ወፈፌው ይልቃል አዲሴ፣ የእድራችን መሪ አቶ አህመድ ይመርን በክርክር ከረታ ወዲህ እንደዚህ ቀደሙ በየቀኑ ሌሊት እየተነሳ መጮሁን አቁሟል። ወትሮ ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል መጮህ የጀመረ ማታ የሌሊት ወፎች ከዋሻቸው ወጥተው ውር ውር ማለት ሲጀምሩ ነበር የሚያቆመው። አሁን ላይ ግን በክርክሩ የእድራችንን መሪ ካሸነፈ በኋላ እንኳንስ ቀኑን ሙሉ ሊጮህ ይቅርና እሁድ እሁድ እንኳን ለሰፋራችን ሰዎች መልዕክት ለማስተላለፍ ሲፈልግ ብቻ ነው የሚገኘው። ጩኸቱም እንደዚህ ቀደሙ በወፈፌነት የሚታለፍ አይደለም። ሁሉም የእድራችን እና የሰፈራችን ሰዎች በጥሞና እየተከታተሉ በጭብጨባም ያጅቡታል እንጂ።
የዛሬው የይልቃል አዲሴ የዋርካው ስር ንግግር ትንሽ ጠጠር ያለ እና በምሳሌዎች የታጀበ ነበር። የዛሬ ንግግሩን የጀመረውም በእርሱ መምጣት የተደሰቱ ሰዎችን በመገሰጽ ነው። የሰፈሩ ሰዎች በይልቃል አዲሴ መምጣት ተደስተው ሲያጨብጭቡ፤ ምን የሚያስጨበጭብ ነገር አለና ነው የምታጨበጭቡት! ? ሲል ንግግሩን ጀመረ።
ንግግሩን ቀጠሎም…..ዛሬም ካለፈው ስህተታችሁ አትማሩም ? ባለፈው ጊዜም ለእድራችን እና ለሰፈራችን መሪ እንዲሁም አላዋቂዎች ለሆኑ ተፎካካሪ ሃይሎች በሆነ ባልሆነው እጃችሁ እስኪላጥ አጨብጭባችሁ አጨብጭባችሁ አላዋቂዎችን እንዲታወቁ አደረጋችሁ። ሳያውቁ እንዲታወቁ የተደረጉት ኃይሎች ከማንም በላይ ያወቁ መስሏቸው ራሳቸውን በግብዝነት ቆለሉ። እነኝህ አላዋቂዎችም ከእድራችን ህግ እና መርህ ውጭ ለራሳቸው በመሰላቸው መንገድ ነገሮችን እየሰፉ እና እየቀደዱ ሰፈራችን እና እድራችንን እንዳልሆነ አድርገው እየበጠበጡት ነው።
በእነኝህ ሰዎች ሰበብ ሰፈራችን እና እድራችን ለመበጥበጡ ከእነሱ በላይ ተጠያቂዎች እኛ ነን። ምክንያቱም ሳያውቁ እያጨበጨብን እንዲታወቁ ያደረግናቸው እኛ ስለሆንን። ዛሬ ለእኔ እዳጨበጨባችሁት ሁሉ በዚያን ጊዜም ለግብዞቹ ዝም ብላችሁ ስታጨብጭቡ ምን ብያችሁ ነበር….? ወፈፌ ተብየ ሰሚ አጣሁ እንጂ።
ያኔ እኔን ወፈፌ ስትሉኝ ደስተኛ ነበርኩ። ምክንያቱም በእኛ ሰፈር ከወፈፌዎች፣ ከእድር መሪዎች እና ተፎካካሪ ኃይሎች በቀር እንደልባቸው እንዲናገሩ ለማንስ ይፈቀዳል? ይሄን በወፈፌነት ስም እንደፈለጉ መናገርን ማንስ ሊታደል ይችላል? እኔን ወፈፌ ብላችሁ ስትፈርጁኝ ደስ ብሎኝ ነው የተቀበልኳችሁ።
በአንጻሩ ግን ሲያስነጥሱም ሳይቀር ስታጨበጭቡላቸው የነበሩ በተለይም እድራችንን ለመምራት የሚፎካከሩ ሃይሎች በእናንተ ጭብጨባ የተነሳ ከሚችሉት በላይ ሃላፊነት አሸከማችኋቸው። እነኝህ ከአቅማቸው በላይ ሃላፊነትን የወሰዱ ሰዎችም በእድራችን ህግ እና ስርዓት መመራትን እንደ ነውር እየቆጠሩ በየጎጣቸው ራሳቸውን የጎበዝ አለቃ እያደረጉ ሾሙ። የእድራችን መሪ ስለምን ይህን ታደርጋላችሁ? ቢላቸው ምን አገባህ! ሲሉ መለሱ። እነኝህ ሃይሎች ከእድር መሪያችን ህግን እንዲያከብሩ ማስጠንቀቂያ በተሰጣቸው ቁጥር እንወክለዋለን የሚሉትን ጎሳ ጥፋት ታውጆብሃል እያሉ ለጥፋት በማስነሳት እድራችን እና ሰፋራችንን ሲያበጣብጡ ይሄው ድፍን አራት አመት ተቆጠረ።
ራሳቸውን እንደ ጎበዝ አለቃ በሚቆጥሩ ኃይሎች ተገርመን ሳንጨርስ ሰፈራችንን እና እድራችን እንዲያስተዳድሩ ስልጣን የተሰጣቸው ሰዎች እርስ በርስ በጎጥ ይነታረኩ ይዘዋል። ከሁሉም የሚያስገርመው ደግሞ የእነሱ ንትርክ ነው። ስልጣን ይዘውም ይነታረካሉ? ያኔ የለውጡ ሰሞን በተለይ በእድራችን ውስጥ የሚገኙ መደበኛም ሆኑ ኢመደበኛ ጡሩምባ ነፊዎች እኔን ወፈፌ እያሉ ሲሳደቡ እና ሲያብጠለጥሉ አላዋቂዎችን ደግሞ ሲያሞካሹ ስመለከት ይች ቀን እንደምትመጣ እርግጠኛ ነበርኩ። ለማንኛውም ዛሬም አረፈደም፤ ከዚህ በኋላ ነገሮችን በስሜት ከመወሰናችሁ በፊት፡-
“አስበን እንስራ ለነገም እንዲሆን፤
ይሁን ይሁን ብለን የማይሆን እንዳይሆን፤”
የሚለውን የአንዳርጌ መስፍን ግጥም ደጋግማችሁ፣ ደጋግማችሁ እንድታስቡት እሻለሁ፤ ሲል ትዕዛዝም ማሳሰቢያም አክሎ ነገራቸው።
ይልቃል ንግሩን ቀጠለ፤ ……ፈረስ እህህህ …. ማለቱ ሁኔታዎች ቢያስገርሙት አይደል! ፈረስ ስል በሰፈራችን የነበረን አንድ ፈረስ አስታወስኩ። በሰፈራችን በባለቤቱ ይጨቆን የነበረ ፈረስ ነበር። መጨቆኑ ያንገበገበው ፈረስ ከዕለታት በአንድ ቀን የት ገባ ሳይባል ከቤቱ ይጠፋል። እንደጠፋ ሳይመለስ በዚያው ያድራል። ውጭ ባደረ ጊዜም ያገኘውን ሰብል ያለማንም ከልካይ እንደልቡ ሲበላ ያድራል። ሆዱም ያለመጠን ይጠግባል። ቁንጣንም የሚይዘውን ሚጨብጠውን ያሳጣዋል። በዚህም ሳቢያ አነጋጉ ላይ አቶ ፈረስ ባገኘው ቦታ ላይ ተዘራግቶ ይተኛል። ይህ በእንዲህ እዳለ በጠዋት ምግባቸውን ለመፈለግ የተነሱ ጥንብአንሳ አሞራዎች ከላይ ወደታች ሲመለከቱ አንድ ፈረስ መሬት ላይ ተዘርሮ ያያሉ። አቶ ፈረስም በጣም ጠግቦ ስለነበር ምንም አይነት እንቅስቃሴ አያደርግም ነበር።
ይህን የተመለከቱ አሞራዎች ፈረሱ የሞተ ይመስላቸዋል። በጠዋቱ ብዙ ሳንለፋ ቀናን ብለው ወደ ተዘረረው ፈረስ ተጠጉ። ፈረሱ የሞተ የመሰላቸው አሞራዎች በቁንጣን ያበደውን ፈረስ ለመብላት ቋምጠው በፍጥነት በምንቋራቸው አቶ ፈረስን ውግት ….ውግት ማድረግ ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ የአሞራዎች ንክሻ ያመመው ፈረስ አይኑን ገለጥ አድርጎ ሲመለከት አሞራዎች ከበውታል። በምንቋራቸውም እየወጉት ነው። በዚህ ጊዜ በቁንጣን መሬት ላይ የተዘረረው ፈረስ አንገቱን ብቻ ቀና አድርጎ በንዴት ምን እያደረጋችሁ ነው!? ሲል አሞራዎችን ጠየቃቸው። አሞራዎችም ያልጠበቁት ነገር ስለገጠማቸው ተደናግጠው «ታመሀል ተብሎ ልንጠይቅ» አሉት። ፈረሱም አሞራዎች ለምን እንደተሰባሰቡ ስለገባው «እህህህ …..» አለ ይባላል። ከዚያ በኋላም የፈረሰ ጩኸት እህህህ ሆኖ ቀረ።
እኔ እና የሰፈራችን ሰዎችም ለዘመናት በጭቆና ወድቀን በመኖራችን እና ለውጡን ተከትሎ ከችግር እና ከመከራ ተላቀቅን እፎይ ልንል ነው ብለን በደስታ ቁንጣን ሰክረን በተኛንበት ስለምን የእድር መሪዎቻችን እና ተፎካካሪ ሃይሎች እኛን በጎሳ ስም እየከፋፋሉ ሊያጠፉን እንደፈለጉ ስለገባን እንደ አቶ ፈረስ እህህ ብለናል!
ቅቤን ወተት ማድረግ አይቻልም። ወተትን መጠጣት የሚፈልግ ሰው ወተቱን በጊዜ መጠጣት ይኖርበታል። ጊዜው አልፎ ወተት ወደ ቅቤ ከተቀየረ በኋላ ቅቤን ወተት ላድርግ ቢሉ የማይቻል እና የማይሞከር ነው ትርፉ ድካም ነው ። አሁን ላይ የእድራችን መሪዎች እና እድራችንን ለመምራት የምትራኮቱ ሃይሎች ወተቱን መጠጣት ከፈለጋችሁ በወተትነቱ መጠጣት ተገቢ ነው። ነገር ግን ወተቱ እረግቶ እና ተንጦ ወደ ቅቤነት ከተቀየረ በኋላ ቅቤውን ወተት አድርጉ ብሎ የሰፋራችንን እና እድራችንን ሰዎችን ማስቸገር አግባብነት ለውም። ከአሁን በኋላ እንደዚህ አይነቱን ግብዝነት የምንታገስበት ትከሻ የለንም።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት የነበረው ዋረን ሃርዲንግ «ተገቢ ለሆነ ምክንያትም እንኳን ቢሆን ህሊናን የሚወቅስ ስራ አትስራ» ይሉ ነበር። እውነት ነው! የእኛ መሪዎች እና ተፎካካሪዎች ግን ተገቢነት ለሌለው እና ህሊናን የሚያቆስል፤ ቅቤን መልሳችሁ ወተት አድርጉ አይነት ትዕዛዝ እያስተላለፉ የሰፋራችንን ሰዎች በጎሳ በመከፋፈል ለማጣላት ሲጥሩ ይታያል፤ ይሄ እኮ በእነሱ ቤት ፖለቲካ መሆኑ ነው ? ድንቄም ፖለቲካ…!
ታላቁ የቻይና ፈላስፋ ኮንፊሼስ “በራስህ ላይ ሊደረግብህ የማትፈልገውን በሌላ ላይ አታደርግ። “ይላል። እናንተ አቅልላችሁን በክፋት እና በጥፋት የተሳተፋችሁ የእድራችን መሪዎችና ተፎካካሪዎች ምን አለበት በእናንተ ላይ ሊፈጽምባችሁ የማትፈልጉትን በጥላቻ እና በቅናት ጠርዝ ላይ ቆማችሁ በወንድም እና በእህቶቻችሁ ላይ ባትፈጽሙ?
የጤና ሚንስትራችን ፎቶ ያሉበት በአንበሳ አውቶብስ ማቆሚያ ቦታዎች ላይ የሚገኝ አንድ ቀልቤን የሳበኝ አባባል አለ። «የወገኔ ጤነኝነት ያሳሳስበኛል.. » የሚል። ይህን አባባል ስመለከት የጤና ሚንስትሯ የእድራችን መሪዎችን እና ተፎካካሪ ሃይሎችን ተመልክተው የተናገሩት ንግግር መስሎኝ ተግርሜአለሁ። ለነገሩ አያስገርምም!… ስለወገናችን ጤነኝንት ከጤና ሚንስትራችን በላይ ማን ሊያውቅ ይችላልና?
በሰፈራችን እና በእድራችን እየተፈጠረ ያለው ችግር ለመሪዎቻችን እና ለተፎካከሪዎች የወደዱት ይመስላል። ሰው መጥፊያውን እንዴት ሊወድ ይችላል? ይህን ስል አንድ ነገር ትዝ አለኝ። ልጅ እያለሁ በሰፋራችን በስካሩ የሚታወቅ አቶ ፈጠነ የሚባል ሰው ነበር። አቶ ፈጠነ፣ ከአጎቴ ማህበር ተጠርቶ መጣ። ከመጠን በላይም ጠጣ። ከመጠን በላይ ጠጥቶ ከቤት ሲወጣ ከአጎቴ ቤት በር ላይ ያለው የቀጋ ዛፍ ጋቢውን ጥርቅም አድርጎ ያዘው። የቀጋው እሾህ ጋቢውን በያዘው ጊዜ ጋቢውን የያዘው አጎቴ መስሎት እባከህ ወዳጄ ልቀቀኝ ከዚህ በላይ አልጠጣም! ልቀቀኝ ልሂድበት እያለ ጋቢውን ሞጭጮ ከያዘበት የቀጋ ዛፍ ጋር ይሟገታል። የቀጋው ዛፍ ግኡዝ ስለሆነ አልመለሰም። አቶ ፈጠነም ቀጋው ጋቢውን አለቅ ስላለው የአጎቴን ስም እየተጣራ ጋቢውን ከአስቀረህ አስቀረው እንጂ ከዚህ በላይ አልጠጣም፣ በቅቶኛል ብሎ ጋቢውን ቀጋው ላይ ጥሎት ሄደ። እኔም በአቶ ፈጠነ እና በቀጋው ዛፍ መካከል የነበረውን ትዕይንት ለአጎቴ እና አጎቴ ቤት ተጠርተው ለመጡ እንግዶች ተናገርኩ።
አጎቴ እና ለማህበር ተጠርተው የመጡ ሰዎችም አቶ ፈጠነ ወዴየት እንደሄደ ጠየቁኝ። እኔም የሄደበትን አቅጣጫ አሳየሁ። ሰዎችም አቶ ፈጠነ የሄደበትን አቅጣጫ ተከትለው ቢሄዱ የሰፋራችን ሰዎች ውሃ ከሚቀዱበት ጅረት መሀል ተኝቶ ተገኘ። የማህበሩ ሰውም ሰውየው የሆነ ነገር ቢሆን ነገ እዳው ለእኛም ጭምር ይተርፋል በማለት ከወደቀበት ሊያነሱት ሞከሩ። አቶ ፈጠነም የተኛሁበት ተመችቶኛል ማንም ሰው እንዳይነካኝ!… አልነሳም! ብሎ እምቢ አለ። ሰው መጥፊያውን ይወዳል ማለት ይሄ አይደል !
የሰፈራችን እና የእድራችን መሪዎች እና ተፎካካሪዎች እንደ አቶ ፈጠነ ያለመጠን ያገኙትን እየበሉ እና እየጠጡ በጥጋብ ሰክረው በሰፈራችን ላይ ችግር መፍጠራቸው ሳያንስ፤ በእነሱ ችግር ሰፈራችንን እና እድራችንን ሊፈርስ መሆኑን የሚነግራቸው ሰው ሲመጣ እንኳን ለመስማት ፈቃደኛ አይደሉም። የሚጠየቁት ሌላ የሚመልሱት ሌላ …. አራምባ እና ቆቦ።
ይህን ስል ……..
“ጥርስ የለውም እንጂ ይናከሳል ጉዳን፤
የፈረንሳይ ዋና ከተማ እንደምነሽ ሱዳን፤” የሚውን የተስፋየ ካሳ ቀልድ ያስታውሰኛል።
በመጨረሻም በአንድ ሃገር ሰላም ፣ መረጋገት እና እድገትን ለማምጣት ከተፈለገ ተገቢው ቦታ ለተገቢው ሰው መሰጠት አለበት የሚለውን የኮንፊሼስ አባባል ያለምንም ማንገራገር መዋጥ ያስፈልጋል ባይ ነኝ። አይደለም ሃገርን ይቅርና በአንድ ቤት ውስጥ እንኳን ሰላም እና እድገትን ለማምጣት ከተፈለገ ተገቢው ቦታ ለተገቢው ሰው መሰጠት ያስፈልጋል። የአባትን ቦታ ለልጅ ከሰጠን ልጅ የአባትን ያህል ቤቱን ሊመራ አይችልም። የቄስን ቦታ ለጨዋ ሰው ከሰጠንም እንዲሁ የቄሱን ያህል ቤተክርስቲያኗን ስርዓት እና ወግ ማከናወን አይችልም። ስለዚህ የሰፈራችንን እድር ሰላም እና እድገት ለማምጣት ተገቢውን ቦታ ለተገቢው ስጡ። መልዕክቴ ነው ! ብሎ ይልቃል አዲሴ ንግሩን ሲጨርስ ሊያጨበጭቡ የነበሩ ሰዎች መልሰው እጃቸውን ሰበሰቡ። የተነገራቸውንም እያወጡ እና እያወረዱ ወደ መጡበት ተመለሱ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም