ትንሹ ልጅ ያደረበት መኝታ አልተመቸውም። ደጋግሞ ይገላባጣል። ማምሻውን ሲሰማው የቆየው ጉዳይ አሁንም ከስጋት እንደጣለው ነው። ሰዎቹ በየደቂቃው የአባቱን ስም እያነሱ ያወጋሉ። የሚጠሩት የገንዘብ መጠን ደግሞ ከዚህ በፊት ሰምቶት አያውቅም። ልጁ ውስጡ እየተረበሸ፣ ሆዱ እየተላወሰ ነው። ጥቂት ቆይቶ ምን እንደሚገጥመው አያውቅም። ክፉኛ ተጨንቋል።
ትንሹ ልጅ ሰዎቹ ምሽቱን ከቤት እንደሚያሳድሩት ገምቶ ነበር። እንዳሰበው አልነሆም። ዛሬም ከቤቱ ውጭ ካለ የጭድ ክምር ውስጥ እንዲያድር ፈርደውበታል። ከቀናት በፊት በወላጆቹ ቤት በፍቅር የሚያዩት ብዙ ዓይኖች ነበሩ። ያሻውን ቢጠይቅ ይደረግለታል፣ ያማረውን ቢበላ ከልካይ የለውም። ዛሬ ግን ይህ ሁሉ ታሪክ ሆኗል። የልጅ አንጀቱ ተላወሰ። ዓይኖቹ በትኩስ ዕንባ ተሞሉ።
ትንሹ ልጅ አጠገቡ ያሉት ሰዎች ከአንድ ሰው ጋር በስልክ ሲያወሩ ሰምቷል። ደጋግመው የሚጠሩትን ግለሰብ በደንብ ያውቀዋል። ሰውዬው ከነዚህ ሰዎች ጋር በምን እንደተዛመደ አልገባውም። ስሙ ሲነሳ ሁሉ አብሮት የሚጠራው የገንዘብ መጠን አሁንም እያስደነገጠው ነው። ልጁ መሸቶ በነጋ ቁጥር ዓይኖቹ መንከራተት ያዙ፣ ቤተሰቦቹ በውስጡ ውለው ቢያድሩ ክፉኛ ናፈቁት። የሚወረወርለት ቁራሽ እንጀራ የእናቱን እጅ ቢያስታውሰው መላልሶ ሆድ ባሰው።
ልጁ ዕንባ እየተናነቀው ጆሮዎቹን ጥሎ ማዳመጥ ያዘ። ሰዎቹ አሁንም ከሰውዬው ጋር በስልክ ያወራሉ። በወሬያቸው መሀል የአባቱ ስም ሲጠራ የሰማ መሰለው። አዎ! አልተሳሳተም። የገንዘብ መጠኑ ጭምር እየተብራራ ነው። ይህኔ የልጅነት አይምሮው ፈጥኖ መንቃት ያዘ። አሁን ነገሩ ሁሉ ገባው። እሱ በሶስቱ አጋቾች እጅ የወደቀበት ምክንያት የገንዘብ ጉዳይ ነው።
ሰዎቹ ልጅን አግተው አባትን ገንዘብ እየጠየቁ ነው። ለዚህ ድርጊታቸው የሚተባበራቸው አንድ ሰው ከጎናቸው አለ። ታጋቹ ህጻን ንግግራቸውን በጥንቃቄ ማዳመጡን ቀጥሏል። ደጋግመው የሚጠሩት ግለሰብ የአባቱ የቅርብ ጓደኛና የሰፈራቸው ትልቅ ሰው ነው። የልጅነት ልቡ በሰውየው ላይ ተስፋ አደረገ። ካለበት፣ ችግር ከታገተበት ዓለም ፈጥኖ እንዲያወጣው ተመኘ።
ታጋቹ ልጅ ጥቂት ቆይቶ ለጆሮው የደረሰው መልዕክት ክፉኛ አስደነገጠው። ሰውየው እንዳሰበው አይነት አልሆነም። ሰዎቹ ለሚያቀርቡለት ጥያቄ አስደንጋጭ መልስ እየሰጠ ነው። እሱ እንደተረዳው ቃል የተገባላቸው ገንዘብ በተባለው ጊዜ ከእጃቸው አልደረሰም።
‹‹ፈላው›› የተባለውና ጓደኞቹ ሰውዬውን ምን ማድረግ እንዳለባቸው እየጠየቁት ነው። ሰውዬው ብሩን አባትዬው ካላመጣ ልጁ መገደል፣ አልያም ለሌሎች መሸጥ እንዳለበት ትዕዛዝ አስተላልፏል። ታጋቹ ህጻን የስልክ ምልልሱን አንድ በአንድ አዳመጠ። ተደብቆ ካለበት የጭድ ክምር የሚያወጡትን እጆች እየናፈቀም በሀሳብ ነጎደ።
ከቀናት በፊት…
ምዕራብ ጎጃም ዞን ዱርቤቴ ከተማ። በማለዳው ፈንጥቃ የወጣችው ጸሀይ የዕለቱን ውሎ በድምቀት ያስጀመረች ይመስላል። ሁሌም በዚህ ሰአት ጉዳይ ያላቸው ሁሉ ወዳሰቡት ይተማሉ። ገበያተኞች፣ መንገደኞች፣ ተማሪዎች፣ በየተራ ከተማዋን ይሸፍኗት ይዘዋል። ህጻን ሀብታሙ ታዬን በጠዋት የቀሰቀሰው የትምህርቱ ጉዳይ ነበር። እሱም እንደ እኩዮቹ ቁርሱን በልቶ፣ ደብተሩን ይዞ ወደትምህርትቤት መሄድ አለበት።
ሀብታሙ ሁሌም ማለዳ በዚህ ሰአት ወደትምህርትቤት ለመሄድ ከጓደኞቹ ይገናኛል። የዕለት ትምህርቱን አጠናቆ ከቤቱ ሲደርሰ ወላጆቹ በስስት እያዩ ይቀበሉታል። ስለነገው ታላቅ ተስፋን የያዙበት ትንሹ ልጃቸው የቤታቸው በረከት ነው። ለትምህርቱ ይጨነቃሉ፣ ለነገው ማንነቱ ያስባሉ።
ሀብታሙና ባልንጀሮቹ ሰፈራቸውን አቋርጠው ትምህርትቤት የሚሄዱት በአንድነት ነው። እኩያሞቹ አንገት ለአንገት ተያይዘው ትምህርትቤት ሄዶ መመለስ የዘወትር ልምዳቸው ነው። የዛን ቀንም ሀብታሙ ከእነሱ ጋር በአንድ ተራምዶ ትምህርትቤቱ ግቢ ደርሷል።
ጓደኛሞቹ ወደየክፍላቸው ከመሄዳቸው በፊት አንዲት ባጃጅ አጠገባቸው ደርሳ መቆሟን አስተዋሉ። ሁሉም ዓይናቸውን ተክለው በየተራ ከውስጥ የሚወጡትን ሰዎች ተመለከቱ። ሰዎቹ ጓደኛሞቹን አልፈው ወደ ሀብታሙ ቀረቡና ይዘውት መሄድ እንዳለባቸው አሳወቁት። ከአባቱ እንደተላኩ የተነገረው ሀብታሙ ጓደኞቹን ተሰናብቶ ወደ ባጃጁ ወንበር አመራ። አፍታ ሳይቆይ ባጃጁ ፍጥነቱን ጨምሮ ወደፊት ተፈተለከ። ጓደኛሞቹ የባልንጀራቸውን መራቅ እያስተዋሉ እርስ በርስ ተያዩ።
የትምህርቱ ሰአት ተጠናቆ ልጆቹ ወደ የቤታቸው ለመሄድ ተፈላለጉ። ሁሉም ጠዋት ከእነሱ የተለየውን ጓደኛቸውን አልረሱም። ከበርካታ ተማሪዎች መሀል በዓይናቸው ቃኙት። እንደቀድሞው ሀብታሙን በቶሎ አላዩትም። ወደ ክፍሉ ተመልሰው በወጉ ፈለጉት። አላገኙትም።
ልጆቹ ክፉኛ ተጨነቁ። ጠዋት ያዩዋቸው ሰዎች መልሰው እንዳላመጡት ቢገባቸው ወደሰፈር ለመሄድ መንገድ ጀመሩ። ሰፈር የደረሱት ባልንጀሮች የሀብታሙን ጉዳይ ለማወቅ ወላጅ አባቱ ዘንድ መሄድ ነበረባቸው። አባትየውን እንዳዩት ሀብታሙ ወደ ቤት መጥቶ እንደሆን ጠየቁ። አባት ልጆቹ የሚናገሩት አልገባ ቢለው ከልብ ደነገጠ። ልጁ ዛሬ ማለዳ ከእነሱ ጋር ወደ ትምህርትቤት መሄዱን ያውቃል። ጉዳዩን እንዲያብራሩለት ጠየቀ። ሀብታሙን የማይታወቁ ሠዎቹ በባጃጅ ይዘውት መሄዳቸውን ገለጹለት።
