ኤች አር 6600ም ሆነ የኤስ 3199 ረቂቅ ህጎች በምክር ቤት ጸድቀው ተግባራዊ የሚሆኑ ከሆነ የሚኖራቸው ተጽዕኖ ምንድን ነው? ጉዳታቸው ምንያህል ነው? ከእዚህ ለመውጣት ምን መደረግ አለበት? የራሺያና የዩክሬን ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረውን ተፅዕኖ በሚመለከት እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ወቅት ዲፕሎማሲ ላይ መሠራት ያለበት ምንድን ነው?
አቶ እንዳለ፡- ውስጥ ላይ ደካማ ከሆንን ማንም አይሰማንም፡፡ከውስጥ ጠንካራ ከሆንን ውጪም ተደማጭ እንሆናለን። ዲፕሎማሲ የሚጀምረው ከውስጥ ነው። ለእዚህ ደግሞ እኛ ምቹ ነን። አሁን ከውስጥ የተከፋፈልን እንዲመስል ፕሮፖጋንዳ እየተሠራ ነው። በዓለም በየትኛውም አገር አንድ አይነት ባህል ወይም ሕዝብ የለም። በዓለም ያሉ አገራት ውስጥ የተለያዩ ባህሎች አሉ። በየሥራቸው ንዑሳን ባህሎች አሉ። በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ነው። ኦሮሚያ ቢሔዱ የተለያዩ ባህሎች አሉ። ጉራጌ ጋር ሲደርሱም የተለያየ ባህል አለ። ብዝሀነት የትም መኖሩ መታወቅ አለበት። ብዝሃነት ውበት እና ጥንካሬ ነው። ብዝሃነት መለያየት አይደለም።
ህወሓት ብዝሃነትን ልዩነት ብሎ ተርጉሞታል። ትክክል አይደለም። እኛ መለያየት አይመጥነንም። ሕዝቡ አንድነት ሲባል እንዴት እያለቀሰ እንደተቀበለ ታይቷል። መጀመሪያ መንግሥት ለአንድነት ዕውቅና ሰጥቷል። ከዚህ በፊት በነበረው ስህተት በንብረትም በሕይወትም ብዙ አስከፍሎናል በማለት ግልፅ ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱ ሲያልቅ ወደ ጎረቤት አገር መኬዱም የሚታወስ ነው። ወንድሞቻችን እና ቤተሰባችን ከሆኑት ከኤርትራውያን ጋር እጅግ አሳፋሪ ውጊያ አካሂደዋል። ምክንያት የሌለው ውጊያ አካሂደናል። የአሜሪካ መንግሥት ስለፈለገው በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰፊ ልዩነት ኖሮ እንዲቀጥል ያ ጦርነት ተካሒዷል። በዛ ጊዜ የተካሔደው ጦርነት ስለወደብ እና ስለድንበር ጉዳይ አይደለም። የደህንነት ጉዳይ ነው። የእኛ ህልውና ከኤርትራ ጋር የተያያዘ ነው። የእነርሱም ህልውና ከእኛ ጋር የተያያዘ ነው።
እኛ ጋር የሚፈጠረው ችግር ከሁሉም ቀድሞ የሚገባው ኤርትራ ላይ ነው። የእነርሱም እኛ ጋር ነው። ስለዚህ አንዳንዶች እንደውም ከገዛ ወንድሞቻችሁ ጋር ያልተስማማችሁ እንዴት ሌላ አገርን ታስታርቃላችሁ? እንዴት የአፍሪካ መዲና ትሆናላችሁ? ይሉ ነበር። ይህ ሁሉ አልፎ ወደ ጎረቤት አገር መግባት ተቻለ፤ አፍሪካ፣ ኤዢያ እና አውሮፓ ድረስ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በተመሳሳይ ከባቢ ውስጥ ገቡ። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን ለማስፈፀም የተመቸ ፖሊሲ ሆነ። ምክንያቱም ዲፕሎማሲ አገርን የሚወክል ነው። በአመለካከት ላንግባባ እንችላለን። ብዝሃነት አይመርጥም ሁሉንም የሚያገለግል ነው። ዲፕሎማሲ የሚያገለግለው ሁሉንም ነው።
ቀደም ሲል ዲፕሎማቶቹ የተወሰኑት ወጣ ብለው ይስሩ እንጂ ብዙዎቹ ንቁ አልነበሩም። በህወሓት ዘመን አንድ ጥያቄ ያቀረበ ሰው ከመባረር አልፎ ዕድሜ ልኩን እንዲሰቃይ ይደረግ እንደነበር አይዘነጋም። የሚጠይቅ አመራር፣ የሚጠይቅ ምሁርም ሆነ ዲፕሎማት አይፈለግም። ለዲፕሎማሲ ምቹ መሠረት ያስፈልገው ነበር። ለዛም የመከፋፈል መሠረት ተቀይሮ የዜግነት ዲፕሎማሲ መሆን ነበረበት አሁን ያ ሆነ። ይሄ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ለአገራቸው ዲፕሎማቶች እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን ፈጠረ። ይሄ ትልቅ አገር አምስት እና ስድስት በሆኑ ዲፕሎማቶች ወይም በተወሰኑ ኤንባሲዎች ሊሸፈን አይችልም። ይሄ ታይቷል።
ምርጫ፣ የሕዳሴው ግድብ እና የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ ውጪም ውስጥም ያሉ ኢትዮጵያውያን አንድሆነው በዲፕሎማትነት ታይተዋል። ይህ ምዕራባውያንን ያሳስባቸዋል። ስለዚህ ምዕራባውያን ኢትዮጵያውያንን የሚያዳክም የሚከፋፍል ሥራ መሥራት ጀመሩ። በተለይ በግለሰብ ደረጃ እነሰማንታ ሳይቀሩ ከሽብር ቡድኑ ጋር እጅግ የጠበቀ ግንኙነት የነበራቸው የኢትዮጵያ ነፃነት የማይጥማቸው ሁሉ ኢትዮጵያን ማዋረድ እንደሚፈልጉ ታይተዋል። አሁን ደግሞ ወደ ማስፈራራት መጥተዋል። የኢትዮጵያን ስም ወደ ማጥፋት ገብተዋል። እዚህ ውስጥ ሆኖ እንኳ ኤንባሲው ይሠራ የነበረው ታይቷል። በጣም የተሳሳተ ከትልቅ አገር የማይጠበቅ ውሸት ጭምር ሲያስተጋቡ ነበር። ያንን ከማድረግ አልፈው አሁን ፖሊሲ ወደ ማውጣት ገብተዋል፡፡
ኤች አር 6600ም ሆነ ኤስ 3166 ሁለቱም 95 በመቶ ተመሳሳይ ናቸው። በተለያየ መልኩ ጉዳዩ ወደ ታችኛው ምክር ቤትም ሆነ ወደ ላይኛው ምክር ቤት እንዲሔድ አስበዋል። እንደገና አመጣጡ የአንድ ፖሊሲ ሒደትን የጠበቀ አይደለም። አንድ ፖሊሲ ሲወጣ ሰባት ደረጃዎች አሉት። የመጀመሪያው አጀንዳ ሲወጣ ችግሩ ምንድን ነው? በሚል የፍላጎት ዳሰሳ ጥናት ይሠራል። ከዛ ፖሊሲ ለማውጣት የሚመለከታቸው አካላት ይወያያሉ። በእዚህ ላይ ግን የተወያየ አካል የለም። በተጨማሪ በእኛም በኩልም ሆነ በእነርሱ በኩል የተፈጠረ ክፍተትን አያሳይም። አሜሪካ ምን ምን ጥሩ ሥራ ሠራች? አሜሪካ ምን ጉድለት አሳየች? የኢትዮጵያ መንግሥት ምን ጥሩ ነገር ሠራ? በውጭ በኩል ተፅዕኖ ያሳደሩ ምን ጉዳዮች ነበሩ የሚሉት ጉዳዮች በሙሉ አልታዩም። ውይይትም አልተደረገባቸውም።
ህግ እያወጡ ያሉት እና ኢትዮጵያ ላይ ወደ መደፍደፍ የሔዱት ተጠያቂነትን ለመዝለል ነው። በዚህ በኩል ሁለቱም አካሄዳቸው አንድ አይነት ነው። ሂደታቸውን የጠበቁ አይደሉም። እዛው ራሳቸው በተገቢው መልኩ አልተወያዩባቸውም። ሌላው በፖሊሲ ቀረፃ ላይ ግብን ማስቀመጥ የሚባል ነገር አለ። ቅደም ተከተልም ይኖረዋል፡፡መጀመሪያ ይህንን እሠራለሁ፤ ቀጥሎ ይህንን እሠራለሁ ይባላል። ሶስተኛው ባይሠራስ የሚል ሶስተኛ አማራጭ ይቀመጣል። ዕቅድ አንድ ዕቅድ ሁለት ይባላል። ነገር ግን ይህም አልተደረገም። ይህንን ሁሉ ደረጃ ጠብቆ በተወካዮች ምክር ቤት ገብቶ መፅደቅ ነበረበት። ነገር ግን ደረጃውን ሳይጠብቅ ተዘጋጅቶ በላይኛውም ምክር ቤት በታችኛውም ምክር ቤት ፀድቆ ፕሬዚዳንቱ ፈርሞ ህግ እንዲሆን ብቻ ታስቧል። ማንኛውም ፖሊሲ ሲያወጡ እኛን ብቻ የሚጎዳ አይሆንም፤ እነርሱንም ይጎዳል። ስለዚህ ፖሊሲው ራሱ ሒደቱን ያልጠበቀ እና ከሽብር ቡድኑ ጋር ግንኙነት በነበራቸው ሰዎች ከፍተኛ ፍላጎት ኢትዮጵያ ላይ ጉዳት ለማድረስ ታስቦ የተሠራ መሆኑን ማንኛውም አካል ማወቅ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ረቂቅ ህጎች በምክር ቤት ጸድቀው ተግባራዊ የሚሆኑ ከሆነ የሚኖራቸው ተጽዕኖ ምንድነው? ከእዚህ ለመውጣስ ምን መደረግ አለበት?
አቶ እንዳለ፡- ረቂቁ ግልፅ የሆነ ጣልቃ ገብነት ነው። የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚጥስ፣ ታሪክን የሚሰርዝ የአሜሪካንም ሆነ የኢትዮጵያ ጥቅም የሚጎዳ ነው። አልፎ ተርፎ የግለሰቦች ጉዳይ ድረስ የሚገባ ሲሆን፤ ልክ እንደውጫሌው ላይ ላዩን ጥሩ መስሎ ውስጡ ግን በተዘዋዋሪ የቅኝ ግዛት ሃሳብ እና ፍላጎትን የያዘ ነው። ሰላም፣ መረጋጋት እና ደህንነት ቢልም ተግባሩ ተቃራኒ ነው። ኢትዮጵያ የደከመ ኢኮኖሚ ይዛ የደከመ ደህንነት ይዛ ያልተረጋጋች አገር እንድትሆን የሚያደርግ፤ እንደውም ጨርሶ የአዲሱ ቀኝ ግዛት ፖሊሲ ነው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር እንዳትገናኝ ከአፍሪካ ህብረትም ሆነ ከዓለም ባንክ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከማንም ጋር እንዳትገናኝ የሚያደርግ ነው። የማሰደም ፖሊሲ ነው።
በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሊታሰብ የሚገባ አይደለም። ያ ቡድን ወደ መቃብር እየወረደ ነው። በህዝብ ልብ ውስጥ የሞተን ቡድን መመለስ አይቻልም። የትግራይ ህዝብም ቢሆን ተበዳይ ነው። 30 ዓመት ሙሉ በስማቸው ሲዘረፍ ቆይቶ ለአሜሪካ ደላሎች እና ለሎቢስቶች እየከፈሉ ኖረዋል። ለኢትዮጵያ የተሰጠው ዕርዳታ ተመልሶ የሚሔደው ለነዚሁ ሎቢስቶች ነበር። የጊዜው ቅንጡዎች የተወሰነ 2 በመቶ ዱባይ ቢዝናኑበትም ለእኛ ዕዳ እያስቀመጡ የሚልኩት መልሰው ወደ አሜሪካ ነበር።
አሁን ግን እንደዛ ጊዜ አይደለም። በዚህ ምክንያት የአሁኑ የእነርሱ ፖሊሲ የአፍሪካ ህብረትን ቻርተር የጣሰ ነው። በቻርተሩም ሆነ የአፍሪካ ሕብረት ሰብዓዊ መብት ቻርተር ላይ ቀኝ ግዛትን መዋጋት ዋነኛው መሥመር ነው። አሁን አዲሱ ቅኝ ግዛት የሚመጣው በፖሊሲ ነው። ይህንን ህግ አሜሪካ ራሺያ ላይ ወይም ሰሜን ኮሪያ ላይ ብታወጣ ብዙ ላይገርም ይችላል። በወዳጅ አገር በኢትዮጵያ ላይ ይህንን ማሰቧ ራሱ በጣም የሚገርም ነው። ኢትዮጵያውያንን የሚያዋርድ ነው። ቀን ያስቀምጣል። ለ10 ዓመት የሚፈፀም ይሆናል ይላል። ሁለቱም የሚወስኑት በፕሬዚዳንቱ ነው። ዲሞክራቶች ሁልጊዜም የውጪ ፖሊሲያቸው ችግር ያለበት ነው። በክሊንተን ጊዜ እነኢጎዝለቪያ ፈርሰዋል። በደላሎች እና በግለሰቦች የሚመራ ኢትዮጵያን ለማዳከም እና ብሎም ለማፍረስ ታስቦ የተዘጋጀው ይህ ሰነድ ማንም ኢትዮጵያዊ ሊደግፈው አይችልም፡፡
ኢትዮጵያውያን ከዚህ ኢትዮጵያን ከሚያዋርድ ሰነድ ጎን አይቆሙም። በእርግጥ ጥቂቶች ምንም ቢያደርጉ የማይመለሱ ከስልጣናቸው ውጪ ምንም የማያሳስባቸው አሉ። በማኪቬሊ ህግ የሚሔዱ ናቸው። ለስልጣን ሞራላዊም ሆነ ሞራላዊ ባልሆነ መንገድ ምንም ነገር ቢሆን የትኛውንም አድርግ የሚለውን መንገድ በመከተል ላይ ናቸው። ይሄ የማይለወጥ ባህሪ ነው። አንዳንዶች በደንብ የሕጉን ጭብጥ ሳይረዱ የሚናገሩ ይኖራሉ። ሆኖም ይሄ ነገር ቢወሰን ኢትዮጵያውያን የምንሆነው ባሪያ ነው። ነፃነት ሊተመን የማይችል ዋጋ ያለው ነው። ሊገዛ የሚችል አይደለም። ስለዚህ ነፃነታችንን አሳልፈን አንሰጥም።
አዲስ ዘመን፡- የኤች አር 6600ም ሆነ የኤስ 3199 ጉዳት ምንድን ነው?
አቶ እንዳለ፡- ጉዳቱ አንዳንዶች ባለስልጣንን ብቻ ወይም መንግሥትን ብቻ የሚነካ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ባለስልጣን አንድ አገር ቢከለከል ሌላ አገር መሔድ ይችላል። ቢቀርም ችግር የለም። ነገር ግን 99 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ በኢኮኖሚ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎ የሚጎዳ ነው። እዛ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ራሱ ይነካል። ለምን ተንቀሳቀሳችሁ? እንዴት ሄዳችሁ? እያለ ውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ሳይቀር የሚያስጨንቅ ነው። ለቤተሰባቸው ብር መላክን በሚመለከት ራሱ እንዲያጣራ ይታዘዛል። ስልክ ደውሎ ማነጋገርን ይገድባል። የራሳቸውን የአሜሪካንን ህገመንግሥት ይጥሳል። የጄኔቫ ስምምነቶችን ይጥሳል። በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ ጣልቃ ይገባል።
ኢትዮጵያ ደካማ እንድትሆን፤ መከላከያዋ ደካማ እንዲሆን ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ሕብረት እና ከአውሮፓ ሕብረት እንድትነጥል ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው። ኤዢያዎችም ሳይቀሩ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ጋር መሆን ይፈልጋሉ። የረቂቅ ህጎቹ ግብ መንግሥትን መጉዳት ሳይሆን ኢትዮጵያውያንን ማዋረድ ነው። ኢትዮጵያ ከሌሎች ጋር እንዴት መገናኘት እንዳለባት ሁሉ ያስቀምጣል። እንደውም በዝርዝር ላየው ሰው እጅግ አስገራሚ ነው። ኢትዮጵያ እነርሱ ካመጡባት የዘረኝነት መዘዝ ለመውጣት ጥረት እያደረገች ነው። ይህንንም ብዙ አገራት በመረዳት ላይ ናቸው። ለ30 እና ለ40 ዓመታት ወንጀል ሲሰራ የኖረውን ህወሓትን አንድም ቦታ ላይ አይጠቅሰውም። ስለዚህ ይህ ህግ የረቀቀው ኢትዮጵያን አዳክሞ ለግብፅ ለመስጠት ነው። ግብፆቹ እንደፈለጋቸው ያድርጓት፤ የሚል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እነዚህን ረቂቅ ህጎች በመቃወምም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች እያደረጉ ያለው በጎ ተግባር በተለይ ለዲፕማሲያዊ ግንኙነት መጠናከር የሚኖረው አንድምታ ምንድነው? በተቃራኒው ጉዳዩን ሰፊ ቦታ አለመስጠት እና አልፎ አልፎም አንዳንዶች በተቃራኒው ለመደገፍ ዳር ዳር ይላሉ። በዚህ ላይ የእርሶ አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ እንዳለ፡- ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ከድህነት መውጣት እና መልካም አስተዳደር ነው። በፊትም ቢሆን የተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ዋለልኝ የፃፈው ፅሑፍ ምንም ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ፍፁም የሚገናኝ አይደለም። በእኛ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስ ዲፓርትመንት አለ። ፊርማ እንኳን የሌለው አምስት ገፅ ፅሁፍ ነው። ይሄንን ግብፆች አሰናድተው የሰጡት ነው። አሁንም ይህ ህግ እንዲወጣ ለሴናተሮቹ ከፍተኛ ገንዘብ የሠጡት ግብፃውያን ናቸው። ብሩ ግን ሄደ የሚባለው በጁንታው በኩል ነው። ነገር ግን አሁን ለህወሓት ግብፆች ካልሠጧቸው እና ካልደገፏቸው በስተቀር እያለቀላቸው ነው።
ከህዝቡ አንፃር ከተወሰደ ኢትዮጵያውያን ጠንካሮች ነን። ያንን በጠንካራ መንግሥት እየተደገፈ ሲያስተዳድር የነበረን ቡድን መገፍተር ተችሏል። በውጪም ኢትዮጵያውያን በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ሳይቀር እየተቃወሙ ነው። ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊም ዝም ያለው አሜሪካንን ማባበል ስለሰለቸው ነው። ራሺያዎች ስለአሜሪካ ማስረዳት አይፈልጉም። ዩክሬን ላይ የደረሰው ይታወቃል። ሶሪያ እና ሌሎችም በነአሜሪካ ጦስ ፈርሰዋል። መንግሥት መጀመሪያ በፐብሊክ ዲፕሎማሲ በደንብ መንቀሳቀስ አለበት። የሕዳሴን ግድብ ገና ሳናጣጥመው ወደ ችግር ልንገባ ነው። ሰው ይህንን በደንብ ይረዳዋል። ነገር ግን ተራ ማዕቀብ አለመሆኑን ሕዝቡ እንዲረዳ መደረግ አለበት። ይህንን ማሳወቅ ደግሞ የምሁራኑ እና የሚዲያ ኃላፊነት ነው። በእኔ እምነት ኤች አር 6600ም ሆነ ኤስ 3199 በኢትዮጵያ ታሪክ ከውጫሌ ቀጥሎ አሳሳች እና መላው ኢትዮጵያውያንን የሚጎዱ ረቂቅ ህጎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ከአሜሪካም ሆነ ከጥቂት ምዕራባውያን ጋር ያላት ግንኙነት እንዴት ይታያል? ይህንን ግንኙነት ለማጠናከር ምን መደረግ አለበት?
አቶ እንዳለ፡– ምን መደረግ አለበት? ለሚለው የቤት ሥራው መሠራት ያለበት ከቤት ጀምሮ ነው። ኢትዮጵያን የሚያዋርዱ ትንንሽ ቡድኖች ቀይ መሥመር እንዳያልፉ ማገድ ያስፈልጋል። ሕዝቡ ራሱ ህወሓትን እና ሸኔንም ሆነ ሌላውን በቃ ማለት አለበት። ብዙ ሃሳብ ይኖራል። የተለያየ ፓርቲ እና የተለያየ ሃሳብ ፀጋ ነው። ነገር ግን በፓርቲ ስም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መነካት የለበትም። ስለዚህ ህዝቡ አሁን እንደጀመረው ህወሓትን እና ሸኔን እረፉ ማለቱን መቀጠል አለበት።
ወሳኙ ነገር ቤት ውስጥ መሥራት ነው። ከዛ ቀጥሎ ውጪ ያሉት ኢትዮጵያውያን በዕውቀትም በገንዘብም ተንቀሳቅሰው ጁንታው የከፈለው ብር ያቅታቸዋል ተብሎ አይታሰብም። በእውቀትም ቢሆን ብቃት ያላቸው በቂ ኢትዮጵያውያን ውጪ አሉ። አሁን የዜግነት ዴሞክራሲ ነው፤ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፤ ስለዚህ መንቀሳቀስ አለባቸው። ከዛ ቀጥሎ መጀመሪያ ኢትዮጵያ ማስረዳት ያለባት ለአፍሪካ ሕብረት ነው። ለጎረቤቶቻችንም ማስረዳት አለባት። የሕዳሴው ግድብ እየተሠራ ስለመሆኑ ሲወራ ያልታሰበብን ነገር የለም፤ ነገር ግን እኛ አያቅተንም። ሁሉም ይህንን ነገር ቢሰማ ባሕርዳርም ሆነ አርባምንጭ በየአቅጣጫው ሲሠራ የነበረው ብዙ ነበር። ነገር ግን ያ ሁሉ ቢሆንም በኢትዮጵያውያን ጠንካራ ድጋፍ እየተገባደደ ነው። ስለዚህ የነፃነት ተምሳሌት ከሆነችው ከኢትዮጵያ አልፎ ይህ ለአፍሪካውያን የሚተርፍ በመሆኑ ኢትዮጵያን መደገፍ እንዳለባቸው ማሳወቅ አለብን።
እጅግ የተሳሳተ እና ኒዮ ኮሎኒያሊዝም መሆኑን መንገር አለብን። ከዛ ደግሞ አሜሪካን ሊገዳደሩ የሚችሉ ትልልቅ የኢትዮጵያ ወዳጆች አሉ። ከእነርሱ ጋር መሥራት ያስፈልጋል። አሁን የተነደፈው የኢትዮጵያ ፖሊሲ እጅግ ጥሩ ነው። ወደ ቀኝም ወደ ግራም አይልም። አማካኝ ቦታን የያዘ ነው። ታሪኳን የሚመጥን ነው። ሁሉንም ያስተናገደች አገር ነች። የትኛውም ሃይማኖትም ሆነ ሌላ ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ አልተሸማቀቀም፤ አልተዋረደም። ሰላማዊ ነው። ከዛ በኋላ ለአፍሪካ ህብረትም ሆነ ለተባበሩት መንግሥታት በይፋ እንዲህ ዓይነት ወዳጅነታችንን የሚያሻክር ፖሊሲ እየተነደፈ ነው ብለው ኢትዮጵያውያን መሥራት አለባቸው። መንግሥትም ማገዝ አለበት።
ነገር ግን ከውስጥ አሁን አንዳንድ ባለሥልጣናት የሚሠሩት ደስ አይልም። ወደ ፊት ቢወድቁ ጥሩ ነበር። ነገር ግን ወደ ኋላ ሕዝብ ወደማይፈልገው መውደቅ የሚፈልጉ አሉ። እነዚህን ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል። በቃ በሰላም ቤትህ እደር መባል አለባቸው። እነርሱ በሚፈጥሩት ስህተት አገሪቷ ዋጋ መክፈል የለባትም። እዚህ ላይ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። እዚህ ላይ መገናኛ ብዙሃን ቡድን ፈጥረው መሥራት አለባቸው። ጊዜያዊ ኮሚቴ መቋቋም አለበት። አውሮፓ ድረስ ቅርንጫፍን ማቋቋም ያስፈልጋል። ለደቂቃም ሳይዘገዩ መሥራት የግድ ነው። ወደ ልዩነት መሔድ ሳይሆን ብዝሃነታችንን አጣጥመን መቀጠል አለብን።
አሁን ብሔራዊ ውይይት ሊደረግ ነው። ከውይይቱ በኋላ ደግሞ ለውጦች ይኖራሉ። ሕገመንግሥት ይሻሻላል፤ ሌላም ሌላም ይሠራል። ነገር ግን ይህ እንዳይሆን ቀድመው ፈንጂ እየቀበሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ስለራሺያና ዩክሬን ምን ይላሉ? ኢትዮጵያ በእነርሱ ጦርነት የሚፈጠረውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ምን ማድረግ አለባት?
አቶ እንዳለ፡- ተፅዕኖ ብቻ አይደለም በረከትም አለው። አሜሪካኖቹ ከራሺያና ዩክሬን ጦርነት በፊት አፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዝግጅት ሲያደርጉ ነበር። ብዙ አቅደው እንደነበር የሚታወቅ ነው። ህጉ ራሱ ከሶስት ወር በፊት ሊፈፅሙት ያሰቡት ነው። እዚህ ላይ ሌላውን ምን ያህል ለመጉዳት እንደሚንቀሳቀሱ ታይቷል። አሁን ግን ዓለም በምዕራቡ ብቻ የሚመራ አይደለም። ምዕራቡ አንድ ባለድርሻ ነው። ስለዚህ ድሮ እየመሩት በነበረ ሰዓት ከተጎዱ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች። ብዙ ዋጋ ከፍላለች። ከወንድሞቿ ጋር ተጣልታ የሰው ሕይወት ገብራለች። ግብፅ የበላይ እንድትሆን የማያደርጉት ጥረት የለም። ስለዚህ አሁን የዩክሬን እና የራሺያ ግጭት ኢኮኖሚካሊ በአሜሪካም ጭምር ተፅዕኖ አለው። እንደሚታየው ራሺያ ወደ ጦርነቱ የገባችው አስባበት አጥንታ እና ተዘጋጅታ ነው። ዩክሬን አልተዘጋጀችም የአሜሪካንን ትዕዛዝ ጠበቀች፤ አሁን አመድ እየሆነች ነው። አሜሪካኖቹ የሚፈልጉት ይህንን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከራሺያ ጋር ያላት ግንኙነት ታሪካዊ ነው። ራሺያዎች እንደአሜሪካን አይደሉም። ራሺያዎች በኢትዮጵያውያን ላይ ችግር በተፈጠረ ቁጥር አብረውን ናቸው። ይህንን በሚመለከት ከጣሊያን ጀምሮ ያለውን የጦርነት ታሪክ በማጣራት መረጋገጥ ይቻላል። ተራ ምሳሌ ቢጠቀስ ባልቻ ሆስፒታልን መውሰድ ይቻላል። አሜሪካ አንድ ሆስፒታል እንኳ አልሠራችም። በእርግጥ ራሺያ ስትወጠር የሚጎድልብን ነገር ይኖራል። የዓለም ባላንስ ወደ ራሺያ እየሔደ ነው ይህ ዕድል ነው። አሜሪካኖቹን የሚያዋጣቸው ከአገራት ጋር አብሮ መሥራት ብቻ ነው።
አዳዲስ ተዋናዮች ሲመጡ፤ እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት ያስፈልጋል። ቱርክ ከድሮ ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጎን ናት። ከፋሲለደስ ጀምሮ ታሪክ ማገላበጥ ይቻላል። ፋሲለደስ አውሮፓዎችን ትቶ የሚሠራው ከቱርክ ጋር ብቻ ነበር። ስለዚህ ምዕራቡ ዓለም ይመራበት የነበረው አቅሙ በመቀነሱ ተጠቃሚ ነን። በተረፈ እኛ ማንም እንዲጎዳ አንፈልግም። ፖሊሲያችንም ይህንን አይልም። መስተጋብሩ በረከትም ያመጣል። አሁን ዝናብ እየመጣ ነው፤ ዝግጅትም እየተደረገ ነው። አሁን ኢትዮጵያውያን እንደነግብፅ አይደለንም። በዓለም ላይ የነዳጁም ሌላውም ብዙ ችግሮች አሉ። በተረፈ ለዓለም መረጋጋት እና ለዓለም ዴሞክራሲ እንዲህ ዓይነቱ ለውጥ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከሳውዲአረብያ ብዙ ኢትዮጵያውያን እንዲመለሱ ጫና እየተፈጠረ ነው። ወደ አገር በመግባት ላይ ናቸው፡፡ይሄ የግብፅ አሻጥር ያለበት ይመስላል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ እንዳለ፡– ይሄ መንግሥት ለዜጎች ምን ያህል ትኩረት እንደሰጠ የሚያሳይ ሲሆን፤ ሳኡዲ ይህንን ያደረገችው ለግብፅ ይሁንታ ብላ መሆኑ ግልፅ ነው። ኢትዮጵያ እና ሳኡዲ የፍላጎት ግጭት የለባቸውም ። እንደውም ኢትዮጵያ በቁርዓን አደራ የተሰጣች ነች። ሳኡዲዎች ገና አሁን በዩክሬን ምክንያት መንቃት የጀመሩ ይመስላሉ። ስንት አረብ አገራት በአሜሪካ ምክንያት ፈርሰዋል። አረብ አገር ቆሞ እንዳይሔድ ተደርጓል። በጣም የሃብት አገር የንግድ አገር ነበሩ። ብዙ ስልጣኔ መነሻው ከዛ ነው።
ነገር ግን ምዕራቦች የእነርሱ ጊዜያዊ የማይጠቅም ሥልጣኔ እንዲታወቅ አስበው የሚያደርጉት ነው። ሰዎች ከስደት መመለሳቸው በኢኮኖሚው ላይ ጊዜያዊ ጫና ቢፈጥርም ጥቅምም አለው። ቻይና ሕዝቧ ብዙ መሆኑ በእጅጉ ጠቅሟታል። ዜጎቻችን ደግሞ እዛ ከሚሰቃዩብን ያለንን ቆሎም ቢሆን ብንካፈል ይሻለናል። አሁን በቅርቡ 100ሺህ ይመጣሉ ተብሏል። ቀላል አይደለም፤ በቤተዕምነትም ሆነ በሌላ መንገድ ሕዝቡ ድጋፍ ማድረግ አለበት። መጠንቀቅ ያለብን ይህን ያደረገው የሳኡዲ ሕዝብ አይደለም። የተወሰኑ የመንግሥታቸው ሰዎች ናቸው።
በተረፈ ግብፅ የተቋቋመችው የአረብ አገራትን ለማዳከም ነው። ግብፆች ከፍተኛ የመከፋፈል አቅም አላቸው። አሜሪካ ከእስራኤል ቀጥሎ ከፍተኛ ገንዘብ የምትረዳው ለግብፅ ነው። ይህም የአረብ አገራትን ለመከፋፈል ነው። የመን፣ ሊቢያ እንደዛ እየወደመ ዝም ብለዋል። በእርግጥ የራሳቸውን የሃይማኖት ህግ እየጣሱ መሆኑን ማሳወቅ ያስፈልጋል። በእርግጥ አሁን ዩክሬንን በተመለከተ ተለያይተዋል። ግብፅ ወደ አሜሪካ ሲያደላ ሳኡዲ ወደ ራሺያ እና ቻይና አድልታለች። እኛ ይሄንን ቀዳዳዎች መጠቀም አለብን። እርግጥ የአሜሪካንን ሰባት ሰዎች ስላባረርን እንዴት እንዳበዱ እናውቃለን ለዜጎቻችን ክብር አለመሰጠቱ ቢያበሳጨንም እኛም ከመቀበል ወደ ኋላ አንልም።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበርን ቆይታ እጅግ አመሰግናለሁ።
አቶ እንዳለ፡- እኔም እጅግ በጣም አመሰግናለሁ።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 3/2014