በጀርመን የጸደይ ወራት ከሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች ትልቁ የሃምቡርግ ማራቶን ነው። የተጀመረው እአአ ከ1986 የሆነው ይህ የማራቶን ውድድር፤ በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው የጎዳና ላይ ውድድሮች መካከል አንዱ ነው።
በዘንድሮው ነገ በሚካሄደው በዚህ ሩጫ ላይም 25ሺ ሰዎችን በማካፋል እንደሚካሄድም የውድድሩ አዘጋጆች አስታውቀዋል። በውድድሩ ላይ ከመላው ዓለም የተወጣጡ በርካታ አትሌቶች ተካፋይ ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ደግሞ አሸናፊ ይሆናሉ የሚል ቅድመ ግምት አግኝተዋል።
ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በብዛት ከሚካፈሉባቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያኑ በውጤታማነትም ውድድራቸውን የሚያጠናቅቁበት ነው። ለዚህም ማሳያ ከሚሆኑት መካከል በሴቶች የቦታውን ክብረወሰን በኢትዮጵያዊቷ ጠንካራ አትሌት መሰለች መልካሙ እስካሁን መያዙ ነው። አትሌቷ ክብረወሰኑን ያስመዘገበችው እአአ በ2016 ሲሆን፤ በወቅቱ የገባችበት 2:21:54 የሆነ ሰዓት እስካሁን ሊሻሻል አልቻለም።
በዚህ ውድድር ላይም ተሳታፊ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የተሻለ ሰዓት በማስመዝገብ ያጠናቅቃሉ በሚል ከሚጠበቁት መካከል አንዷ በግማሽ ማራቶን የምትታወቀው አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ናት። በጎዳና ላይ ሩጫዎች ፈጣን ሰዓቶችን በማስመዝገብ የምትታወቀው አትሌቷ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በሃምቡርግ የማራቶን ውድድሯን ታደርጋለች፤ ይሁንና የተሻለ
የአሸናፊነት ግምት ካገኙት አትሌቶች መካከል ቀዳሚዋ ሆናለች።
በግማሽ ማራቶን ውድድሮች ስኬታማ የሆነችው አትሌቷ፤ ርቀቱን 1:03:51 የሆነ ሰዓት በመሮጥ የዓለም ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት የግሏ ነው። ከሁለት ወራት በፊት በ10 ኪሎ ሜትር ሩጫ 24 ደቂቃ ከ29 ሰከንድ ከ14 ማይክሮ ሰከንዶች በመሮጥ የዓለም ክብረወሰኑን በእጇ ማስገባቷ ይታወሳል። በታላቁ የኢትዮጵያ ሩጫ ላይም ውድድሩን በቀዳሚነት ማጠናቀቋ አይዘነጋም።
በአሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ የምትሰለጥነው አትሌቷ ግማሽ ማራቶንን ከ10 ጊዜያት በላይ በመሮጥና አሸናፊም በመሆን ከፍተኛ ልምድ አላት። ይህም አትሌቷን ለተሻለ ተፎካካሪነት እንድትጠበቅ አድርጓታል። የውድድሩ አዘጋጆችም የመጀመሪያ ውድድሯን በስኬት የማጠናቀቅ አቅም ያላት አትሌት ናት ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
አትሌቷ ውድድሩን አስመልክቶ በሰጠችው አስተያየትም ‹‹የማራቶን ሩጫዬን በሃምቡርግ በመጀመሬ እጅግ ደስታ ይሰማኛል። በዚህ ውድድር ለመሳተፍ ብቻም ሳይሆን ክብረ ወሰን የሆነ ሰዓት ለማስመዝገብ እፈልጋለሁ›› ብላለች።
በወንዶች በኩል ደግሞ እአአ በ2017 የሀምቡርግ ማራቶን አሸናፊ የነበረው አትሌት ጸጋዬ መኮንን ተካፋይ እንደሚሆን የውድድሩ አዘጋጆች አረጋግጠዋል። አትሌቱ አሸናፊ በሆነበት ውድድር ያስመዘገበው 2:07:26 የሆነ ሰዓት ይሁን እንጂ፣ እአአ በ2014 የዱባይ ማራቶን የገባበት 2:04:32 የሆነ ሰዓት ምርጡ ነው። የ26 ዓመቱ ወጣት አትሌት በቦታው ያለውን ልምድ ተጠቅሞ የውድድሩ አሸናፊ አሊያም ተፎካካሪ ያደርገዋል የሚል ግምት አግኝቷል።
የበርሊን ማራቶን ቻምፒዮኑ ጉዬ አዶላም የዚህ ውድድር ተካፋይ ሲሆን፤ ሁለቱ አትሌቶች አሸናፊዎች እንደሚሆኑ በስፖርት ቤተሰቡ ይጠበቃሉ። ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱም አትሌቶች ከ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ በታች የሆነ ሰዓት ስላላቸው ነው። ያለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶን አሸናፊ አትሌት ጉዬ አዶላ 2:03:46 የሆነ ፈጣን ሰዓት አለው። አትሌቱ ከጉዳት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ እና ሌሎች ምክንያቶች ጋር በተያያዘ ለሁለት ዓመታት ከውድድር ርቆ ቆይቶ በተካፈለበት ውድድር ነበር ውጤታማ የሆነው። በምርጥ አቋም ላይ የሚገኘው አትሌቱ በሃምቡርግ ሲሮጥ ይህ የመጀመሪያው ቢሆንም ለተፎካካሪዎቹ ፈተና እንደሚሆን ተገምቷል።
እአአ 2019 ላይ ቫሌንሺያ ማራቶንን 2:03:51 በሆነ ሰዓት የሮጠው ክንዴ አጣናውም በውድድሩ ሌላኛው ተጠባቂ ነው። የፓሪስ ማራቶንን 2:04:48 በሆነ ሰዓት የሮጠው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አበበ ደገፋም በውድድሩ አንደሚሳተፍ ታውቋል። የጎረቤት ሃገራት ኬንያ፣ ኤርትራ እና የኡጋንዳ አትሌቶችም የኢትዮጵያዊያኑ አትሌቶች ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 /2014