አባት ይህን ሲሰማ በእጅጉ ደነገጠ። ልጁን ማንም በባጃጅ ይዞት እንደማይሄድ ያውቃል። ውስጡ ጥርጣሬና ድንጋጤ ገባው። እየተጣደፈ ወደ ልጁ ትምህርትቤት ገሰገሰ። መምህራን በተማሪያቸው መጥፋት እንደተደናገጡ አገኛቸው። ጊዜ አልፈጀም። ጉዳዩን ለህግ ለማሳወቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመራ።
አባት ጉዳዩን ለህግ እንዳሳወቀ መላው ቤተሰብ በጭንቀት ተዋጠ። የአካባቢው ነዋሪ የህጻኑ መጥፋት በእጅጉ አሳሰበው፣ ወዳጅ ዘመድ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ፍለጋውን ያዘ። አባት የአካባቢውን ጫካ፣ ጉድባና ጉድጓዱን በፍለጋ አሰሰ። መራዊና፣ ቢኮሎ ከተባሉ ስፍራዎች ደርሶም ‹‹ልጄን ያያችሁ›› ሲል ተማጸነ። ታዳጊውን ተማሪ ‹‹አየነው ›› የሚል አላገኘም። እየተጨነቀ ከአንድ ገዳም ገባ፤ ልጁን በሰላም ያገኘው ዘንድም እያነባ ተሳለ።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ የአባትዬው የእጅ ስልክ አንቃጨለ። እየተጣደፈ አፈጠጠበት። ከዚህ በፊት የሚያውቀው ቁጥር አይደለም። እጁ እየተንቀጠቀጠ ፈጥኖ አነሳው። ከወዲያኛው ጫፍ አንድ ሰው ጎርነን ባለ ድምጽ ‹‹ ሀሎ ›› ሲል ተሰማው።
ሰውየው ጊዜ ያለው አይመስልም። ጥርት ብለው በሚሰሙ ቁጥብ ቃላቶች መልዕክቱን በሚገባ አደረሰ። አባት የሚሰማውን እውነት ማመን አልቻለም። ደዋዩ ስምንት መቶ ሺህ ብር ከከፈለ ህጻን ልጁን መረከብ እንደሚችል እየነገረው ነው። አባት ጉዳዩን እሰኪያስብ ጊዜ አልተሰጠውም። ስልኩ በፍጥነት ከጆሮው ተዘጋ።
የደቡብ አቸፈር ወረዳ ፖሊስ ከልጁ አባት የደረሰውን የስልክ መልዕክት እንደመረጃ ይዞ ፍለጋውን ቀጠለ። ፖሊስ ከ‹‹አፋልጉኝ›› ማስታወቂያው ጋር ተያይዞ ያልተገባ ጥቅም የማግኘት ፍላጎት እንደሚኖር ገምቷል። ‹‹አገኘነው›› ብለው የሚደውሉ ሁሉ ትክክል ናቸው ብሎ አያምንም። አባት ይህን በማወቁ ልቡ ለሁለት ተከፍሏል።
በማግስቱ የልጁ አባት ስልክ አቃጨለ። ፈጥኖ አነሳው። የትናንቱ ደዋይ ነበር። ሰውየው ቀድሞ ያነሳለትን ጉዳይ ሳያዛባ ደገመለት። አባት ቃሉን ሰምቶ በትህትና ለማናገር ሞከረ። እነሱ የጠየቁትን ያህል ገንዘብ እንደሌለውና በእጁ ያለውን ሁሉ እንደሚሰጥ ቃል ገባ።
ደዋዩ ይህን ሲሰማ ያባብለው ያግባባው፣ ያዘ። እሱና ጓደኞቹ በግል እንደማያውቁት፣ ልጁን አሳልፎ የሰጣቸው የቅርብ ጎረቤቱና ወዳጁ መሆኑን በእርግጠኝነት ነገረው። አባት ግራ ተጋባ። በተለይ ሰውዬውን ይቅርታ እንዲጠይቅ መጠየቁ ይበልጥ አደናገረው። ተረጋግቶ ይህን ያደረገውን ሰው ማንነት ጠየቀ። ደዋዩ ጥቂት ምልክቶችን ጠቅሶ ስልኩን ጠረቀመው።
አውጫጭኝ…
