መንደርደሪያ ቢሆነን…፤
የዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ የቀድሞው ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፤ ከ1954 ዓ.ም በኋላ ደግሞ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዩኒቨርስቲ በመባል የሚታወቀው የአገሪቱ ታላቅና አንጋፋ የትምህርት ተቋም በየዓመቱ ተወዶና ተናፍቆ የሚጠበቅ የኮሌጅ ቀን የሚባል ዓመታዊ የተማሪዎች በዓል ነበረው:: በዚህ በዓል ላይ በከፍተኛ የክብር እንግድነት የሚገኙት ንጉሠ ነገሥቱ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ነበሩ:: ንጉሡ በበዓሉ ላይ ሲገኙ በተለይም በግጥም ውድድር አሸናፊ የሚሆኑትን “ተማሪ ልጆቻቸውን” (ቀኃሥ፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን የሚጠሩት ልጆቻችን እያሉ መሆኑን ልብ ይሏል) የሚሸልሙትና የሚያበረታቱት በታላቅ የደስታ ስሜት እንደነበር የዘመኑ ታሪክ ማስረጃችን ነው::
እየዋለ እያደረ ግን በበዓሉ ላይ የሚቀርቡት አብዛኞቹ ግጥሞች ንጉሠ ነገሥታዊውን ሥርዓት፣ ሥር ሰዶ የኖረውን ፊውዳላዊ ፖለቲካና ንጉሡን ራሳቸውን ሳይቀር ግልጥልጥ አድርገው ይተቹና ይሄሱ ስለነበር መዳፈሩ እየጠነከረ በመሄዱ ንጉሡ በበዓሉ ላይ ላለመገኘት እርም ብለው ሊቀሩ ግድ ሆኗል::
በ1951 ዓ.ም በተከበረውና ንጉሡ በታደሙበት በዓል ላይ ተገኝ የተሻወርቅ የተባለ ተማሪ “ሰው ዕንቆቅልሽ ነው” የሚል ግጥም አቅርቦ ንጉሡ ከመደሰታቸው የተነሳ ትምህርት ሚኒስቴር መ/ቤት ግጥሙን አባዝቶ ለአገሪቱ ተማሪዎች በሙሉ እንዲሠራጭ እስከ ማዘዝ ተደርሶ ነበር:: ዘለግ ያለውና ንጉሡን “ከዙፋን አስነስቶ ያስጨበጨበው”፤ [ማስጨብጨቡና ከዙፋን ላይ የመነሳቱ ገለጻ ሥነ ጽሑፋዊ ውበት ለማከል ታስቦ መሆኑ ይሰመርበት]፤ ሙሉው ግጥም በዚህ ገጸ-ዘመን ላይ እንዳይታተም ዐውዱም ሆነ የጋዜጣው የዓርብ ውሱንነት ስለማይፈቅድ ስድስት ያህል ስንኞችን መርጠን በማውጣት ለማሳያነት እንገለገልበታልን፤ ወዲያውም ለመንደርደሪያ እንዲያግዘን ጭምር::
“ንገሩን እናንተ ገባን የምትሉ፣
ይሄ ነው ብላችሁ የአገር ልጅ ባህሉ::
ክፋቱን ጥፋቱን ባንድ ፊት አርጉና፣
ልማት ደግነቱን ወደዚህ ለዩና፣
አንፍሱ አንጓሉና ብጥር አድርጋችሁ፣
ንገሩኝ [የአገር] ልጅ ይሄ ነው ብላችሁ::
ከዚህ በላይ ተቆንጥረው የተጠቀሱት ጥቂት ስንኞች ለዚህ ጽሑፍና ለጊዜያችን ዐውድ መንደርደሪያነት የተሻለ መልዕክት ያስተላልፋሉ ተብሎ በመታሰቡ እንጂ ሙሉ ግጥሙ በራሱ የያዘው እምቅና ሞጋች መልእክት በስፋት ቢተነተን ብዙ እንማርበት ነበር::
“እፍረተ ቢሱ” ዘመናችን፤
በግጥሙ ውስጥ እንደተጠቀሰው ሁሉ ይህ የእኛ ዘመንም በዕንቆቅልሽ በተተበተቡ በርካታ ክስተቶች የተሞላ ነው:: በጎነቱንና ክፋቱን አንፍሰንም ሆነ አንጓለን ውጤቱ ይህን ይመስላል ለማለት አቅምም፣ ዕድልም አሳጥቶ ያሽመደመደን ይመስላል:: ያለምንም ማመንታት ደፈር ብለን ለመወያየት ወኔያችን ለማኮስተር ከፈቀድን ጊዜያችን ሰልጥኖብን አስገብሮን ካልሆነ በስተቀር ጊዜውን ለመዋጀት አቅም እንዳነሰን መገንዘቡ አይገድም:: ጊዜው ይበራል፤ ይከንፋል:: አብረን ለመክነፍና ለመብረር ክንፍም ሆነ ጥበብ የራቀብን ይመስላል:: ተወዳጁ መምህራችን ደበበ ሰይፉ በገጣሚነት ምናቡ ጊዜን የገለጠበት ምልከታ ለጥጠን ለነካካነው ሃሳብ ጥሩ መሰብሰቢያ ስለመሰለን እዚህ ስፍራ እናስታውሰዋለን::
ጊዜ በረርክ በረርክ፣
ጊዜ በረርክ በረርክ፣
ግና ምን አተረፍክ?
ግና ምን አጎደልክ?
ሞትን አላሸነፍክ፣
ሕይወትን አልገደልክ::
እውነት ነው፤ ጊዜ ይበራል ይከንፋል:: ለአብነት ያህል ከጋራ ጉዳዮቻችን እንምዘዝና ጊዜው እየተገዳደረን ከእጃችን ላይ ያስጣለንን ጥቂት ማሳያዎችን እናመላክት:: በየብሔረሰቡ “ነዎሩ” ሲሰኙ የኖሩት የሰው ለሰው መስተጋብር ባህሎች፣ በእድሜ የከበሩ ወግና ልማዶች፣ ተፈጥሮ የሚያስተምርንና በህሊና የምንዳኝባቸው በጎ ተግባራትና ድርጊቶች አደጋ ላይ እየወደቁ ግራ በመጋባት አመሳቅለውናል:: መልካም የሚሰኙ ማሕበራዊ እሴቶቻችንም ከእጅ ወድቆ እንክትክት እንደሚል ብርጭቆ በፊታችን ዕለት በዕለት ሲሰባበሩና ሲፈረካከሱ እያስተዋልን ነው::
እጅግ የሚገርመው ተቃርኖ ደግሞ ይሄው ኅብረተሰባዊ ስብራታችን እንደ “ጀግንነት” መቆጠሩ ነው:: በርእሱ ላይ በትምህርተ ጥቅስ ውስጥ የተቀነበበው “ጀግንነት” በበጎና በአርአያ ገላጭነት ተግባሩ ወካይነት የሚጠቀስ ሳይሆን ለምጸታዊ ገለጻና ማሳያ የቀረበ መሆኑን ማስታወሻ በማኖር ወደ ዝርዝሩ እንዝለቅ:: ለምሳሌ፡- በርካታ ዜጎች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎችና የብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ፊት ለፊት ብቅ እያሉ ወይንም በቴክኖሎጂ መጋረጃዎች ተጋርደውና አሸምቀው፤ ሲያሻቸው በራሳቸው ማንነት፣ ሲፈልጉም ስምና ፎቶግራፋቸውን በግላጭ እያስተዋወቁ አጉራ ዘለልነታቸውን ሲገልጹ “መብታቸው እስኪመስላቸው” ድረስ በልበ ሙሉነትና በድፍረት ነው::
ሥነ ምግባር ይሉትን የኅብረተሰብ ኬላ እየጣሱ መሳደብና የፈለጉትን ሰው እስከ ማዋረድ መድረስ የተለመደ ክስተት ከሆነ ውሎ አድራል:: መለመዱም እንደ “ጀግነንት” እየተቆጠረ በተመሳሳይ ቢጤዎቻቸው ለአጉራ ዘላዮቹ ድርጊት በአደባባይ ይጨበጨብላቸዋል:: አድናቆቱም በፉጨት ታጅቦ ይዥጎደጎድላቸዋል:: “ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ ገደልኝ” እንዲሉም ስድቡ እንደ ወዳጅ የግብዣ ጥሪ አድራሻቸው፣ አካውንታቸው፣ የፌስ ቡክ ገጻቸው፣ ቲዩተራቸው፣ ኢንስታግራማቸው ወዘተ. እየታሰሰ እንዲደርሳቸው ይደረጋል::
ስለ አጉራ ዘለልነት ካነሳን ዘንድ ጥቂት ማብራሪያ ያስፈልግ ይመስለናል:: ሕጋዊ ፍቺ ሳትፈጽም በቅብጠትም ይሁን በክህደት ከባሏ ቤት ጠፍታ የኮበለለችን ሴት ወይንም ሚስቱን የከዳ ወንድን ባህላችን የሚበይናቸው “አጉራ ዘለል” በማለት ነው:: የፈሊጡ ፍቺ እየሰፋ ሄዶም “አጉራ ዘለልነት”፡- ስድ አደግነት፣ ባለጌነት፣ ጋጥወጥነትና ሥርዓት አልበኝነትን እንዲገልጽ ሆኖ ትርጉሙን አስፍቷል:: ይህን መሰሉ አጉራ ዘለልነት ከማፈሪያነትና አሸማቃቂነት ነፃ ወጥቶ ተግባሩን የሚፈጽሙት ዜጎች ልክ እንደ “ጀግናና ቁምነገር ፈጻሚ ባለውለታዎች” በሆታና “በዕልልታ” እየደመቁ ሲበረታቱ ማስተዋልና ተከታዮች ሲያበዙ መመልከት ከአሳፋሪነቱ ይልቅ እንደ “ክብር” ተቆጥሯል:: ቅዱስ መጽሐፍ “ነውራቸው ክብራቸው” እንደሚለው መሆኑ ነው::
“ላም እሳት ወለደች፤ እንዳትልሰው ፈጃት እንዳትተወው ልጅ ሆነባት” እንዲል አገራዊ ብሂላችን፤ የዘመናችን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያጎናጸፈን የማኅበራዊ ሚዲያው “በረከተ መርገም” ለብዙ አጉራ ዘለሎች የመፈንጫ ነፃ መድረክ እንደሆነ እስኪያቅረንና እስኪያጥወለውለን ድረስ ሳንወድ በግድ ለመጋት ተገደናል::
በመግቢያው ላይ በተጠቀሰው የንጉሡ ዘመን እንደ ከዋክብት ደምቀው ከነበሩት የዚያ ትውልድ አባላት መካከል ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው) በ1959 ዓ.ም ለዚያው የኮሌጅ ቀን በዓል ያቀረበውን አንድ የግጥም ሥራውን በዚህ ቦታ ማስታወስ ግድ ይላል:: ሳይንስና ቴክኖሎጂው የወለዳቸው መልካም ነገሮች ለግፍና ለበቀል ማወራረጃነት ሲውሉ የተመለከተው ገሞራው፤ “በረከተ መርገም” በሚል ርዕስ እንደ ገሞራ እሳት በሚፋጀው ብዕሩ አንድ ዘለግ ያለ ዘመን አይሽሬ ግጥም ጽፎ ነበር:: ይህ ግጥም ስሜቱን የኮረኮረው የዘመናችን ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም “በረከተ መርገም ቁጥር 2” በሚል ርዕስ መሰል ይዘት ያለውን ትዝብቱን በተባ ብዕሩ የገለጠው እንዲህ በማለት ነው::
ኮምፒውተር የሚሏት የደብተራ ሳጥን ከመጣች ጀምሮ፣
በወግ መኖር ቀረ አስማት ሆነ ኑሮ::
ከተፈጥሮ ሸሸ ሰው ከሰው መነነ፣
መኖርና መሞት ክሊክ ማድረግ ሆነ::
ወንበር ላይ ተጥዶ ወንበር ላይ እንዲያረጅ፣
ትውልዴ ላይ አዚም የጣልክበት ፈረንጅ፣
የፌስቡክ ፈብራኪው ጎረምሳው ዲታ ሰው፣
የግፍ ንብረትህን በልተህ ሳትጨርሰው፣
የየካው ሚካኤል ዐይንህን ያፍስሰው::
እቤት ተቀምጬ ባለ ሥልጣን ሳማ፣
ቤቱ ተቀምጦ አጅሬ እንዲሰማ፣
በጅ የማይዳሰስ የሃሜት ሰንሰለት የዘረጋህለት፣
ሞባይል ፈጣሪው የቴሌፎን ጌታ፣
በኖርክበት ዘመን ባለህበት ቦታ፣
አቡነ አረጋዊ ይጣሉህ በቴስታ::
በመምህሩ ይቀጣ እንደ ነበር የቀድሞ ታዳጊ ተማሪ ይህ ዘመን በእንብርክክ እያስኬደንና እየቀጣን “አጉራህ ጠናን” (ተሸነፍን፣ ተረታን አንዲሉ) ብዙ ዜጎች የአጉራ ዘለሎቹን ተግባር በአሜንታ በመቀበል፤ አንድም፡- “ዘመኑ ነው መቼስ ምን ይደረጋል” በሚል ቁጭት እየተብሰለሰሉ፤ ሁለትም፡- እንደ “እብድ ገላጋይ” መልሰው እሳትና ጭድ ጎን ለጎን እያቀባበሉ የአለሌዎችን ስድቦች ሲያራግቡና ሲያቀጣጥሉ መመልከት እፍረትንም ሆነ አሸማቃቂነት ወደ ጎን በመግፋት ነው::
ከፍታና ዝቅታ፣ ሥልጣነ ክህነትና ሥልጣነ ፖለቲካ ሞገሳቸው ተገፎ በስድብ ሲገረፉ መዋል የዕለት ክስተት፣ በየደቂቃው የሚፈጸም “የጀግኖች ድርጊት” ሆኖ ሥር ከሰደደ ሰንብቷል:: ለታላላቆችና ለአንቱዎች የሚሰጠው ክብርም እንዲሁ ታሪክ ሆኖ በነበር ሊዘከር የቀረው አንድ ሐሙስ ብቻ ነው::
በዚህ ዘመን ወለድ የቴክኖሎጂ ዘመን ያበዱትና የሚያሳብዱን በአንድ የዕድሜ ክልል ውስጥ የተጠለሉ ዜጎች ብቻ አይደሉም:: ከሕጻናት እስከ ታዳጊዎች፣ ከወጣት እስከ ባለሽበቶች፣ በመንበረ ሥልጣን ላይ ከተቀመጠ ቁንጮ መሪ እስከ የቤተ እምነት አውራ መሪ፣ ከካህን እስከ መምህር፣ ከአዋቂ እስከ ተደናቂ፣ ከማጀት እስከ ፍርድ አደባባይ በዋልጌዎች ያልተለከፈ፣ ለአጉራ ዘለልነት ገብሮ ከማኅበራዊ ባህሎቻችን ያልተፋታ ዜጋ በወረንጦ እንኳን ቢታሰስ የሚይገኝበት ጊዜ ፈጥኖ እንዳይደርስብን ከፍ ያለ ስጋት ላይ ጥሎናል:: በአጭሩ፡- “የዘመነ ነፃነቱ ባሪያ ሆኖ የዋልጌነት ዛር ያልሰፈረበት” ዜጋ ማግኘት አዳጋች ሆኗል እስከ ማለት እንዳንደፍር ያሰጋል::
ተሳዳቢነት እንደ ጀግንነት፣ ተዋርዶ ማዋረድ እንደ ኒሻን ተሸላሚ አስቆጥሮ በአድናቆት ሲጨበጨብ ከማስተዋል ውጭ ምን ምስክር መጥራት ይቻላል:: ሃይማኖት ተንቆ ርኩሰት የገነነበት፣ ቀኖና ተሽሮ የሕሊና ዐይን የታወረበት ይህ ዘመን ተዋርዶ አዋርዶናል:: እርስ በእርስ መዘነጣጠላችን እንደ ወግ ተቆጥሮ ድጋፍ ይሰበሰብበታል፤ ቅንጥብጣቢ የዩቲዩብና “የሼር” ያልተቀደሰ ሀብት ይጋበስበታል:: በርግጡ ይህ “ሰድቦ ለሰዳቢ” አሳልፎ ለመስጠት ትውልዱን ያጀገነው ዘመን የት ደርሶ ምን ላይ ይጥለን ይሆን? ርዕሰ ጉዳዩን ዳግም ጫን ብለን ለማብላላት እንመለስበታልን:: ሰላም ይሁን::
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 5 /2014