የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፉ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ የማይተካ ሚና ያላቸውን የሰው ኃይልና ቴክኖሎጂን በማውጣት ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት ነው። ይሄን ኃላፊነት ለመወጣትም ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ወደሥራ የገባ ሲሆን፤ በሚፈለገው ልክ ባይሆንም አበረታች የሚባል ሥራን ሲያከናውን ቆይቷል። ሰሞኑንም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የ2011 በጀት ዓመት የስምንት ወር እቅድ አፈጻጸም በአዳማ የተገመገመ ሲሆን፤ በመድረኩም ከፌዴራል፣ ከክልልና ተቋማት፣ እንዲሁም ከአጋር አካላት የተገኙ ባላድርሻዎች ተሳትፈዋል።
እኛም በዛሬው ዕትማችን በዚህ ጉባኤ በተደረገ ግምገማ በተለይ በሙያ ደረጃ ምደባና የብቃት ምዘና፣ የሰልጣኝ አሰልጣኝ ልማትና የተቋማት ግንባታ፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ሥራዎችን አስመልክቶ የታዩ ጉዳዮችን፤ የተለዩ ችግሮችንና የተቀመጡ የመፍትሔ ሃሳቦችን አስመልክቶ የፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐብታሙ ክብረት ጋር ያደረግነውን ቆይታ ለንባብ እንዲመች አድርገን ይዘን ቀርበናል።
የሙያ ደረጃ ምደባና የብቃት ምዘና ሥራዎች
ጉባኤው ካተኮረባቸው ጉዳዮች አንዱ የሙያ ደረጃ ምደባና የብቃት ምዘና ሥራዎች በምን መልኩ እንደተከናወኑና የሚታዩ ችግሮችን በትኩረት ገምግሟል።በዚህም የተደራሽነት ጉዳይ፤ ሙያ ደረጃ ጥራት ችግር እና ነባር የሙያ ደረጃዎች ክለሳ ላይ መዘግየቶች ታይተዋል። የአዳዲስ ሙያ ዝግጅት ጉዳይም የተነሳ ሲሆን፤ የአርሷደር የብቃት ምዘናና የአጫጭር ስልጠና የሙያ ብቃት ምዘና እንዲሁም በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን የሚደገፉ የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች ምዘና አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑም ጎልቶ ተነስቷል። ለምሳሌ፣ በአርሷደር ምዘና የዓመታዊ እቅዱ በጣም ሰፊ መሆን፤ እንዲሁም የሥራ ምዘናና ገበያ ተኮር አጫጭር ስልጠና፣ ስልጠናው ከተጠናቀቀ በኋላ በምዘና መቋጨት እንዳለበት እቅድ ላይ ተቀምጦ ነበር።
ይሄም ቢሆን አፈጻጸሙ ደካማ ሆኖ ታይቷል። የጥቃቅንና አነስተኛውም በተመሳሳይ ዝቅተኛ መሆኑ ታይቷል። በእነዚህ ላይም ዝርዝር ግምገማና ሰፊ ውይይት በማድረግ አቅጣጫ ተቀምጧል። በዚህም የአጫጭር ስልጠናዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ማስቻልና ማንኛውም ስልጠናም ውጤታማ እንዲሆንና ዘላቂነት እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባ ጉባኤው አስምሮበታል።የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽንም በአራቱ የድጋፍ ማዕቀፎች ከተሰጠ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽኑ የጥራት መለኪያው ምዘና እንደመሆኑ ሥራው ዘላቂና አስተማማኝ ሆኖ የልማታዊ ባለሀብት መፈልፈያና የኢንዱስትሪያሊስቶች መሰረት እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ ተመላክቷል።
የሙያ ደረጃዎችም ቢሆኑ ጊዜ ያለፈቻቸው እየታዩ በኢንዱስትሪው ፍላጎት መሰረት እንዲከለሱ የሚል አቅጣጫ ተቅምጧል። በዚህ ረገድ በተለይ በቀጣይ አራት ወራት ሊከናወኑ የሚገባቸውን ተግባራት በመለየት በእቅዱ ያልተፈጸሙና የተንከባለሉትንም ኃይልን አስተባብሮ መሥራት እንደሚገባ ተመልክቷል። በዚህም ከሙያ ዝግጅት ጀምሮ ተጨማሪ የሙያ መሣሪያ ዝግጅት ሥራ እቅድንም በአራት ወራት ውስጥ ለማሟላት በጉባኤው መስማማት ተችሏል።
የሰልጣኝ አሰልጣኝ ልማትና የተቋም ግንባታ
ጉባኤው የተመለከተውና በርካታ ነገሮች የተነሱበት ሌላው ጉዳይ የሰልጣኝ አሰልጣኝ ልማትና የተቋማት ግንባታ ሲሆን፤ በዚህም ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ሲታይ የሰልጣኝ ቅበላ ሂደቱ የተሻለ መሆኑ ተገምግሟል። የአጫጭር ስልጠናም ቢሆን በተሻለና ጥራት ባለው መንገድ እየተሰጠ መሆኑ ታይቷል። በተለይ አንዳንድ ክልሎች በጥራት ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅተው በመሥራት ያሳዩት ተግባር መልካም ጅምር መሆኑ የታየ ሲሆን፤ የልምድ ልውውጥም ተካሂዶበታል።
የተቋማት ግንባታን በተመለከተም አዳዲስ ኮሌጆችን በማቋቋም በተለይም ህዝብን በማስተባበር ኮሌጆችን በወረዳ ደረጃ ለማዳረስ የተደረጉ ጥረቶች መኖራቸው የታየ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ ጥሩ የሠሩ ክልሎች (እንደ ሶማሌ ክልል ያሉ ታዳጊ ክልሎች ሳይቀር የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ በጀት በመመደብ ሞዴል የሚሆኑ አዳሪ ኮሌጆችን በመገንባት) በሞዴልነት ወጥተው ተሞክሯቸውን ማስተላለፍ ችለዋል።
የአሰልጣኞች ጉዳይን በተመለከተም በአሰልጣኝ ቅጥር ረገድ ጥሩ ነገር መኖሩ ተገምግሟል። ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ ስር የተከናወኑ መልካም ሥራዎች የመኖራቸውን ያክል በእጥረትነት የተነሱም አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ፣ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ በማድረግ በኩል አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንደመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተገምግሟል። በአጫጭር ስልጠናዎችም ቢሆን አሁንም ድረስ ምዘና ሳያልፉ የሥራ ዕድል እየተፈጠረላቸው መሆኑ፤ መደበኛ ስልጠና አጠናቃቂዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ከሥራ ማስተሳሰር መኖሩ እንደክፍተት የተነሳ ነው። በተለይ አጫጭር ስልጠና ላይ ከውጭ ስምሪት ጋር በተያያዘ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ለግል ኮሌጆች የተሰጠ ቢሆንም፤ የጥራት ችግርና ኪራይ ሰብሳቢነት ስሜት እንዳለበት ተገምግሟል።
በፈቃድ አሰጣጥ ሂደት ላይም ተናብቦ ያለመሥራት በመኖሩም እነዚህ ታርመው በተለይ ከአገር ገጽታ መበላሸት ጋር የሚያያዝ እንደመሆኑ በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ ተለይቷል። የተቋማትን ስታንድርድ ጠብቆ ኦዲት በመሥራትም የሚጎድላቸው በመኖሩ እንዲስተካከል አቅጣጫ ተቀምጧል። ለዚህም በህግና አሠራር መሰረት እንዲመራና በዚያው አግባብ የክትትልና ድጋፍ ስርዓቱ እንዲከናወን ይደረጋል።
የ”ሲ” ደረጃ አሰልጣኞች ጉዳይም በተለይ ከ”ሲ” ስልጠና መቼ እንወጣለን፣ የሚለው በጉባኤው በስፋት የተነሳ ሲሆን፤ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት አሰልጣኞችን ደረጃ በደረጃ በአሠራርና ሕግ መሰረት አቅማቸውን ማብቃት እንደሚገባም ተመላክቷል። የዘርፉን ስትራቴጂ ማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያዎች መውጣት እንደሚገባቸውና እስከአሁንም ባልጸደቁ መመሪያዎች መሥራት በመኖሩ ትክክል ስላልሆነ አሁን ላይ በረቂቅ ደረጃ ያሉ መመሪያዎች ቶሎ ጸድቀው ወደሥራ እንዲገባባቸው የሚል ሃሳብም ተነስቷል። በቴክኒክና ሙያ ዘፍር ሴቶችን በአሰልጣኝነትና በአመራርነት በማሳተፍ ረገድ አሁንም ክፍተት እንዳለ ተለይቷል።
ይሄንንም በደንብና መመሪያ መመለስ ስለሚገባ በዚያው አግባብ ለመተግበር የሚያስችሉ ጅምር ሥራዎች አሉ። እንደ አጠቃላይ የሰልጣኝ አሰልጣኝ ልማትና የተቋማት ግንባታ ሥራው ምንም እንኳን ብዙ ርቀት የተሄደ፣ በቀጣይም ሥራው የሚሠራ ቢሆንም የታዩ ክፍተቶች በቀጣይ አራት ወራት በትኩረት ተሠርቶ ሊታረሙና ሊስተካከሉ እንደሚገባቸው፤ በውጤት ተኮር አሠራሩ መሰረትም በቀሪው ጊዜ የዓመቱን እቅድ ለማሳካት መሥራት እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።
የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ልማት ሥራዎች
ሦስተኛው የጉባኤው አብይ ጉዳይ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ መሰረትም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የጥቃቅንና አነስተኛ መፈልፈያና የቴክኖሎጂ ማዕከል እንደሚሆኑ ባስቀመጠው አግባብ እየተሠራ መሆን አለመሆኑን በስፋት የተመለከተበት ነው።ከዚህ አኳያ ያለው ጅማሮ ጥሩ እርሾ ያለው ስለመሆኑ፤ ነገር ግን በጥራት ዙሪያ ደንበኞችን ማርካት ላይ ጉድለት እንዳለ ተለይቷል። ይህ ደግሞ አንደኛ፣ በአስተሳሰብ ወጣ ገባነት የተፈጠረ እንደሆነና አሰልጣኞችም ሆነ ተቋሙ ይህ ተግባር የእኔ ነው ብለው አለመያዛቸው፤ ሁለተኛም የአጋር አካላትና የአስፈጻሚ አካሉ ተቀናጅቶ አለመሠራት፤ ሦስተኛም፣ በፌዴራል ደረጃ የወረደው የጋራ እቅድ ታች ላይ ተግባራዊ አለመሆን ውጤት ነው። ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘም፣ ቴክኖሎጂን የማፍለቅ ሂደት ከአሰልጣኞች የዕድገት ደረጃ ጋር መያያዝን ጉባኤው እንደ ችግር ተመልክቶታል።
ምክንያቱም አንድ አሰልጣኝ አንድ ቴክኖሎጂ ማውጣት አለበት የሚለው ሊያሠራቸው እንዳልቻለና ቴክኖሎጂው ደግሞ በባህሪው ለአንድ መምህር ቀርቶ በአንድ ተቋም ሊሠራ እንደማይችል በመገንዘብ መመሪያው መታየት እንዳለበት ግንዛቤ ተይዟል። ለዚህም ጥናት ተደርጎ በጥናቱ ግኝት መሰረት እንዲሠራ አቅጣጫ ተቀምጧል። ሆኖም ጥቃቅንና አነስተኛን መደገፍ እንደ ሸክም የሚታይ ሳይሆን ከዚህ ተቋም የሚጠበቅ እንደመሆኑ በዚህ ላይ ሁሉም በባለቤትነት መሥራት እንደሚገባቸው ነው የተቀመጠው።
የዘርፉን ገጽታ ከመገንባት አኳያ በተቋሞች የሚሠሩ ቴክኖሎጂዎችንና ሌሎችንም የፈጠራ ሥራዎች ፌስቲቫል በማዘጋጀት ህዝቡ እንዲያያቸውና ግንዛቤ እንዲይዝባቸው ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።ይሄንንም ከተቋም ጀምሮ ሁሉም በየደረጃው ካካሄደ በኋላ በዚህ ዓመት (ሰኔ መጀመሪያ) በአገር አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂ ፌስቲቫል የሚካሄድበት አቅጣጫ ተቀምጧል።
እንደ ማጠቃለያ
ጉባኤው በእነዚህና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በስፋት ተወያይቶና ችግሮችን ለይቶ አቅጣጫ አስቀምጠቋል። ሆኖም ችግሮቹ ሰፊና ሰብሰብ ያሉ እንደመሆናቸው በተወሰኑ ጊዜ ይፈታሉ ተብሎ አይወሰድም። እናም እንደየባህሪያቸው በአጭር፣ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የሚፈቱ ይሆናል። ከዚህ አኳያ ከላይ የተጠቃቀሱትን ጨምሮ በርከት ያሉ ሥራዎች በአራት ወር ውስጥ ይፈታሉ ተብሎ የተቀመጡ ሲሆን፤ የተቀሩት የተግባር እቅድ(አክሽን ፕላን) የሚፈልጉ ናቸው።
ምክንያቱም የፖሊሲና ስትራቴጂ ችግሮች አሉ፤ የአሠራርና አደረጃጀት ችግሮች አሉ፤ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂና የሰው ኃይል ችግሮች አሉ። ለምሳሌ፣ በዘርፉ የፋይናንስ ጉዳይ ትልቅ ችግር ነው። ይህ ግን የረዥም ጊዜ የፋይናንስ ምንጭ በማፈላለግ እንጂ በዚህ አራት ወር ውስጥ ሊፈታ አይችልም። በተመሳሳይ የሰው ኃይልና የመምህራን ችግርን በቀንም ሆነ በማታ መርሐ ግብሮች በምን መልኩ ሠርቶ ማብቃት ይቻላል በሚለው ላይ ሠርቶ የሚመጣ ውጤት ነው። የ”ሲ” አሰልጣኞችንም ወደ “ቢ” ደረጃ ለማሳደግ እንዴት ይኬዳል የሚለውም በተከናወነ ጥናት መሰረት ወደተግባር የሚገባ ይሆናል።
የምዘና ስርዓቱን ማሻሻል፣ በተለይ ከሐሰተኛ ማስረጃ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከማስወገድ አኳያ የምዘና ስርዓቱን የማዘመንና አገራዊ ባህሪ ማስያዝን ስለሚጠይቅም በዚህ ላይ የተጀመሩ ሥራዎች አሉ። እነዚህ ደግሞ በአጭር ጊዜ ሳይሆን በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ሥራ የሚፈቱ መሆናቸው ታይቷል። በመሆኑም ጉባኤው፣ በእቅድ ተይዘው ያልተፈጸሙትን ከማሳካትም ሆነ በስትራቴጂ የሚመለሱትን ሥራዎች ከዳር ለማድረስ እንዲቻል፤ የፌዴራል አካላት፣ ክልሎች፣ ኮሌጆችና አጋር አካላት በተናጥልም ሆነ በጋራ ለመሥራት የየድርሻቸውን ኃላፊነት ለመወጣት የቤት ሥራ የወሰዱበት ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 9/2011
በወንድወሰን ሽመልስ