በምድራችን የትኛውም ያለ እንቅፋት አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ የተጓዘ ሰው የለም። በተለይ የሴት ልጆች ጉዞ እንደ ዕድል ሆኖ እንቅፋት አያጣውም። ሥራ ፈልገው የሄዱትን ለአብነት ብንጠቅስ ዝቅ ተደርጎ መታየት ይገጥማቸዋል። የተለየ ፍላጎት የሚያሳድርባቸውና አላስፈላጊ ጥያቄ የሚያቀርብላቸውም አለ። ሴቶችን ወደ ኋላ የሚያስቀሯቸው ነገሮች ብዙ ናቸው። በሕይወት ዘመናቸው ማግኘት ሲገባቸው የሚያጡትም ያይላል። ይሄኔም ጥሎ ያልጣላቸው ልባሞቹ ሴቶች መባነናቸው አይቀርም። እንቅፋቶቹ አእምሯችንን ባይሰርቁን ኖሮ ምን አልባት የበለጠ ደረጃ ላይ እንገኝ ነበር ይላሉ። “ድሮ ገናም የምንፈልገውን መሆን እንችል አልነበረም እንዴ?” ብለው ራሳቸውን ይጠይቃሉ። አለመርፈዱን ተስፋ አድርገውም ካሰቡበት ለመድረስ ለሌሎች አጋሮቻቸው አርአያ የሚሆን ሩጫቸውን ይቀጥላሉ።
ከነዚህ ልባም ሴቶች መካከል አንዷ የሆነችው የዛሬ የሕይወት ገጽታ እንግዳችን ወይዘሪት ፍሬዘር ዘውዴ በብዙ የሕይወት ውጣ ውረዶች ተፈትናለች። የፈተናው ጫና 30 ሳይሆን 70 እና 80 ዓመት የኖረች እስኪ መስላት ቀምበሩ ከብዶባታል። በመቻሏ ተጠራጥራ በሕይወት ዘመኗ ተስፋ እንድትቆርጥና እንድታዝን አድርጓታል። ቢሆንም ሳትሸነፍለት ዛሬም ያሰበችበት ለመድረስ የሚያስችላትን ጥረት በማድረግ ላይ ነች። የኪነ ጥበብ እና ጋዜጠኝነት ዝንባሌዋን በእጇ ለማድረግ የሄደችበት ርቀት ያስደምማል። ሁለቱን ጥምር ሙያዎች ያቀፈ ዓለም አቀፍ ካምፓኒ ለማቋቋም ያሰበችው ራዕይዋ ይበረታታል። ያለፍላጎቷ የተማረችውን ትምህርት ከጫንቃዋ በማውረድ በምትወደው መስክ ለመሥራት የተከተለችው ስልትም ያስተምራልና እንሆ ተሞክሮዋን ተካፈሉልን።
ምጥን ጭብጥ
ፍሬዘር ዘውዴ ትባላለች። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ቤተ-መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት ኤጀንሲ በከፍተኛ የኮሚኒኬሽን ባለሙያነት እየሰራች ትገኛለች። የኪነጥበብና የጋዜጠኝነት ጥምር ተስጥኦ ያደረባት ገና ብላቴና ሳለች ነው። ተማሪ በነበረችበት ወቅት ክፍል ውስጥ እሷ ግጥም ሳታነብ የአማርኛ ትምህርት እንዳይጀመር በማድረግ መምህሯ እያበረታቷት ነው ችሎታዋን እያጎለበተችው የመጣችው። በትርፍ ሰዓቷ በነዚሁ ላይ እየሰራች ትገኛለች። መረዋው ድምጿ በምትሰራባቸው የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በአድማጮቿ ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፎላታል። ተቋማቱንም ታዋቂ አድርጓቸዋል። ከእነዚህ መካከል ሰለሞን ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ከኢቢሲ ጋር በመተባበር በሚያቀርበው አዲስ አውቶሞቲቭ ፕሮግራም በከፍተኛ አዘጋጅና አቅራቢነት የምትሰራበት፣ በኤዲተር ኢን ቺፍ የምትሰራበት ሀበሻ ኤክስፓት ዩቲዩብ ቻናል ይጠቀሳሉ። ፍሬዘር venufrez የተሰኘ የራሷ ዩቲዩብ ቻናልም ያላት።
ፍሬዘር በተደጋጋሚ የጉብኝትና የትምህርት ግብዣ ሲያቀርብላት ከኖረው ከኢራን ኢምባሲ ጋር በሴቶች ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች ታቀርባለች። በስልጠናም ትሳተፋለች። “የፍቅር ገፆች” (ሚያዝያ 2007) በሚል ርዕስ የራሷ መጽሐፍም አሳትማለች። ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በሰራችበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው አሰባስቦ “ይድረስ ለሟቹ እና ሌሎችም…” በሚል ርእስ ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥም ሥራዎቿ ተካትተዋል። አሁን ላይ በጋዜጠኝነትና በኪነ ጥበብ ዘርፉ ትልቅ ካምፓኒ የመክፈት ራዕይ ሰንቃ በመንቀሳቀስ ላይ ነች። እንቅፋቱ በዝቶ ባያደነቃቅፋት ራዕዩ ዕውን መሆን ያለበት ድሮ እንደነበር ብታምንም አሁንም አለመርፈዱ ላይ ከራሷ ጋር ትስማማለች።
ልጅነትና ዝንባሌ
የተወለደችው በ1982 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ልዩ ስሙ ቀራንዮ መድኃኒዓለም በተሰኘ አካባቢ ነው። ያደገችውም እዚሁ ሲሆን አስተዳደጓ ጠበቅ ያለና ከሌሎች ልጆች ለየት የሚል ይመስላል። ምክንያቱም በሙያቸው ሲቪል ኢንጅነር የሆኑት ወላጅ አባቷ ዘውዴ ሁንዴ፤ እንዲሁም በሙያቸው የሂሳብ ባለሙያ (አካውንታንት) የሆኑት ወላጅ እናቷ ወይዘሮ ቀፀላ በለጠ የዋዛ አልነበሩም። ትልቅ ትኩረት ይሰጡ የነበረው ለትምህርት ነው። ልጆቻቸው በሙሉ ትኩረታቸው ትምህርትና ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲሆን ከመፈለጋቸው የተነሳ ጊዚያቸውን በበዛ ጨዋታ እንዲያሳልፉ እንኳን አይሹም ነበር። በተለይ ነፍስ እያወቁና ዕድሜያቸው ወደ ታዳጊነት እየተሸጋገረ ሲመጣ ከቤት መውጣትም የተከለከሉበት ጊዜ አለ።
ከኢንጅነር ዘውዴና የሂሳብ ባለሙያዋ ወይዘሮ ቀፀላ ከተወለዱት ልጆች መካከል ፍሬዘር በተለይ የኪነ ጥበብ እና የጋዜጠኝነት ዝንባሌ ያላት መሆኗ በወቅቱ በወላጆቿ ፈፅሞ አልተወደደላትም ነበር። በጥናት ወቅት የተዘረጋ ደብተሯን ከለላ አድርጋ ረጃጅም እና አጫጭር ልቦለድ ታነባለች። ግጥሞችን ትጽፋለች። መገናኛ ብዙሃን ትከታተልና በዚሁ ላይም ንቁ ተሳትፎ ታደርጋለች። ሆኖም ወላጆቿ ይሄ ዓይነቱ ዝንባሌዋ በተለይም የተለያዩ መጽሐፍቶችን ከየትም ከየትም ብላ ተውሳ ወደ ቤት አምጥታ ማንበቧ በፍፁም አልተመቻቸውም። “የትምህርት ጊዜዋን ይሻማና ያሰንፋታል” በሚል ስጋት በጥናት ክፍሏ ውስጥ ከትምህርቷ ውጭ ምንም ነገር እንዳትሰራ ክትትል ሲያደርጉባት ነው ያደገችው። ብዙ ጊዜም ተቀጥታ ታውቃለች። የማንበብ ሱሷ ክፍል ውስጥ በአስተማሪም አስይዞና አስገርፏታል። በተለይ መጽሐፍ ስታነብና ጽሑፍ ስትጽፍ ከፍተኛ ተመስጦ ውስጥ ስለምትገባ ወላጅ እናቷ ከኋላዋ መጥተው ሲቆሙ እንኳን አታያቸውም። የምታነብበውን መጽሐፍ የሚወስዱባት ነገር ያበሳጫት እንደነበርም ታስታውሳለች።
ትምህርት
ትምህርትን አሀዱ ብላ የጀመረችው ‹ህሊና› በተባለ አፀደ ህፃናት ነው። እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቷን “ቀራንዮ መድኃኒዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት” ሲሆን፤ የሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን ደግሞ ጦር ኃይሎች አካባቢ በሚገኝ ‹ፋሚሊ› የተሰኘ የግል ትምህርት ቤት ነው የተከታተለችው። የዘጠነኛ እና የ10ኛ ክፍል ትምህርቷንም ኮልፌ ኮምፕሪንሲቭ በመማር አጠናቃለች። የ10ኛ ክፍል ፈተናን (ማትሪክ) ጥሩ ነጥብ በማምጣት አልፋ አዲስ ከተማ መሰናዶ ትምህርት ቤት ገ ብታ ተምራለች።
ለማህበራዊ ሳይንስ ልዩ ፍቅር ሲኖራት የታሪክ ትምህርትን አብዝታ ትወደው ነበር። የማህበራዊ ሳይንስ መስኩን ከመውደዷና ከጉጉት የተነሳ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሳለች “መቼ ነው መሰናዶ ገብቼ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ ነኝ የምለው?” የሚል ሀሳብ በልቦናዋ እስከማጠንጠን ደርሳለች። ማትሪክ ተፈትና ስታልፍ “ኤ” ካመጣችበት የኢንግሊዝኛ ትምህርት በተጨማሪ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበችባቸው የትምህርት ዓይነቶችም ዋናዎቹ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርቶች ነበሩ።
ፍሬዘር የመሰናዶ ትምህርቷን በከፍተኛ ነጥብ አጠናቅቃ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በቅታለች። ሆኖም በወቅቱ ምርጫን መሰረት ያደረገ ምደባ ለማካሄድ ይቻል ዘንድ ይሞላ የነበረውን ፎርም ባለመሙላቷ ባለው ቦታ እንድትመደብ ግድ አለ። በመሆኑም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመደበች። ወላጅ እናቷ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሕግ እንድታጠና ይፈልጉ ነበር። አባቷ እንዲያሳምኗት ለማድረግም ሞክረዋል። አባቷም ቢሆኑ የእናቷን ያህል ተጭነው ባይሆንም ሀሳቡን እንደ ሀሳብ ሳያቀርቡላት አላለፉም። እሷ ግን ልቧ ውስጥ ያለው ጥበብ ነው።
እንኳን ትምህርት ለማማረጥ ከትምህርት ቤት ቤት፤ ከቤት ትምህርት ቤት እንጂ ከቤት ወጥታና ውጭ በማደር ከወላጆቿ ተለይታ ለማታውቀው የያኔዋ ታዳጊ ፍሬዘር ጎንደር መመደብ ከባድ ነበር። ከቤተሰብ መራቁና ናፍቆቱ ቀርቶ አካባቢውንና ሁኔታዎችን መልመዱ በራሱ ያሳደረባት ጫና ቀላል አልነበረም። ከቤተሰብ መለያየቱ እጅግ አስከፍቷታል። እሷ ባለችበት ዕድሜ ከቤተሰብ ተለይቶና ለብቻ ቤት ተከራይቶ መኖር እንደሚቻል እንኳን ከዩኒቨርሲቲ ከወጣች በኋላ ነው ያወቀችው። ይሄም ቢሆን በወቅቱ ለእሷ ፈፅሞ በአእምሮዋ የሚታሰብ አልነበረም። በአጠቃላይ በፍፁም ደስተኛ አልነበረችም። ጫናውንም በቀላሉ መቋቋም ተሳናት።
ያም ሆነ ይህ ፍሬዘር በምስራቅ አፍሪካና በልማት ጉዳይ ላይ የሚያወራውንና “ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ማኔጅመንት ስተዲ” የተሰኘውን ትምህርት ክፍልን መቀላቀል የመጀመሪያ ምርጫዋ አደረገች። በሲሳይ ንጉሱ ‹‹ሰመመን›› መጽሐፍ የምታውቀውን የዩኒቨርሲቲ ሕይወት ከራስዋ ጋር ለማጣጣም መፍጨረጨሯን ቀጠለች።
ሆኖም ፍሬዘርን ከትምህርት ክፍሉ ከዚህ ቀደም ብሎ ለዩኒቨርሲቲ በነበራት አመለካከት የምትጠብቀውን አላገኘችበትም። ፈተና ከየትኛው ክፍል ነው የሚወጣው ተብሎ የሚጠየቅበት፣ በተለያየ ብልጠት ነጥብ ለማምጣት የሚኬድበት ሂደት እሷ እንደምትፈልገው አልነበረምና ምቾት አልሰጣትም።
እንደውም በወቅቱ 18 ዓመት የሞላት ወጣት ከመሆኗ፤ እየበሰለች ከመምጣቷና ተጨማሪ ሀላፊነቶች ከመምጣታቸው ጋር ተዳምሮ “ፍላጎቴ ይህ አልነበረም” የሚል ሀሳብ በአእምሮዋ ይመላለስ ጀመር። ወደዚሁም በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ጥብቅ ከሆነው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ “በትምህርቴ ደካማ ሆኜ እባረር ይሆን?” በሚል ስጋትም ነበር። ያ ሁሉ ሆኖ ግን በመጀመሪያው ዓመት ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ቻለች።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሥነጽሑፍ ዝንባሌ
በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የሥነ ጽሑፍ ዝንባሌዋ አሸነፋት። የዩኒቨርሲቲውን ባህል ማዕከል እንድት ቀላቀልም አስገደዳት። በማዕከሉ ግጥሞቿን ማቅረብና የተለያዩ መርሐ ግብሮች ላይ መሳተፍ ጀመረች። የተለያዩ የግጥምና ሥነ ጽሑፍ ውድድሮችን የማሸነፍ ዕድልም አገኘች። ጎንደር የሚገኘው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አባል ሆነች። በማህበሩ አባል መሆኗ አዳዲስ መጽሐፎችን ተውሶ ለማንበብ ሰፊ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የሥነ ጽሑፍ ጥማቷን የምትወጣበትን መድረክ አልጋ በአልጋ በማድረግ አግዟታል። ሆኖም የሥነ ጽሑፍ ዝንባሌዋ አሁንም በዩኒቨርሲቲው ለጀመረችው ትምህርት ፈተና እንደሆነባት ላስተዋሉት መምህራኖቿ አልተዋጠላቸውም። መምህራኖቿ በተመደበችበት ትምህርት ክፍል ደስተኛ እንዳልሆነች ያውቁ ነበርና ዝም ብለው አላስተዋሏትም። በትምህርት ክፍሉ ደስተኛ ባትሆንም ትምህርቷን በውጤታማነት መማርና ማጠናቀቅ የሚያስችል ጥሩ አቅም እንዳላት በተደጋጋሚ ነገሯት። የትምህርትና ጥናት ጊዜዋን በሥነ ጽሑፍ ባህል ማዕከል በተለያዩ መርሐ ግብሮች በመሳተፍ እንዲሁም መጻሕፍትን በማንበብ ታሳልፍ ነበር። ይህም ውጤቷ እንዲቀንስ እያደረጋት መጣ። ውጤቷ በመቀነሱም መምህራኖቿ ደስተኛ ሊሆኑ አልቻሉምና በግልፅ ይገስጿት ነበር። በተለይ ያኔ ዶክተር የነበሩትና ዛሬም በዛው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገሉ የሚገኙት ፕሮፌሰር ሲሳይ ምስጋናው ለሥነ ጽሑፉም ሆነ ለጋዜጠኝነት ሙያ የነበራት ዝንባሌ የትም እንደማይሄድና ውስጧ ያለ በመሆኑ “ወደፊት ትደርሽበታለሽ አሁን ላይ ትኩረትሽን ትምህርትሽ ላይ አድርጊ” ሲሉ ብዙ ጊዜ መክረዋታል። የመጀመሪያ ዲግሪዋን በ”ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ማኔጅመንት ስተዲ” ጥናት መስክ አጠናቅቃ ከወጣች በኋላም ሁለተኛ ዲግሪዋንም ሆነ የሥራ መስክዋን በምትወደው የጋዜጠኝነት ሙያ ዘርፍ እንድታደርግ ያበረታቷት እኚሁ ፕሮፌሰር በመሆናቸው ባለውለታዋ ናቸው።
የወጣቷ ባለውለታዎች ተቆጥረው አያልቁም። ብቃቷን ያስተዋሉና ጥሩ አቅም እንዳላት ያረጋገጡ ሁሉ ዛሬ ላለችበትና ለደረሰችበት ደረጃ የየራሳቸውን አስተዋጾ በማድረግ ታግለውላታል። ከነዚህ አንዱ በወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ናቸው።
ፕሮፌሰር ሲሳይ ምስጋናው ወደምትወደውና ከሥነ ጽሁፍ ተስጥኦዋ ጋር ወደ የሚቀራረበው የጋዜጠኝነት ሙያ እንድትገባ ቢያበረታቷትም ፍላጎቷን ዕውን በማድረግ መሬት በማስነካቱ ረገድ የፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ አስተዋጾ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ የሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር የሚያስችላትን የመግቢያ ፈተና ካለፈች በኋላ በሙያው ያላትን የካበተ አቅምና ልምድ በማየት ሥራዋን እየሰራች ትምህርቷን በቀኑ ክፍለ ጊዜ እንድትከታተል ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ፈቅደውላታል።
ያም ሆነ ይህ ፍሬዘር ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም ተማሪ በነበረችበት ወቅት የነበረው የወጣቷ የሥነ ጽሑፍ እና የጋዜጠኝነት ሙያ ዝንባሌ በዩኒቨርሲቲው “ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ማኔጅመንት ስተዲ” መስክ ትከታተል ለነበረው ትምህርቷ እንቅፋት ከመሆን አልተመለሰም።
ሙሉ ትኩረቷ ቅን ለሁለቱ ዝንባሌዎቿ በመስጠቷ ዋናውንና የመጀመሪያ ዲግሪ ሥራዋን ረስታዋለች። የረሳችበት ሁኔታ ደግሞ አስገራሚም አስቂኝም ነው። በአንድ የፈተና ዕለት እንደሌሎች ተማሪዎች ፈተናው እስኪጀመር ፈተና ክፍል ውስጥ ተቀምጣ ነበር። ሰርክ በየደረሰችበት ሥፍራ በአእምሮዋ የመጣላትን ሀሳብ የምታሰፍርበት ብዕርና ወረቀት ከእጅዋ የማይጠፋው ፍሬዘር ፈተናው እስኪጀመር በሚል ብዕርና ወረቀቷን አውጥታ ግጥሟን መፃፍ ትጀምራለች። በዚሁ ትመሰጥናም ጭራሽ ፈተናውን ትረሳዋለች። ሌሎቹ ተማሪዎች በፊናቸው ለፈተናው ከተሰጠው ሰዓት ገሚሱን አገባደዋል። ፈተናውን ሰርተው ጨርሰው የወጡ ተማሪዎችም ነበሩ።
በዚህ አይነቶቹ ሁኔታዎች ፍሬዘር ብዙ ጊዜ ከመምህራኖቿ ጋር ሁሉ ትጋጭ ነበር። ታዲያ ከዚህ ድርጊቷ እንድትታቀብ በወቅቱ ፕሮፌሰር ሲሳይ ምስጋናውን ጨምሮ በትምህርቷ ትልቅ ብቃት እንዳላት የሚያውቁ መምህራኖቿ ትምህርቷን ትኩረት ሰጥታ እንድትከታተል ሳያሰልሱ መክረዋታል።
መድረክ የመምራት ልምድ
ፍሬዘር መድረክ የመምራት ልምድ የቀሰመችው በዚሁ በካምፓስ ቆይታዋ ነው። የስርዓተ ጾታ እና የኤች አይ ቪ/ኤድስ ክበባት አባል መሆኗ ለመምራቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላታል። በዚህ ውስጥ የሕይወት ስልጠና ማግኘት ችላለች። “የሕይወት ክሂሎት ስልጠና” አሰልጣኝም ለመሆን አብቅቷታል። ዩኒቨርሲቲው እሷን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎቹን ባስመረቀበት በዛው ዓመት ኪነ ጥበብና ባሕል ማዕከል ላይ የነበሩ ወጣቶች በየምሽቱ ያቀረቧቸውን ሥራዎች በማሰባሰብና ከዚያ ላይ በመምረጥ “ይድረስ ለሟቹ እና ለሌሎቹም” በሚል ርዕስ መጽሐፍ አሳትሞ ነበር። ታዲያ በዚሁ በ2003 ዓ.ም በታተመ መጽሐፍ ላይ የእሷም የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ተካትተው ወጥተውላታል። ወጣቷ የተዋጣላት ጸሐፊና ንግግር አዋቂ ከመሆንዋ አንፃር ለጋዜጠኝነት ሙያ መስክ የምታደላ ነች። በመመረቂያዋ ዓመት መጨረሻም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ወጣቶች ፕሮግራም ላይ ቀርባ መድረክ የመምራትና የንግግር ችሎታዋን አስመሰከረች። ቀደም ሲል በሬዲዮ ጣቢያዎች የነበራትን ተሳትፎ አጠናከረች። በደምሳሳው ይሄ የዩኒቨርሲቲ ቆይታ የተለያዩ ሥራዎችን በውጤታማነትና በፍጥነት መሥራት የቻለችበት ወቅት ነበር። ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀችውም ከብዙ ዓላማና ተስፋ ጋር ነው። ከካምፓስ ስትወጣም ትልቅ ህልም ነበራት። የትኛውንም ዓይነት ሥራ መሠራትና ብዙ ነገር ማድረግ እችላለሁ ብላም አስባለች።
ከዩኒቨርሲቲ በኋላ
እንዳሰበችው ህልሟን የምታሳካበት መንገድ አልጋ በአልጋ አልሆነላትም። ዋናው ምክንያት ደግሞ በተመረቀችበት ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኢንቫይሮመንታል ማኔጅመንት ስተዲ የተሰኘው የትምህርት መስክ አገሪቱ ውስጥ በተለይም ደግሞ እሷ ተወልዳ አድጋ ትኖርበት በነበረው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሥራ አለመኖሩ ነው። እሷ ተመረቃ ወደ አዲስ አበባ በተመለሰችበት ወቅት በትምህርቱ መስክ ቀድመው የተመረቁም ሥራ አለማግኘታቸው በእጅጉ አሳሰባት። ሥራ ፍለጋ ሲንከራተቱ ማየቷ ምነው ትምህርቱን ባልተማርኩ በሚልም አስቆጫት። ጊቢ በነበረችበት ሰዓት ትምህርቱን አቋርጠው የሄዱ ተማሪዎችም ታወሷት። የትምህርቱ ዓይነት አዲስ በመሆኑ ይሁን በሌላ ባይገባትም ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ ወጥቶ ለውድድር በምትሄድበት ጊዜ ራሱ በምዝገባ አከናዋኙ ተቋም ሠራተኞች የትምህርት መስኩ ፍፁም አለመታወቁ እንኳን በእጅጉ ገረማት። “ምንድነው ይሄ ሶሻል ሳይንስ ነው ዴቨሎፕመንት?” የሚል ግራ አጋቢ ጥያቂያቸውንም መመለስ ታከታት። ያኔ ስትመደብበት የፈራችው አልቀረላትምና በጣም አሳዘናት። ከሁኔታው የተማረችው ትምህርት የሚያዋጣት አለመሆኑንም በሚገባ ተረዳች። በመሆኑም ፍሬዘር ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ከወጣች በኋላ ያለውን ጊዜ እንዳሰበችው ቀላልና ተስፋማ ሳይሆን እሾህና ጋሬጣዎች የበዙበት ፈታኝ ሆኖ ነው ያገኘችው።
የሥራ ዓለም
ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀጠረችው በመምህርነት ሙያ ነው። ሥራ የጀመረችውም በግል ትምህርት ቤት ነበር። በሦስት የግል ትምህርት ቤቶች የሰራች ሲሆን ከግል ትምህርት ቤት መምህርነት በኋላ በዲግሪ በተመረቀችበት ስራ ያገኘችው የኢትዮጵያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር)፣ በ2007 ነሐሴ 1 በስራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት ባለሙያነት ነበር። ከ2010 መስከረም ጀምሮ በዝውውር ብሔራዊ ቴአትር በስራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት ባለሙያነት መጣች። ታኅሳስ 1/2013 በተመረቀችበት ዘርፍ ለመስራት ከብሔራዊ ቴአትር ወደ ወመዘክር በዝውውር መጥታ በከፍተኛ የኮሚኒኬሽን ባለሙያነት እያገለገለች ትገኛለች።
ፍሬዘር ሥራ ለማግኘት ወዳደረገችው ጥረት እንግባና ሥራ ፍለጋ ብሎ መንከራተቱ ሲደክማትና አማራጭ ስታጣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የወሰደችው የሕይወት ክሂሎት የአሰልጣኞች ስልጠና ትዝ አላት። በትዝታዋ ውስጥም ምንም እንኳን የፔዳጎጂ ትምህርት ባትወስድም የማስተማር ልዩ ተስጥኦ እንዳላት የተገነዘበችበት ጊዜ መኖሩ ተገለፀላት። ከዚሁ በመነሳትም በዚሁ በጨበጠችው የሕይወት ክሂሎት በመምህርነት ተቀጥራ ለማስተማር የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተወዳደረች። በውድድሩም በጥሩ ውጤት አለፈች። እናም አማርኛና ሲቪክስ ትምህርቶችን ለሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች መስጠት ጀመረች።
ሆኖም ያኔ እሷ በዕድሜ ልጅ ነበረች። በአንፃሩ ተማሪዎቿ ትልልቆች ነበሩ። በዕድሜ ብቻ ሳይሆን በአካልም የጎለበቱ መሆናቸው ለሚያየን ያስቃል። እንደውም አንዳንዴ ወላጆች በሚመጡበት ሰዓት ልጅ ከመሆንዋ የተነሳ ተማሪ እየመሰለቻቸው አስተማሪው የታለ ይሏት ሁሉ ነበር። ሆኖም ፍሬዘር ከዚህ የመምህርነት ሥራዋ ብዙ ነገር አይታና ተምራበታለች።
በተለይ ወላጆች በልጆች ላይ ትልቅ ሚና እንዳላቸው የተማረችበት ሕይወት ነበር። ምክንያቱም ክፍል ውስጥ በምታስተምርበት ጊዜ በተማሪዎችዋ ላይ በጣም አስቸጋሪ ባሕርይ ታይ ነበር። በዚህ በማስተማር ሥራ ሦስት የግል ትምህርት ቤቶች ያሉ ተማሪዎችን ፀባይ የማየት ዕድል አጋጥሟታል። በተለይ ቀረብ አድርጋ ለማናገር በምትሞክርበት ሰዓት ከተማሪዎችዋ የሚያሳዝን ታሪክ ትሰማ ነበር። የብዙዎቹ ወላጆች እንደሌሉ ከኢትዮጵያ ውጭ ዕቃ ሊያመጡ እንደሄዱ ሳይቀር ይነግሯት ነበር። በተለይ ቤት ውስጥ ያለ ችግር ወላጆቻቸው ሳይቀር እየመጡ በትዳራቸው ውስጥ ያለውን አለመስማማት ጭምር ያወሩላት ነበር። “ስታድጉ ምን መሆን ነው የምትፈልጉት?” ስትላቸው አንዳንዶቹ መማር እንደማይወዱና ሲያድጉ ትምህርት የማቆም አላማ እንዳላቸው ይገልፁላታል። እንዲህ ብላ መልስ የሰጠቻት ተማሪ ነገ ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ልትወድቅ እንደምትችል ማሰቡ በራሱ ራስ ምታት ሆነባት ነው የቆየችው።
በዚህም የመማር ዓላማውና ፍላጎቱ ያልነበራቸው ልጆች መኖራቸውን ታዝባለች። በዚህ የተነሳ የማስተማር ሥራውን የጀመረችበት ጊዜ በጣም ብስጩና ቁጡ የሆነችበት ሁኔታ ተፈጥሮባት ነበር። በተለይ ደግሞ እሷ በምን ዓይነት መልኩ እንዳደገች ስታስበው እርስ በእርስ የሚያወሩት ጆሮ የሚጎረብጥ ወሬ በእጅጉ ያስደነግጣትና ይገርማት ሁሉ ነበር። በሶስቱም የግል ትምህርት ቤቶች ያለው ነገር በሙሉ የሚረብሽ ሆነባት። በስተመጨረሻ በዚህ ሁሉ በመጨነቋ ጨጓራና ማይግሬን ያዛት። የፀና የራስ ህመም ውስጥ ገብታ አረፈች። እምትሆነውና የምታደርገው እስኪሳናት ጭንቀቶች ሲደራረቡባት ከመምህርነቱ ሙያ መውጫ መንገድ ሁሉ አልታይሽ እስከማለት ድረስ ደረሰች። ሕይወቷን እስከ መጥላት እንዲሁም ራስዋ ላይ ጥቃት እስከማድረስና መኖር የለብኝም እስከ ማለት ድረስ ዘለቀች። “ለዚህ ነው እንዴ የጓጓሁት” በማለትም ተፀፀተች። በመምህርነት የሰራችባቸውን ዓመታት በዚህ መልኩ አሳለፈች።
ሌላኛው የፍሬዘር የሥራ አማራጭ
በሰዎች ጥቆማ አማካኝነት የሜዳ ቴኒስ አሰልጣኝ በነበረውና ሰለሞን ደነቀ፣ የድርጅቱ ስም “ድሪም ቢግ ስፖርት አካዳሚ” በሕዝብ ግንኙነትነት የሥራ ዕድል በማግኘቷ ከመምህርነት ሙያው ተላቀቀች። “የፍቅር ገጾች” (2007 አ.ም) የሚለውን ግጥሞችና አጫጭር ታሪኮችን የያዘውን የመጀመሪያ መጽሐፏንም አሳተመች። የታተመው አንድ ሺህ ኮፒ ቢሆንም ለስዋ መጽሐፉ መታተሙ ልጅ ወልዶ እንደመሳም ያለ ትልቅ፤ በራሱ ትልቅ ደስታ የሚሰጥ ነበር።
ሥራ ፈታ በተቀመጠችበትና ምን እንደምታደርግ ግራ በገባት ወቅት በተመረቀችበት ዘርፍ ሥራ ወጣ። የሥራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት ባለሙያ የሚለው የሥራ መደብ ለእነሱም ተፈቀደ። ተወዳደረችና አለፈች። በዚህ መካከልም ብዙ ነገሮችን ስትሞካክር ቆይታለች። ከሞከረቻቸውና ስልጠና ከወሰደችባቸው አንዱ ኢራን ኤምባሲ የሚሰጣቸው ኮርሶች ላይ መሳተፍ ሲሆን አንዱ ኮርስ የፖለቲካል ሳይንስ ዘርፍ ያለው በኢራንና በኢትዮጵያ ግንኙነት ላይ የሚያተኩር ነበር። ሌላኛው ደግሞ ትኩረቱን የኢራን ቋንቋ ላይ ያደረገ ነው። ከዚህ በተጓዳኝ ኢምባሲው የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን እንድትሰራ ዕድል ይሰጣት ነበር። ሴቶችን የሚመለከቱ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎችን ሰርታ አቅርባለች። ጽሑፎቹ ሴቶች በአገር ዕድገት እና በማህበራዊ ኩነቶች ላይ ያላቸው ሚና ምንድነው? እንዲሁም በሃይማኖትስ እንዴት ይደገፉና ይታያሉ? የሚሉ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ነበሩ።
የሥራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት ባለሙያ ሆና በተመረቀችበት ትምህርት መስክ የመሥራት ዕድልም አግኝታለች። ይሄ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ስትይዝ የነበረባት በብዙ ሺህ የሚቆጠር የወጪ መጋራት ክፍያ እንድትከፍል ረድቷታል። ወደ እዚህ የመንግስት ተቋም ከመጣች በኋላም በአንዳንድ የራሷ የግልና በሌሎች ምክንያቶች ባትቀበለውም ከኢራን ኢምባሲ ተደጋጋሚ የጉብኝት ጥያቄዎች ቀርበውላት ነበር።
በዚህ ወቅት ጎን ለጎን በአንዳንድ የግል መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ፕሮግራም አቅራቢ በመሆን ትሰራ ነበር። ከሰራችባቸው መካከል ከሬዲዮ “ሰላም ሀበሻ” ዛሚ ላይ ይቀርብ የነበረ የጋዜጠኛ ዘሪሁን አሰፋ፤ እንዲሁም “ፍቅርና ወንጀል” አሀዱ ሬዲዮ ላይ ይቀርብ የነበረ የጋዜጠኛ ዳዊት በቀለ ፕሮግራም፤ በተጨማሪም “የሀበሻ ኤክስፓ” ዩቲዩብ ቻናል ኤዲተር ኢን-ቺፍ ሆና የምትሰራባቸው ይጠቀሳሉ። አሁን እየሰራችበት ያለችውና ረዥም ጊዜ የቆየችበት ሰለሞን ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ከኢቢሲ ጋር የሚያቀርቡት የጋዜጠኛ ሰለሞን ጥዑመልሳን ፕሮግራም አዲስ አውቶሞቲቭ የማክሰኞው ፕሮግራም ከፍተኛ አዘጋጅና አቅራቢ የሆነችበትም ይጠቀስላታል። የራሷ ዩቲዩብ ቻናል (venufrez)ም አላት።
ወጣቷ ያሳለፈችው ውጣ ውረድ እንዲህ እንደምናወራው ቀላል አይደለም። ያሳለፈችውን ጫና ስታስታውሰው 30 ዓመት ሳይሆን 70 እና 80 ዓመት የኖረች ነው የሚመስላት። በተማረ ቤተሰብ በመወለድና በማደግ ማህል በጣም ብዙ የሚታለፉ ነገሮች እንደመኖራቸው ፍሬዘርም የነዚህ ሰለባ ሆናለች። ልክ እንደማንኛውም ሴት ሁሉ መሥራት እንደማትችል፣ ትንንሽ ነገሮችን እንድትጠብቅና ተስፋ እንድታደርግ፤ ህልሟ ትንሽ እንዲሆን እየተነገራት ነው ያደገችው። በመሆኑም በዚህ የተነሳ እጅግ ብዙ ጫና የበዛባቸውን ውጣ ውረዶች ማሳለፍ ችላለች።
ሥራ ለማግኘት በራሱ ያሳለፈችው ውጣ ውረድ ቀላል አልነበረም። የቅርብ የምትላቸውን ሰዎች አንዴ ብቻ እድሉን ስጡኝና ልሞክር ብላ እስከመለመን የደረሰችበት ነበር። ሆኖም አንዳንዶቹ ዝቅ አድርጎ የማየት፤ ሌሎቹ ደግሞ የተለየ ፍላጎት በማሳደርና አላስፈላጊ ጥያቄዎችን በመጠየቅ በጣም ተስፋ እንድትቆርጥና እንድታዝን አድርገዋታል። ስለ ሕይወት የተዛባና ጥሩ ያልሆነ አመለካከት እንዲኖራትም አድርገዋታል። ፍሬዘር አንዳንዴ ካገኘቻቸው ነገሮች ይልቅ ያለፈችባቸው ነገሮች ጫና ይበዛባትና “መሥራት ችያለሁ፤ እችላለሁም!!!” እንዳትል ያደርጓታል። “አልችልም እንዴ?” የሚሉ ጥርጣሬዎች እንዲፈጠሩባት ያደረጉ ሁኔታዎችንም አልፋለች።
በተጨማሪም በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንዳየችው ከማገዝ፣ ከማበረታታትና እንዲህ ዓይነት ባህርይን ከማዳበር ይልቅ የአንድ ፈጣን፣ ለወጥ ያለና የተማረ ማህበረሰብ ሠራተኛ ባህርይ ነው ተብሎ የማይጠበቅ፣ ለማጥፋት ሁሉ የሚደረጉ ተግባራት ሲፈፀም መታዘብ ችላለች።
በእርግጥ ሰው ያለ እንቅፋት አልጋ በአልጋ በመሆን በተደላደለ መንገድ ላይ አይጓዝም። ሆኖም ሴቶችን ወደኋላ የሚያስቀረው ነገር በጣም ብዙ ነው። የሚያጡት ነገርም እንዲሁ ይበዛል። “እነዚህ ነገሮች አእምሮዬን ባይሰርቁኝ ኖሮ ምን አልባት የበለጠ ቦታ ላይ አልገኝና ገና ድሮ የምፈልገውን መሆን እችል አልነበር እንዴ?” ብላም ራሷን እስከ መጠየቅ ደርሳለች። ሁኔታው እጅግ ከባድና አስቸጋሪ ነው። ሆኖም ማንኛውም ሰው በተለይም ሴቶች እንዲህ ዓይነቶቹን ለማሸነፍ መቆም ያለባቸው እራሳቸው እና ከራሳቸው ጋር ብቻ እንደሆነ ተምራ አልፋበታለች። ‹‹ብዙ የሚያሰናክሉና የሚያደናቅፉ ምክንያቶች አሉ›› የምትለው ወጣቷ ሆኖም ምክንያቶቹ ውጤት እንደማይሆኑም ታምናለች። ብዙ ነገሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ በማመን ራስን ማዘጋጀትና ማጠንከር እንደሚገባ ምክሯን ትለግሳለች። እሷን የገጠማት የሚያስደነግጥ፣ የሚያስፈራ… ግንዛቤ ስላልነበራት አዲስ ነገርም ነበር። “እንዴት እንዲህ ይደረግና ይሆናል?” የሚለው ላይ እንጂ ወደ መፍትሄው የመምጣቱ ነገር ጊዜ ፈጅቶባታል። ዛሬም ቢሆን በጣም በጣም ወደ ኋላ እንደቀረች ይሰማታል። መድረስ ከምትፈልግበት ግማሹ ላይ እንኳን መድረስ ችያለሁ የሚል ዕምነት የላትም። ሆኖም ዛሬም የምትፈልገው ቦታ ለመድረስ የምታደርገውን ጥረት አላቋረጠችም። የምትፈልጋቸውን ነገሮች አሻግራ የምታይበት ትግል ላይ ነች። በፍፁም አላረፈችም።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 9 ቀን 2014 ዓ.ም