አገር የግለሰቦች አስተሳሰብ ናት። አገር የምትቆመው በእኔና በእናንተ በጎ ሀሳብ ነው። ዜግነት ከዚህ ውጪ ትርጉም የለውም። አሁን ላይ እኔና እናንተ የምንሆነው ነገር ነው የአገራችንን የወደፊት ዕጣ የሚወስነው። አገራችን ለእኛ ምቹና አስፈላጊ እንድትሆን ከሁሉ በፊት እኛ ለአገራችን ምቹና አስፈላጊዎች መሆን ይጠበቅብናል። ለአገራችን መልካሙን ሳናዋጣ፣ ለሕዝባችን በጎውን ሳናደርግ አገርና መንግሥትን ብንወቅስ ዋጋ የለውም። ብዙዎቻችን ማድረግ ያለብንን ሳናደርግ ለወቀሳ የምንቸኩል ነን። ከእኛ የሚጠበቅብንን ሳናደርግ ለትችት የምንሮጥ ነን። ይሄን ሀሳብ እንዳነሳ ያደረገኝ ወቅታዊውና ብዙዎቻችንን ያማረረውን የኑሮ ውድነት ነው። በአገራችን ሁሉም ቦታ የኑሮ ውድነት ተከስቷል። ይሄ የኑሮ ውድነት እንዴት መጣ ብለን ስንጠይቅ መጀመሪያ የምናገኘው መልስ በስግብግብ ነጋዴዎች አማካኝነት የመጣ እንደሆነ ነው። እርግጥ ለዚህ የኑሮ ውድነት የሰሜኑን ጦርነት፣ የኮሮና ወረርሽኝን፣ የፖለቲካ ሽኩቻውን እንዲሁም የገንዘብ የመግዛት አቅም መውረድና ሌሎች ምክንያቶችን መጥቀስ እንችላለን።
እነዚህ ሁሉ ችግሮች እንዳሉ ሆነው ግን የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት እኚህ «የቀን ጅቦች» ያልኳቸው በአቋራጭ መበልጸግ የሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ናቸው። በየትኛውም መመዘኛ ብንመዝነው በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ያን ያክል የምርትና የአቅርቦት ችግር አለ ተብሎ አይታሰብም። ነገር ግን አንዳንድ ነጋዴዎች የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ምርት በመደበቅና ዋጋ በማናር ለአገራችን ተጨማሪ ስቃይን ፈጥረዋል። እኚህ ነጋዴዎች በወንጀል ሥራ ረጅም ሰንሰለት ያላቸው ናቸው። የመንግሥትን የሥራ ኃላፊዎች እጅ መጠምዘዝ የሚችሉ፣ ትንሽ ሰጥተው ብዙ ለመቀበል የተሰናዳ ስነ ልቦናን ያነገቡ ናቸው። ወቅት እየጠበቁ፣ የአገራችንን ሁኔታ እየተከታተሉ ዋጋ መጨመር ያደጉበት ነው። ከማኅበረሰቡ በቅለው ማኅበረሰቡን እንዴት ማገልገል እንዳለባቸው አያውቁም። ከዛሬ ሌላ ነገ የሌላቸው በወገናቸው ስቃይ የሚስቁ አዳፋ ነፍሶች ናቸው። እኚህ አዳፋ ነፍሶች ራሮቶችን ቢያውቁ ኖሮ፣ እኚህ ገፍ ነፍሶች ጽድቅናን ቢማሩ ኖሮ የሕዝባችን የመኖር ጥያቄ በዚህ ልክ ባልሆነ ነበር።
ከትናንት እስከዛሬ ራሳችንን ብቻ ስንጠቅም የኖርን ነን። አብሮ የመብላትና፣ ተካፍሎ የመጋራት ኢትዮጵያዊ ባህላችን በጥቂት ራስ ወዳድ ግለሰቦች እየተሸረሸረ ነው። በሁሉም ነገር ላይ ኢትዮጵያዊነትን ለመግለጥ ምቹ ጊዜ ላይ ነበርን። ግን ራስ ወዳድነታችን ከኢትዮጵያዊነታችን በላይ ገዝፎ በመከራ ለተያዘ ሕዝብ ሌላ መከራ ሆነነዋል። እንዲህ ዓይነቱ ጊዜ አንድነታችንን ለመመለስ፣ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህላችንን ከፍ ለማድረግ ጥሩ ጊዜ ነበር። ግን አልተጠቀምንበትም። ይሄ የኑሮ ውድነት ያልነካው የማኅበረሰብ ክፍል የለም። ከግለሰብ ባለፈ በፖለቲካውና በኢኮኖሚው እንዲሁም በማህበራዊ ሕይወታችን ላይ የከፋ ችግር እየፈጠረ ነው። በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል በእጅጉ እየጎዳው ይገኛል። የሚሰጡ እጆቻችን፣ የሚያዝኑ ልቦቻችን ወዴት ገቡ? እነዛ የሚራሩ ነፍሶቻችን፣ ድሀ ሲያዩ የሚያነቡ አይኖቻችን ወዴት ተሰወሩ? ፈሪሀ እግዚአብሔርን የተማረው በኢትዮጵያዊነት ተለቁጦ የተሠራው ግብረ ገብ ሰውነታችን ወዴት አለ?
መንግሥት የገበያውን ሁኔታ ለማረጋጋት እያደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ቢሆንም፤ ከዚህም በላይ የቤት ሥራ እንዳለው ብዙ አመላካች ሁኔታዎች እየታዩ ነው። የፍላጎት መጠን መጨመር፣ የሕዝብ ቁጥር ከአመት አመት መጨመር፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰው የማኅበረሰብ ክፍል ማደግ እና በመሳሰሉ ምክንያቶች አቅርቦቱን ከፍላጎት ጋር የማጣጣም ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። አጋጣሚዎችን በመጠበቅ ዋጋ በሚያንሩና ምርት በሚደብቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ መንግሥት የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል። ሕይወትን ከድጡ ወደ ማጡ የወሰዱ ወጪት ሰባሪ የቀን ጅቦች እያደረሱ ላሉት የሰብዓዊ እንግልት ፈር እስኪይዙ ድረስ ተገቢውን ቅጣት ሊያገኙ ግድ ነው። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ የምናስተካክለው
ነገር አይኖርም። ጩኸታችን ዋጋ የሚያወጣው ችግር ፈጣሪ ግለሰቦች ለሕግ ሲቀርቡ ነው። አሁን ላይ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተደረገ ፍተሻ በርካታ የተደበቁ ምርቶች እየተገኙ ነው። ማስጠንቀቂያ ተሰቷቸው ማስጠንቀቂያውን ቸል ብለው በተገኙ ድርጅቶች ላይ ደግሞ እስከ መታሸግ የሚደርስ ቅጣት እየተላለፈ ነው። ይሄ ይበል የሚያሰኝ ነው። ግን ደግሞ በእጅ መንሻ የመንግሥት አካላትን እያታለሉ አሁንም ድረስ ከጥፋታቸው ያልታረሙ በርካታ ስግብግብ ነጋዴዎች አሉና እነሱም ሀይ ሊባሉ ይገባል።
ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት አገራዊ ችግሮች ሲፈጠሩ አብዛኞቻችን ወደ መንግሥት ጣታችንን የምንቀስር ነን። አገራዊ ችግሮች በመንግሥት ብቻ አይፈቱም የኔም የእናንተም አብሮነት ግድ ይላል። ከመንግሥት ይልቅ እኔና እናንተ ለማኅበረሰቡ ቅርብ ነን። በአካባቢያችን የሚሆነውን እያንዳንዱን ኩነት የመታዘብ ዕድሉ አለን። ችግሮች ሲፈጠሩ፣ በአካባቢያችን ሕገ ወጥ ነጋዴዎችን ስናይ የመጠየቅ መብት አለን። ከፍ ሲልም ለሚመለከተው አካል በማጋለጥና ጥቆማ በመስጠት ኃላፊነታችንን መወጣት እንችላለን። ሌቦቻችንን አቅፈን እየተኛን፣ ችግር ፈጣሪዎችን ደብቀን እያሳለፍን የምንከላከለው ሕገ ወጥ ወንጀል አይኖርም። ይሄን የኑሮ ወድነት የፈጠረው እኮ ማንም አይደለም አብረውን የሚኖሩ የአካባቢያችን ነዋሪዎች ከፍ ሲልም ነጋዴ ቤተሰቦቻችን ናቸው። እነሱን በማጋለጥና ለሕግ በማቅረብ ለድሀ ሕዝባችን አለኝታ መሆን እንችላለን።
ይሄ ሕዝብ በድህነት፣ በጦርነት፣ በኋላ ቀርነት ለዘመናት ሲጎዳ የኖረ ሕዝብ ነው። ይሄ ሕዝብ በድርቅ፣ በፖለቲካ ሽኩቻ የሚገባውን አጥቶ የኖረ ሕዝብ ነው። እንደ አገር ብዙ ነገር አጥተናል። በታሪካችን ላይ ማስታወስ የማንፈልጋቸውን ነውረኛ ትናንቶች ጽፈናል። አሁን ላይ እንደ መንግሥትም ሆነ ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ለዚህ ሕዝብ ማንኛውንም በጎ መስዋዕት ልንከፍል ይገባል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ፣ በቆረቆር ላይ ቁምጥና ሆነን ለችግሩ ሌላ ችግር ከመሆን ይልቅ ለመፍትሄና ለለውጥ ብንበረታ አሁን ላይ የምናያቸው ችግሮቻችንን ማስወገድ እንችላለን። ምክንያት እየፈለግን ከመገፋፋት ይልቅ ምክንያት እየፈለግን ብንተቃቀፍ ያዋጣናል። አንዳንድ ቀኖች አሉ፤ ልክ እንደ አሁኑ በጋራ ኖረን እንድንሻገራቸው የተፈጠሩ። አንዳንድ ጊዜዎች አሉ፣ ልክ እንደአሁኑ የእኛን አብሮነት የሚፈልጉ። አንዳንድ ቀኖች አሉ፣ ለብቻ ኖረን፣ ለብቻ ሮጠን የማናልፋቸው። እነዚህ ቀኖች የሚታለፉት በአንድነትና በመተሳሰብ ነው። ስለዚህ ሀብታም ከሆነን ለድሀው ወገናችን፣ ነጋዴ ከሆንን አቅም ለሌለው ሸማች ልንራራ ይገባል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ድሀ ሕዝብ ነው። ማጣት ያስጎነበሰው ሕዝብ ነው። በራስ ወዳድነት ይሄን ሕዝብ ድጋሚ አንገት እንዲደፋ መፍቀድ የለብንም። ከሌለው ላይ ቆርሶ ቀን ያወጣን ሕዝብ ነው፤ ውለታውን ለመመለስ ዛሬ ላይ በጎ ሆነን ከጎኑ ልንቆም ይገባል። በራስ ወዳድነት በዚህ ሕዝብ ላይ የምናደርገው ማንኛውም ነገር ነገ ላይ የማንችለውን ዋጋ ነው የሚያስከፍለን። ዛሬ ላይ ምርት ጨምረንም ሆነ ዋጋ አንረን የምናሰቃየው ሕዝብ ትናንት ላይ ከሌለው ላይ የሰጠን ነበር። ዛሬ ላይ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጫና የምናሳድርበት ማኅበረሰብ ትናንት ላይ ዛሬን እንድናይ መንገድ የጠረገልን ነበር። ዛሬ ላይ በጎነታችንን የነፈግነው ሕዝብ ትናንት ላይ ከፍ እንድንል ምክንያት የሆነን ሕዝብ ነው። ይሄን ሕዝብ ማገልገል በምን ይለካል? ለዚህ ሕዝብ መገዛት ዋጋው ምን ያህል ነው? ውለታ በል መሆን የለብንም። ዛሬ ላይ ያሉን ነገሮች ሁሉ ማኅበረሰባችን የሰጠን ነው። ይሄን ሕዝብ በታማኝነት በማገልገል ውለታውን መመለስ ይኖርብናል። እንደ ነጋዴ በእውነትና በታማኝነት ልናገለግለው ይገባናል። እንደ መንግሥትም የማኅበረሰቡን ችግሮች በመፍታትና አፋጣኝ መፍትሄዎችን በመፈለግ ከጎኑ ልንቆም ይገባል።
ወቅቱ በመተሳሰብና በመተጋገዝ የምንኖርበት እንጂ በራስ ወዳድነት የምንበለጽግበት አይደለም። አይደለም በዚህ አስከፊ ጊዜ ቀርቶ በደህናው ጊዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም የሌለው ነው። እያንዳንዷን ክፍተት እንደ ምክንያት በመቁጠር ስቃይ መፍጠር የለብንም። ዜግነት ትርጉም የሚኖረው በእንደዚህ ዓይነቱ ጊዜ ላይ አገርና ሕዝብን በታማኝነት ስናገለግል ነው። ለአገራችን ዋጋ መስጠት አለብን፣ ለሕዝባችን ዋስትና ልንሆነው ይገባል። በመረዳዳትና በመተጋገዝ የትናንቱን የአብሮነት መንፈስ መድገም እንጂ ስር በሰደደ የእኔነት ስሜት በጭፍን መጋለብ አይኖርብንም። ልብ ቢኖረን ኖሮ ይህ ጊዜ የአገራችንን ውለታ የምንመልስበት ነበር። ብናስተውል ኖሮ ደግነታችንን በማሳየት ድሃውን ሕዝባችንን የምንክስበት ነበር።
እስኪ አንድ ጊዜ ወደ ዓለም እንመልከት፤ የዓለም ኃያላን አገራት ስንዴ ረድተውን ያውቃሉ፣ ገንዘብ አበድረውንና ረድተውን ያውቃሉ። በፖለቲካው በኢኮኖሚው፣ በማህበራዊ ሕይወታችን የረዱን ብዙ ነገር አለ። እኛ ግን ራሳችንን ረድተን አናውቅም። እኛ ለእኛ ንፉጎች ነን። ኢትዮጵያዊነት እኮ የራስ መልክ ነው። በዙሪያችን ያለው ሕዝብ የእኔና የእናንተ መልክ ነው። ይሄን ሕዝብ መርዳት ሲገባን ምርት እየደበቅንና ዋጋ እያናርን እናሰቃየዋለን። ለምን? በዚህ ለምን ውስጥ ራሳችሁን ፈልጉት። ድሀ ገድሎ የሚከብር ሀብታም የለም። ድሀ አስጨንቆ ቀን የሚወጣ ባለጸጋ የለም። በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለአገራቸው ቸር የማያስቡ፤ በዚህ ሰዓት አጋጣሚ እየጠበቁ በአገርና ሕዝብ ላይ ስቃይ የሚፈጥሩ፤ በዚህ አገር በጭንቅ ባለችበት ሰዓት አጋጣሚውን በመጠቀም ለአገርና ለሕዝብ የማይራሩ ሁሉ «የቀን ጅቦች» ናቸው። ስልጣናቸውን ተገን አድርገው ከድሀ አገርና ሕዝብ ላይ የሚሰርቁም እነሱ «የቀን ጅቦች» ናቸው።
በምንም ነገር ላይ ራሳችንን መፈተሽ ይኖርብናል። ምን እያደረግን ነው ያለነው? ችግር ፈጣሪዎች ነን ወይስ ችግር ፈቺዎች? የሕዝባችን ችግር ያመናል ወይስ ችግሩን እንደ መወጣጫ ተጠቅመን ከፍ ለማለት እየሞከርን ነው? ዜግነታችን በዚህ ጥያቄ ውስጥ ነው ያለው። የአገር ፍቅር ስሜታችሁ እነዚህን ጥያቄዎች ስትጠይቁ የሚጸና ነው። ራሳችሁን ጠይቁ። አገር መውደድ፣ ለአገሬ ምን እያደረኩ ነው ከሚል ከመልካም ሀሳብና ተግባር የሚጀምር ነው። የአገር ፍቅር ከመስጠትና ከበጎነት የሚጀምር ነው። ሰውነት በዙሪያችን ያሉትን ማቀፍና ማፍቀር ነው። ወደ መጥፎ የምንራመዳት አንድ ርምጃ ነገ ላይ ለእኛ መውደቂያ ጉድጓድ የምትሆን ናት።
በደህናው ጊዜ በቀን ሦስት ጊዜ የማይበላ ማኅበረሰብ በዚህ የኑሮ ውድነት ዛሬ ላይ ምን እንደሚሆን መገመት አይከብደንም። የምናገኘው ወርሀዊ ደመወዝ አይደለም የወር አስቤዛ ሊገዛ ቀርቶ አምስት ሌትር ዘይት ለመግዛት አቅም እያጣ ነው። በዚህ ሕዝብ ላይ ክፉ መሆን እውነት ስርየት የሌለው ሀጢዐት እንደሆነ ነው ማስበው። በማንኛውም መስክ ላይ የተሰማሩ የአገርና የሕዝብ ጠላት የሆኑ ውለታ በል የቀን ጅቦች መጋለጥ አለባቸው። ሕዝብ እያስጨነቁና ድሀ እየበዘበዙ ያሉ ነውረኛ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሕግ መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ጅብነታቸውን እስኪተዉ ድረስ በሥራቸው መጠየቅ ይኖርባቸዋል። ነገ ላይ ጅብ እንዳይወልዱ የአገር ፍቅር ስሜትን ሊማሩ ይገባል። ይህ እንዲሆን ግን ዛሬ ላይ ያለን ሁላችን እኛ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10 /2014