ማገዶም ሆነ በቴክኖሎጂ የታገዘ የኤሌክትሪክ ኃይል ሳያስፈልግ፣በአካፋና ዶማ ለመቆፈርም የሰው ጉልበት ሳይጠይቅ፣በራሱ ኃይል ገፍቶ ከምድር ውስጥ እየተፍለቀለቀ በመውጣት ለሰው ልጅ አገልግሎት የሚሰጥ የተፈጥሮ የምድር ውስጥ የሙቀት ኃይል አንዱ የተፈጥሮ ፀጋ ማሳያ ነው። ሰዎች የጤና ችግር አጋጥሟቸው ፈውስ ሲፈልጉ ተፍለቅልቆ ወደላይ ከሚወጣው ፍልውሃ ሥር ሆነው በሙቀቱና በእንፋሎቱ ይታከማሉ። ድንች፣የበቆሎ እሸት፣እንቁላልና ሌላም ተቀቅሎ ለምግብነት የሚውል ነገር በላስቲክ ቋጥረው በፍል ውሃው ቀቅለው ይመገባሉ። አካባቢን ሳይበክሉ ምግቦቻቸውን አብስለውና የጤና ፈውስ አግኝተው ወደቤታቸው ይመለሳሉ። ደጋግመውም ወደስፍራው ይሄዳሉ። አንዳንዶችም ይህን የተፈጥሮ የፍል ውሃ ፀጋ ከሃይማኖታዊ ፈውስ ጋር አያይዘው ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። በአንዳንድ አካባቢም ቦታውን በመከለል ለመታጠቢያ አገልግሎት በማዋል የገቢ ምንጭ አድርገው ይጠቀሙበታል። ያለድካምና ያለከልካይ ከምድር ውስጥ በሚገኘው ፍል ውሃ መጠቀም በኢትዮጵያ እንዲህ ተለምዷል። ይህ የምድር ውስጥ ሙቀት ሀብት ለአዲስ አበባ ከተማ መመሥረትም ምክንያት መሆኑ ይነገራል። በአዲስ አበባ ከተማ የመታጠቢያ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የፍልውሃ አገልግሎት እቴጌ ጣይቱ ከመኖሪያቸው ከእንጦጦ ቤተመንግሥታቸው አዲስ አበባ ብለው ወደ ሰየሟት ስፍራ በደረሱ ጊዜ በፍልውሃው ተማርከው አሁን የምትጠራበትን ስም አዲስ አበባ ብለው እንዳወጡላት የሚናገሩ የታሪክ ድርሳናት አሉ ።
የምድር ውስጥ ሙቀት (ጂኦተርማል) በተለይ በስምጥሸለቆ (ሪፍትቫሊ) የኢትዮጵያ ክፍል በስፋት መኖሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሀብቱ ለኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭነት በመዋል አገራዊ ኢኮኖሚን ከፍ በማድረግ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ። በዚህ ረገድም በኢትዮጵያ ጅምር ሥራ ቢኖርም ተጠናክሮ ባለመቀጠሉ፣በኢንቨስትመንትና በሰው ኃይል የአቅም ውስኑነት፣በትኩረት ማነስ ከሀብቱ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ተጠቃሚ መሆን ሳይቻል ቆይቷል። እንዲህ ያለውን ሀብት በአማራጭነት በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ማዳረስ አለመቻሉና 60 በመቶ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ በጨለማ ውስጥ ለመኖር መገደዱ ቁጭት ያሳድራል። አማራጮች ሳይታዩ በተወሰነ የኃይል አቅርቦት ላይ ብቻ መረባረብ ተገቢ እንዳልሆነም አንዳንዶች አስተያየት ይሰጣሉ።
በኢትዮጵያ ስለሚገኘው የምድር ውስጥ ሙቀት (ጂኦተርማል) ሳይንስን መሠረት አድርገው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የምድር ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ይርጉ እንደሚከተለው አስረድተዋል። ምድር በተፈጥሮ ውስጧ የጋለ ነው። በመሆኑም በምድር ውስጥ የታመቀ የሙቀት ኃይል አለ። ውስጥ ያለው ሙቀት የምድር ቅርፊት ወደሚባለው የላይ አካል የሚወጣው እንጂ የጂኦተርማል ኃይል በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ የተፈጥሮ ፀጋ ነው። ወደ ምድር ውስጥ ጠለቅ ባለ ቁጥር ሙቀቱ እየጨመረ ነው የሚሄደው። ይህን ሀብት ከምድር ውስጥ በማውጣት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። ኢትዮጵያን አቋርጦ የሚሄደው የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ለየት ያለ የስነምህዳር አቀማመጥ(ጂኦሎጂ) ያለውና አካባቢው በጥልቀት በተቆፈረ ቁጥርም የሙቀት መጠኑ እየጨመረ ይሄዳል።
በዚህ የስምጥሸለቆ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ይከሰታል። ይህንኑ ተከትሎም እሳተጎመራ (ቮልካኖ) ፍንዳታም ይከሰታል። እነዚህ ክስተቶች አካባቢውን ለየት የሚያደርጉ ሲሆን ለኃይል ምንጭ መገኛ ቁልፍ ስፍራ ነው። ፍልውሃ፣እንፋሎት የሚባሉት ሁሉ የምድር ሙቀት መገለጫዎች ናቸው። ኢትዮጵያ የዚህ ፀጋ ባለቤት ስትሆን፣ከአፋር ጀምሮ በመተሐራ፣አዳማ፣ሀዋሳ፣ውስጥ ለውስጥ የስምጥ ሸለቆን ተከትሎ ሀብቱ መኖሩን ማረጋገጫዎች አሉ። በራሱ ኃይል ወደላይ ከወጣው በተጨማሪ አንድና ሁለት ኪሎ ሜትር ቁፋሮ ቢከናወን የሚፍለቀለቅ ኃይለኛ ግፊት ያለው ውሃ ይገኛል። ይህን ኃይለኛ ግፊት ያለው የሚፍለቀለቅ ውሃ ለኤሌክትሪክ የኃይል ምንጭ ጥቅም ማዋል ይቻላል።
የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ የሚባለውን ዋና የአፋር አካባቢን ተከትሎ የሚገኘውን ሀብት ለመጠቀም ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ጀምሮ ልዩ ትኩረትና ጥናት ሲደረግ ቆይቷል ። አንዳንድ ለውጦችም ታይተው ነበር። ይሁን እንጂ በተመሳሳይ ወቅት ኬንያ ላይ የታየው ውጤት ኢትዮጵያ ውስጥ አልታየም። ኬንያ በጣም በመሥራት በምድር ሙቀት(ጂኦተርማል) ከአንድ ሺ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ትጠቀማለች። ሀብቱ ቢኖርም ጥቅም ላይ ለማዋል በምርምርና ጥናት የታገዘ ብዙ ሥራ መሥራትና መዋዕለ ንዋይ ይጠይቃል። ኢትዮጵያ ውስጥ ሀብቱ በስፋት ይገኛል። ጥቅም ላይ ለማዋል ግን ውስንነቶች አሉ። ዝዋይ አሉቶላንጋኖ በሚባል አካባቢ እስከ ሰባት ሜጋዋት የሚያመነጭ የሙከራ ኃይል ተጀምሮ ነበር ። ይሁን እንጂ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ አይደለም። ከሙቀት ኃይል ኤሌክትሪክ የማመንጨት ተግባር በአገር ሀብትና የሰው ኃይል ብቻ የሚከናወን ተግባር አይደለም። በዘርፉ አቅም ያላቸውን ባለሀብቶች መሳብ ይጠይቃል። ኬንያም የውጭ ባለሀብቶችን በመሳብ ነው ከሀብቱ ተጠቃሚ ለመሆን የቻለችው ። በኢትዮጵያ ላለፉት አስር አመታት አበረታች የሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ተከናውነዋል።
ጥናትና ምርምር መቋረጥ የለበትም የሚሉት ፕሮፌሰር ገዛኸኝ፤ እስካሁን በዘርፉ በተካሄደው መለስተኛ ጥናትና ፍለጋዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ከ10ሺ ሜጋዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል በከርሰምድር ውስጥ የእንፋሎት ኃይል (ጂኦተርማል)መኖሩ ተረጋግጧል። ይህ ግምታዊ ውጤት እንጂ ሀብቱ ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም። ያልተቋረጠ ጥናትና ምርምር ያስፈልጋል የሚባለው የሀብት መጠን ለማወቅ ስለሚያግዝ ነው። በከርሰምድር ውስጥ ያለው እንፋሎት አሁን ላይ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጥቅም ላይ እየዋለ ካለው፣እንዲሁም ለመጠጥ፣ለግብርና ሥራና ለተለያየ አገልግሎት ከሚውለው ውሃ የሚለይበትንም ፕሮፌሰሩ እንዳስረዱት፤ለተጠቀሱት አገልግሎቶች የሚውለው ውሃ በቅርብ ጥልቀት ውስጥ ነው የሚገኘው። እስከ ሶስት መቶ ኪሎ ሜትር ድረስ በቁፋሮ ይገኛል። ሙቀትም የለውም። ለአብነትም ከአቃቂ አካባቢ የሚወጣው የከርሰምድር ውሃ ከተከማቸ አለት ውስጥ ነው። ጂኦተርማል ግን በጥልቀት ውስጥ ነው የሚገኘው።
ኢትዮጵያ አማራጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ እያላት ነገር ግን ተጠቃሚ አለመሆኗን በእርሳቸው እይታ እንዲገልጹልን ፕሮፌሰሩ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤እንደአገር የተለያዩ የኃይል አማራጮች መኖራቸው ይታወቃል። ነገር ግን ተመራጭ ሆኖ እየተሠራበት ያለው ከግድቦች በሚመነጭ ኃይል ነው ኤሌክትሪክ እየተዳረሰ ያለው። ዝናብና ወንዞች ስላሉ ነው ግድብ ተመራጭ የሆነው። ይህም ኢትዮጵያ የውሃ ሀብት እንዳላት ማሳያ ነው። ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣የምህንድስና ሙያ ያለው የሰው ሀብት መኖርም ሌላው ነጥብ መሆኑም ወደግድቡ ለማድላት በምክንያትነት ሊጠቀስ ይችላል። እነዚህ ሁሉ ወደሌላ አማራጭ ላለመሄድ ምክንያት ቢሆኑም አማራጭ ሀብቶችን መጠቀሙ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የበለጠ ያጎለብታል።
መንግሥትም ፖሊሲን ከማሻሻል ጀምሮ የተለያዩ የኃይል ምንጮችን ለመጠቀም ጥረት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል። ከነፋስ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ተጨማሪ ኃይል ተፈጥሯል። ጂኦተርማል አንዱ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጭ እንደሆነ በመንግሥት በኩል ትኩረት ያገኘ መሆኑም ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ይከናወኑ የነበሩ ሥራዎች ማሳያ ናቸው። ኬኒያ በጂኦተርማል ላይ ትኩረት ያደረገችው እንደ ኢትዮጵያ በግድብ ለመጠቀም የሚያስችላት ሀብት ስለሌላት ነው።
በጂኦተርማል ዘርፍ የተማሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ያስታወሱት ፕሮፌሰር ገዛኸኝ፤በጂኦተርማል ተጠቃሚ የሆኑና በዘርፉም እውቀቱ ያላቸው እንደ ጣሊያን፣ኒዚላንድ አይስላንድ ያሉ አገሮች ሲሆኑ አገራቱ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላሉ አገሮች የትምህርት ዕድል በመስጠት ባደረጉት እገዛ ኢትዮጵያውያንም የመማር ዕድሉን አግኝተዋል። ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ አገራቸው ቢመለሱም ብዙዎች ተመልሰው በመሄድ የተማሩትን ሙያ ለሌላ አገር በማዋል ላይ ነው የሚገኙት። ትምህርቱና እውቀቱ ያላቸው ሙያተኞች ከአገራቸው ይልቅ በሌላ አገር መሥራትን የመምረጥ ነገር በኢትዮጵያ እየተለመደ ነው።
በጂኦተርማል ዙሪያ አፋር ውስጥ ተንዳሆና ዝዋይ አካባቢ አሉቶ ላንጋኖ ላይ ለሙከራ የተቆፈሩ ጉድጓዶች በጣሊያኖች ድጋፍ ነው የተከናወነው። ብዙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችም በቁፋሮ ቴክኖሎጂ በመሰልጠንና ልምድ በማግኘት ጥሩ የሚባል ተሞክሮ እንደነበር አስታውሰዋል። በጂኦተርማል ዙሪያ አፍሪካ ውስጥ ማሰልጠኛ ተቋቁሞ ትምህርት ለምን አይሰጥም የሚል ሀሳብ በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ማሰልጠኛ እንዲቋቋም ሀሳብ ቢኖርም እንደአገር በነበረው የድጋፍ ማነስ ሳይሳካ ቀርቷል። ይህ እድል ወደ ኬኒያ እየተወሰደ ነው። በዚሁ ዙሪያ ብዙ ዝግጅት የነበረ ቢሆንም፤ጀምሩ ተጠናክሮ ባለመቀጠሉ ይህ ነው የሚባል ውጤት ላይ መድረስ አልተቻለም።
እንደፈገርም የሚታየውን ክፍተት አስመልክተው ሲናገሩም፤ አንድ ነገር ይጀመራል ነገር ግን አይቀጥልም። በዘርፉ ልምድ ያላቸው አገር ውስጥ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ መንግሥት ያደረገውን የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃ በመልካም ጎኑ ያነሳሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር የውጭ ኩባንያዎች ኃይል አመንጭተው እንዴት መሸጥ እንዳለባቸው የሚገልጽ ሕግና ፖሊሲ አልነበረም። ኃይል የሚመነጨው ከግድቦች ነው። የማመንጨቱ ሥራም የሚከናወነው በመንግሥት ነው። በተሻሻለው ፖሊሲ የውጭ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ኃይል ማመንጨት ይችላሉ። ከእንፋሎት ወይንም ከንፋስ ኃይል ማመንጨት የሚችሉበት አሠራር ተፈጥሯል።
ኩባንያዎቹ ያመነጩትን ኃይል ቀጥታ ለተጠቃሚው አያደርሱም። ለመንግሥት ነው የሚሸጡት። ምክንያቱም በኤሌክትሪክ ገመድ ማስተላለፍ የሚችለው መንግሥት በመሆኑ። በዚህ አሠራር ኩባንያዎቹ ግንኙነታቸው ከመንግሥት ጋር ነው ። በዘርፉ የሚሠማሩ ኩባንያዎች የግድ የውጭ አገር መሆን የለባቸውም። አቅም ያላቸው አገር በቀል ኩባንያዎችም ሊሆኑ ይችላሉ። ፖሊሲው ተሻሽሎ ከወጣ ዓመታት ተቆጥሯል። በዚህ መሠረት አገር ውስጥ የገቡ ኩባንያዎች የተለየ ነገር ካልገጠማቸውና በሥራው ከገፉበት በዘርፉ ውጤት እንደሚያዩ ተስፋ አድርገዋል።
በዘርፉ የምርምር ሥራ እንዲጠናከር በተለይም በዩኒቨርስቲ በኩል መከናወን ስላለበት ተግባርም ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር ገዛኸኝ በሰጡት ምላሽ፤በዩኒቨርስቲ በኩል ተወዳድረው ለሚያልፉ የምርምር ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ ይደረጋል። ይሁን እንጂ ለጂኦተርማል የምርምር ሥራ ብቻ በሚል ቀጥተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ አይደረግም። እንፋሎት አለባቸው ተብለው የሚታወቁ ቦታዎች የእሳተጎመራ ቦታዎች ናቸው። በውስጡ የታመቀ አለት ይዞ የተቀመጠ ስፍራ ነው። በአንድ ወቅት ሊፈነዳ ይችላል። ይህ ቦታ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝና በውስጡም ስላለው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ጥናትና ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል። ዘርፉ አዋጭ ኢኮኖሚ እንዲኖረው በጥናትና ምርምር መደገፍ አለበት።
የሀብቱ መገኛ በሆነው አፋር ክልል ስላለው እንቅስቃሴም በሰመራ ዩኒቨርስቲ ጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር ጀማል አህመድን እንዳስረዱት፤በተለያየ ጊዜ በተደረገ የጂኦሎጂ ጥናት በአፋር ክልል ወደ ስምንት የሚደረሱ ቦታዎች ዳሉል፣ጊዱ፣ተንዳሆ፣ሚሌ፣መተከል፣ጎፋ፣ፈንታል ሀብቱ አለ። በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኘው ሀብት እንፋሎቱ ከውስጥ ወጥቶ በትክክል የሚታይና ሰዎችም የሚያውቋቸው ናቸው። መምህር ጀማል እንዳሉት የጂኦተርማል ሀብት ለኤሌክትሪክ ኃይልነት ከመዋል ባለፈ ሁለት አበርክቶዎች አሉት። በውስጡ የተለያዩ ማዕድናት ሊገኝ ይችላል። ሁለተኛው ጥቅም ደግሞ የጂኦሎጂ የቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ በማገልገል የኢኮኖሚ ምንጭ ይሆናል። በአካባቢያቸው የሚገኘው ሀብት አሁን ላይ ለቱሪስት መስህብ ከመሆን ባለፈ ለኤሌክትሪክ ኃይል እየዋለ አይደለም። የሰመራ ዩኒቨርስቲ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል በአፋር የሚገኙ የጂኦሎጂ ሀብቶች በአንድ ወቅት በተካሄደ ሲምፖዚየም ላይ ቀርቧል። በተቻለ መጠን ሀብቱን የማስተዋወቅ ሥራ እየተሞከረ ይገኛል።
ሀብቱን የሚመራውና የሚያስተዳድረው ማዕድን ሚኒስቴር ሰሞኑን በድረገጹ ባስተላለፈው መረጃ ኢትዮጵያ በጂኦተርማል ኃይል ዘርፍ ያላት እምቅ ሀብት በመንግሥትም ይሁን በግሉ ዘርፍ ጥቅም ላይ ሲውል ለአገራችን የኃይል አቅርቦት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆን አመልክቷል።
እንደ ሚኒስቴሩ መረጃ ባለፉት ዓመታት በአርሲ ኢተያ የጂኦተርማል ኃይል ለማምረት እንቅስቃሴ ላይ የቆየው TM Geothermal operation PLC.(TMGO) በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ 50 ሜ.ዋት ኃይል የሚያመነጭ ሲሆን፣ኩባንያው የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ግንባታውን ለማከናወን ከMitsubishi Corporation እና SEPCOlll Electric Power Construction co., ltd ጋር የ 100 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ተፈራርሟል። ኃይል የማመንጫ ግንባታው በሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ኃይል ማመንጨቱ ይገባል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7 /2014