“መንግሥት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በኅብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ ድርጊቶች እየተከታተለ እርምጃ ይወስዳል” -ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡- መንግሥት ምክንያታዊ ባልሆነ መንገድ በኅብረተሰቡ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የትኛውንም አይነት ድርጊቶች እየተከታታለ እርምጃ እንሚወስድ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በጥር ወር የመጀመሪያዎቹ ቀናት የዓለም አቀፉ የነዳጅ መሸጫ አማካይ ዋጋ በሊትር 1 ነጥብ 25 የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ በሊትር በ0 ነጥብ 805 የአሜሪካን ዶላር እየተሸጠ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ዋጋ ከዓለም አቀፉ አማካይ የመሸጫ ዋጋ የ35 በመቶ ቅናሽ አለው ያሉት ለገሰ (ዶ/ር)፤ ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች አኳያም በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በኬንያ 1 ነጥብ 351፣ በሩዋንዳ 1ነጥብ 136፣ በኡጋንዳ 1ነጥብ 299፣ በታንዛንያ 1ነጥብ 127፣ ማላዊ በ1 ነጥብ 459፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ 1ነጥብ 746 እንዲሁም በአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች ከ1 ነጥብ 3 የአሜሪካ ዶላር በላይ እየተሸጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የሰሞኑን የነዳጅ ጭማሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን የእግር እሳት የሚሆኑባቸው አንዳንድ ወገኖች እንደተለመደው በባንዳነት ተግባር ተጠምደዋል ነው ያሉት።

እነዚህ ባንዳዎች የሚኖሩባቸው ሀገሮች የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ፈጽሞ አይታያቸውም፤ ራሳቸውን ለሕዝቡ አሳቢና ተቆርቋሪ ሌላውን ደግሞ ለሕዝቡ ችግሮች ደንታ ቢስ አድርገው እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

ይህን የሚያደርጉት እውነታውን ስለማያውቁ ሳይሆን ድብቁ ባህሪያቸው እንዳይገለጥ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ተሳስተው እንኳን በየአካባቢዎቹ ስላለው በጎ የልማት እንቅስቃሴ፣ የሰላም ሁኔታ፣ በኅብረተሰቡ መካከል መግባባት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን እንደማያነሱ ገልጸዋል፡፡ሃሳቦችን ማመንጨት፣ ጥናትና ፈጠራ፣ ተጨባጭ አብነትና የሃሳብ ልዕልናን ስለሚጠይቅ ነው፤ እነሱ ይህ የላቸውም በማለት ድርጊታቸውን ኮንነዋል፡፡

“በየአካባቢው የተፈጠሩ ትናንሽ ክስተቶች በወሬ ለቃሚዎቻቸው አማካይነት እየቃረሙ ቆርጦ በመቀጠል እኩይ ፍላጎታቸውን ማሳካት ነው፤ የሚያተርፉት ከግጭት፣ ከሁከትና ግርግር ነው፤ ሰው መረጃ የሚያገኝም አይመስላቸውም። ነውር የሚባል ነገር በደጃቸው አልዞረም። ነፃ ገበያ እና በነፃ ገበያው ውስጥ የመንግሥት ሚና ሚዛን መጠበቅ መሆኑ ለነሱ ምንም ነው፣” ያሉት ሚኒስትሩ በጽሑፋቸው፤

“በነጻ ገበያ ውስጥ ይቅርና በሶሻሊስት ሥርዓት መንግሥት እንዲያደርግ የማይገደድባቸው ጉዳዮችን በማንሳት መንግሥትን ይከሳሉ፡፡ መረጃዎችን በማዛባት ለራስ እኩይ የፖለቲካ ፍላጎት ለመጠቀም የሚደረግ ሙከራ የቱንም ያህል ርቀት አይወስድም” ብለዋል።

“መንግሥት ልማትን ለማፋጠን የሚወሰዱ እርምጃዎች በማህበረሰቡ ላይ ጫና ሊያሳድሩ እንደሚችሉ ይገነዘባል፤ በጥንቃቄ መፈፀም እንደሚገባም ያምናል፤ ለዚህም አቅዶ እና አልሞ የኅብረተሰቡን ዘላቂ ጥቅም መሠረት አድርጎ ይሠራል፤ ሸክሙን በመጋራት ጊዜያዊ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ይረዳል” ሲሉ አመልክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለነዳጅ፣ ለአፈር ማዳበሪያ፣ ለመድኃኒትና መሰል የጤና ጉዳዮች በዓመት ከፍተኛ የሚባለውን ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ ድጎማ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፍጥነት እና ፈጠራን መሠረት ያደረጉ ለነገው ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑና የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን የሚያደርጉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮች እና የልማት ፕሮግራሞችን እውን እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የሰብል ምርት (የስንዴ፣ በቆሎ፣ ማሽላ፣ገብስ፣ሩዝ፣ ጤፍ)፣ የሌማት ቱሩፋት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ኢኒሼቲቮች ወደ ሁሉም አካባቢዎች ወርደው በውጤታማነት እየተተገበሩ ስለመሆናቸው ጠቅሰዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመጥኑ ከተሞችን እየገነባ ነው። የገጠሩን የአኗኗር ሁኔታና የመሠረተ ልማት አቅርቦት ታሳቢ ያደረገ ሥራም ተጀምሯል ብለዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያውን ተከትሎ በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ማዕድን ላይ የተደረገው ማሻሻያ ገና ግማሽ ዓመት ሳይሞላ ለሀገሪቷ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያስገኘ መሆኑን ጠቁመው፤ ሕዝቡንም ተጠቃሚ በማድረግ የአኗኗር ዘይቤውን እየለወጡት መሆኑን መንግሥት በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።

“መንግሥት ሰላምን በማስፈን የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ውጤታማ እየሆነ ነው፤ እነዚህን ማጽናት፣ ዘላቂ እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል” በማለት በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት አሳስበዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You