርጉ፣ ልቦቻችሁን ለፍቅር ክፈቱ መስጠት እግዜርን ከምናስቅበት ሰውኛ ጸጋችን ውስጥ ፊታውራሪው ነው። መስጠት በብዙ ፌስታና ደስታ ነፍሳችንን ከነውር የምንሸሽግበት እግዚአብሔራዊ ጥጋችንም ነው። በብዙ ነገር ስቀን ሊሆን ይችላል፣ በብዙ ነገር ረክተንና ደስ ብሎን ሊሆን ይችላል፣ በብዙ..በጣም በብዙ ነገር ሀሴት አድርገን ይሆናል፤ እመኑኝ በመስጠት ከምናገኘው ደስታ ጋር ሲወዳደር የእስካሁኑ ሳቃችን ምንም ነው። የሰሞኑን ድርብ በዓል ምክንያት በማድረግ እጆቻችንን ለመስጠት መዘርጋት ማስለመድ አለብን። መስጠት ወቅታዊ ጉዳይ አይደለም። በሕይወት እስካለን ድረስ መስጠት አብሮን ሊኖር የሚገባው አንዱ የኑሮ ዘይቤአችን መሆን አለበት። እንደ ኢትዮጵያዊነት ስናየው ደግሞ መስጠት ከትላንት ይዘነው የመጣነው መገለጫችን ሆኖ እናገኘዋለን።
ስንሰጥ በዓልና ምክንያት እየፈለግን የምንሰጥ ከሆነ እርሱ መስጠት አይባልም። እውነተኛ መስጠት ከእያንዳንዱ ማለዳችን ጋር አብሮ የሚነቃ ሲመሽም አብሮን የሚያንቀላፋ ሰውኛ ባህሪያችን ነው። እጆቻችን ለዛሬውም ሆነ ለነገ ሕይወታችን የጽድቅ መንገድ ናቸው። በመስጠት ያተረፉ በርካታ ነፍሶችን አውቃለሁ። በመስጠት ውስጥ ኪሳራ የለም። እንዳውም እላለሁ የዚህ ዓለም እድለኛ እጆች የሚሰጡ እጆች ናቸው። የሚሰጡ እጆች ባዶአቸውን አይመለሱም ብዙ ትርፍን ይዘው ነው ወደ ስፍራቸው የሚመለሱት። በደግነት በፈጣሪና በእኛ መካከል ያለ ዘላለማዊ ድልድያችንን እንገንባ። በሕይወታችን ብዙ ነገር ላይ ያልተሳካልን ሰዎች አለን። ደስታ አጥተን በምሬት የምንኖርም ሞልተናል። በዛው ልክ ደግሞ በደስታና በምስጋና የሚኖሩ በርካታ ሰዎችን እናውቃለን። በነዚህ ሁለት ነፍሶች መካከል የተፈጠረ የኑሮ ልዩነት የሕይወትን ሚስጢር ባለመረዳት የመጣ ነው።
በአሁኑ ሰዓት ሕይወትን በደስታ የሚኖሩ ሰዎች በመስጠት የሚኖሩ ናቸው። በተቃራኒው ደግሞ በሕይወታቸው ደስታን አጥተው የሚኖሩ እነሱ በጎነትን ከልባቸው ውስጥ ያጎደሉ ናቸው። ልባችንን፣ ቤታችንን በአጠቃላይ ሕይወታችንን ለሌሎች እናጋራና በኑሯችን ውስጥ የሚመጣውን ተአምር ብናይ ደስ ይለኛል። መስጠት የተአምራቶች መገኛ ነው። በኪሳችን ብዙ ገንዘብ ይዘን፣ በቤታችን በአካውንታችንም ውስጥ ብዙ ንብረት ሞልቶን መስጠትንና ማካፈልን ካላወቅን ደስታ የራቀን ሰዎች ነው የምንሆነው። ብዙ ነገራችን ልክ የሚመጣው በሚሰጡ እጆቻችን በኩል አልፎ ነው። በክርስቲያኑም በሙስሊሙም ዘንድ በድምቀት በሚከበር በዓል ላይ እንገኛለን። በዚህ በዓል ላይ ደግሞ እኛ ሁሉን አግኝተን በደስታና በፍሰሀ ስናሳልፍ ምንም የሌላቸው ብዙ ወገኖች ይኖራሉና እነሱንም እያሰብን በጋራ ማሳለፉ የተሻለ ደስታን ይፈጥርልናል ብዬ አስባለው። መስጠት የዚህ ዓለም ትልቁ የበረከት መገኛ ነው። ከትላንት እስከዛሬ ዓለም ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ፤ መስጠት ከመቀበል በላይ ኃይል እንዳለውና በሰጠነው ልክ ወደ ሕይወታችን የሚመጡ በርካታ የበረከት ትሩፋቶች አሉ።
