ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው በግብርና ሥራ የተሰማራ ቢሆንም በአገሪቱ ውስጥ የሚመረተው ምርት የአገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ ሊሸፍን ባለመቻሉ በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ከውጭ አገራት ታስገባለች። ለመስኖ ምቹ የሆነ መሬት እና የውሃ ሀብት ባለቤት ብትሆንም የአገሪቱ አርሶ አደሮች በክረምት በሚዘንበው ዝናብ ላይ በአመዛኙ ጥገኛ በመሆን የአገሪቱ አርሶ አደሮች የድካማቸውን ያህል ፍሬ ሳያገኙ ዘመናት ተቆጥረዋል።
በአገሪቱ ውስጥ የሚስተዋለውን የግብርና ምርት እጥረት ለመቋቋም የግብርና ምርቶችን በከፍተኛ ውጭ ምንዛሬ እየገዛች ወደ አገር ውስጥ እያስገባለች ትገኛለች። ይህንን ሁኔታ ለመቀየር መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለመስኖ ልማት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። ከለውጥ መንግሥት ወዲህ በአገሪቱ ያለውን ለመስኖ ምቹ መሬትና ውሃ ወደ መስኖ ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው ። በተለይም በበጋ መስኖ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።
የለውጡ አመራር ወደ ስልጣን ከመምጣቱ አስቀድሞም የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት መጠነኛ ጥረት ሲደረግ የነበረ ቢሆንም የመስኖ ልማት በተለያዩ ችግሮች የተበተበ ነበር። የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በተባለላቸው ጊዜ እና በጀት የመጠናቀቅ ችግር ይስተዋልባቸው ነበር። አገር በቀል ብሔራዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ዲዛይን ጥናትና ግንባታ ስታንዳርድና የአሠራር መመሪያ አለመኖር ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት አገሪቱ ከመስኖ ልማት ማግኘት ያለባትን ምርት ሳታገኝ ቆይታለች።
በመስኖ ዲዛይን፣ ጥናትና ግንባታ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመድፈን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የመስኖ ዲዛይን፣ ጥናትና ግንባታ ስታንዳርድና ሥራ መመሪያ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ ጀምሯል። የሥራ መመሪያውን እና ስታንዳርዱን ለማዘጋጀት በቅርቡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክርም አካሂዷል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከአሁን ቀደም አገር በቀል የመስኖ ልማት ዲዛይን፣ ግንባታና ቴክኖሎጂ ስታንዳርድና የአሠራር መመሪያ አልነበራትም። መስኖ ዲዛይን፣ ግንባታና ቴክኖሎጂ ስታንዳርድና መመሪያ ያልተዘጋጀበት ምክንያት ደግሞ የመስኖ ዘርፍን በባለቤትነት የሚመራ አካል ባለመኖሩ ነው። በዚህም ምክንያት መስኩ ተዘንግቶ ነው የኖረው። መስኖ አንዴ በውሃና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ስር ሌላ ጊዜ ደግሞ ከየትኛውም ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስር ሳይካተት የቆየ እጅግ ወሳኝ ነገር ግን የተዘነጋ ዘርፍ ነበር።
ሆኖም አልፎ አልፎ ግን አንዳንድ ተቋማት የመስኖ ዲዛይን፣ ግንባታና ቴክኖሎጂ ስታንዳርዶችን ሊያዘጋጁ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። አንዳንድ ሙከራዎች ቢኖሩም የሚፈለገውን ያህል ሊሄድ አልቻለም። ለምሳሌ የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን የመስኖ ልማት ሥራ በቀጥታ ባይመለከተውም እንኳን የመስኖ ግንባታ፣ ቴክኖሎጂ እና ዲዛይን ስታንዳርድ እና የሥራ መመሪያ አዘጋጅቶ ነበር። ሆኖም የሚጎድሉት ነገሮች ስላሉ ሙሉ አይደለም። በመሆኑም እንደሚፈለገው ሊሰራበት አልተቻለም። በመሆኑም የተዘጋጀውን መመሪያን ስታንዳርድ በባለቤትነት ወስዶ በሥራ ላይ የሚያውል አካል አልነበረም።
እስከ ዛሬ የመስኖ ሥራን የራሴ ነው ብሎ የሚሠራ ተቋም አለመኖር የመስኖ ግንባታ፣ ዲዛይንና እና ቴክኖሎጂ የአሠራር መመሪያና ስታንዳርድ እንዳይኖር ምክንያት ሆኖ መቆየቱን የጠቆሙት አቶ ብዙነህ፤ በቅርቡ የተቋቋመው የመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የመስኖ ሥራን እንደ አገር አቀፍ ደረጃ በባለቤትነት እንዲሠራበት በመደረጉ የስታንዳርዱና መመሪያው እንዲዘጋጅ በር ከፍቷል። የዚህ መመሪያ እና ስታንዳርድ ዝግጅት መጀመር ለዘርፉ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይጠበቃል።
እንደ አቶ ብዙነህ ማብራሪያ እስካሁን ድረስ አገር በቀል ስታንዳርድና የሥራ መመሪያ አልነበረም ማለት የመስኖ ግንባታ እና የጥናት ሥራዎች ያለምንም ስታንዳርድ እና ሥራ መመሪያ ይሠሩ ነበር ማለት ግን አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራባቸው እስታንዳርዶችና መመሪያዎች ሥራ ላይ ሲያውሉ ነበር። መሐንዲሶች የእንግሊዝ፣ የህንድ እና የአሜሪካ ስታንዳርዶችና መመሪያዎች ሲጠቀሙ ነበር። ከዚያ ባሻገር መሐንዲሶች ከትምህርት ቤት ጀምሮ በተማሯቸው ትምህርቶች ባገኙት እውቀት የሚሠሩበት አለ። እነዚህ መመሪያዎች በአመዛኙ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ አልነበሩም።
ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ የሌሎች አገራት መመሪያዎችን እና ስታንዳርዶችን ወደ ኢትዮጵያ አምጥተው ሥራ ላይ በሚያውሉበት ወቅት የመስኖ ሥራ ወጥነት እንዳይኖረው እንቅፋት ሆኖ ነበር። ባለሙያዎች የፈለጉትን ነው ሲጠቀሙበት የነበረው። አንዳንዶቹ የአሜሪካንን መመሪያዎችና ስታንዳርዶችን ሲጠቀሙ ሌሎቹ ደግሞ፤ የእንግሊዝ፣ ሌሎቹ ደግሞ የህንድ መመሪያዎችንና ስታንዳርዶችን ሲጠቀሙ ነበር። እነዚህ አገሮች ስታንዳርዶቹንና መመሪያዎቹን ለኢትዮጵያ ብለው ያዘጋጁት አይደለም። የራሳቸውን አገራት ነባራዊ ሁኔታዎችን ታሳቢ አድርገው ያዘጋጁት ነው።
እነዚህን መመሪያዎች እና ስታንዳርዶችን መጠቀማቸው ዲዛይን፣ ግንባታና ሌሎች ነገሮች ወጥነት እንዳይኖረው እንቅፋት ሆኖ ነበር። የሌሎች አገራትን መመሪያዎችና ስታንዳርዶችን ሥራ ላይ ማዋላቸው እንደ አገር የመስኖ ሥራ ላይ ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖ መቆየቱን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ስታንዳርድና የአሠራር መመሪያው እንደ አገር አንድ ወጥ ሆነው ሲዘጋጁ እንደ አገር ሁሉም አገር በቀል የአሠራር መመሪያ እና ስታንዳርድ ተከትለው ለመስራት እንደሚገደዱ የጠቆሙት አቶ ብዙነህ፤ በዘርፉ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ገባ ወጣ አይኖርም። በመላ አገሪቱ ተመሳሳይ ስታንዳርዶች እና መመሪያዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስገድድ ይሆናል።
የሥራ መመሪያ እና ስታንዳርዱ ሥራ ላይ ሲውል የመስኖ ግንባታ እና ዲዛይን እንዲቀላጠፍ የበኩሉን እንደሚያበረክት የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ጥናት፣ ዲዛይንና ግንባታው መቀላጠፍ የሚገነቡ የመስኖ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀትና ጊዜ እንዲጠናቀቅ በማድረግ የጊዜ፣ የገንዘብና የጉልበት ብክነትን ለመቅረፍ ይረዳል ብለዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የመስኖ ግንባታና ዲዛይን በሚሠራበት ወቅት ከዚህ ውጪ መውጣት አይቻልም፣ በዚህ መሠረት መሠራት አለበት፣ በዚህ መሠረት መሠራት የለበትም የሚል አገር በቀል ስታንዳርዶች የሉም። የሚሠሩ የግድብ ሥራዎችም አገር በቀል ስታንዳርድ እና መመሪያ ላይ መሠረት ያደረጉ አልነበሩም።
በቅርቡ ምክክር የተደረገበት አገር በቀል የመስኖ ግንባታ፣ ዲዛይንና ቴክኖሎጂ ስታንዳርድ ግድቦች ስታንዳርድን ያሟሉ እንዲሆኑ፣ የመስኖ ግድቦች ሂደቱ ራሱ ምን መሆን አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው። የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የስታንዳርዱንና መመሪያውን አስፈላጊነት፤ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ምደባ ኢንስቲትዩት ደግሞ ስታንዳርዱን ያሟላ ነው የሚባለው የትኞቹን ደረጃዎች ያሟሉ እና ሂደት የተከተለ ሲሆን ነው የሚለውን ሀሳቦችን አቅርቧል። ከተጠቀሱት ባሻገር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ስታንዳርድ እና መመሪያ ዝግጅት ላይ የሚሳተፉ ይሆናል።
ከኢንተርናሽናል ዋተር ማኔጅመንት ኢንስ ቲትዩት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከአማካሪዎች፣ ከአገር በቀል የኮንስትራክሽን ድርጅቶች አገር አቀፍ ኮሚቴ በማዘጋጀት ወደ ሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አቶ ብዙነህ ጠቁመዋል። በተያዘው በጀት ዓመት ወይም በቀጣይ ዓመት የመጀመሪያ ወይም ሁለተኛው ሩብ ዓመት ውስጥ ስታንዳርድና የሥራ መመሪያ ዝግጅቱን ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል። በታሰበለት ጊዜ ለማጠናቀቅም ርብርብ እየተደረገ ነው።
በስታንዳርድ እና መመሪያ ዝግጅት ዙሪያ ምክክር በተካሄደበት መድረኩ ላይ የተገኙት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ አገራዊ ስታንዳርድ እና መመሪያ መዘጋጀት ከመስኖ ግንባታና ዲዛይን ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችል እንደመሆኑ የመስኖ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ስለሚያስችል አገሪቱ በዓመት አንድ ጊዜ ከማምረት በዓመት ሦስት ጊዜ ወደ ማምረት ለመሸጋገር ለሚታደርገውን ጥረት እውን ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው መናገራቸውን የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ክፍል በፌስቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው ዘገባው አመላክቷል።
ኢትዮጵያ፤ ለመስኖ ሊውል የሚችል ከፍተኛ መጠን ያለው መሬትና ውሃ የታደለች አገር ብትሆንም እስካሁን ድረስ በአግባቡ ሳትጠቀምበት ቆይታለች። በዚህም ምክንያት ወንዞቻችን ለጎረቤት አገራት ሲሳይ ሆነው ቆይተዋል። አገሪቱ ውስጥ በመስኖ ሊለማ ከሚችል መሬት ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ማልማት ቢቻል እንኳን አገሪቱ በምግብ ራሷን ለመቻል የሚታደርገውን ጥረት ማሳካት እንደምትችል የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ። በዝግጅት ላይ የሚገኘው የመስኖ የሥራ መመሪያ እና ስታንዳርድ አገሪቱ ወንዞቿን ለማልማት ለምታደርገው ጥረት እውን እንዲሆን ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በሚኒስቴሩ የመስኖ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ እንደተናገሩት፤ «ኮዶች እንደ አገር በመስኖ ዘርፍ የሚስተዋሉ የአሠራር ብልሽቶችን ለመቅረፍ ጠቀሜታቸው ጉልህ ነው ፤ እንደ መስኖ ደግሞ የውኃ ሀብታችንን በአግባቡ ለመጠቀም ኮዶችና ስታንዳርዶች መዘጋጀታቸው ቁልፍ ሥራ ነው» ብለዋል።
በመስኖም ሆነ በሌሎች ግድብ ግንባታ ወቅት የጥራት ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ሲሆን አገር በቀል መመሪያ እና ስታንዳርድ መዘጋጀት መጀመሩ ለጥራት መጠበቅ እገዛ ይኖረዋል። በስታንዳርድና ሥራ መመሪያ ዝግጅት ላይ ከሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት እንዱ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ሲሆን፤ የኢንስቲትዩት የስታንዳርድ ዝግጅት ዳይሬክተር ተወካይ በበኩላቸው ስታንዳርዱና መመሪያው የሚሠሩ የመስኖ ግድቦች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል «የሚሰሩ ግድቦች ጥራት እንዲኖራቸውና ውጤታማ እንዲሆኑ የአሠራር ማሻሻያ ኮዶችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል» ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
የአሠራር መመሪያ እና ስታንዳርድ ዝግጅት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014