ያለንበት ሁኔታ የሚታይ፣ የሚዳሰስ፣ የሚሰማ …. ነው። ችግርም አለ፤ ደስታም አለ። ሁለቱንም እያስተናገድን ሲሆን፤ በተለይ “ችግር” ሆኖ እያስቸገረን ላለው ምክንያቶቹ፣ መነሻዎቹ፣ ምንጮቹ እኛው ሆነን ነው የምንገኘው።
ያለንበት ወቅት፣ በተለይ ሁለቱ በርካታ ምእመናን ያሏቸው ኃይማኖቶች ተከታዮች ሁለቱም በየራሳቸው ፆም (ሁዳዴ እና ሮመዳን) ላይ ያሉበትና ኃይማኖታዊ ስርአታቸው በሚፈቅደው (በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው) መሰረት፤ ከፆምና ፀሎት ባሻገር፣ ሰብዓዊ ተግባራትን በማከናወን ላይ ናቸው። ይህ በበርካታ አገራት የሌለ፤ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሁሌም ያለ፤ በአግባቡ ከተያዘ የቱባ ባህላችንና እሴቶቻችን አካል በመሆን በማንኛውም መልኩ ማህበረ-ባህላዊ ፋይዳ ያለው ነው።
ያለንበት ሁኔታ በአላትን ለማክበር፤ ፆም ፍቺን ለመያዝ በከፍተኛ ደረጃ ሽር ጉድ የምንልበት፤ የደራ ገበያን የምናስተናግድበት፤ ኢኮኖሚያዊ አቅማችን በከፍተኛ ሁኔታ የሚፈተንበት፤ እንኳን አደረሰን፣ አደረሳችሁ ለመባባል ቀናት እየቀሩን ነው። እነዚህና ሌሎች ሁሉ ይሁን እንጂ እነዚህን ሁሉ የሚያደበዝዝ ሁኔታ ደግሞ አለ – ገበያው።
ያለንበት የገበያ ሁኔታ የሰከረ የሚመስል፤ ሰክሮም ሰውንም የሚያሰክር የሚመስልበት ነው። ሁኔታው ሁሉ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረ ሁሉ ይመስላል። የትናንት ዋጋ ዛሬ የለም፤ የዛሬ ዋጋ ነገ የለም። ገበያው “አበደ” ሲሉት አፍታም ሳይቆይ ወደ “ከነፈ” ይሸጋገራል። ሲበዛ እየጨከነ፤ በጣም ሲበዛም ርህራሄ የለሽ እየሆነ ሰውን ሁሉ ከለመደው፣ ከባህሉና ከዓመት በዓሉ አውድ ሊነጥለው ሁሉ እየዳዳው ይገኛል።
ገበያው ለማበዱ መገለጫው ብዙ ሲሆን አንዱና ዋናው ግን ደላላ መር የገበያ ሁኔታ መኖሩ ነው። ነጋዴው ነገ ለማስወደድ ሲፈልግ ዛሬ ደላላውን ያስፏጨዋል፤ “ፍየል 40ሺህ ብር ገባ” ያስብለዋል፤ “በሬ 100ሺህ …” ይል ዘንድ ያስምለዋል። ሲሚንቶ ….፤ ጤፍ ….. ዘይት ….፣ በቃ … ገበያው ይህ ሆኖ ካረፈው ቆየ። ሃይ ባይ ከጠፋ ሰነበተ። በሻጭ ነጋዴው ዘንድ እፍረት ከኮበለለ፣ አገራዊም ይሁን ሙያዊ ሀላፊነት ጨርቁን ከጣለ፤ ይሉኝታ ኮፍያውን ካወለቀ፤ ከመተሳሰብ ተርታ ከወጣ … ወቅቱ አሁን ሳይሆን ከርሟል። እንደ ነጋዴው ቢሆን ኖሮ ነባሩ የመተሳሰብ፣ የመተጋገዝ … ኢትዮጵያዊ እሴት ጓዙን ጠቅልሎ ገና ድሮ በጠፋ ነበር። ግን ለህሊናቸው ባደሩት ኃይላት እነሆ እስካሁን አለን እንጂ እንደ አንዳንዶችማ ብን ብለን በተነንን ነበር።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ይህ ጸሐፊ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ያሉ ሲሆን የሁሉም ድምፅ ተመሳሳይ ሲሆን፤ ይጠቃለል ከተባለም ተስፋ የመቁረጥ፤ የሚያሳዝንና የተማፅኖ የሚመስል ነው።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ፣ በተለይም ከወቅታዊው የገበያ ይዞታ አኳያ ያለውን አስተያየት እንዲያካፍለን የጠየቅነው የባንክ ባለሙያው አብረሃም ማርቆስን ነው። ወጣት አብረሃም በጉዳዩ ላይ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዳለው ባለሙያ ሆኖ አይደለም ሲያነጋግረን የነበረው። አብረሃም ለጥያቄያችን መልስ ሲሰጥ የነበረው ሙያውን ተንተርሶ ሳይሆን ወደ ማህበራዊነት ባደላ መልኩ ነበር።
ለአብረሃም “ስለ ገበያው ሁኔታ ምን አስተያየት አለህ?” ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ ገራገር በሆነ መልኩ “ምናለ ብንተሳሰብ፤ ምናለ ብንደጋገፍ፤ ለምን አንዱ በከፍተኛ ደረጃ ሲያከብር ለምን ሌላው ከዛ ውጭ እንዲሆን ይደረጋል? እኔ ይሄ ነው ይሄ ነው የምለው ነገር የለም፤ ለምን አንተሳሰብም? ካልተሳሰብን እኮ እንደ ሰው መኖር አንችልም። መተሳሰብ የግድ ያስፈልገናል። ያለውም የሌላውን እንድያስብ ጭምር።” በማለት ነበር የመለሰልን። ሰፋ ባለ መልኩ በጉዳዩ ላይ የተነጋገርን ቢሆንም አጠቃላይ ሀሳቡ የመተሳሰብ አስፈላጊነት፤ ያልተፈለገ ትርፍ መሻት አላስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ነበር። ሕግን የሚፈራ፣ ሀይ ባይ በታጣበት ቦታና ሁኔታ … የአብረሃም “እንተሳሰብ፣ አስቡልን …” አስተያየት ልክ ሳይሆን አይቀርምና የሚሰማ ካለ “እባካችሁ እንተሳሰብ፤ ቀድማችሁ አውዳመታችንን አትንጠቁን፤ ፍየል 40ሺህ …. ምናምን አትበሉን” ቢባል ያስኬዳል።
አብረሃም “ለመላው ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን አደረሳችሁ!!!” ከሚለው ሌላ፤ ለሕዝቡም፣ ለሸማቹም የሚያስተላልፈው መልእክት አለው፤ ሕዝቡ ህገ ወጥ ንግድን በማጋለጥ ከመንግስት ጎን እንዲቆም፤ ሸማቹም ለአመት በአል ብሎ የህገ ወጥ ነጋዴዎች ሰለባ እንዳይሆን ይመክራል።
ሌላው ያነጋገርነው የፈረንሳይ አካባቢ ነዋሪ፣ በግል ስራ የሚተዳደረው፣ መልእክቱንም “በዓሉ የሰላም፣ የመተሳሰብ፣ የፍቅርና አብሮነት ይሁንልን!!!” በማለት የደመደመው አቶ ሸዋንዳኝ ታደሰ ነው። እንደ አቶ ሸዋንዳኝ አስተያየት መንግስት በህገወጥ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል። ሸማቹም ለአንድ ቀን ዓመት በዓል ብሎ ለህገ ወጥ ንግድ መጋለጥ፤ ተጠቂ መሆን የለበትም። መንግስትም እንደ ሸማቾች አይነቶችን በስፋት በማደራጀት ለሕዝቡ ምርቱን ተደራሽ ማድረግ አለበት።
ሌላው ያለንበት ሁኔታ የሰላምና ፀጥታው ጉዳይ ነው። ይህንን ጉዳይ እየተካሄደ ወዳለው የእርስ በእርስ ግጭት አልወስደውም። ከዛ በመለስ ያለውንና በተለይ ከትንሽ እስከ ትልቅ ከተሞቻችን ድረስ የነዋሪዎች ራስ ምታት የሆነውን ወጥቶ የመግባትና ያለ ስጋት የመንቀሳቀስ ጉዳይ ነው የማነሳው። በተለይም በተለምዶ “ጫኝ” እና “አውራጅ” ከሚባለው ስራና ሰራተኞቹ ከሚባሉት አኳያ ከተሞቻችን ምን ይመስላሉ የሚለውን ቆም ብሎ ላገናዘበ የሚደርስበት ድምዳሜ ቢኖር ያለንበት ሁኔታ የሕግ ሳይሆን የጉልበተኞች የበላይነት የተንሰራፋበት መሆኑን ነው።
ዛሬ በከተሞች የፌስታል እቃ እንኳን ባለ ፌስታሉ ከታክሲ ላይ ማውረድ አይችልም። ይህንን የማድረግ ምንም አይነት መብት የለውም። ባለቤቱ እኔ ነኝ፤ በሕግ አምላክ …. የሚሉት ከምንም የሚያድኑ አይደሉም። እቃዎትን አንድ ገረምሳ (ወይም የጎረምሶች ቡድን) ምጥቶ ያወርደዋል። የፈለገውን ያህል ብር አምጣ/ጪ ይላል። ይወስዳል። ይህንን አልፈፅምም ካለ የባሰ እንጂ ሌላ የሚያተርፈው ነገር የለምና መክፈሉ “አማራጭ የሌለው መፍትሄ?” ይሆናል (ወደ ፖሊስ ቢኬድ “ተስማሙ”)።
በከተሞቻችን በሞተር እየሄዱ ንብረት መንጠቅ፣ ቁልፍ የሆኑ መንገዶች ላይ ተሰብስቦ በመቀመጥ ገበያተኛ ገዝቶ ሲወጣ ገንዘብ አምጣ (ክፈል) ማለት፤ አልሰጥም ካለ ወደ ማስገደድ መሄድ …. የተለመዱና የከተማ ነዋሪዎች የእለት ተእለት ሕይወት አካል እየሆኑ ነው።
ያለንበት ሁኔታ የፖለቲካ ንቁሪያ የበዛበት፣ የመግባባት ሚዛኑ ወደ አለመግባባት ያጋደለበትና ሰርክ ጭቅጭቅ የሆነበት ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ፖለቲካ መስማት የማይፈልግ፣ በተለይም የብሄር ፖለቲካ በደረሰበት መድረስ የማይፈልግ ሰው የሚኖርባት አገር አልመስል እያለች ነው። አስቀድሞ ሁሉ አዋቂ፣ ሁሉ ተቺ … እንደ ተባለው የነሸጠው ሁሉ እየመጣ የአገሪቱን ፖለቲካ በዘር ከረጢት ውስጥ ከትቼ ያሻኝን ካላደረኩ ባይ ነው። የሰላም፣ እድገትና አብሮነት አማራጭ ሀሳብ ይዞ የመምጣት ምንም አይነት እቅድ የሌለው ፖለቲከኛ ቁጥሩ እየጨመረ ሲሄድ እንጂ ሲቀንስ አይስተዋልም። ባጭሩ፣ ፖለቲካችን ወከባ እንጂ ሌላ ጠብ እሚል ነገር እያጠጠው ይገኛል።
ያለንበት ሁኔታ የምዕራቡ ዓለም እንደ ፈለግሁ ካላደረኳችሁ እያለ ሌት ተቀን እያስፈራራን የሚገኝበት ነው። አሜሪካና ተባባሪዎቿ እነ ኤችኤር 6600ን በመሳሰሉ የማእቀብ ጋጋታዎች እጃችንን ለመጠምዘዝ እየጣሩ ነው። ይህ ጊዜ ከምን ጊዜውም በላይ አንድ ልንሆን የሚገባን ጊዜ ሆኖ ሳለ፤ አንድ እንዳንሆን፣ ሆነንም ጥቃትን እንዳንከላከል እኛኑ እየሸነሸኑ እርስ በርሳችን በማናከስ የሚፈልጉትን ለማድረግ እየጣሩ ያሉበት ወቅት ነው።
በአጠቃላይ ያለንበት ሁኔታ መልኩ ብዙ ነው። ይሁን እንጂ መፍትሄው ግን አንድ ነው – አንድ መሆን፤ ከላይ ያነጋገርናቸው አብረሃምና ሸዋንዳኝ እንዳሉት መተሳሰብ፤ መደጋገፍ … ነውና እሱው ላይ እንበርታ።
መልካም በዓል!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም