የተወለዱትና ያደጉት በቀድሞው አጠራር አሩሲ ክፍለ አገር ዴራ አማኑኤል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሲሆን፤ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ዴራ አማኑኤል እንዲሁም አሰላ መለስተኛ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል፡፡ በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በነገረ-መለኮት (ቲዮሎጂ) የሰሩ ሲሆን፤ በአልፋ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህርነት ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፊሎሎጂ፤ ካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ፤ በትምህርት አመራርና አስተዳደር የትምህርት መስኮች ሶስት ማስተርሶችን መስራት ችለዋል፡፡ እንዲሁም ከቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በድህረ- መረቃ ዲፕሎማ ሀገረ በቀል ነገረ-መለኮት እና ሲስተማቲክ ነገረ-መለኮት ተጨማሪ ማስተርስ ማግኘት ችለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአገር ውስጥ ቋንቋ ስነ-ፅሁፍ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡
በደብረሊባኖስ ገዳም ለአስር ዓመት ያህል በትምህርትም በአገልግሎትም የቆዩት የዛሬው የዘመን እንግዳችን፤ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላም በ1999 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት አዘጋጅነት ለአንድ ዓመት ያህል ቀርቦ በነበረው የሚሊንየም አውደ ርዕይ ላይ ለዘጠኝ ወራት አገልግለዋል፡፡ በኋላም በስብከተ ወንጌል አያት ኪዳነ ምህረት፣ ቀበና ኪዳነ ምህረት፣ ቁስቋም ማርያም፣ እየሱስ፣ ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን አገልግለዋል፡፡ ሰወስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅ የንፅፅር ነገረ መለኮት በመምህርና በአሰልጣኝነት ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም ሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በአስተዳዳሪነት አገልግለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የነገረ-መለኮትና የስነልቦና መምህር እንዲሁም፤ ደብረአሜን መርካቶ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን በስብከተ-ወንጌል እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ እኚህ አባት መላከምህረት ቆሞስ አባ ጌዴዎን ብርሃነ ይባላሉ፡፡ አዲስ ዘመንም የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ እንግዳ አድርጎ ያቀረባቸው ሲሆን፤ ከእንግዳችን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከመንፈሳዊ ትምህርቱ ጎን ለጎን በቀለም ትምህርት ከፍተኛ ደረጃ እንዴት ሊደርሱ እንደቻሉ ያስረዱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አባ ጌዴዎን፡– ለእኔ እዚህ መድረስ ዋነኛ ምክንያት ናት ብዬ የማስበው እናቴን ነው። እናቴ አባቴን ያገባችው የተማረ ሰው ስለሆነ የመማር ፍላጎቷን ያሳካልኛል፤ ያስተምረኛል በሚል ሃሳብ ነው። በዚያ ጊዜ እንዲያውም ‹‹የኛ ሙሽራ አገባች አስተማሪ›› ሲባል እየሰማች ስላደገችና ህብረተሰቡም ለመምህርነት ትልቅ እሳቤ ስለነበረው አባቴ ህልሟን እንደሚያሳካላት ፅኑ እምነት ነበራት። ግን እንዳሰበችው ሳይሆን ቀረ። አባታችን በተለያየ ምክንያት ከተለየ በኋላ ነው ከመጀመሪያ ልጇ ጋር ትምህርት ቤት አብራ የገባችው። እስከ አራተኛ ክፍል ከተማረች በኋላ ግን እንዳልኩሽ አባታችን ስላልነበር ሶስት ልጆችን ይዛ ሕይወት በቀላሉ የሚገፋ አልሆን አላት። በመሆኑም ትምህርቱን ጥላ ወደ ንግድ ዓለም ገባች። እናም ገና እንጭጭ በሆነው ማንነታችን ውስጥ የእናታችን ፍላጎትና ጉጉት ሳናስበው ውስጣችን ተቀርጾ ነበር። በተለይ እኔ የእሷን ህልም ማሳካት አለብኝ ብዬ ነው የተነሳሁት። አሁንም ላይ ሆኜ ሳስበው የእሷ ህልም ወደ እኔ የተጋባ ነው የሚመስለኝ።
ከዚሁ በተጓዳኝ ከልጅነቴ ጀምሮ እግዚአብሔርን የማገልገል ፍላጎት ነበረኝ። እናቴ ‹‹ውለድ፤ ክበድ›› ብላ ስትመርቀኝ አይ እኔ መነኩሴ ነው የምሆነው እላት ነበር። ከህፃንነቴ ጀምሮ በመንፈሳዊ ነገር የመስፋት ፍላጎቴ እያየለ መጣ። እና እነዚህ ሁለቱ ህልሞቼ እንደሰው መነሻ ምክንያቶቼ ናቸው ብዬ ባምንም፤ ከዚያ በላይ አገልጋይ የሆንኩት በእግዚአብሔርም ጥሪ ይመስለኛል። ይህንን ስልሽ ግን በእዛ እድሜዬ ሁሉንም ነገር አገናዝቤ፤ ጉዳት ጥቅሙን ለይቼ አይደለም፤ ግን ለአምላኬ መገዛትና የማገልግል ፅኑ መሻት ነበረኝ። ነፍስ ካወኩኝ በኋላ ደግሞ ይህ መሻቴ እየጎለበተ ሄደ።
አዲስ ዘመን፡- ሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በአስተዳዳሪነት በሰሩበት ወቅት አንድ ፈታኝ ችግር አጋጥሞት እንደነበር ሰምተናል። እስቲ ስለነበረው ሁኔታ ያብራሩልን?
