“ቅርስ እንደ ኩል” – የማዋዣ ወግ፤
ቅርስና ኩልን ምን ያገናቸኛዋል? ምንም አያገናኛቸውም። “እንደ” ተብለው በተነጻጻሪ አያያዥ መጣመራቸው ለርዕሰ ጉዳያችን ማዋዣነት ይበጁ ይሆን ብለን በማሰብ እንጂ አንዱ ከአንዱ ጋር የባህርይም ሆነ የተፈጥሮ ዝምድና የላቸውም። ኩል የወይዛዝርት መኳኳያና መዋቢያ ነው። ለዐይን ጥራትና ቁርቋሬም እንደ መፍትሔ ተቆጥሮ ከመድኃኒት ዝርያ ጋር የሚያዛምዱ ግለሰቦችም እንዳሉ ይታወቃል።
ኩል የተፈጠረበት ዋናው ዓላማ ለመዋቢያነት አገልግሎት ስለሆነ ተዘውትሮ የሚጎዳኘው ለቅንድብና ለሽፋሽፍት መሽቀርቀሪያነት እንጂ፤ በተቀጥያ ተግባሩ እጅግም ይወደስ አይባልም። እንዲያም ሆኖ ግን በአጠቃቀም ወቅት ጥንቃቄና መጠኑ በዝቶ ዐይን ላይ ሲሞጀር ወይዛዝርት የሚኳሉበትና “እረ ኩሉን ማን ኳለሽ” እየተባለ የሚደነቁበት ኩል መዋቢያነቱ ቀርቶ ዕይታን እየጋረደ ለእንቅፋት ይዳርጋል። ይህንን እውነታ የተረዱት እናቶች ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው ሲመክሩ፤ “ሲያጌጡ ይመላለጡ” እንዳይሆንባቸው ለማስጠንቀቅ “ባለ ኩል ያሰናክል” የሚለውን ብሂል እንደሚጠቀሙ ሥነ ቃላችን ይመሰክርልናል።
ከወይዛዝርት የመዋቢያ ኩል ጋር በስሱም ቢሆን ለማመሳሰል የሞከርነው አገራዊ ቅርስ ልክ እንደ ኩል ሁሉ የታሪክ ውበት ወይንም መቆዘሚያ ሆኖ ለትውልዶች በቅብብሎሽ የሚተላለፍ ምስክር እንጂ ራሱ ታሪክ አይደለም። ለቁንጅና ሲባል የሚመረጠው ኩል እየተመጠነና በጥንቃቄ ግልጋሎት ላይ ካልዋለ በስተቀር ዐይንን እያጥበረበረና እየቆረቆረ ለእንቅፋት እንደሚዳርግ ሁሉ፤ ለታሪካችን ምስክር ሆነው የኖሩና እንደ አንድ የአገር ጌጥ በክብር መታየት የሚገባቸው ቅርሶቻችንም እንዲሁ ወካይ እንጂ የታሪኩ ዋነኛው አካል ያለመሆናቸው እየተዘነጋ አልፎ አልፎ በእንቅፋትነት ሲነወሩ ይስተዋላል።
በተንሸዋረሩ የታሪክ አተያየቶችና አተረጓጎሞች ምክንያትም የጋራ ያልናቸው ታሪካዊ ቅርሶች ከውበታቸውና ከታሪካዊ ወካይ ፋይዳቸው ይልቅ የእርስ በእርስ መሰነካከያና እንቅፋት በመሆን በአብሮነታችን ድምቀት ላይ ጥላ እያጠሉ ብርሃናማውን የሕዝቦች ትስስርና ተጋምዶ እየጋረዱ “ባህል” ወደ መሆን ደረጃ ላይ የተደረሰ ይመስላል። የታሪኮቻችን መገለጫዎችና ውበት አድርገን ተቀብለናቸው የኖርነውና በኩል የመሰልናቸው አንዳንድ ቅርሶቻችን ከመዋቢያነት ይልቅ ለምን ጥላሸት እየሆኑ ስንጎሻሸምባቸውና ስንደነቃቀፍባቸው ውለን እንደምናድርም ልብ ተቀልብ ሆነን ልንመካከርበት ይገባል።
ቅርስ ማርከስ ታሪክን ማስኮረፍ፤
በአገራዊ ቅርስነት የምንፈርጃቸው የሕዝባችን የታሪክ ምስክሮች፣ የባህሎቻችን ውበቶችና የእምነቶቻችን ትሩፋቶች ዓይነታቸው፣ መልካቸውም ሆነ ቁጥራቸው በዋዛ ተዝርዝሮ የሚገለጽ አይደለም። የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ፣ ተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ወዘተ. እያልን በፈርጅ በፈርጃቸው እየመደብን እንተንትናቸው ብንል በተከታታይ የመጻሕፍት ቅጾችም ቢሆን ሰንዶ ለማጠናቀቅ ተግዳሮቱ ቀላል እንደማይሆን መገመት አይከብድም።
በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጥንታዊና በታሪካቸው የከበሩ አገራት ዋነኛ መታወቂያቸውና መከበሪያቸው የተትረፈረፈው የቅርስ ሀብታቸው እንደሆነ በሚገባ ይታወቃል። የአገራት የቅርስ ሀብቶች በአግባቡ ተሰንደውና ተሰድረው ከብረው እያስከበሩ እንዳይኖሩ በተለያዩ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ በየዘመናቱ ለአደጋ መጋለጣቸው አልቀረም። “አዋጁን በአዋጁ” እንዳይባል እንጂ በቅርሶቻችን ላይ የሚደረሱትን ውድመቶችና ዘረፋዎች፣ ዳተኝነቶችና ንዝህላልነቶች በተመለከተ ብዙ ጊዜያት ብዙ ስለተባለ በዚህ ቦታ ደግመን ነጋሪት መጎሰሙ እጅግም አስፈላጊ አልመሰለንም።
ያለመታደል ሆኖ በበረሃና በባህር፣ ኬላ አሳብረውና ወንዝ አቋርጠው ወይንም ቪዛ እያስመቱና ሕጋዊ ሰነድ እያውለበለቡ ለስደት የሚዳረጉት ዜጎቻችን ብቻ ሳይሆኑ አገራዊ ቅርሶቻችን ጭምር ናቸው። በአንዱ ዐይናችን ለዜጎቻችን፣ በሁለተኛው ዐይናችን ለቅርሶቻችን እምባ እንዳፈሰስንና በቁጭት እንደተንገበገብን እነሆ ዘመን በዘመን ላይ፤ ሥርዓትም በሥርዓት ላይ ተነባብሮ ለዛሬ ጀምበር በቅተናል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ እንኳንም በኩብለላ እየሸሹን ላሉት ወይንም ለኮበለሉብን የሩቅ አገር ነዋሪ “ስደተኛና ምርኮኛ ቅርሶቻችን” ቀርቶ የታሪካቸው እትብት በተቆራኘበት በራሳቸው ሕዝብና አገር ውስጥ የሚኖሩት ታሪክና ውበት አጣምረው የያዙት ቅርሶቻችንም ሳይቀሩ የተለያዩ የጥፋት አደጋዎች እየተጋረጠባቸው መሆኑን ተቆርቋሪ ዜጎች በነጋ በጠባ ኡኡታቸውን እያሰሙ ስለመሆናቸው አልሰማንም ማለት አንችልም። “እዚያ ሰፈር ታሪካዊ ሕንጻዎች እየፈረሱ ለባለ ሃብቶች ብሎኬት መደርደሪያነት ሊሰጡ መወሰኑን ሰምተናል” የሚሉ ኡኡታዎች ይደመጣሉ።
ወዲያ ማዶ ደግሞ “ለሥዕል ጥበብ ማሳያነት ግልጋሎት ሲሰጥ የኖረ ታሪካዊ ሕንጻ ‹ለሪፎርሚስት ቢሮክራቶች› በቢሮነት እንዲያገለግል እየተሸነሸነ በመታደል ላይ ነው” የሚል ጩኸት ይደመጣል። መሃል ከተማችን ላይ ገዝፎ የሚገኘው ታላቅ ታሪካዊ ቅርስ “ምን ፋይዳ አለው” በማለት የሚያክፋፉ “ውሎ ገቦች” በገሶና በአካፋ ካላፈረስን እያሉ ለያዥ ለገራዥ ማስተቸገራቸው ያልመሸበት የትናንት ትዝታችን ነው። በታሪክ ስም ታሪክን ለማምከን የሚጥሩ፣ በእውነት ስም እውነትን ለመስቀል እንቅልፍ የሚያጡ ፀረ ቅርስ ዜጎች መገኛቸው የትም መሆኑን በርካታ አጋጣሚዎችንና አካባቢዎችን በመጥቀስ ማስታወስ ይቻላል።
የተለጠጠውን ትዝብታችንን ትንሽ ሰብሰብ አድርገን “ትዝታ አያረጅም” እንዲሉ አንድ ነጠላ ጉዳይን ብቻ መዘን እናስታውስ። በቀዳሚዎቹ ዘመናት እንደ ባህል ተቆጥሮ በበርካታ መንግሥታዊ ተቋማትና የኃላፊዎች ቢሮ ውስጥ የአገራችን ታላላቅ ሠዓሊያን የጥብብ ስራዎች በየግድግዳዎች ላይ ተሰቅለው ታሪክና ውበትን እንዲያሳዩ ይደረግ እንደነበር ዕድሜውን ያደለን ዜጎች ምስክሮች ነን።
ዓመታቱ ቢርቅም አንድ ጉዳይ እናስታውስ። በዛሬው የፓርላማ ሕንጻ የፊት ለፊት ገጽ ላይ የሦስትዮሽ ሥዕሎች (በሞዛይክ ጥበብ የተከሸኑ ሳይሆኑ አይቀሩም(?)” ተደርድረው አላፊ አግዳሚውን ይማርኩ እንደነበር ጸሐፊውን መሰል ለታሪኩ ምስክር የሆኑ ዜጎች የሚዘነጉት አይደለም። በፓርላማው የውስጠኛው ክፍሎች ደግሞ አገኘሁ እንግዳና እምአእላፍ ኅሩይን የመሳሰሉ የዘመኑ ጠቢባን የተራቀቁባቸው ሥዕሎች በየግድግዳው ላይ በክብር ተሰቅለው ስሜትን በሀሴት ያረሰርሱ ነበር።
ይህ ጸሐፊም በታዳጊነት የዕድሜ ዘመኑ ይማርበት ከነበረው የቀድሞ አራት ኪሎ ወወክማ ከብጤዎቹ ታዳጊዎች ጋር ፕሮግራም እየተመቻቸ ያንን የንጉሠ ነገሥቱን ግዙፍ የወንበረተኞች መንበር ደጋግሞ ለመጎብኘት ዕድል አጋጥሞት ስለነበር ዛሬም ድረስ ትዝታው ከአእምሮው ሊደበዝዝ አልቻለም። የደርግ መንግሥት ገና ሥልጣን ላይ እንደተቆናጠጠ ፈጥኖ የወሰደው እርምጃ እኒህን መሰል የታሪክ ምስክሮችን ማጥፋት ነበር። ታሪክ ፍርድ አሰጣጡን ያውቅበታልና ዳኝነቱን ከእርሱ እንጠብቃለን። እንዲያም ቢሆን ግን እነዚያ ክቡር የታሪክ ማስታወሻ ሥዕሎች የት እንደወደቁ ዛሬ ላይ ቆመን ብንጠይቅ ረፈዶባችኋል አሰኝቶ በይርጋ ሊዘጋ አይገባውም።
የሥዕልን ነገር ካነሳን ዘንድ ለዚህ ጽሑፍ መቆስቆሻ የሆነውን የሰሞኑን አንድ ክስተት እግረ መንገድ እናስታውስ። በሠንጋ ተራ አካባቢ በሚገኘው የቀድሞው የሞርጌጅ ባንክ፤ ዛሬ ብሔራዊ ባንክ በወረሰው ሕንጻ ወደ ውስጥ ሲዘለቅ የታላቁ የሥዕል ባለሙያ የገብረ ክርስቶስ ደስታ ገጸ ምድር (ላንድ ስኬፕ) ሥዕል በግዙፉ ግርግዳ ላይ ዧ ብሎ ተዘርግቶ የአላፊ አግዳሚውን ቀልብ፣ መንፈስና ስሜት በመማረክ የደስታ ምክንያት ሆኖ ከግማሽ ክፍል ዘመን በላይ እንደኖረ የሚያውቁ ያውቁታል። መኖሪያ ቤት ለመገንባትና የባንኩን ቢሮክራቶች ደጅ ለመጥናት ይመላለሱ ለነበሩ “ደም የለሽ ቤተ ሠሪዎች” ያ ሥዕል የስሜት መረጋጋት ይሰጥ እንደነበር ጎጇችንን በባንኩ ብድር ያዋቀርን በርካታ ዜጎች የምንዘነጋው አይደለም።
እንዳለመታደል ሆኖ ከሰሞኑ ያን የመሰለ የሥዕል ጥበብ ያረፈበት ግርግዳ በፓርቲሽን እየተከፋፈለ ለቢሮ አገልግሎት እንዲውል መደረጉን ያስተዋልነው እምባና ሣግ እየተናነቀን ነው። ያንን በመሰለ ግዙፍ ሕንጻ ላይ ቦታ ሳይጠብ ለምን ያ ድንቅ የጥብብ ሥራ እንዲረክስ እንደተደረገ በእውነቱ ምክንያቱ ግልጽ አይደለም። ይህንን የልብ ሀዘን በፎቶግራፍ አስደግፌ የላክሁለት አንጋፋው የሥዕል ጠቢብ ወዳጄ እሸቱ ጥሩነህ “ጥበብ ምን ተዳቸው” የሆኑ የተቋሙ ኃላፊዎች የፈጸሙትን ይህንን መሰል ግዙፍ ስህተት ከተመለከተ በኋላ በግሉ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ የሰጠው አስተያየት እንዲህ የሚል ነው።
“አኹንም በሕግ አምላክ! በጥበብ አምላክ! ጸረ የጥበብ ቅርስ በተለይም የሥዕል ጥበባት አጥፊዎችና አውዳሚዎች እንደ ተስቦ በሽታ!…የዛሬ ሃምሳ ዓመት በሞርጌጅ ባንክ የእንግዳ መቀበያና ማረፊያ አዳራሽ ውስጥ በሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ የተሣለውና የተቀባው ኪነ ግድግዳ ሥዕል (Monumental Art) [እንዳልነበረ ሆኗል]። …ኪነ ግድግዳ ሥዕሉን ያሠራው ልበ ብርሃኑ የቀድሞ ሥራ አስኪያጅ ነው። [ምን ያደርጋል?] ከሃምሳ ዓመት በኋላ የሚመጣውን ልበ ጨለማ የባንክ ትውልድን አለማወቁ ነው! በሕይወት ካለ እንዴት ይቆጨው… ሌላው ቢቀር በዘመኑ በስንት ብር ተሰራ? ከዚያም የሥዕሉ ዕድሜ የሚያስገኘው እሴት! አልፎም ቅርስነቱ ያውም የሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ሥዕል ነው መባሉ ብቻ ምን ያህል ባንኩን ባኮራው ነበር።”
አገራዊ ውበትንና ታሪክን አጣምሮ የያዘ የጥበብ ቅርስ የሚመሰለው በዘር እህል ነው። የዘር እህል አይበላም። የዘር እህል የሚቀመጠው በጥንቃቄ ነው። በክፉ ዘመን እንኳን ቢሆን “መቼም አላለኝ ከዘሩ ቁይልኝ” እንዳለው ምስኪን አርሶ አደር ለጊዜያዊ ፍጆታ አይውልም። ለምን ቢሉ ቅርስ በትውልዶች መካከል መታሰቢያ ሆኖ የሚቆም ምስክር እንጂ የመጣና የሄደው ሁሉ የሚቆነጥረው፣ የጠገበ አሌ እየተነሳ ዱላ የሚያሳርፍበት ወይንም ለጊዜያዊ ጥቅም ማርኪያ አልፎ የሚሰጥ “የመስዋእት በግ” ይሉት ብጤ አይደለም። ለጋራ አገራዊ የጥበብ ሀብት ተቆርቋሪ ሆነን የምንጮኸው ጩኸት እንደሚደመጥ ተስፋ እናደርጋለን።
አሳፋሪው የባንኩ እርምጃ አሳስቦት ይህ ጸሐፊ ሰባ አምስት ዓመቱን ሊያከብር ሽር ጉድ ማለት ወደጀመረው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሥራ ኃላፊ ወዳጁ ዘንድ ስልክ ደውሎ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው። በቅርቡ በህልፈተ ሕይወት ከተለዩን ዐሥር ዓመት የሆናቸው የታላቁ የጥበብ ሰው የሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ እጅግ አስደናቂ ሥዕል በዚያ አንጋፋ ሆስፒታል ዋና ግድግዳ ላይ ተንጣሎ እንደሚገኝ ይህ ጸሐፊ በሚገባ ያውቅ ስለነበረ ምናልባትም ያም ሥዕል “የሞርጌጅ” ባንኩ ጓደኛው ዕጣ ደርሶት ይሆን ወይ ብሎ በመጠራጠሩ ነበር። ምሥጋና ለሆስፒታሉ የሥራ ኃላፊዎች ይድረስና እንኳንም ሥዕሉ ሊጎሳቆል ቀርቶ በቅርቡ በተሻለ ይዞታ እንክብካቤ ሊደረግለት እንደታሰበ ተጠቁሜያለሁ። እንደነገሩኝ የሚሆን ከሆነ በርግጥም የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉ ሲከበር በቦታው ተገኝተን እናመሰግናለን።
ኅሊናችን የሚመሰክርልንን አንድ እውነታ እናስታውስ። አሁን እያስተዳደሩን ያሉት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ከአብዛኞቹ ቀደምት መሪዎች ስሜታቸው ለጥበብ ቅርብ እንደሆነ ባንመሰክር አደራ በል እንሆናለን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን በያዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጀመሪያ ሥራቸው ካደረጓቸው ተግባራት መካከል አንዱ የእንጦጦን የሥዕል ጋላሪ ማሰራታቸው ነው።
ቢያንስ ለዚህ ታላቅ ተግባራቸው፣ አብርሆትን ያህል ግዙፍና ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት በአራት ኪሎ እምብርት ላይ ማቆማቸውና ለመጀመሪያ ጊዜ “ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች” በማለት ከየጥበብ ዘርፉ በተመረጡ ጎምቱ ባለሙያዎች አንገት ላይ የወርቅ ሜዳሊያ በማጥለቅ ማክበራቸው እጅግ የሚያስመሰግናቸው ነው። በአንጻሩ “ጥበብን ለማርከስ” የሚዳፈሩ ሹመኞቻቸው የሚሰሯቸውን የማፍረስ ተልዕኮ በቅርበት እየተከታተሉ ቢገሯቸውና ቢያርቋቸው ጫጫታው ሊቀንስ ስለሚችል አደራችንን እንዲቀበሉ መልእክታችን ይድረስ እንላለን። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 12 /2014