እስካሁን ከመኸር እርሻ 374 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፡- በ2016/17 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት እርሻ 374 ሚሊዮን 149 ሺህ 498 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2016/17 የመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው 20 ሚሊዮን 528 ሺህ 697 ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ድረስ 17 ሚሊዮን 642 ሺህ 512 ሄክታር መሬት ሰብል ተሰብስቧል፡፡ከዚህም 374 ሚሊዮን 149 ሺህ 498 ኩንታል ምርት መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል፡፡

በምርት ዘመኑ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ሲዳማ፣ ትግራይ፣ ሀረሪ ክልሎች እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 20 ሚሊዮን 411 ሺህ 450 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፍን ታቅዶ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው፤ 15 ሚሊዮን 742 ሺህ 408 ሄክታር መሬት በባህላዊ፣ 5 ሚሊዮን 49 ሺህ 114 ሄክታር በትራክተር በድምሩ 20 ሚሊዮን 791 ሺህ 522 ሄክታር ማረስ ተችሏል፡፡ ከዚህ ውስጥ 20 ሚሊዮን 528 ሺህ 697 ሄክታር መሬት በመኸር ዘር መሸፈኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተጠቀሰው ጊዜ በዘር ከተሸፈነው አጠቃላይ መሬት ውስጥ 11 ሚሊዮን 833 ሺህ 603 ሄክታር የሚሆነው መሬት በክላስተር የተዘራ እንደሆነም አቶ ኢሳያስ አመላክተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በተያዘው 2016/17 ምርት ዘመን በመኸር ወቅት በዳግም ሰብል በአማራ ፣ በኦሮሚያ ፣ ትግራይ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች 900 ሺህ 818 ሄክታር መሬት በመሸፈን 9 ሚሊዮን 895 ሺህ 335 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን 517 ሺህ 663 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።

በአርሶ አደሩ ጉልበት ከሚሰበሰበው ምርት በተጨማሪ በሜካናይዝድ ዘዴ ምርት የመሰብሰብ ሥራ መሠራቱን ገልጸው፤ ቀሪውን ምርት ለመሰብሰብ በተቀናጀ መንገድ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።በምርት አሰባሰብ ወቅት ብክነት እንዳይከሰት ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

በሌላ በኩል በ2016/17 ምርት ዘመን በመንግሥት ዘር አምራችና በግል አባዢ ድርጅቶች እንዲሁም በክልሎች 148 ሺህ 43 ሄክታር መሬት በምርጥ ዘር ብዜት ለመሸፈን ታቅዶ 83 ሺህ 635 ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ ከዚህ ውስጥ 734 ሺህ 829 ኩንታል የዘር ምርት መሰብሰቡን ጠቁመዋል፡፡

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You