በሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ የተጣለው ቅጣት የሀገር እና የሕዝብ ሀብትን እንደሚታደግ ተገለጸ

አዲስ አበባ፡- በሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ የተጣለው የእስር እና የገንዘብ ቅጣት በሀገር እና በሕዝብ ሀብት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን እንደሚታደግ ተገለጸ፡፡

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ በአራተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ትናንት ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባው የነዳጅ ውጤቶችን ግብይት ሥርዓት ለመደንገግ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል፡፡

የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አይሻ ያህያ ረቂቅ አዋጁን አስመልክተው ለምክር ቤት አባላቱ እንዳብራሩት፤ የነዳጅ ውጤቶች ካላቸው ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ፋይዳ አንጻር ስትራቴጂክ ምርቶች ናቸው፡፡ አቅርቦታቸው፣ ክምችታቸው፣ ስርጭታቸው ፣ ደህንነታቸው እና ጥራታቸው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆን ይኖርበታል፡፡ በሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ የተጣለው የእስር እና የገንዘብ ቅጣት በሀገር እና በሕዝብ ሀብት ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን የሚታደግ ነው፡፡

ከነዳጅ አስመጪዎች ጀምሮ እስከታችኛው ተጠቃሚ ድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፣ ቀልጣፋ፣ ግልጽ አስተማማኝ፣ ፍትሐዊ እና ተደራሽ የአቅርቦት፣ የስርጭትና የችርቻሮ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ያሉት ሰብሳቢዋ፤ በነዳጅ ውጤቶች የግብይት ሰንሰለቶች ውስጥ እየታዩ ያሉ ሕገ-ወጥ ተግዳሮቶችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ነዳጅ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገዛ፤ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የግብይት ሥርዓቱ በጥንቃቄና በአግባቡ ሊመራ እንደሚገባ አመልክተው፤ በዚህም የተነሳ የነዳጅ ውጤቶችን ግብይት ሥርዓት ለማስያዝ የሚያግዝ ሕግ ማውጣት አስፈልጓል ነው ያሉት፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ ነዳጅ እያለ ሆነ ብሎ ገበያውን ለማወክና ለግል ጥቅም ሲባል ነዳጅ የለም የሚሉ ማደያዎች መኖራቸውን እና ነዳጅን በኮንትሮባንድ የሚነግዱ አካላት እንዳሉ ጠቅሰዋል፤ እነዚህ አካላት ከሥራ ቢታገዱ ኅብረተሰቡ የበለጠ ተጎጂ ስለሚሆን በቅጣት ታርመው ሥርዓት ይዘው እንዲሠሩ ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል፡፡

እንደ ሀገር ያለው የነዳጅ ማደያዎች ብዛት በቂ አለመሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ ከ500 በላይ ወረዳዎች አሁን ድረስ የነዳጅ ማደያ እንደሌላቸው አመላክተዋል፡፡ ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት አንጻር ሲታይ ኢትዮጵያ ትንሽ ወይም ያልተመጣጠነ ማደያ እንዳላትም ጠቅሰዋል፡፡

ነዳጅ ማደያዎች ሕገ-ወጥ የነዳጅ ዝውውርና ኮንትሮባንድ ንግድን ማዕከል አድርገው እየተገነቡ ያሉት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በሌላቸው ጠረፋማ አካባቢዎች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የአቅርቦት አለመመጣጠን እንዲባባስ ያደረጉትም እንደዚህ አይነቶቹ ችግሮች ጭምር መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አቅርቦትን ከፍላጎት ጋር ለማጣጣም በየጊዜው ጥናት እያደረገ ማሻሻያ የሚያደርግ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የነዳጅ ማደያ ግንባታ ፈቃድ የሚሰጠው አዋጭነቱ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት እና በሌሎች አካባቢያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ የማያሳድር መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነው ብለዋል፡፡

አዋጁ በአጠቃላይ በነዳጅ ግብይት ላይ የሚታየውን ሕገ-ወጥ ግብይት ሥርዓት ለማስያዝ የሚረዳ፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን እና አሠራሮችንም የሚያዘምን ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

እያንዳንዱ ማደያ ምን ያህል ነዳጅ አለው? እንዴት አይነት አገልግሎት እየሰጠ ነው? የሚለውንም ጭምር ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ከኢትዮ ቴሌኮምና ከሚመለከታቸው ድርጅቶች ጋር በመተባበር የግብይት ሥርዓቱን ለማስተካከል ይሠራል ብለዋል፡፡

የተጣለው ቅጣት የተጋነነ አይደለም ያሉት ወይዘሮ ሳህረላ፤ አንድ የነዳጅ ቦቴ በአንድ ጉዞ ሸጦ ሊያተርፍ ከሚችለው አንጻር በጣም አነስተኛ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

አዋጁ እስከ አስር ዓመት ጽኑ እስራት እና እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ቅጣት የሚያስጥል ድንጋጌ ያለው ሲሆን፤ በሁለት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምፀ-ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አዋጅ ቁጥር 1363/2017 ሆኖ ጸድቋል፡፡

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You