ይሄ ብቻ አይደለም መስጠት በአሁኑ ሰዓት አደገኛ በሽታዎችን እየፈወሱ ካሉ መድኃኒቶች ውስጥ አንዱ ነው። ደስተኛና እድሜአቸው ከመቶ ዓመት በላይ በሆኑ እድሜ ባለጸጋ አዛውንቶች ላይ በተደረገ ጥናት ሁሉም እድሜ ባለጸጋ አዛውንቶች ባለፈ ሕይወታቸው ሰጪና የመልካም ሰውነት ባለቤት እንደሆኑ ተረጋግጧል። ከሁሉም ከሚበልጠው ከመስጠት ጎለን በሕይወታችን የምናሳካው ህልምና ራዕይ የለም። ብዙዎቻችን ከመስጠት ይልቅ መቀበል ላይ ያተኮርንን ነን። እጆቻችንን ለመስጠት ከመዘርጋት ይልቅ ለመቀበል የዘረጋን ነን። ብዙዎቻችን መስጠት የሚያስገኘውን ሕይወታዊ በረከት አናውቀውም። ሩጫችን ሁሉ በመቀበል ለማትረፍ፣ በመቀበል ለማሸነፍ ነው። ነገር ግን መቀበል አሸናፊ አያደርግም። ማሸነፍ ያለው በመስጠት ውስጥ ነው። የሚሰጡ እጆች ብሩካን ናቸው። የሚሰጡ ልቦች አሸናፊዎች ናቸው። የሚሰጡ ነፍሶች ደስተኞች ናቸው። ምንም የሌለውን አንድ ድሀ ስናስቅ ፈጣሪን እንዳሳቅን መቁጠር አለብን። ምንም የሌለውን አንድ ምስኪን ስንረዳ ለፈጣሪ እንዳደረግን በማሰብ መርዳት አለብን። የዚህ ዓለም ስኬትና ውድቀታችን ለሌሎች በምንሆነው ልክ የተሰፈረ ነው እላለሁ። የሚሰጡ እጆች አያጡም። የሚሰጡ እጆች በበረከት የተከበቡ ናቸው። የሚሰጡ እጆች በብርሃን ያሸበረቁ አምላካዊ ጸዳሎች ናቸው። በብርሃን መከበብ ካሻችሁ በሕይወታችሁ ደስተኛና ጤነኛ ሆናችሁ ለመኖር ከፈለጋችሁ ከመቀበል ይልቅ መስጠትን ልመዱ።
ሕይወትን በብዙ ነገር ላይ አልተረዳናትም እላለሁ። አንዳንዶች ሰርቀውና ከድሀ ላይ ነጥቀው ህልማቸውን ለማሳካት የሚሮጡ ናቸው። በክፋትና በተንኮል ሌሎችን እየጎዱ አንደኛ ለመሆን የሮጡም ሞልተዋል። በሌሎች ላይ ግፍና በደልን በማድረስ በብልጠት ለማሸነፍ የሚሞክሩም ሞልተዋል። ይሄ ሁሉ ስህተት ነው። ይሄ ሁሉ ሩጫችን እኛን ከመጉዳትና ጠልፎ ከመጣል ባለፈ የሚዘይድልን ነገር የለም። አሸናፊነት የሚገኘው ሌሎች እንዲያሸንፉ ባገዝናቸው ሰዓት ነው። የዚህ ዓለም ስኬታማ ሰዎች ሌሎች ስኬትን እንዲያገኙ የለፉ ናቸው። የዚህ ዓለም ፊተኞች ሌሎች እንዲታዩ ከኋላ የቆሙ ናቸው። ውስጣችን እውነት ካለ፣ በልባችን ውስጥ መልካምነት ካልጎደለ ከኋላ ብንሆን እንኳን እናሸንፋለን። ፈጣሪ ሰማይና ምድርን ሰውና ፍጥረቱን ሲፈጥር የሕይወትን ምስጢር ይፈታ ዘንድ የሰውን ልጅ በእውቀት እንዲኖር በማስተዋል ፈጥሮታል። ይህ እውቀታችን ደግሞ ያለው ልባችን ላይ ነው። ልብ ለምንም ነገር መሪ ነው። መሪያችን በጎ ከሆነ ጎዳናችንም በጎ ይሆናል። ሁሉ ነገራችን የልባችን ውጤት ነው። በልባችን ውስጥ ባለው ጥሩነት ልክ ነጋችን ይገነባል ማለት ነው። በሕይወት ሳለን በምንኖረው በእያንዳንዱ ቀናችን ውስጥ ለሌሎች የሚሆን በጎ ልብ ያስፈልገናል። ሌሎች እንዲስቁ፣ ሌሎች እንዲሳካላቸው እስካላደረግን ድረስ ስኬታችን ትርጉም አይኖረውም። ለሌሎች ባለን መልካምነት ልክ ነው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚሆነው። ለሌሎች ባለን ፍቅር ልክ፣ በዙሪያችን ላሉ በምንሰጠው መስጠት ልክ አምላክ እንዳይመለስ ሆኖ ወደ ሕይወታችን ይመጣል።
ኢትዮጵያ አገራችን የድሆች አገር ናት። በዙሪያችን የእኛን እርዳታ የሚፈልጉ በርካታ ወገኖች አሉን። የእለት ጉርስ አጥተው ጎዳና የወደቁ፣ ወላጅ የሌላቸው ህጻናት፣ ጧሪ ያጡ አዛውንቶች ሞልተዋል። በበሽታ የሚሰቃዩ፣ በየሆስፒታሉ ጠያቂ ያጡ ህመምተኞች እኛን የሚጠብቁ ናቸው። መማር እየፈለጉ ያልቻሉ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ ያጡ፣ እኛ በማናውቀው በብዙ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ያሉ ወንድምና እህቶች አሉን። እኚህ ወገኖቻችን የእኛን መልካም ልብ በመጠበቅ ላይ ናቸውና አይዧችሁ ልንላቸው ይገባል። ምናልባት ሁሉ ያለን ባለጸጋ ስለሆንን ድህነት ምን ማለት እንደሆነ ላይገባን ይችላል። ማጣት የሚያስከፍለውን ዋጋ ላናውቀው እንችል ይሆናል። ግን ደግሞ የሌሎችን ህመም እንደመታመም ባለጸግነት የለም። የሌሎችን ስቃይ እንደመሰቃየት፣ የሌሎችን መከራ እንደመጋራት ደስታ የለም። በሕይወቴ እውነት ናቸው ብዬ ከተቀበልኳቸው እውቀቶቼ ሁሉ መስጠት የደስታ ጥግ ነው የሚለው ይበልጣል። በመስጠት ሞታችንን እንግደለው። በመስጠት ከእርኩሰታችን እንንጻ። በደግነት ነጋችንን እንስራ።
ሀሳባችሁ ምንድነው? ማደግ? መለወጥ? በስራችሁ፣ በትምህርታችሁ ስኬታማ መሆን? ወይስ ሌላ ጥሩ ነገር? የሆነው ይሁን በሕይወታችሁ የምትፈልጉት ነገር ሁሉ ልባችሁ ውስጥ ባለው ደግነት ልክ የእናንተ የሚሆን ነው። እድሉን ካገኛችሁ አሁን ላይ እናንተ የምትደነቁባቸውን በውጭም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ ሰዎችን መርምሩ፤ ሕይወታቸው በመስጠት የተሞላ ሆኖ ካላገኛችሁት ምናለ በሉኝ። ከትላንት እስከዛሬ ሲያስገርሟችሁ የነበሩ እነሱ በመስጠት የከበሩ፣ በደግነት የለመለሙ ናቸው። ምንም ነገራችሁን በክፋት ውስጥ ሆናችሁ አትፈልጉት። ምርጡ ነገራችን ያለው በምርጡ ልባችን ውስጥ ነው። ከመስጠት ርቀን ባለጸጋ ሆነን ይሆናል። በውሸትና በማጭበርበር የፈለግንበት ደርሰን ይሆናል። የድሀውን ጩኸት ላለመስማት ጆሮአችንን ደፍነን ይሆናል፤ እመኑኝ በዚህ መንገድ ሀብታችንን አንበላውም። እግዚአብሔር የሌለበት ሀብት፣ በመስጠትና በደግነት ያልተገኘ ተድላ አጥፊ እንጂ አልሚ አይደለም። የአለማችን ባለጸጋዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ ለጋሾች ናቸው። አሁን ላይ በስኬታቸው ዓለም ያጨበጨበላቸው ግለሰቦች እነርሱ ሰጪዎች ናቸው።
እኛም ለሌሎች የሚሆን መልካም ነገር ከሌለን ህልማችን አይሰምርም። ህልማችንን፣ ስኬታችንን የሚፈጥረው ደግ ልባችን ነው። መንገዳችን ሁሉ ወደ ጽድቅ ይሁን። ለሚለምኗችሁ መስጠትን አታቁሙ። በሰጣችሁ ቁጥር እግዚአብሔር ወደ እናንተ እየመጣ እንደሆነ ልብ በሉ። ቤታችሁን ለድሀ በከፈታችሁ ቁጥር ላትሞቱ ህያው ሆናችሁ እየኖራችሁ ነው። ደግ ልብንና ቀና መንፈስን በተላበሳችሁ ቁጥር ራሳችሁን በዓለም ካለው የሰው ልጅ ሁሉ ድንቅ እያደረጋችሁት ነው። መልካም በሆናችሁ ቁጥር የምትፈልጉትን እያገኛችሁ ነው። የዚህ ዓለም እውቀትና ጥበብ በመስጠት ውስጥ ተደብቋል። እውቀትና ጥበባችሁን የትም አትፈልጉት በመልካምነታችሁ ውስጥ አለና። ሰዎች ደስታን ፍለጋ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። የደስታ ስፍራው በመስጠት ውስጥ ነው። እጆቻችሁን መስጠት አስለምዷቸው። አይኖቻችሁ ወደ ድሀ እንዲያዩ፣ ጆሮዎቻችሁ የሚስኪኑን ጩኽት እንዲያደምጡ፣ እግሮቻችሁ ወደ ችግረኞች እንዲሄዱ አሰልጥኗቸው። ካለን ላይ መቁረስን፣ ካለን ላይ ማካፈልን እንልመድ። ካለን ላይ ብቻ አይደለም ከሌለን ላይም መስጠትን እንልመድ። ደሞ ከሌለ ላይ መስጠት ይቻላል እንዴ? እንዳትሉ። አዎ ይቻላል.. እንዳውም እውነተኛ መስጠት ከሌለ ላይ መስጠት ነው። ልብ ለመስጠት ከተዘጋጀ የሚሰጠው አያጣም።
ቤታችሁ ለድሀ ሁሌም ክፍት አድርጉ። በስራና በተግባር እግዚአብሔርን ምሰሉ እንጂ እንዳው ዝም ብላችሁ አታስመስሉ። ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ በፍርድ ቀን ሀጣንን ‹ተርቤ አላበላችሁኝም፣ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም፣ ታርዤ አላለበሳችሁኝም’ ብሎ በረከትን እንደሚነሳቸው ይነግረናል። እነሱም ‹ጌታ ሆይ ተርበህ አይተን መች ዝም አልንህ? ተጠምተህ አይተን መች አናጠጣም አልንህ? ታርዘህ አይተን መች አናለብስም አልን? ታስረህ አይተንህ መች ሳንጠይቅህ ቀረን?’ ሲሉት፤ እርሱም ‘እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ለሚያንሱ ለእነሱ ብታደርጉ ለኔ እንዳደረጋችሁት እቆጥረዋለሁ’ ነበር ያላቸው። እንግዲህ በፍርድ ቀን ከምንጠየቅባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የመልካምነት ስራ ነው ማለት ነው። ምን አላችሁ ሳይሆን ምን ሰራችሁ ነው የምንባለው። መልካም ልቦች በእግዚአብሔር ፊት ብርሃን ለብሰው ይቆማሉ። በምድር ላይም ሲኖሩ በብዙ ደስታና በብዙ ፍሰሀ ተከበው ይሆናል። በሕይወታችሁ ውስጥ ርህራሄን አስገቡ። እግዚአብሔርን የምታገኙት በደግነት ነው። የፈጣሪ የምትሆኑት በርህራሄ ነው። በተለይ የኮሮና ቫይረስ በተስፋፋበት፣ የኑሮ ውድነቱ ሰማይ በደረሰበት፣ ብዙ ሞቶችና ብዙ መፈናቀሎች በበዙበት በዚህ አስጨናቂ ጊዜ ላይ ከወገኖቻችን ጎን በመቆም አጋርነታችንን ማሳየት ግድ ይለናል።
በፍቅርና በደግነት እግዚአብሔርን የምንፈልግበት ጊዜ አሁን ነው። በመስጠት በማካፈል ሕይወታችንን በበረከት የምንሞላበት ሰዓት ላይ ነን። በደግ ልባችን የሌሎችን መከራ ለመካፈል አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው። እዛም እዚም የሚጮሁ የተማጽኖ ድምጾች እየበረከቱ ነው። የተሰበሩ ልቦች ያዘኑ ነፍሶች በዙሪያችን አሉ። እንድረስላቸው። መኖር ዋጋ የሚኖረው፣ ሕይወት ትርጉም የሚያገኘው ለሌሎች የሚሆን በጎ ነገር ሲኖረን ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም