ኮትዲቯር አዘጋጅ የሆነችበት 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ምድብ ድልድልን ካፍ ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በምድብ አራት ከግብጽ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር መደልደሏ ታውቋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በበላይነት የሚመራው የአህጉሪቷ ታላቅ የእግር ኳስ ውድድር በመጪው ዓመት በኮትዲቯር አዘጋጅነት እንደሚካሄድ ይታወቃል። በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ እአአ በ2019 ካሜሮን፣ 2021 ኮትዲቯር እንዲሁም በ2023 ጊኒ አዘጋጅ በመሆን ተደልድለው ነበር፤ ይሁንና በመላው ዓለም በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የውድድር መርሃ ግብሩ በመሸጋሸጉ ካሜሮን ከወራት በፊት ውድድሩን ማስተናገዷ አይዘነጋም።
በመሆኑም ኮትዲቯር በቀጣዩ የፈረንጆቹ ዓመት ለ34ኛ ጊዜ የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ታስተናግዳለች። በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ብሄራዊ ቡድኖችን ለመለየት የሚያስችለው የማጣሪያ ጨዋታ የምድብ ድልድልም ከትናንት በስቲያ ተካሂዷል።
በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ በተካሄደው የእጣ ማውጣት ስነስርዓት ላይም 48 የካፍ አባል አገራት በ12 ምድብ ተደልድለዋል። እያንዳንዱ ምድብ አራት አገራትን የሚያቅፍ ሲሆን፤ በፊፋ እግድ የተጣለባቸው ኬንያ እና ዚምቧቡዌም (ማጣሪያው ከመጀመሩ ሳምንታትን አስቀድሞ ከእገዳ ነጻ ስለሚሆኑ ) በድልድሉ የተካተቱ አገራት ሊሆኑ ችለዋል።
ኢትዮጵያም በምድብ አራት፤ ከግብጽ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር መደልደሏ ታውቋል። የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤቷ ግብጽ በሴኔጋል ተሸንፋ ዋንጫውን ከማጣቷ ባለፈ ከኳታሩ የዓለም ዋንጫም በተመሳሳይ በሴኔጋል በደረሰባት ሽንፈት ከውድድር ውጭ መሆኗን ማረጋገጧ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ጊኒ እና ማላዊ በካሜሩን በተካሄደው የዓለም ዋንጫ ከዚህ ቀደም ከሚታወቁበት አቋም በተሻለ ሁኔታ የተገኙ ሲሆን፤ ምርጥ 16 ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል። በአንጻሩ ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የተመለሰችው ኢትዮጵያ ከምድቧ ማለፍ አለመቻሏ ይታወሳል።
የ33ኛው አፍሪካ ዋንጫ ባለቤት የሆነችው ሴኔጋል በመጨረሻው ምድብ 12፤ ከቤኒን፣ ሞዛምቢክ እና ርዋንዳ ጋር ተደልድላለች። የውድድሩ አዘጋጅ አገር ኮትዲቯር በበኩሏ በምድብ ስምንት ከዛምቢያ፣ ኮሞሮስ እና ሌሴቶ ጋር የምትጫወት ይሆናል። ኮትዲቭዋር ለአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታው በቀጥታ የምታልፍ ሲሆን፣ ከተቀሩት አገሮች ጥሩ ውጤት ያገኘው ለአፍሪካ ዋንጫው የሚያልፍ ይሆናል። ምድብ 11 ጠንካራ ተፎካካሪዎች ያሉበት ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካ ከሞሮኮ፣ ዚምቧቡዌ ከላይቤሪያ ጋር ይገናኛሉ።
በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ከ12ቱ ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ብሔራዊ ቡድኖች የአፍሪካ ዋንጫን ተቀላቅለው በኮትዲቯር የዋንጫ ፍልሚያቸውን ያደርጋሉ። የማጣሪያ ውድድሩም በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት በመጪው ግንቦት 2014ዓ.ም ላይ እንደሚጀመርም ታውቋል።
ኮትዲቯር እአአ በ1992 እና 2015 የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ስትሆን፤ ለበርካታ ጊዜያት ደግሞ ወደ ዋንጫው ተቃርባ እንደነበር ይታወቃል። አገሪቷ እአአ በ1984 ይህንን ውድድር ካዘጋጀች በኋላም በቀጣዩ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ የምታስተናግደው ይህ የአፍሪካ ዋንጫ 24 አገራትን የሚያሳትፍ ይሆናል። ለዚህም አገሪቷ ስድስት ስታዲየሞችን እያሰናዳች ሲሆን፤ 40ሺ፣ 20 እና 15ሺ ሰዎችን መያዝ የሚችሉ የሁለት ሁለት ስታዲየሞች ዝግጅትም ይደረጋል።
በስታዲየሞቿ ብቁ አለመሆን ምክንያት የትኛውንም አህጉራዊም ሆነ ዓለም አቀፋዊ ጨዋታ በአገሯ እንዳታስተናግድ የታገደችው ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በተሰጧት ግብረ መልሶች ላይ ማሻሻያ አድርጋ አላሳወቀችም። በዚህም ምክንያት ማጣሪያው የት ሊካሄድ ይችላል የሚለው የስፖርት ቤተሰቡ ጥያቄ ሆኗል። እንደ ከዚህ ቀደሙ በሌሎች አገራት ሜዳዎች ላይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት ጨዋታ ከማድረግ ባለፈ በደጋፊ ፊት ከመጫወት ጋር ተያይዞ የሚገኘው ጥቅም በማጣት ውጤታማነቱ ላይ ተጽእኖ እንዳይፈጠርም ስጋት አሳድሯል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም