አሁን አሁን አብዛኛው ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ባህላዊ አልባሳት አምረው፣ ተውበውና ደምቀው መታየታቸው የተለመደ ሆኗል። በተለያዩ መድረኮች ላይም ባለስልጣናት ሳይቀሩ በዚሁ በባህል አልባሳት ደምቀው ይታያሉ። ባህላዊ አልባሳቱን የሚጠቀመው ሰው ቁጥር ዕለት ዕለት እየጨመረ በመምጣቱም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የባህል አልባሳት በዘመናዊ መልኩ ለገበያ እየቀረቡ ይገኛሉ።
አልባሳቱ በስፋት እየተለመዱ በመምጣታቸው በዘርፉ ለተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ከማስቻላቸው ባለፈም ባህሉን ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል መፍጠር ችለዋል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከተፈጠሩ የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች መካከልም በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ተሰማርተው የባህል አልባሳትን ጨምሮ የተለያዩ አልባሳትን የሚያመርቱ በርካታ ኢንተርፕራይዞች ተፈጥረዋል።
መንግሥት ለኢንተርፕራይዞች የፈጠረውን ዕድል ተጠቅሞ ውጤታማ መሆን የቻሉ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ በርካታ ማህበራት በተለያዩ ክልሎችና የክልል ከተሞች ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ የሚካሄድባት በደቡብ ክልል በጌዲኦ ዞን የምትገኘው የዲላ ከተማ አንዷ ናት። የዝግጅት ክፍላችን በዲላ ከተማ በነበረው ቆይታ በከተማዋ ከሚገኙ የጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት መካከል በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ተሰማ ርተው ውጤታማ መሆን የቻሉ የቤተሰብ አባላትን የመጎብኘት ዕድል ገጥሞታል።
የመንግሥት ሰራተኛ የነበሩት አቶ ዳዊት ሞገስ እና የቤት እመቤት የሆኑት ባለቤታቸው ወይዘሮ ገነት ሳሙኤል ነዋሪነታቸው በዲላ ከተማ ነው። ኑሮን ሲጀምሩ ቀላል የነበረ ቢሆንም ልጆች ተወልደው የቤተሰቡ አባላት ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ግን ኑሯቸው እየከበደ በመምጣቱ በአንድ ሰው የወር ደመወዝ የሚገፋ አልሆነም ይላሉ።
ለኢኮኖሚ ጥያቄያቸው ምላሽ ለመስጠትና ኑሯቸውን አሸንፈው ለማሻሻል ያስችለናል ያሉትን የስፌት ሥራ በአንዲት ሲንጀር መኪና አንድ ብለው ጀመሩ። በዚህ እርሾ የተጀመረው ሥራ በአሁኑ ወቅት ሃብት ለማፍራት አብቅቷቸዋል። ኑሯቸው የተሻለ ሆኗል። ልጆቻቸውን አስተምረዋል። ከዚህ ባለፈም ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል። የመሥሪያ ማሽኖቻቸውም ቢሆኑ ውጤታማ ለመሆናቸው አይነተኛ ምስክሮች ናቸው።
‹‹ወደ ልብስ ስፌት ሥራ ለመግባት ትልቅ ድርሻ ያላት ባለቤቴ ናት›› የሚሉት አቶ ዳዊት፤ ባለቤታቸው ወይዘሮ ገነት ከወላጅ አባታቸው የወረሱትን አንዲት ሲንጀር የስፌት መኪና እንዲሁም የሴቶች ቀሚስ የመስፋት ሙያ ይዘው በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ ለሥራ ሲወጡ እርሳቸው የመንግሥት ሥራ ይሰሩ እንደነበር አጫውተውናል።
በመንግሥት ሥራ ረጅም ጊዜ ያሳለፉት አቶ ዳዊት፤ ባለቤታቸው በቤት ውስጥ የጀመሩት የልብስ ስፌት ሥራ ዕለት ከዕለት መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ተረድተው ወደ ሥራው በመቀላቀል በጋራ ለመሥራትና ሥራውን ለማስፋፋት ወስነው የመንግሥት ሥራቸውን ለቀዋል። ሙሉ ጊዜያቸውን ከባለቤታቸው ጋር በማድረግ ዘርፉን ተቀላቅለዋል። ሥራቸውን እያስፋፉ ሲመጡም መንግሥት ያቀረበውን የመደራጀት ዕድል ተጠቅመው በጥቃቅንና አነስተኛ በመደራጀት ኖጲቾ ልብስ ስፌት ኢንተርፕራይዝን አቋቋሙ።
በወቅቱ ሥራውን ለማስፋፋት በቂ ገንዘብ ስላልነበራቸው በአካባቢው ከሚገኝ ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም መነሻ ካፒታል 25 ሺ ብር በመበደር ሥራውን አስፋፍተው ቀጠሉ። ብድሩ ለሁለት ዓመት የነበረ ቢሆንም ሥራው ውጤታማ በመሆኑ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መመለስ ችለዋል። በተጨማሪ ጠቀም ያለ ብድር ለሁለተኛ እና ለሶስተኛ ጊዜ በመበደር የተለያዩ ማሽኖችን በመግዛት ሥራውን አስፋፍተዋል ።
በአሁኑ ወቅትም ከተለመደው የስፌት ሲንጀር ማሽኖች በተጨማሪ ዘመኑ የደረሰበትን ኢምብሮደር ማሽን ከውጭ በማስገባት የተለያዩ አልባሳትን እያመረቱ ይገኛሉ። የዘመኑ ስልጣኔ ጥግ የተባለው ይህ ማሽን በሶፍትዌር የተለያዩ ዲዛይኖች እና የተለያዩ ክሮች የሚሰጡት ሲሆን ማሽኑ ክሮቹን ተጠቅሞ የሚፈለገውን ዲዛይን በከለርም ሆነ በቅርጽ አትሞ የሚያወጣ ነው።
ከአንድ ሲንጀር መኪና በመነሳት 50 ዘመናዊ ሲንጀሮችን እንዲሁም የዘመኑ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ኢምብሮደር ማሽን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የቻሉት አቶ ዳዊት፤ የሚጠቀሙበት ዘመናዊ ማሽን የሰው ፣ የአበባ አልያም የእንስሳት እንዲሁም የሌላ የተፈለገውን ማንኛውም መልክ ማሽኑ በተሰጠው ጨርቅ ላይ ክሮቹን ተጠቅሞ ማተም የሚያስችለው የራሱ የሆነ ሶፍትዌር ያለውና በፍላሽ የሚሰጠው ሲሆን ማሽኑ እራሱ ፍላሹን አንብቦ በሚጎርሰው 12 አይነት ክር እና 12 መርፌ ተጠቅሞ ወደ ክር ይቀይረዋል።
በዚሁ ዘመናዊ ማሽን የሚገኘው ውጤት የተፈለገውን አይነት ሁሉ ሲሆን ለአብነትም አደይ አበባ፣ መስቀል፣ ኃይማኖታዊ ጥቅሶችና የተለያዩ ባህላዊ አልባሳትን ጥልፍ አስመስሎ ያመርታል። ከዚህ በተጨማሪም ጋርመንት ፕሪንቲንግ ማሽን ገዝተው ለመጠቀም በዝግጅት ላይ ሲሆኑ ይህም ቲሸርቶችን በብዛት ማምረት የሚያስችል መሆኑን ይናገራሉ። ኢምብሮደር የተባለው ማሽን በቀን ከ200 እስከ 300 የሚጠልፍ ሲሆን ጋርመንት ፕሪንቲንግ ማሽን ደግሞ በከፍተኛ መጠን በቀን 3000 ቲሸርቶችን ማምረት የሚያስችል ነው ። ይህን ማሽን ወደ ሥራ ለማስገባት ታድያ በአሁኑ ወቅት የግዢ ሂደቱን አጠናቀው ማሽኑን ለመረከብ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ድርጅቱ በዚሁ ማሽን ማምረት ሲጀምር ታድያ በአሁኑ ወቅት ከፈጠረው 52 የሥራ ዕድል በተጨማሪ ከ20 እስከ 30 ለሚደርሱ የአካባቢው ወጣቶች ተጨማሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር የላቀ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ይሆናል። የሚያመርታቸውን ምርቶችም ለጅምላ አከፋፋዮች በማስረከብ በችርቻሮ ከመሸጥ ሥራ የሚወጣ እንደሆነ አቶ ዳዊት አንስተው ይህም የሚከፈተውን የሥራ ዕድል ሰፊ የሚያደርገው መሆኑን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ብሎም በአገሪቱ አሉ የተባሉና እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ማሽኖችን ከውጭ አገር በማስመጣት የተለያዩ አልባሳቶችን በጥራት እና በብዛት እያመረተ የሚገኘው ኖጲቾ የልብስ ስፌት ኢንተርፕራይዝ በዲላ ከተማ ቀዳሚ ኢንተርፕራይዞች መካከል አንዱ ነው። ዘመኑን የዋጀ ማምረቻ ማሽን ያለው ይህ ድርጅት የተለያዩ አልባሳትን በአይነትና ቅርጽ እያመረተ ለገበያ የሚያቀርብ ሲሆን፤ የገበያ መዳረሻውም ከዲላ እስከ አዲስ አበባ ከተማ መሆኑን አቶ ዳዊት ይገልጻሉ። በዲላ ከተማ ብቻ ሶስት የመሸጫ ሱቆች እንዳሏቸውና በከተማዋና በከተማዋ ዙሪያ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ባላቸው አንድ የመሸጫ ሱቅም በተለይም ባህላዊ አልባሳትን ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ለገበያ ከሚያቀርቧቸው ባህላዊ አልባሳት መካከል የጌዲኦ ባህላዊ አልባሳት የወንዶችና የሴቶች እንዲሁም የህጻናት አልባሳት በስፋት ይገኙበታል። በተለይም ሚኒስትሮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት የሚለብሱት የጌዲኦ አልባሳትን ያመርታሉ። ከባህል አልባሳቱ በተጨማሪም በተለምዶ አምባሳደር የሚባ ለውን ሙሉ ልብስም በዘመናዊ ጨርቅ ያመርታሉ። ከዚህ ባለፈም የመዘምራን አልባሳትን በማምረትም በስፋት ይታወቃል።
በአንድ ሲንጀር መኪና እና በ25 ሺ ብር መነሻ ካፒታል የተጀመረው የጨርቃ ጨርቅ ኢንተርፕራይዝ በአሁኑ ወቅት የመሥሪያ ማሽኖቹን ሳይጨምር 10 ሚሊዮን ብር መድረስ ችሏል። ድርጅቱን አሁን ስኬታማ መሆን ያስቻለው ከባለቤታቸው በተጨማሪ ከልጆቻቸው ጋር መሥራት በመቻላቸው እንደሆነ የገለጹት አቶ ዳዊት፤ ባለቤታቸው በቤት ውስጥ የስፌት ሥራውን ከጀመሩበት ወቅት ጀምረው ልጆቻቸው እናታቸውን በማገዝ ሙያውን መልመድ እንደቻሉ አጫውተውናል።
ወላጅ እናታቸውን ለማገዝ በሚል በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ የልብስ ስፌት ሙያን እየተመለከቱ ያደጉት አምስት ልጆቻቸውም ሥራውን ለመልመድ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል። ከወላጅ እናታቸው ከደጃቸው የቀሰሙትን ሙያም በዘመናዊ ትምህርት በማስደገፍ ዘርፉን በተሻለ ጥራት ተቀላቅለው ውጤታማ እንዲሆን የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ከአምስት ልጆቻቸው ጋር ተደራጅተው የሚሰሩት እነዚህ ጥንዶች በቀጣይም ዘርፉን ከዚህ በበለጠ የማስፋፋትና ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ አላቸው። በፋሽን ዲዛይን ሰልጥነው ድርጅቱን በሙያ እያገዙ ከሚገኙት አምስት ልጆች መካከል አንደኛዋ በፋሽን ዲዛይን ውድድር ከክልሉ የዋንጫ ተሸላሚ መሆንዋን አቶ ዳዊት አጫውተውናል።
‹‹ቤተሰብ በጋራ መሥራት ሲችል በእጅጉ ተጠቃ ሚና ውጤታማ መሆን ይችላል ።ለዚህም እኛ ምሳሌዎች ነን›› የሚሉት አቶ ዳዊት፤ ከቤተሰብ ጋር ተናቦ መሥራት ወጪን ለመቆጠብም ሆነ ተቀማጭ በማድረግ ውጤታማ ለመሆን የጎላ ድርሻ አለው። በተለይም ኢትዮጵያውያን በጋራ የመመገብ ልምድ ያለን በመሆኑ በጋራ የመሥራት ልምድንም ማጠናከር ከተቻለ በቀላሉ ማደግ መለወጥ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው ። ልጆቻቸውም በጋራ ተናበው በመስራታቸው ለድርጅቱ ትልቅ አቅም መፍጠር የቻሉ እንደሆነና እነሱ ቢደክሙ እንኳን ልጆቹ ሥራውን ማስቀጠል የሚያስችል ከፍተኛ ፍላጎት ከአቅም ጋር ያላቸው መሆኑን አጫውተውናል።
ከፋሽን ዲዛይን ባለሙያ ልጆቻቸው ጋር የተደ ራጁት አቶ ዳዊት በኖጲቾ የልብስ ስፌት ኢንተርፕራይዝ የሚመረቱትን ሶስት አይነት አልባሳት በሶስት የመሸጫ ቦታዎቻቸው ላይ ለይተው የሚሸጡ እንደሆነ ተናግረ ዋል። ይህም አልባሳቱ የተለያዩ በመሆናቸው ደንበኞች ምርቱ በቀጥታ ከሚገኝበት ሱቅ በቀላሉ የፈለጉትን ምርት ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል።
በዘመናዊ ጨርቅ የሚሰራውን ሙሉ ልብስ፣ ለእምነት ተቋማት የሚያገለግሉ የተለያዩ አልባሳትና ዘመናዊ በሆነው በኢምሮደር የሚመረተውን የህትመትና የጥልፍ ምርቶች እያንዳንዳቸው በተለያዩ ሱቆች ለገበያ የሚቀርቡ ሲሆን አንደኛ ልጃቸው ከማምረቱ ሥራ በተጨማሪ በሽያጩም ላይ ተሰማርታ ትገኛለች።
የቤተሰብ ካምፓኒ በማቋቋም የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉን በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመሸጋገር ዕቅድ ይዘው የሚተጉት ቤተሰቦች በቀጣይ ከአገር ውስጥ ባለፈ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅደው እየሰሩ ይገኛሉ። የሚያመርቷቸውን የተለያዩ የአገር ባህል እና ዘመናዊ አልባሳት በጥራትና በስፋት በማምረት ወደ ውጭ ገበያ የመላክ ዕቅዳቸውን ለማሳካት በቅድሚያ ተወዳዳሪ ሆነው በአቅራቢያቸው በሚገኘው ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ መግባት ያለባቸው መሆኑንና ለአገር ውስጥ በስፋትና በጥራት በማቅረብ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን አልባሳት ለማስቀረት እየሰሩ ያሉበት ሁኔታ መኖሩን አቶ ዳዊት ያስረዳሉ ።
በአሁኑ ወቅትም እያመረቱበት ካለው 400 ካሬ ሜትር የማምረቻ ሼድ በተጨማሪ አዲስ ለሚያስገነቡት ማሽን ተጨማሪ 400 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሼድ ከመንግሥት በኪራይ ተረክበው የማሽን ተከላ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ናቸው።ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ድርጅታቸው በተለያዩ መንገድ ለአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
አጠቃላይ የድርጅቱን የሥራ እንቅስቃሴ የተመለ ከተው የዲላ ከተማ አስተዳደርም ድርጅቱ ቀድሞ ይሰራበት በነበረ ቦታ ላይ 150 ካሬ ሜትር ቦታ ጨምሮ ደረጃውን የጠበቀ ባለ አራት ፎቅ ህንጻ እንዲገነባ ፈቃድ ሰጥቷል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሥራውን በመጀመር ሂደት ላይ ይገኛሉ።
ህንጻው የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ሲሆን በዋናነት ምርቶቻቸውን ለማሰራጨት የሚጠቀሙበት እንደሆነና በቀጣይ በአቅራቢያቸው ወዳሉ ከተሞች ለሚያደርጉት ማስፋፊያ የካፒታል ምንጭ እንደሚሆናቸው ነው የጠቀሱት ። እኛም ዕቅዳቸው ተሳክቶ ፍሬ ያፈራ ዘንድ በመመኘት ጥንቅራችንን አበቃን!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8 /2014