እሁንም የዱርቤቴ ከተማ ነዋሪ በህጻኑ መጥፋት እንደተጨነቀ ነው። ልጁ ባልታወቁ ሰዎች ተወስዷል መባሉ ሁሉንም አሳስቧል። በየጊዜው በስብሰባ እየመከረ። መላምቱን ያስቀምጣል። የሚጠረጥራቸውን እየጠቆመ፣ የአቅሙን ይተባበራል። አንድ ቀን ከተሰብሳቢዎቹ መሀል አቶ ቸኮል የተባለ ወደ ልጁ አባት ቀርቦ ነዋሪውን በስብሰባ ማድከሙ ተገቢ ያለመሆኑን እያነሳ ገሰጸው።
አባት የእንዲህ ባዩ ሰው ንግግር ቢያስገርመው ለምን ሲል ጠየቀ። ቸኮል ከዚህ ቀድሞ የተደወለለትን ስልክ እያስታወሰ የአስጠላፊውን ማንነት በስም ጠርቶ አረጋገጠለት።
ፖሊስ ጠንካራ የምርመራ ቡድን አዋቅሮ ህጻኑን የማፈላለግ ስራውን ቀጥሏል። ስማቸው ሳይታወቅ በምልክት ብቻ የተነገሩትን ተጠርጣሪዎች አድኖ መያዝ ቀላል አልሆነም። የዳንግላ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ገጠሮች የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን በማስረጃ አረጋግጦ ለመያዝ ፈታኝ ትግል ይጠይቃል።
በተደጋጋሚ በእጅ ስልኩ እየተደወለ ዛቻና ማስፈራራት የሚደርሰው አባት ጉዳዩን ለፖሊስና ለሌሎች ቢናገር ልጁን በህይወት እንደማያገኝ ተነግሮታል። አባት ሚስጥሩን ደብቆ ለማቆየት ከራሱ መክሮ በሚሉት ሁሉ ተስማምቷል። በተለይ የልጁን አንገት እንቆርጠዋለን ካሉት ወዲህ ውስጡ በፍርሀት እየራደ ነው። አሁን ዝምታን መምረጡ ለልጁ ህይወት እንደሚበጅ አውቋል። ለማንም ትንፍሽ እንደማይል ቃል ገብቶም ለሚሰጡት ትዕዛዝ ተገዢ ሊሆን እየተዘጋጀ ነው።
መልዕክተኛው…
በሁለቱ ወገኖች መሀል መልዕክት የሚያመላልሰው አቶ ቸኮል በሽምግልና ገብቶ እያደራደረ ነው። ገንዘቡን ከሰባ ሺህ፣ ወደ ስልሳ ሺህ አድርሶም ለሚገባቸው ሰዎች ለማድረስ ቀን ቆርጧል። ገንዘቡን ከአባትዬው ተቀብሎም አራት ሺህ ብር እንዲቀነስለት አድርጓል።
የፖሊሰ እርምጃ …
አባት ገንዘቡን ከፍሎ ልጁን ከተረከበ በኋላ እውነቱን ያወቁት ፖሊሶች ጉዳዩን በዋዛ አልተውትም። በእገታው ተሳትፈው ገንዘብ የወሰዱትን ተጠርጣሪዎች ለመያዝ አሰሳቸውን ቀጠሉ። ለፖሊስ በቂ መረጃ በመስጠት ታላቁን ድርሻ የተወጣው ህጻን ሀብታሙ በእገታ ቆይታው ያስተዋለውንና የደረሰበትን በአግባቡ በማስረዳት ለነገሮች ስኬት መንገዱን ጠረገ።
በአስተዋዩ ታዳጊ ምሪት መንገድ የጀመረው ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን በእጁ ለማስገባት ሰፊ ዕድል አገኘ። ተፈላጊዎቹን ከያሉበት አድኖ በቁጥጥር ስር እንዳዋለም ድርጊቱን እንዲያስረዱት ጠየቀ። ሶስቱ ወጣቶች ስለፈጸሙት ወንጀልና ስለተቀበሉት ጥቅም አልካዱም። ሁሉም በድርጊቱ ስለመሳተፋቸው በቃላቸው አረጋገገጡ። ፖሊስ እነሱ በሰጡት ቃል ብቻ አላበቃም። የድርጊቱን መነሻ በማስታወስ ለውጥኑ ማን እንዳደራጃቸው እንዲነግሩት ጠየቀ።
ሶስቱ ወጣቶች በየተራ በሰጡት ቃል ህጻኑን ለማገት ትዕዛዝ የተቀበሉት ከአባትዬው ጎረቤትና የቅርብ ወዳጅ አቶ ሽታ አወቀ መሆኑን አረጋገጡ። ሰውዬውና የልጁ አባት የአመታት ጎረቤትና የልብ ወዳጆች ናቸው። አብረው በልተው፣ ጠጥተው ክፉ ደጉን ስለማለፋቸው በርካቶች ይመሰክራሉ። ህጻኑ በሚፈለግበት ወቅት ሽታ ከተሰብሳቢዎች መሀል ሆኖ የሚባለውን ሲያዳምጥና ሲታዘብም ነበር።
ፖሊስ አራቱን ተጠርጣሪዎች በእጁ ካስገባ በኋላ በአጋቾቹና በአባትየው መሀል እንደሽማግሌ ሆኖ የማደራደሩንና ገንዘብ የማቀበሉን ስራ የከወነውን አቶ ቸኮል ዋሴን በቁጥጥር ስር አዋለ። ግለሰቡ ጉዳዩን ለፖሊስ ሳያሳውቅ የድርጊቱ ተባባሪ መሆኑ በህግ አስጠይቆታል።ፖሊስ የአምስቱን ተጠርጣሪዎች ቃል በአግባቡ መዝግቦ በእማኞች ፊት አስፈረመ።
ውሳኔ…
አሁን የደቡብ አቸፈር ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን በአግባቡ አጠናቆ ተጠርጣሪዎች በህግ የሚጠየቁበትን አግባብ አመቻችቷል። በበቂ ማስረጃና መረጃ የተጠናከረው የተከሳሶች መዝገብ ወደ ዓቃቤህግ ተላልፎም በችሎት መዳኘት ይዘዋል። የባህርዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድቤት ተከሳሾችን በአካል አቅርቦ የክስ መዝገባቸውን እየፈተሸ የድርጊቱን መፈጸም ከግለሰቦቹ ቃል ሲያረጋግጥ ቆይቷል።
ተከሳሾቹ በቀረበባቸው ህጻንን የማገትና ገንዘብ የመቀበል ወንጀል ጥፋተኞች ተብለዋል። ይህን ማረጋገጫ ተከትሎም ፍርድቤቱ መከላከል እንዲችሉ ዕድል ሰጥቷል። ተከሳሾቹ ወንጀሉን ማስተባበል አልቻሉም። ሁሉም በድርጊቱ ተሳታፊና ተጠቃሚዎች እንደነበሩ በህግ ፊት አረጋግጠዋል።
የባህርዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድቤት ታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት ሲመረምር የቆየውን የተከሳሾቹን መዝገብ አጠናቆ ተከታዩን ውሳኔ አሳልፏል።
1ኛ ተከሳሽ ሽታ አወቀ በአስራ ስምንት አመት ጽኑ እስራትና በሶስት አመታት የህዝባዊ መብት እግድ፡–
2ኛ 3ኛና 4ተኛ ተከሳሾች በመሆን የቀረቡትና የእገታ ወንጀሉን የፈጸሙት ሶስት ወጣቶች እያንዳንዳቸው በአስራ ሰድስት አመት ከአስር ወር እስራት፡–
3ኛ ተከሳሽ አቶ ቸኮል ዋሴ ከህጻኑ አባት ገንዘብ በመቀበል የእገታ ወንጀሉን በማሰፈጸሙ የአስራ ሶስት አመት ጽኑ እስራት እንዲወሰንበት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ በማሳለፍ የክስ መዝገቡን አጠናቋል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 /2014