ከስታርትአፕ ረቂቅ አዋጁ የሚጠበቁ በረከቶች

ዜና ትንታኔ

ስታርትአፕ ከዲጅታል ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ አዲስ ሃሳብ እንደመሆኑ በሀገር ደረጃ እስካሁን የሕግ ማሕቀፍ እንዳልተበጀለት ይታወቃል፡፡ ይሁንና አሁን ላይ የስታርትአፕ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቅርቡ አስታውቋል። ረቂቅ አዋጁ ምን አዲስ ነገሮችን እንደያዘ፣ ፋይዳውና የስታርትአፕ ምህዳርን ከማስፋት አንጻር ምን ድርሻ ይኖረዋል? ስንል የዘርፉ ባለሙያዎችን አነጋግረናል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በዋንኛነት ከስታርትአፕ ጋር ተያይዘው የሚነሱ አብዛኛዎቹን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችል መሆኑን የሚናገሩት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ስታርትአፕ ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ፤ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል ስታርትአፕ በመባል የሚታወቅ ቢዝነስ አልነበረም ይላሉ፡፡

ረቂቅ አዋጁ የስታርትአፕ ቢዝነስ በራሱ እንዲታወቅና ስታርትአፓች እነማን ናቸው? ሥራቸውስ ምንድን ነው? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት በግልጽ እንዲታወቅ የሚያደርግ ነው የሚሉት አቶ ሰላምይሁን፤ ስታርትአፕ ማነው ያልሆነውስ የሚለውን በመወሰን ለስታርትአፕ ስያሜ የሚሰጥ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሠረት ረቂቅ አዋጁ የሚመለከታቸው ስያሜ የተሰጣቸው ስታርትአፖች እንደሆኑም አመላክተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ የስታርትአፕ ሥነምህዳሩ ገንቢዎች የሚባሉት እንደ ኢንኩቬሽን፣ አክስለሬሽን፣ ኢንቨስትመንት እና የመሳሰሉ ፕሮግራሞች እንዳሉት ጠቅሰው፤ ለእነዚህም እውቅና እንደሚሰጥ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ፕሮግራሞች እስካሁን ድረስ ሥነምህዳሩ (በኢኮ ሲስተሙ) በግልጽ ስለማይታወቁ እውቅና እንዲያገኙ ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የፈንድ ፕሮግራም ያሉት መሆኑን ገልጸው፤ የመንግሥት የግራንት ፕሮግራም፣ ፈንድ ኦፍ ፈንድ የሚባል በካፒታል ገበያ የሚቋቋሙ እና የክሬዲቲየጋራንቲ ፈንድ በባንክ የሚቋቋሙ ሦስት ፈንዶች እውቅና የሰጠ ነው ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ እንዴት ይመራል የሚሉት ጉዳዮች በዋናኝነት የያዘ ነው የሚሉት አቶ ሰላምይሁን፤ የዲጂታል  ኢንፎርሜሽን ካውንስል የበላይ ጠባቂ የሚሆን ሲሆን፤ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ደግሞ አብዛኛውን የግራንትና ስያሜ የመስጠት ሥራው እንዲመራው የሚያሳይ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ ቀደም ሲል ፈጠራ የሚለው አዲስ ሃሳብ ወደ ገበያ ይገባል ወይስ አይገባም በሚሉ ሲነሱ የነበሩትን ክርክሮች ሳይቀር ረቂቅ አዋጁ ይፈታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢኖቬሽንና የሥራ ፈጠራ ሥነምህዳሩ (ኢኮ ሲስተሙ) አመጋግቦ ለመሄድ የሚያደርግ ጉዞን ያመቻቻል፡፡ ይህም ኮንቬሽናል ቢዝነሶችን አይመለከትም። አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝም የራሱ ፖሊሲ ስላለው በራሱ የሚሄድ ነው። ሌሎችም እንዲሁም በመደበኛ የሚሄድ ቢዝነሶች አዲስ የሚጀመሩ ስታርትአፕ ያልሆኑ ቢዝነሶችን በሌላ ማሕቀፍ የሚታዩ ይሆናል ብለዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ በአጠቃላይ ስታርትአፕ የተመለከቱ ጉዳዮችን ግልጽ የሚያደርግና የሚወሰን ሕግ ነው ያሉት አቶ ሰላም ይሁን፤ አብዛኛው እስካሁን ያሉ ችግሮች በአዋጁ የሚፈቱ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

አሁን ላይ ስታርትአፕ አዋጁን የመጨረሻው ረቂቅ ለፍትሕ ሚኒስቴር መላኩን ጠቅሰው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከታየ በኋላ የሚጸድቅበት ሁኔታ መኖሩን አመላክተዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ተግባራዊ ሲደረግ አሁን ላይ ስታርትአፕ ምህዳሩ እንዳይሰፋ እንቅፋት ሆኖ የቆየ አብዛኛዎቹን ጥያቄዎች ይመልሳል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአሸዋ ቴክኖሎጂ አክሲዮን ማህበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው፤ እስካሁን ድረስ የስታርትአፕ ምህዳሩ (ኢኮ ሲስተሙ) የተለያዩ ተግዳሮቶች ያሉበትና አስፈላጊ የሆነ የሕግ ማሕቀፍ ያልነበረው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ ከመጽደቁ በፊት ለሕዝብ ይፋ ሆኖ ሃሳብና አስተያየት የተሰጠበት እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፤ በረቂቅ አዋጁ በርካታ ጉዳዮችን በውስጡ የያዘ ነው። አንደኛውና ትልቁ ስታርትአፕ በራሱ ምንድነው ከሚለው የሚጀመር ነው። ስታርትአፕ የሚለው ሃሳብ እስከዛሬ ድረስ በሀገሪቱ ካለው ቢዝነስ አንጻር የተለየ ነገር ስላለው ያንን በሚገባ ለመለየት ያስችላል፡፡ ስታርትአፕ ጀማሪ ቢዝነስ ቢሆንም ጀማሪ ቢዝነሶች ሁሉ ግን ስታርትአፕ ሊባሉ አይችሉም፡፡ በአይነታቸው ለየት ያሉ ከፍ ያሉ የሕዝቡን ችግር የሚፈቱ መፍትሔዎች የያዙትን በውስጡ ያካተተ ነው ብለዋል፡፡

የስታርትአፖች ምህዳሩ (ኢኮ ሲስተሙ) በጣም ትልቅ ለሀገር እድገት፣ ለኢኮኖሚ እድገት፣ ለሥራ እድል ፈጠራ እና የሕዝቡን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው፡፡ ወደ ኋላ ሲጎትቱት ከነበሩ ተግዳሮቶች አንዱ የፖሊሲ አለመኖር እንደሆነ ጠቅሰው፤ ፖሊሲ አለመኖሩ የስታርትአፕ ሥነምህዳሩ እንዳይስፋፋ፣ እንዳያድግና የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዳይችል አድርጎት መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡

እነዚህ ተግዳሮቶች ምክንያት ደግሞ ሀገር ውስጥ ሆነ ውጭ ያለው ባለሀብት ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችለው ሁኔታ ስለሌለ ወደኋላ እንዲል ያደረገው መሆኑን ገልጸው፤ የተለያዩ ኢንኩቤተሮች በዘርፉ ላይ እየገቡ ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን ኢንቨስት አድርገው እንዳይሰሩበት እና ሌሎችን ተግዳሮቶች እንዲኖሩ አድርጓል ይላሉ፡፡ እሳቸው እንዳብራሩት፤ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የስታርትአፕ ሥነምህዳሩ (ኢኮ ሲስተሙ) ላይ ያለው እንቅስቃሴ በዓለም ላይ ካለው ከአንድ በመቶ በታች መሆኑን ነው። የዓለም ባንክ መረጃዎችም የስታርትአፕ ሥነ ምህዳር በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉ የሚያሳዩ ናቸው፡፡በተለይ ፋይናንስ ከማግኘት አንጻር ብዙ ችግሮች እንዳሉ ያሳያል፡፡

አዋጁ የስታርትአፖች ሥነምህዳሩ (ኢኮ ሲስተም) በሕግ የታቀፈ እንዲሆን ያስችላል የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ በተለይም ስታርትአፖች የሚገጥሟቸውን የፋይናንስ ችግር በመቅረፍ ረገድ ሰፊ አማራጮች የያዘ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ በተጨማሪም ኢንኩቤሽን ማዕከላት በደንብ እንዲጠናከሩና ሥራቸውን ለማስፋት ሰፊ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

‹‹እኔ እንዳየሁት አዋጁ በጣም ብዙ ተግዳሮቶችን የሚፈታ ነው›› የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ በፍጥነት ተግባራዊ ቢደረግ ብዙ ተግዳሮቶችን በመፍታት ዘርፉ እንዲያብብ የሚያደርግ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You