አባ ጌዴዎን፡- ሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል በአስተዳዳሪነት በተመደብኩበት ጊዜ እንደምታስታውሱት በሲዳማና ወላይታ ማህበረሰቦች መካከል ግጭት ተፈጥሮ ነበር። ያንን ግጭት ለማርገብ የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ስናደርግ ነበር። በእርግጥም የሽማግሌዎቹ ሚና የማይተካ ነበር። ግጭቱ በከፍተኛ ደረጃ በተፋፋመበትና በርካቶች እየሞቱ በነበረበት ቦታ ሁሉ በድፍረት እየገባን ሰዎችን እያረጋጋን ነው የነበረው። የነበረው ሁኔታ በጣም የሚያስፈራና ጭካኔ የተሞላበት፤ እኔ በተለይ የጭካኔንም ልክ ሳልፈልግ በሕይወቴ ያየሁት ያኔ ነው። ለሚዲያ የማይመጥኑ በጣም አሳዛኝ ነገሮች ነው ያየነው። ወደየት እየሄድን እንደሆነ የሚያስደነግጥ ሁኔታ ነው የተፈጠረው። እነሱ መንገድ እየዘጉና ሰው እያቃጠሉ ባለበት ጊዜ እኛ ብንሞትም እንሙት ብለን ነው ወደ እሳቱ ስንገባ የነበረው።
በተለይ እኔ መስቀል ይዤ ስቆም ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ይለፉ›› ይሉኝ ነበር። ይህም የሚያሳይሽ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስራ ነው። ምክንያቱም በእምነት አንመሳሰልም፤ ግን አክበረውኝ እንድገባ ይፈቅዱልኝ ነበር። እሳት ብቻ ሳይሆን ነገር እንደ እሳት የሚነድበት ሁኔታ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር ክብርና ሞገስ ሆኖን የተጋጩትን ወገኖች እስከማስታረቅ ደርሰናል። በዚህም የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ድጋፍ አድርጎልናል። የሰላም ሚኒስቴሯና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ ላበረከትነው አስተዋፅኦ እውቅና ተሰጥቶናል። በዚያ ላበረክትነው አስተዋፅኦ ‹‹የማይተካ ሚና የሚል ሰርተፍኬት›› ከመንግስት አግኝተናል።
ስለዚህ ሀዋሳ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በአጠቃላይ ሕዝባችን ወዴት እየሄደ እንደሆነ እንድንጠይቅና ሁኔታው ምን ያህል ወደ ጭካኔ እየተለወጠ እንደሆነ እንድናይ አድርጎናል። በተለይ እኔ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ምን አይነት ትውልድ ነው እያፈሩ ያሉት? የሚል ጥያቄ ፈጥሮብኛል። የደቡብ አፍሪካ አንድ ዩኒቨርሲቲ ላይ ‹‹አንድን አገር ለማፍረስ ከፈለግህ ረጅም ተወርዋሪ ሚሳኤል አታምርት፤ ትልልቅ ቦንቦችንም አትስራ፤ ይልቁን ስርዓተ ትምህርቱን አበላሽ›› ይላል። ምክንያቱም ከዚያ የሚወጡ ዳኞች ፍትህን ያዛባሉ፤ ከዚያ ተመርቀው የሚወጡ ዶክተሮች በእጃቸው ህሙማን ይሞታሉ፤ በአካውንታንቶች ገንዘብ ይመዘበራሉ፤ በእምነት መሪዎች ወገንተኝነት ይሰበካል። ቶሎ አገርን ለማጥፋት ከቦንብና ከሚሳዔል ይልቅ ስርዓተ ትምህርትን ማበላሸት ከፍተኛ ውድቀት እንደሚመጣ ነው በዚህ ፅሁፍ ለመግለፅ የተሞከረው። ልክ እንደዚያ ሁሉ በእኛም አገር አሁን ለተከሰተው ችግር ዋነኛ መንስኤ ነው ብዬ ነው የማምነው።
በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተማሪዎች እንዴት? እና ለምን? ጠበቡ የሚለው ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖተኞች ሆነን ሰላን ከእምነታችን አስተምሮ ውጭ ዘረኝነትን ጎጠኝነት ልንስፋፋ ባልተገባ ነበር። በዩኒቨርሲቲም ደረጃ ልዩነቶቻችን ላይ እንድናተኩር ተደርገን ነው የተቀረጽነው። 85 ቋንቋ መናገራችን ለመግባቢያ እንጂ እርስበርስ መለያያና የግጭት ምክንያት ሊሆነን ባልተገባ ነበር። በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ምሁራን ይህንን እንዴት መገንዘብ እንዳቃታቸው አይገባኝም። የምንማረው እኮ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ነው። ትምህርት የመዳረሻ ግቡ የጠራ አመለካከት ማምጣት ነው። ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎቻችን እያመረቱ ስላለው ትውልድ ትኩረት ሊሰጠውና መፈተሽ አለበት የሚል እምነት ነው ያለኝ።
ሁለተኛው፣ ሕዝባችን ይህንን ያህል ለምን ተጨካከነ? የሚለው ነገር ያሳስበኛል። የእለት ምግባቸውን እንኳን በልተው በማያድሩ ምስኪኖች ላይ ጦር የመስመበቁ ዓላማም እስካሁን ድረስ ግልፅ አልሆነልኝም። ከዚያ
የሚገኘው ትርፍም አልገባኝም። ሌላው ዋነኛው ነገር ግን ሁላችንም ከበረታን ሥራ መስራት እንደምንችል እረዳለሁ። ለምሳሌ፣ ሀዋሳ በነበርኩበት ጊዜ በትህትና ተቀብሎኝ ሲያስተናግደኝ የነበረው በእምነት ከእኔ ጋር የማይመስለው ነው። ከሁሉም በላይ ክብር ሰጥተውኛል፤ ስቸገር በችግሬ ሁሉ ገብተው ስራዬን በብቃት እንድወጣ ከአጠገቤ አልተለዩኝም። በመሆኑም ይህ ሁኔታ አገሪቱ ከገባችበት ችግር ለመታደግ የምንችልበት እድል አለ ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል። ለዚህ ደግሞ በተለይ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። ህብረተሰቡ በዚህ ደረጃ ሊጨካከን የቻለበትን ምክንያት መመርመር ይገባናል። እንዳልኩሽ ግን ከተሰራ ለውጥ ማምጣት የማንችልበት ሁኔታ የለም።
አዲስ ዘመን፡- የወገንተኝነትና ጎጠኝነት ችግር በቤተ እምነቶች ውስጥም ጎልቶ እየታየ ነው ያለው። ለመሆኑ የዚህ ምክንያት ምንድነው ያለው?
አባ ጌዴዎን፡- እውነት ነው፤ ግን እንደሚታወቀው ክርስቶስ ምድር ላይ ሳለ 12 ሐዋሪያቶች ነበሩ። ግን ከእነሱ አንዱ የሆነው ይሁዳ ከክርስቶስ ሃሳብ ጋር አልነበረም። ይሁዳ ከገንዘብ ፍላጎቱ የተነሳ የማይገዛውን አምላክ በብር እስከመሸጥ፤ የማይለወጠውን ፈጣሪ በገንዘብ ሲለውጥ ታያለሽ። ክርስቶስ ራሱ ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም ብሎ ነበር። እንደሚታወቀው ከ12 ሐዋሪያት አንዱ ይሁዳ ነው። በተለይ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ቁጥር 70 ላይ ‹‹እኔ መረጥኳችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ ከመረጥኩት አንዱ ግን ፍፁም ዲያቢሎስ ነው›› ይላል። ከዚያ የምንማረው በክርስቶስ ከተመረጡትና ከተማሩት ከሁሉም ሐዋሪያት መካከል አንዱ ዲያቢሎስ ከሆነ አሁን ያለነው የመንፈሳዊ አባቶችም ፍፁም ልንሆን እንደማንችል ነው።
በሌላ በኩል ይሁዳም ሆነ ሁሉም ሐዋሪያት ንፁህ ቢሆኑ ኖሮ ሰው ሁሉ በዳኝነት ጣልቃ እየገባ ከአሁኑ የባሰ ችግር ውስጥ በገባን ነበር። እንደእኔ አላሰብሽም ማለት አንቺ መጥፎ ነሽ ማለት አይደለም። አንቺ የምታይበት አቅጣጫ ሌላ ነው፤ እኔም የማይበት የተለየ ነው። ክርስቶስ ይሁዳን ቢያስወግደው ኖሮ አሁን ላይም እንደእኔ አላሰብክም ብለን የምናስወግደው አካል ይበዛ ነበር። ሁሉንም ነገር በእኛ ሚዛን የምንመዝን የሃይማኖት መስፈርቱ ከእነአካቴው ይበላሽ ነበር። ስለዚህ ልክ እንደይሁዳ አይነት ሰዎች በመካከላችን ሊኖሩ ይችላሉ፤ ልክ እንደእሱ በአቋራጭ ሊከብሩ የሚፈልጉም አይጠፉም። እንግዲህ ከቅዱሱ መምህር ስር የተማረው ይህ ሃዋርያ እንዲህ ከሆነ አሁን ካለነው መምህራን ውስጥም ሁላችንም እንደክርስቶስ ቅዱሳን ልንሆን አንችልም። ምክንያቱም የሰው ንፁህ የለውም።
በዚህ እሳቤ መሰረት ብዙ ነገሮች ዓላማቸውን እየሳቱ እየመጡ እናያለን። አሁን ያለው ውጤት መነሻው መሰረቱ እሱ ነው። የሰው ልጅ ከአዳም ጀምሮ ነፃ ፈቃድ ተሰጥቶታል። አዳም የተከለከውን ፍሬ የበላው ነፃ ፈቃድ ስለተሰጠው ነው፤ ይሁዳም ክርስቶስን የሸጠው ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ ነው። ስለዚህ ሰዎች አሁንም ክፉ ማድረግም፤ ነፃነትም ለእነሱ የተተወ ነው። የሃይማኖት አባት ሆነሽ ሃይማኖቱ የሚያዝሽን ብቻ መስራት የአንቺ መብት ነው፤ ሃይማኖትሽን ሽፋን አድርገሽ ክፉ ነገር መስራትም የአንቺ መብት ነው። ለሁሉም የመጨረሻ የዳኝነት ፍርድ አለ። እስከዚያ የፍርድ እለት በሁሉ ነገር ጣልቃ አይገባም፤ ምክንያቱም የነፃነት አምላክ ነው።
አሁን ላይ የሚያጠያይቀው ነገር ለምን እንከን ኖረ አይደለም፤ ዓለም ከተፈጠረች ጀምሮ ከእንከን የተለየችበት ጊዜ የለም። ግን ደግሞ እንከኑ ለምንድን ነው ጎልቶ የወጣው? የሚለው ነገር በእውነት ያነጋግራል። መጠየቅ ያለብንም ይህንኑ ነው። አሁን ላይ በተለይ የአውሮፓውያኑ እሳቤ በስርተ-ትምህርት በኩል በቀጥታ ለዘመናት የቆየውን አገራዊ እሴት አስወግዶ የራሱን መሰረት ጥሏል። አይደለም ለሺ ዓመታት የቆየው እሴት ለጥቂት ዓመታት የነበረውን ስርዓተ ትምህርት በአንድ ጊዜ ተነቅሎ ሌላ ሲተካ የሚፈጠረውን የትውልድ ክፍተት ምን ያህል ችግር እንደፈጠረ አይተናል። አሁንም የነበረው መንግስት ሲቀየር እየተከፈለ ያለውን ዋጋ እያየን ነው። የነበረን በአንድ ጊዜ ማስወገድ በሕዝቦች መካከል መተማመን ላይፈጥር ይችላል፤ መረጋጋት ይጠፋል፤ በሚታየው ነገር አለማመን ሊመጣ ይችላል። ስለዚህ ከብዙ ነገር አንፃር በመሃል የሚፈጠረው ክፍተት ቀላል አይደለም። ነባሩ ስርዓተ ትምህርታችን ምዕራብውያንን ማዕከል ወደ አደረገው ስርዓት በመቀየሩ አንደኛ የኢትዮጵውያን የሕይወት ፍልስፍናቸው እንዲጠፋ ሆኗል፤ ከሁሉ የባሰው ደግሞ ራስን ማጣታችን ብቻ ሳይሆን እነሱንም በቅጡ መምሰል አለመቻላችን ነው። ይሄም በመሃል የሚወላውሉ ሰዎች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በእምነት ተቋማቱ ላይ የሚታየው ያልተገባ አሰራር የሚመነጨው በምዕራብውያኑ ተፅዕኖ ነው እያሉ ነው?
አባ ጌዴዎን፡– በትክክል፤ የሚገርምሽ የእነሱ ተፅዕኖ ትምህርት ስርዓቱንና ባህላችንን ከመቀየር ባለፈ ሌላው አውሮፓውያኑ የራሳቸውን ሃሳብ ለማስረፅ ያደረጉት ነገር እምነትን መበረዝ ነው። የሕዝቡን መንፈሳዊ ልዕልና የመምታት አጀንዳ ይዘው ነበር ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት። ይህንን የምልሽ ዝም ብዬ አይደለም፤ በመረጃ ላይ ተደግፌ እንጂ!። በራሳችን የምንተማመንባቸውን ነገሮች ሁሉ ስንጥል እነሱ እንደፈለጉት ለዘላለም የእነሱ ባሪያ እንድንሆን ያደርጉናል። እነሱ እኛ እንድናድግ ፈፅሞ አይፈልጉም፤ በእነሱ እሳቤ ነፃ የሚባል ነገር የለም፤ የሚሰጡን ብድርና እርዳታም ከበስተጀርባው ሌላ ድብቅ ሴራ ያለው ነው። እኛ ለጊዜው ያለብንን ችግር መወጣታችን እንጂ ከስጦታው በኋላ ሊመጣብን የሚችለውን ነገር አናየውም። ነፃ የትምህርት እንኳን የሚሰጡን የእነሱን አስተሳሰብ በእኛው ሰዎች ልቡና ለመጫን ነው። ምዕራብውያን በጣም በጥንቃቄ ነው አላማቸውን የሚያሳኩት። የሃይማኖት አባቶችን ሳይቀር በዚህ እሳቤ ውስጥ እንዲጠለፉ አድርገዋል።
አዲስ ዘመን፡- በመንግስታዊውም ሆነ በሃይማኖት ተቋማት የአገልጋይነት መንፈስ እየቀነሰ መምጣት፤ በምትኩ ሙሰኝነትና ኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ እየጎለበተ የመጣበት ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ? በተለይ የእምነት ተቋማት ለሌሎች አብነት መሆን ሲገባቸው የዚሁ ችግር አካል እንዴት ሊሆኑ ቻሉ?
አባ ጌዴዎን፡- ይህ የዘመናችን አስደንጋጩ ችግር ነው!። ለምን አስደንጋጭ ሆነ? ካልሽኝ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ በሃይማኖት ስር ያሉ አካላትን ገንዘብን ማዕከል አድርገው መስራት በመጀመራቸው ነው። አንቺም ብትሆኚ በተለይ ስለሃይማኖት ተቋማቱ ችግር ያነሳሽልኝ የተጨበጠ መረጃ ስላገኘሽ ይመስለኛል። ያነሳሽው ችግር በተግባርም ይኖራል። በመሰረቱ ዘረኝነት ራሱ ሙስና ነው። ሃይማኖቱ የማይፈቅደውን ሥራ መስራትና በተቃራኒ አስተምህሮ መቆሙም ሙስና ነው። ሰዓት አለማክበር ሊሆን ይችላል፤ የማይገባሽን ቃል ሳይቀር መናገር ሙስና ነው። እንደአጠቃላይ የእከሌ ሃይማኖት ሳልል ሁሉም ላይ የምታዘበውን ነገር ነው የምነግርሽ። በዚህ ረገድ አገራችን አስደንጋጭ ሁኔታ ላይ የቆመችበት ጊዜ ላይ ነን። አንዳንዱ በረቀቀ መልክ ያደርገዋል፤ አንዳንዱ ደግሞ በግልጽ ያደርገዋል። ልዩነቱ የድርጊቱ ግልፅ መሆንና አለመሆን ካልሆነ በስተቀር ይህ ጉዳይ አሳሳቢ ከሆኑ ችግሮች መካከል ዋነኛው ነው። ይህም የሆነው አለማዊነት (secularism) በመስፋቱ ነው።
በተለይ ከ1739 ዓ.ም በኋላ ድህረ-ዘመናዊነትና ዘመናዊነት የሚል አስተሳሰብ መጥቷል። ይህ አስተሳሰብ ትልቁ ዓላማው ግላዊነትን ማሳደግ ነው። ለሰዎች ዋጋ ከመክፈል ይልቅ ለራስ መቆምንና ለራስ ብቻ መኖርን ነው የሚያበረታታው። ይህ አይነቱ ፍልስፍና የመጀመሪያ ዓላማው ደግሞ የሃይማኖትን እሳቤ መምታት ወይም መበረዝ ነው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የመጣው ትውልድ የዚያ ችግር ሰላባ ነው የሆነው። በአጠቃላይ የምዕራብውያኑ አስተሳሰብ ነው በእምነት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ገብቶ እንደሚገባን ሕዝብን እንዳናገለግል ያረገን።
አዲስ ዘመን፡- ግን ለሁሉም ችግራችን ምዕራብውያንና የምዕራብውያንን ፍልሰፍና ማድረጉ ምን ያህል አሳማኝ ነው? በተለይ አሁን ላይ ለተስፋፋው ሌብነት እነሱን ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል?
አባ ጌዴዎን፡- እንዳልሽው ሁሉንም ጥፋት በምዕራብውያኑ ላይ አላከን ራሳችንን ነፃ ለማድረግ ይመስላል። ግን እስኪ ራሳችንን ከማየታችን በፊት በገጠር ያለውን ማህበረሰብ እና በከተማ ያለውን ከፋፍለን እንይ። ከዚህ አንፃር የምዕራብውያን እሳቤ ለማን የበለጠ ተደራሽ እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ርቀት መሄድ አያስፈልግም። በአንድም በሌላም የከተማው ማህበረሰብ የበለጠ የምዕራብ አስተሳሳብ ተፅዕኖ ያደረበት ነው። ገጠር ላይ የምታየውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት አዲስ አበባ ላይ አታገኚውም። ሙስናውን ብታይ ጎልቶ የሚታየው ከተማ ላይ ነው። ገጠር ያለ አንድ ቄስ በየቀኑ ከስድስት ሰዓት በላይ ሲያገለግል ቆይቶ መቅደስ ገብቶ ካህን ሆኖ ሲያገለግል ያመሻል። ገጠር ያለው ካህን በነፃ ጉልበቱን ይሰጣል። ሌላው ደግሞ ለሚሰጠው አገልግሎት እየተከፈለውም በዚያም አረካ ብሎ ያልተፈቀደለትን ነገር የሚወስድ ከሆነ፤ ይህ የአስተሳሰብ ክፍተት ሊመጣ የቻለው ከምንም ሊሆን ይችላል?፤ አስተሳሰቡ በመበረዙ ነው። በዘመናዊነት ሰበብ ሰዎች የራሳቸውን ጨዋ ልዕልና የልብ ንፅህና አጥተውታል።
ሉዓላዊነት በአስተሳሰብ ዓለምን በኢኮኖሚ አንድ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ቢነግሩም ዋናው እሳቤ ግን ሌላ ነው። እነሱ በአስተሳሳብ በመቅደማቸው ተፅዕኖ አሳድሮብናል። ግን ዋናው ጉዳይ በእነሱ ተፅዕኖ ስር መሆናችን ሳይሆን ከተፅዕኗቸው ስር ፈንቅለን መውጣት ያለመቻላችን ነው። ይህ ለእኔም የዘመናት ያልተመለሰ ጥያቄ ነው። በአብዛኛው ጊዜ አርዓያ የምናደርጋቸው ሰዎች በእነሱ እሳቤ የተቃኙ ሰዎችን ነው። ስለዚህ ከእነሱ ጫና ፈንቅሎ ለመውጣት እንቸገራለን። አሁን ላይ ብዙ አገራት እያሉ የአሜሪካ፤ የራሺያና የቻይና ትኩረት እኛ ላይ የሆነው ኢትዮጵያ ላይ ያዩት ነገር ስላለ ነው። እነሱ በያሉበት ሆነው በሳተላይት እኛን መቆጣጠር የሚያስችል አቅም ኖሯቸው ሳለ የእኛ ድህነት ናፍቋቸው ወይም ውበታችን ከሌላው በተለየ አምሯቸው አይደለም፤ ይልቁንም አንድም የጂኦፖለቲካ ጉዳይ ነው፤ ሁለተኛው የአፍሪካ ቀንድ ስትራቴጂክ አገር በመሆንዋ ነው። ያላት የተፈጥሮ ሃብትም የእነሱን ትኩረት ከሚስቡ ነገሮች መካከል ናቸው።
እንደ እኔ እምነት ከዚህ ሁሉ በላይ በመንፈሳዊ ዓለም የሚታይ ምስጢር ስላለ ነው። እኛ ፈጣሪ ራሱ ዓላማ ያለባት አገር ናት ያለችን። ለምሳሌ የአሜሪካ ከተሞች በተደጋጋሚ በአውሎ ንፋስ የሚጠቁት ከራስ ዳሽን በሚመጣ ንፋስ ነው። ትራምፕ ይህንን ተራራ በቦንብ መምታት አለብን ሲል እንደነበር የቅርብ ትዝታችን ነው። ይህ በመንፈሳዊ ዓለም ብዙ ሚስጢር አለው። ግን አሁን ላይ በመረጃ ላይ ብቻ በሚያምን ትውልድ ውስጥ በመንፈሳዊ ያለን መረዳት ሁሉ ለማሳመን ጊዜ መፍጀት ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ እየጎላ የመጣው በተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አለመግባባት እንዲሁም ውስጣዊ ችግር መንስኤና መፍትሔያቸው ምንድን ነው ይላሉ?
አባ ጌዴዎን፡- የመጀመሪያው ችግር የሃይማኖት ተቋማት እንደተቋም ያላቸውን ራዕይ ለማሳካት ቁርጠኝነት ያለመኖሩ ነው። ምክንያቱም ራዕያቸው የእግዚአብሔርን መንግስት መውረስ ነው። አሁን ላይ በብዛት የምናስተውለው ተልዕኮ እና ዓላማ ላይ ያለማተኮር ችግር ነው። ይህ ደግሞ ፅኑ የሆነ ማንነት ካለመኖር የሚመነጭ ነው። በተጨማሪም ለእምነቱ ያለመሰጠት እና መንፈሳዊነት እጦት ውጤት ነው። የቱንም ያህል እውቀትና ጥበብ ቢኖርሽ መንፈሳዊነት ከሌለሽ ከንቱ ነሽ። በእውነትና በጥበብ ብቻ የእግዚአብሔርን መንግስት ሳይሆን ዓለምን አናተርፍ። አሁን ላይ በሃይማኖት ሰዎች ላይ የሚታየው ችግር ከመንፈሳዊነት የራቁ እንቅስቃሴዎች ነው። የሃይማኖት ተቋማት የተመሰረቱበት ዋነኛ ዓላማ ይዘው መዝለቅ ያልቻሉት መንፈሳዊነታቸውን በመተዋቸው ነው። እግዚአብሔርን ማዕከል ያላደረገ ሕይወት ከስጋ ትርፍ አያልፍም።
ስለዚህ የሃይማኖት አባቶች የተሰጣቸውን ሰማያዊ ሃላፊነት ማለትም ብልሃትን፣ እውቀትን፣ ጥበብን፣ ክህሎትን እና መንፈሳዊነት ይዘው ነው ማገልገል የሚገባቸው። እያንዳንዱ አገልጋይ እነዚህን ነገሮች አሟልቶ ካልያዘ ውጤታማ አይሆንም። አመራርነት ደግሞ ቁርጠኝነትና ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል። ራስሽን እንደሻማ አቅልጠሽ ለሌላው ብርሃን የምትሆኚበት እንጂ የምትከበሪበት አይደለም። በተለይ የሃይማኖት መሪዎች እነሱ ሞተው ሕዝቡን ደህና የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው። መሪያችን ክርስቶስ እሱ ሞቶ ለእኛ ሰላምና ደነትን ከሰጠን እኛ የሃይማኖት መሪዎችም የክርስቶስን አርዓያ መከተል ነው የሚጠበቅብን። አሁን ላይ ግን እነሱ ሞተው ሰላምን ከመስጠት ይልቅ ለእነሱ ሲሉ የሌላው መሞት እምብዛም ግድ የማይሰጣቸው ነው።
ይህም የሆነው ከመንፈሳዊነት ጉድለት ነው። መንፈሳዊነት መጽሐፍ ቅዱስ ስለያዝን ወይም ብዙ ስላነበብን አይደለም። መንፈሳዊነት ስለእግዚአብሔር ማወቅን አይጠይቅም፤ ይልቁንም ራሱን እግዚአብሔርን ማወቅን ነው የሚፈልገው። መንፈሳዊነት የሚጠይቀው ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገገርን ነው። ይህ ግን በአሁኑ ወቅት ባሉ የሃይማኖት ሰዎች ዘንድ እምብዛም የማይታይ መሆኑ ነው በእምነት ተቋማት መካከልም ሆነ ውስጥ አለመግባባት እንዲፈጠር ያደረገው። በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ሆነው በጎሳና በቋንቋ እርስ በእርስ የሚጣሉ በርካቶች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከሰማያዊው እግዚአብሔር ይልቅ ጎሳንና ቋንቋን ያስቀድማሉ። ይህም መንፈሳዊነት ያለመኖር ውጤት ነው። ግጭት መፍጠር በሃይማኖት ካባ ውስጥ ሆነው በራሳቸው ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ባህሪም ነው።
መፍትሔ ብዬ የምለው የሃይማኖት ተቋማት የቆሙበትን ዓላማ ብቻ ይዘው ራሳቸውን መፈተሸ አለባቸው። ከዚህም በተጨማሪ መንግስት የሃይማኖት ተቋማት ለሰላምና ለአገር እድገት ሚናቸውን እንዲወጡ ሊያግዛቸው ይገባል። ለምሳሌ፣ የሩሲያ መንግስት የአገሪቱ ሃይማኖት ለሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርግላቸዋል። በተለይ ዜጎችን በትክክለኛ መንገድ ለመቅረፅ ለሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በዓመት 128 ቢሊዮን ዶላር ይደጉማቸዋል። እኛ አገር ስንመጣ ግን ይህ አይነቱ ልምድ የለም። በመጀመሪያ ደረጃ የሃይማኖት ተቋማቱ ራሳቸውን ችለው በበጎነት ግባቸው ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ነው የሚጠበቀው። በሁለተኛ ደረጃ መንግስት ለትውልድ ቀረፃ አስተዋፅኦ ማበርከት በሚችል መልኩ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። ድጋፍ ሲያደርግ ግን ተጨባጭ በሆነ፤ አገሪቱን ማዕከል ባደረገ እሳቤ ላይ መሆን አለበት። ምክንያቱም የአገር ጉዳይ በመሆኑ ነው። ስለዚህ የሃይማኖት ተቋማት ራሳቸውን ፈትሸው ራሳቸውንም አገሪቱንም ከጥፋት መታደግ ይጠበቅባቸዋል። ይህ የሚሆነው ደግሞ የተመሰረቱበትን ዋነኛ ተልዕኮ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። በዚህ መርሆ ውስጣቸው የገባውን አለመግባባትና ቅራኔ ሊያስወግዱ ይገባል ባይ ነኝ።
በተለይም ያሏቸውን አገልጋዮች መፈተሽ አለባቸው የሚል እምነት አለኝ። ይህም ማለት ተልዕኳቸውን መሰረት በማድረግ የሚሄደውና የማይሄደውን መለየት አለባቸው። ይህንን መለየት ካልቻሉ አገርንም ራሳቸውንም ይዘው ነው ገደል የሚገቡት። ስልጠና ለሚያስፈልገው ስልጠና፤ የሙያ ማሻሻያ ለሚያስፈልገው የሙያ ማሻሻያ፤ ድጋፍ ለሚያሻው ድጋፍ በመስጠት፣ መባረር ያለበትንም ማባረር ይገባቸዋል። ይህም ማለት አስተዳደራዊ መፍትሔ ወይም እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ መንግስት ድጋፍ ማድረግ አለበት። ድጋፍ የሚደርገው ለሃይማኖቱ አይደለም፤ ሃይማኖቱ ለአገር ለሚያበረክተው አስተዋፅኦ ነው። ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ከተፈለገ ዜጎችን በበጎ መንገድ የሚቀርፁ የእምነት ተቋማትን ማገዝ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የትንሳኤ በዓልን በማስመልከት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
አባ ጌዴዎን፡– ትንሳኤ ማዕከሉ አዲስ ሕይወት ነው። ያ አዲስ ሕይወት ደግሞ በመብል ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በአስተሳሰብ ትንሳኤ ላይ የተመሰረተ ነው። ትንሳኤ ተስፋ ያጣ የሰው ልጅ ተስፋ ያገኘበት ቀን ነው። ትንሳኤ ሰዎች እንዲኖሩ ክርስቶስ ራሱን በመስቀል ላይ መስዋት አድርጎ ያቀረበበት እሱም በድል የተጠናቀቀበት የመጨረሻው የሰላም ምዕራፍ ነው። ትንሳኤን ስናስብ መሰረታዊ ዓላማው የአስተሳሰብ ለውጥ ነው። ስለዚህ ሁላችንም ትንሳኤ እንዲኖረን ልንጓጓ ይገባል። ትንሳኤ ዶሮ መብላት አይደለም፤ ዶሮና ሌሎቹ ግርግሮች ለስጋችን ደስታ ማድመቂያ የነፍሳችን ደስታ ማዕከል አይደለም። ሁሉም የበዓል ዝግጅቶች የእውነተኛው ደስታችን ማድመቂያ ብቻ ናቸው። የደስታው ምንጭና ማዕከል ክርስቶስ ነው። በእኛ አዕምሮ ውስጥ ደግሞ ሞተ አበቃ ያልነው ነገር እንደ አዲስ የተነሳበትና ተስፋ ያገኘንበት ትልቅ ቀን ነው። ስለዚህ ትንሳኤ ተስፋ ያገኘንበት ብቻ ሳይሆን የግፈኞች ሴራ የከሸፈበትና እውነት ጎልቶ የወጣበት ነው። እውነትን ለመቅበር ብዙ ተረባርበዋል፤ እውነት የሆነው ክርስቶስ ግን ሞትና መቃብሩን ፈንቅሎ ነው የተነሳውና ድል ያደረጋቸው። ከዚህ ደግሞ የምንማረው ከግፈኞች ጋር መተባበር ውድቀትን፤ ከእውነት ጋር መቆም ግን እውነተኛ ትንሳኤን እንደሚያስገኝልን ነው። የክርስቶስ መነሳት የሱ ብቻ አልነበረም፤ ክርስቶስን ለሚከተሉት ሁሉ ትንሳኤያቸው ነው።
ይህ በዓል የኢትዮጵያን ትንሳኤ የምናይበት ቀን እንዲሆን ሁላችንም የበኩላችን መረባረብ አለብን። ለእድገቷ እና ለሰላሟ ማነቆ የሆኑ ችግሮቻችንን ተጋግዘን ማስወገድ ይገባናል። ኢትዮጵያ ለሁላችንም በማንም የማትተካ ወርቃችን ጌጣችን፤ ክብራችን፤ ማንነታችን ናት። ስለዚህ እርስበርስ መለያየትና መጋጨታችንን ትተን በአንድ ልብ ለአገራችን መስራት መቻል አለብን። እርስ በርስ እንድንጋጭ የሚያደርጉ ቆሻሻ አስተሳሰቦች አራግፈን ዳግሞ አገራችን በሰላምም ሆነ በልማቷ ትንሳኤ እንዲሆንላት ሁላችንም የቤት ስራችንን መስራት አለብን። በተለይ ቆሻሻ የሆነውን አመለካከት ከቤታችን ጀምሮ ጠርገን ማውጣት ውስጣችንን ማፅዳት አለብን። በአእምሮ የተፈናቀለ ሰው የተፈናቀለ ሰውን አይረዳም። አሁን ላይ አገራችንን እያተራመሱ ያሉት ከሰውነት አስተሳሳብ የተፈናቀሉ ሰዎች ናቸው። ከበጎ አስተሳሰብ የተፈናቀሉ ሰዎችን በትምህርት፤ በፀሎት የምናግዝበት፤ ከቦታቸው የተፈናቀሉትን፣ የተቸገሩትን ደግሞ ያለንን በማካፈል አገራችንን ከችግር የምትላቀቅበትን ትንሳኤ ማፍጠን ይገባናል። እውነተኛ ትንሳኤ የሚከበረው እቤታችን በምናደርገው የድግስ ልክ ሳይሆን በአስተሳሳብ በመለወጥና ወገኖችን በማገዝና በመደገፍ ነው። ክርስቶስ ስለእኛ ዋጋ እንደከፈለው ሁሉ እኛም በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖችን ከችግር ለመታደግ ዋጋ መክፈል ይገባናል። ያለንን በማካፋል የክርስቶስን ፍቅር መግለፅ እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አባ ጌዴዎን፡– እኔም ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሰላም፤ የፍቅር እንዲሁም ተካፍለን የምንበላበት ይሁንልን እያልኩኝ፤ እናንተም ለሰጣችሁኝ እድል ከልቤ ላመሰግን እወዳለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 15 /2014