በአሁን ወቅት ነዋሪዎች በአንድ ልብ አንድ ቃል ከተናገሩ ስለ ኑሮ ውድነት ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም:: በተለይም በምግብ ሸቀጦች ላይ ዕለት ተዕለት እየታየ ያለው የዋጋ መናር ማኅበረሰቡ ከሚችለው አቅም በላይ እንደሆነበት ምስክር መጥራት አያሻም ::
ማንኛውም መገበያያ ሥፍራ የሚደመጠው እያንዳንዱ የፋብሪካም ሆነ የግብርና ምርት ጨመረ እንጂ ቀነሰ አይደለም። ቀልድ ቁምነገሩ ፤ፌዝ ተረቱ ሁሉ ይሄንኑ የሚጠቁም ነው ::
እርግጥ ነው ኅብረተሰቡ በእጅጉ የተማረረበትን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በሚል መንግሥት በተለያየ ጊዜ የወሰዳቸው እርምጃዎች ቢኖሩም ችግሩ ግን ሊቃለል አልቻለም:: የኑሮ ውድነቱ ከከተሞች ባለፈም በገጠርና በገጠር ከተሞች ጭምር ዜጎችን እየፈተነ ያለ ለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ:: ተባብሶ የቀጠለው የኑሮ ውድነት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ባሉ የክልል ከተሞች ጭምር ጫናው የበረታ ነው ::
የዝግጅት ክፍላችንም በሀዋሳ ከተማ ያለው የገበያ ሁኔታ እንዲሁ አገራዊ የሆነውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ምን ምን ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ መመልከት ችሏል:: በከተማው ነዋሪ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ ቦንሳ ታዲዎስ እና አቶ አርጋው በሰጡን አስተያየት የኑሮ ውድነቱ ከዕለት ዕለት እየተባባሰ ነው። በተለይ እንደ ዘይት አይነቱ ደግሞ ዋጋው ከመጨመሩም በላይ በገበያ ላይ እንደልብ አይገኝም።
አሁን አንዳንድ ምርቶች ትንሽ ቅናሽ ያላቸው የሸማቶች ኅብረት ስራ ማኅበራት የሚያቀርቡት ነው። ዱቄት በሱቅ ውስጥ ከሚሸጠው በተሻለ በድንኳን ውስጥ የስምንት ብር ቅናሽ አለ ። እንዲሁም ሙዝ ዋጋው በኪሎ እስከ 40 ብር ደርሶ ነበር አሁን ግን የመቀነስ አዝማሚያ አለ ። ይሁን እንጂ አሁንም የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አቅቶናል መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በከተማው የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የተሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የኅብረት ሥራ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጴጥሮስ ዮሐንስ ናቸው::
እንደሳቸው ማብራሪያ የኑሮ ውድነቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣ እንደሆነና ለዚህም በዋናነት የሚጠቀሱ ሁለት ምክንያቶች እንደሆኑ ነው:: በቀዳሚነት ያነሱት እንደ ሀዋሳ ከተማ በግብርና ምርቶች እንዲሁም በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ሰፊ የሆነ የአቅርቦት እጥረት አለ:: በዛው ልክ ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለ:: በሁለተኛ ደረጃ መልካም ነጋዴዎች እንዳሉ ሁሉ ሕገወጥ ነጋዴዎች ምርት በመደበቅ የዋጋ ንረት እንዲከሰት በማድረግ ጥቅም የሚያገኙ ነጋዴዎች ለዋጋ ንረትና አጠቃላይ ለኑሮ ውድነት ትልቅ ድርሻ አላቸው::
እንዲህ አይነት ነጋዴዎች በከተማው ምርት በመደበቅ ገበያው ላይ የምርት እጥረት እንዲከሰትና እጥረት ሲከሰት ደግሞ ዋጋ ጨምሮ የመሸጥ አዝማሚያዎችን ያሳያሉ:: በመሆኑም ሀዋሳ ከተማን ጨምሮ በአገር ደረጃ የዋጋ መናር በየቦታው ይታያል:: ይህን ችግር ለመቅረፍም በተለይም የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ንግድና ልማት መምሪያ እንዲሁም የኅብረት ሥራ ልማት ጽሕፈት ቤት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል::
ለአብነትም አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዲከሰት በሚያደርጉ ሕገወጥ ነጋዴዎችን በመከታተልና በመቆጣጠር እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ያሉት አቶ ጴጥሮስ፤ በሀዋሳ ከተማ 80 የሚደርሱ ሸማቾችና ሁለገብ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚገኙ መሆኑን ገልጸው የኅብረት ሥራ ማኅበራቱም የተደራጁበትን ዓላማ ለማስፈጸም እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል:: ኅብረተሰቡን ለማገልገል የተደራጁት እነዚህ የኅብረት ሥራ ማኅበራትም በተቻለ መጠን የግብርና እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማቅረብ እንዲችሉ የተጀመሩ ሙከራዎች አሉ:: ሙከራዎቹን አጠናክሮ ለመቀጠልም እየተሠራ ነው::
በዋናነት የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን ለኑሮ ውድነቱ አይነተኛ ድርሻ ያለው ቢሆንም ማኅበራቱ የግብርና እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ባላቸው አቅም ማቅረብ እንዲችሉ እየተደረገ ይገኛል:: ለአብነትም በሀዋሳ ከተማ አንድ ኪሎ ሙዝ 40 ብር ሲሸጥ የነበረ ሲሆን በአርባምንጭ ዙሪያ የሚገኙ አልሚዎችን በማሰባሰብ በሀዋሳ ከተማ 20 የተለያዩ ቦታዎች ላይ ድንኳኖችን እንዲጥሉና መሸጫ ሼዶችን በማዘጋጀት ሙዝ በ28 ብር መሸጥ እንዲችሉ ማድረግ ተችሏል::
በዚህም በከተማ ውስጥ ሲሸጥ ከነበረው 12 ብር ቅናሽ በማድረግ ገበያውን ማረጋጋት ተችሏል:: ይህ ሥራ በተሰራበት ማግስት አብዛኛው ነጋዴ የሙዝ ዋጋን ከ40 ብር ወደ 30 እና 35 ብር የማውረድ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ::
በአሁን ወቅት በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በድንኳን ውስጥ አንድ ኪሎ ሙዝ በ30 ብር እየተሸጠ ይገኛል:: በዚህም ማኅበረሰቡ ደስተኛ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ጴጥሮስ፤ ሙዝ ላይ የተሠራውን ሥራ መነሻ በማድረግ እንደ ሀዋሳ ከተማ ከዚህ ቀደም በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተከፋፍሎ የማያቀውን የስንዴ ዱቄት እያከፋፈለ ይገኛል።
ጽሕፈት ቤቱ 1800 ኩንታል የስንዴ ዱቄት በመረከብ አንድ ኪሎ የስንዴ ዱቄት በ40 ብር ሂሳብ ለሸማቹ እያቀረበ ይገኛል:: ውጭ ላይ የሚሸጠው 50 እና 52 ብር ሲሆን በዚህም ከ10 እስከ 12 ብር ባነሰ ዋጋ የቀረበ መሆኑን አንስተዋል::
በዚህ መሠረት የኑሮ ውድነት የተጫነውን ኅብረተሰብ እያገለገሉ እንደሆነ ያነሱት አቶ ጴጥሮስ፤ ፓስታ ፣ማኮሮኒን ጨምሮ ሌሎችንም የፋብሪካ ምርቶችን እንዲሁም የግብርና ምርቶችን በማኅበራቱ አማካኝነት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማኅበረሰቡ እያቀረቡ እንደሆነ ነው የጠቀሱት :: በተለይም ሽንኩርት፣ ቲማቲምና ሌሎች አትክልቶችን ጨምሮ በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ወደ ሸማቹ እንዲደርስ በማድረግ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገር ግን አቅርቦት የችግር ማነቆ እንደሆነባቸው አብራርተዋል::
ከፋብሪካ ምርቶች መካከል የዘይት ምርት ላይ የሚታየው እጥረት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ሊሻገሩት እንዳልቻሉ ያነሳሉ። በቅርቡ ሶስት መቶ ሺ ሊትር የሚጠጋ ዘይት ያቀረቡ ቢሆንም አሁንም ድረስ ፍላጎትና አቅርቦቱ ሊጣጣም እንዳልቻለ ነው የገለጹት:: በተለይም መጪው የበዓል ወቅት እንደመሆኑ ሌሎች የምግብ ሸቀጦችን ጨምሮ ዘይት በከፍተኛ መጠን የሚፈለግ በመሆኑ ይህንኑ ፍላጎት ለማሟላት ጥረት ይደረጋል:: በአሁን ወቅትም ከውጭ የሚገቡ የዘይት ምርቶች ሱቅ ላይ እስከ 1200 ብር እየተሸጠ ሲሆን በኅብረት ሥራ ማኅበራት ውስጥ ደግሞ 950 ብር ድረስ ይሸጣል::ሆኖም በቂ አቅርቦት የለም።
ማኅበራት ለትርፍ ያልተደራጁ እንደመሆናቸው ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ማቅረብ እንዲችሉ የተለያዩ ድጋፎች ይደረግላቸዋል የሚሉት አቶ ጴጥሮስ፤ የቦታ የትራንስፖርትና ሌሎች ድጋፎችንም በማድረግ ማኅበራቱ ውጭ ላይ ካለው ዋጋ በተወሰነ መጠን ቅናሽ ድርገው ገበያውን ማረጋጋት እንዲችሉ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል:: ይሁንና እንደ ከተማ አስተዳደር ይበልጥ መሥራት የሚገባውና በተለይም ያለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን ከመቆጣጠር አንጻር የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል::
ከዚህ ጋር በተያያዘም ሸማቹ ማኅበረሰብም በሁሉም ነገር መንግሥትን ብቻ የመጠበቅ አዝማሚያዎች ያሉት በመሆን ይህ አይነቱ አመለካከት መቀየር እንዳለበት አንስተው ማኅበረሰቡ የሚያጋጥመውን ማንኛውም ሕገወጥ ድርጊት የማጋለጥ ሥራ መሥራት እንዳለበት አመላክተዋል::
መጪው ጊዜ የበዓል ወቅት እንደመሆኑ በርካታ ሥራዎች መሥራት የሚጠይቅ መሆኑን ያነሱት አቶ ጴጥሮስ፤ ከግብርና እንዲሁም ከኢንዱስትሪ ምርቶች በተጨማሪ ወተትና የወተት ተዋጽዖ እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽዖዎችን ያቀርባሉ። ለአብነትም በቅርቡ ከስምንት ብር በላይ ሲሸጥ የነበረው እንቁላል እስከ ስድስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም መሸጥ የቻሉ ሲሆን አይብ ቅቤና መሰል የወተት ተዋጽዖም በአርብቶ አደሮች አማካኝነት እየቀረበ ይገኛል:: በመሆኑም በአሁን ወቅት አንድ ኪሎ ቅቤ እስከ በ550 ብር እየተሸጠ ነው :: ይህንኑ አጠናክረው መቀጠል ከተቻለ በቀጣይ ገበያውን ማረጋጋት እንደሚቻል አስረድተዋል::
ለዋጋ ንረት ዋነኛ ማነቆ የሆነውን የምርትና የአቅርቦት እጥረት ለማሻሻል ለአርሶ አደሩም ሆነ ለኢንዱስትሪዎች ምን ድጋፍ አድርጋችኋል? ምንስ መደረግ አለበት ስንል ላነሳነው ጥያቄ አቶ ጴጥሮስ ሲመልሱ፤ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ዙሪያ ከመስኖ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የተለያዩ ድጋፎች እያደረገ ነው።
በተለይም ከግብርና ምርቶች ጋር ተያይዞ ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘርና ሌሎችንም አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ይቀርባሉ:: ይበልጥ ደግሞ በአሁን ወቅት እንደ አገር የተጀመሩ ንቅናቄዎችን ለማስቀጠል ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ::
ይህም ሲባል እያንዳንዱ ሰው ትንሽም ቢሆን ባለው ቦታ ላይ ምግብ ሰብሎችን እንዲያለማ በማድረግ የከተማ ግብርና እንዲስፋፋ ማድረግ ነው:: በተለይም በሃይማኖት ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና ሰፋፊ ይዞታዎች ባሉበት አካባቢ የከተማ ግብርናን አጠናክሮ መቀጠል እንዲቻል እየተሠራ ነው:: ይህን አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር ማቃለል ይቻላል በሚል ዕምነት ወደ ተግባር መገባቱን ጠቁመዋል::
የፋብሪካ ምርቶችን በተመለከተም እንዲሁ አምራቾች ከደላላ ውጭ ሆነው ምርቶቻቸውን በቀጥታ ሸማቹ ጋር ማድረስ የሚችሉበትን መንገድ እየተዘረጋ ነው:: ለዚህም በከተማ ውስጥ የመሸጫና የማከማቻ ቦታዎችን ከክፍያ ውጭ በሆነ መንገድ የማዘጋጀትና የመደገፍ ሥራ ይሠራል:: አምራቾች ያለምንም ችግር በቀጥታ ለሸማቹ ማቅረብ ከቻሉ መሐል ላይ ሆኖ ዋጋ እየጨመረ ያለውን ደላላ ከጫወታ ውጭ በማድረግ ገበያውን ማረጋጋት የሚያስችል መሆኑ ታምኖበት እየተሠራ ነው::
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተወሰደ ተሞክሮም የእሁድ ገበያን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን ያነሱት አቶ ጴጥሮስ፤ በአሁን ወቅት ሁለት አርሶ አደሮች በዋናነት ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ጥቅል ጎመን ለሸማቹ በቀጥታ እያቀረቡ ይገኛሉ ብለዋል:: የመሸጫ ቦታውን ኪራይ ከመሸፈን ባለፈም ጥበቃ በማድረግ ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሸማቹ ማቅረብ እንዲችሉ ተደርጓል:: ከፋብሪካዎች ጋርም በተያያዘ በተለይም የሳሙና ምርቶችን የሚያመርቱ አምራቾች የመሸጫ ቦታ በማመቻቸት ሸማቹም ሆነ አምራቹ ተጠቃሚ እንዲሆን የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም የተሟላ ነው የሚል ዕምነት የሌላቸው በመሆኑ ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው::
ከተደራሽነት አንጻር እንደ ሀዋሳ ከተማ ስፋት ገና ብዙ የሚቀር ሥራ መኖሩን ይናገራሉ አቶ ጴጥሮስ። ስምንት ክፍለ ከተሞችና 32 ቀበሌዎች ላሏት ሀዋሳ ከተማ ሥራው ገና ጅምር መሆኑን አንስተዋል:: በመሆኑም ሥራውን አጠናክረው ለመቀጠል አርሶ አደሩን በመቀስቀስ በቀጣይ በስፋት የሚሠራ ይሆናል::
እንደ አገር የሚታየው የኑሮ ውድነት ረገብ እንዲል ብሎም ገበያውን ማረጋጋት እንዲቻል በሀዋሳ ከተማ ኅብረት ሥራ ማኅበር በኩል የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል:: ከእነዚህም መካከል ከእሁድ ገበያ በተጨማሪ በየዕለቱ በስምንቱም ክፍለከተሞችና በ32 ቀበሌዎች የተለያዩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በሸማቹ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት ለሸማቹ እየቀረበ ይገኛል::
ለዋጋ ንረት መባባስ ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸው ነጋዴዎችን ላይ እርምጃ በመውሰድ ለማስተካከል በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር 147 ቤቶች የታሸጉ መሆናቸውን ለአብነት አንስተዋል።
በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ሶስት ሺ ሊትር ቤንዚንም እንዲሁ ተወርሶ ለመንግሥት ገቢ መደረጉ ከማስተካከያ እርምጃዎች መካከል የሚጠቀሱ ነው :: በቀጣይ ሶስት ወራት ውስጥ እንደ ከተማ አስተዳደር በርካቶች እየተማረሩበት ያለውን የቤንዚን ንግድ ላይ ያለውን ችግር ለማስተካከል እየተሠራ ነው::
ሕገወጥ የንግድ ቤቶችን ከማሸግና እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ የሸማቾችና ኅብረት ሥራ ማኅበራትን አቅም በመገንባት ኅብረተሰቡ አማራጭ ማግኘት እንዲችል በማድረግ እየተባባሠ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት መሥራት አማራጭ የሌለው ምርጫ በሆኑ የተጠናከረ ሥራ እየተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል ::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 /2014