በኢትዮጵያ ለቱሪስት መስህብነት የሚሆኑ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊ ስፍራዎች በእጅጉ በርካታ ናቸው። የሰው ዘር መገኛ ምድር ከመሆኗ አንፃር በእጅጉ ሲበዛ አስደናቂ ሃብቶች ባለቤት መሆኗ ያን ያህል አስገራሚ አይሆንም። ይሁን እንጂ ዓለማችን ላይ በጎብኚዎች መዳረሻነት ከሚታወቁት አገራት ተርታ ግን ለመሰለፍ አልቻለችም። በባህላዊ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ እሴቶቿ በብዙ እጥፍ የምታስከነዳቸው አገራት ሃብቶቻቸውን የመጠበቅ፣ የማስተዋወቅና ምቹ መሰረተ ልማት በመገንባት የመንከባከብ ተግባር በመስራታቸው ብቻ ቱሪዝም የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽና የጀርባ አጥንት እንዲሆን አስችለውታል።
“በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል” ይሉት አባባል ለዘመናት ሰቅዞ የያዛት አገር የቱሪዝም ዘርፉን እሴቶች ከመረዳትና ከዚያም ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ ማንቀላፋትና ዳዴ ማለትን ምርጫዋ አድርጋ ቆይታለች። ጥረት ተደርጎ ይቅርና እንዲያው በደብዛዛውም ቢሆን ከተለያዩ ዓለም ክፍል በአገሪቱ የሚገኙ ድንቅ ድንቅ የቱሪዝም ሃብቶችን ከመጎብኘትና ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በመደነቅ ምስክርነታቸውን ከመስጠት አልቦዘኑም። ይህ ነው የሚባል የአገር ውስጥ ጎብኚ ባይኖርም ቅሉ በአገራቸው ሃብት ኮርተው ዙሪያ ገባውን በመቃኘት ዓለም ትኩረት እንዲሰጠው የሚሞግቱም አልጠፉም።
ዛሬስ? በዚህ ወቅት ቱሪዝምና መዳረሻ ስፍራዎች በማልማት፣ በማስተዋወቅ ጎብኚዎችን በመሳብ እንዲሁም አዳዲስ መዳረሻዎችን በመፍጠር ከሃያላኑ ተርታ የሚያሰልፍ ጠንካራ ኢኮኖሚና እጅግ ተወዳጅ አገርን መፍጠር እንደሚቻል ሁሉም ያምናል። ለዚህም ነው ከከፍታው ማማ ላይ በክብር ለመቀመጥ የቱሪዝም ዘርፉን ከዋና ዋና ምሰሶዎች ዘርፍ የሚያስቀምጡት።
የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ ቱሪዝም ከአምስቱ ዋና ዋና ዘርፎች መካከል ቀዳሚው መሆኑን በመግለፅ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሆነ ይፋ አድርጓል። በተለይ የመስህብ ስፍራ የሆኑት መዳረሻዎችን በማልማት፣ አዳዲስ ስፍራዎችን በመፍጠር፣ ታሪካዊ ቅርሶችን፣ ተፈጥሯዊ ሃብቶችን በመጠበቅና ለጎብኚዎች ክፍት የማድረግ ስራዎች መከናወናቸውን አሳውቋል። በተለይ “ገበታ ለአገር” በሚል ሃሳብ የአዲስ አበባ ተፈጥሯዊ ቦታዎችን በማልማት፣ በተወዳጅ መልከአ ምድር ባላቸው “የኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ” አካባቢዎች ላይ ታላላቅ ግንባታዎችን ለማድረግ እቅድ ነድፎ ወደ ትግበራ መግባቱን መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ጥረት ለዘርፉ መነቃቃትን የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያን በተጨማሪ ሌላ ገፅታ ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ በዘርፉ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የባህልና ቱሪዝም አምድ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት “በገበታ ለአገር” ፕሮጀክት ስር ከያዛቸው ሜጋ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን “የወንጪ ደንዲ ሃይቅ” የመዳረሻ ልማት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ይመለከታል። የዚህ ፅሁፍ አዘጋጅም ከሳምንት በፊት በስፍራው ተገኝቶ የተመለከተውንና ፕሮጀክቱን የሚመሩትን አካላትና አመራሮች አነጋግሮ ያገኘውን ምላሽ እንደሚከተለው ያቀርበዋል።
ገበታ ለአገር #ወንጪ ደንዲ$
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በገበታ ለአገር በመጀመሪያው ዙር ካስቀመጧቸው ፕሮጀክቶች ወንጪ ሐይቅ አንዱ ነው፡፡ ጎብኚዎች ወደ ሥፍራው ቢያቀኑም፣ ያለውን የተፈጥሮ መስህብ ያህል ጥቅም ያልሰጠው ወንጪ ሐይቅ በተፈጥሯዊ መስህብ ተወዳጅ ከሆኑት ስፍራዎች መካከል ነው፡፡
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በወንጪ ወረዳ የሚገኘው ወንጪ ሐይቅ፣ ከአዲስ አበባ በምዕራብ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በወሊሶና አምቦ መሀል ይገኛል። የዝግጅት ክፍላችን ዘጋቢ በስፍራው ተገኝቶ እንደተመለከተው በመጀመሪያው ምእራፍ የወንጪ ደንዲ ሃይቅ መዳረሻን የማልማት ሥራ የመንገድ ጠረጋ፣ የሎጅ ግንባታና የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው “በገበታ ለአገር” የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ ወቅት ስለ ወንጪ ደንዲ ኢኮ ሎጅ በተናገሩበት ወቅት እንደሌሎቹ ፕሮጀክቶች በታቀደለት ጊዜ ለማከናወን በስፍራው የሚንቀሳቀሱት የሸኔ የሽብር ቡድን አባላት እንቅፋት መሆናቸውን ገልጸዋል። ይህን እንቅፋት ለመፍታትና አካባቢውን ለማልማት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እንደነበር አሳውቀው ነበር። ይህን ማብራሪያ ከሰጡ በኋላም በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላት፣ አመራሮችና የፕሮጀክቱ አስፈፃሚዎች “የተቀናጀ ሥራ በመሥራት የመዳረሻ ስፍራውን የማልማት እንቅስቃሴ ቀጥሏል” በማለት በስፍራው ተገኝቶ ሁኔታውን ለቃኘው የዝግጅት ክፍሉ ዘጋቢ አስረድተዋል። ለመሆኑ ይህ እስኪጠናቀቅ በጉጉት የሚጠበቀው ሜጋ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ለጥያቄ የዞኑ አመራሮች፤ የፕሮጀክቱ አስፈፃሚዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ይህን ይላሉ።
“የወንጪ ደንዲ ኢኮ ሎጅ የመንገድ ሥራ እየተፋጠነ ነው” የሚሉት ፕሮጀክቱ የደረሰበትን ሁኔታ ለመመልከት የልኡክ ቡድናቸውን አስከትለው በስፍራው የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ የገጠር ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ድሪሳ ዋቁማ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ የግንባታ ሂደቱ ከዚህ ቀደም በካሳ ክፍያና ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ምክንያቶች ተጓትቶ እንደነበር ይናገራሉ። አሁን ግን ችግሮቹ ተለይተው አቅጣጫ ከተሰጠ ወዲህ በታቀደለት መሰረት በአፋጣኝ ሁኔታ ግንባታዎቹ እየተከናወኑ መሆኑን መመልከታቸውን አስረድተውናል። በተለይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶቹን በርካታ ማሽነሪዎችን በማሰማራትና ማሻሻያ በማድረግ የክረምት ወቅት ከመግባቱ በፊት አብዛኛውን ክፍል እንዲጠናቀቅ ቋሚ ኮሚቴው አቅጣጫ መስጠቱን ገልጸዋል።
“ከአሁን ወዲህ የካሳ ክፍያና የፀጥታ ችግር ምክንያት ሊሆን አይችሉም” የሚሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ የማይሆን ከሆነ የኮንትራክተሮቹ ችግርና ፕሮጀክቱን የሚያስፈፅሙት አካላት የክትትል ችግር እንደሚሆን ይናገራሉ።
የፕሮጀክቱ ምንን ያካትታል
የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም ፕሮጀክት የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ብርሃኑ ተስፋዬ እንደሚገልፁት፤ የወንጪ ደንዲ ኢኮ ሎጅ ሶስት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት። አንደኛው በወንጪ ሃይቁ አካባቢ የሚሰራ፣ ሁለተኛው በደንዲ ሃይቅ አካባቢ እንዲሁም በወንጪና ደንዲ መካከል የሚሰራ ሁሉን አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራ ነው ።
“ከአንድ አመት በፊት ዲዛይን ቀረፃ ላይ ትኩረት አድርገን ስንሰራ ቆይተናል” የሚሉት የፕሮጀክት ማናጀሩ፤ ኤም ኤች ኢንጂነሪንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር እንደሰራው ይገልፃሉ። አሁን ላይ በወንጪ አካባቢ የሚሰሩ ሎጆች፣ የመንገድ ዲዛይንና የተራራ መውጫ ስፍራዎች ዲዛይኖች መጠናቀቁን ይገልፃሉ። በደንዲና በሁለቱ ሃይቆች መካከል በሚገኘው ስፍራ የሚሰራው የቱሪዝም መዳረሻ የሆቴል፣ ሎጅ እንዲሁም መሰል የመስህብ ስፍራ ዲዛይኖችም በዚሁ ካምፓኒ አማካኝነት መጠናቀቁን ይገልፃሉ። ከእነዚህ ውስጥ በረጅም ጊዜ የሚለሙ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በማንሳትም አሁን ላይ በቅርብ ጊዜ ተሰርተው እንዲጠናቀቁ እቅድ የተያዘላቸውን ክፍሎች እንደሚከተለው ያስረዳሉ።
“ከወንጪ ሃይቅ ጋር በተገናኘ መንገዶችና በአካባቢው 18 ሎጆች ለመስራት ታስቦ በሂደት ላይ ነው” የሚሉት የፕሮጀክቱ ማናጀር፤ የሃይኪንግ (ተራራ መውጣት)፣ ፍልውሃ፣ የሚኒራል ውሃ እንዲሁም ፏፏቴን የሚያለሙ ክፍሎችን መያዙን ይናገራሉ። በወንጪ ሃይቅ ላይ በአሁኑ ሰዓት የመንገድ፣ የሎጅ እንዲሁም የመብራት ሥራ ግንባታዎች መጀመራቸውን በመግለፅ፤ የመንገድ ግንባታውን በሁለት ተቋራጭ እየተሰራ ሲሆን የመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝና የቻይና ኮንስትራክሽን ኮምኒኬሽን ካምፓኒ መሆናቸውን ይናገራሉ። የግንባታ ሂደቱ ከካሳ ክፍያና ከጸጥታ ችግር ጋር የተወሰነ መጓተት ቢታይበትም አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ግንባታውን በማፋጠን እስከሚቀጥለው ክረምት ዋና ዋና ሥራውን ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ያነሳሉ።
“የመንገድ ሥራው የቱሪስት መዳረሻ ልማት አካል ከመሆኑ አንጻር የአካባቢውን ተፈጥሮ በተስማማ መንገድ በጥንቃቄ እየተከናወነ ነው” የሚሉት አቶ ብርሃኑ የአስፋልት፡ የፓርኪንግና የመሮጫ ትራክን ጭምር አካትቶ ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑን ያነሳሉ። በአንዳንዱ አካባቢ ከ18 በመቶ እስከ 42 በመቶ የመንገድ ግንባታ ሂደት ላይ መሆኑን አንስተው ከሃሮ ከተማ እስከ ወንጪ ሃይቅ ያለውን ክፍል በአገር በቀሉ የመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኢንተርፕራይዝ እየተከናወነ መሆኑን ያነሳሉ። በዚህም የቆረጣና አፈር ሙሊት ሥራው እስከ 70 በመቶ ድረስ እንደተጠናቀቀ ገልፀው ዋናውን የሚይዘው የማጠቃለያ ስራው በመሆኑ በጥቅሉ 18 በመቶ እንደያዘ ይናገራሉ። እስከ መጪው ክረምትም መንገዱን ክፍት ለማድረግ እየተሰራ ነው። ሁለተኛውን የመንገድ ሥራ የያዘው የቻይና ኮንስትራክሽንም ከሃሮ ወንጪ ተራራውን ዞሮ ፤ ከወንጪ ወደ ደንዲ እንዲሁም የማራቶን ትራክን ጨምሮ ሶስት መንገዶችን የሚሰራ ሲሆን ሂደቱም 42 በመቶ መድረሱን ይናገራሉ።
የወንጪ ደንዲ ኢኮ ሎጅ በስፔን ማድሪድ ተካሂዶ በነበረው በ24ኛው የዓለም የቱሪዝም ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የ2021 ምርጥ የቱሪዝም መንደር ሆኖ መመረጡ ይታወሳል። በሶስት ምዕራፎች ተከፍሎ እንደሚሰራ የተነገረው ፕሮጀክቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ በአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረ ሲሆን ግንባታው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶ ተጓትቶ ነበር።
የማህበረሰቡ ተሳትፎ ለምን ያስፈልጋል?
አቶ ታዬ ጉዲሳ የደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት የወንጪ ደንዲ ኢኮ ቱሪዝም እንደ አገር እየተሰሩ ካሉ ትልልቅ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል አንዱ ነው። የአካባቢው ነዋሪ የነበረው ጥያቄ የተመለሰው በዚህ ፕሮጀክት መሆኑን በማንሳትም በዚህ መልኩ ስራው መጀመሩ ለአካባቢው ሕዝብና ለኢትዮጵያ ሳይሆን ለዓለም የቱሪዝም መስህብ ስፍራ ተጨማሪ ሃብት እንደሆነ ይገልፃሉ።
“በአካባቢው ያለው ህብረተሰብ ከፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ነው” የሚሉት የዞኑ አስተዳደር፤ ይህንን ህብረተሰቡ ተረድቶ እንቅፋት እንዳይፈጠርና የሰላም እጦት እንዳይኖር ሌት ተቀን መጠበቅ እንዳለበት ነው የሚገልፁት። እስካሁንም አንፃራዊ ሰላም የተገኘው በመንግሥት የፀጥታ ሃይል ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ እራሱ የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እየሰራ በመሆኑ ነው። ይሄ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ከዓለም የቱሪዝም መንደሮች መካከል ምርጡ መዳረሻ ተብሎ እውቅና ያገኘው ስፍራ አሁን ካለው በተሻለ የጎብኚዎች መዳረሻ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል። የፌደራል መንግስትም አሁን ካለው በተሻለ መልኩ የአካባቢው ፀጥታ እንዲጠበቅ ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት በማሳሰብ ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።
እንደ ትዝብት
የዝግጅት ክፍላችን ዘጋቢ በስፍራው ሲገኝ ከፍተኛ የፀጥታ ጥበቃ በክልሉ ሃይሎች ሲደረግ ተመልክቷል። ይህ ሊሆን የቻለው በስፍራው ሰርገው የሚገቡ የሸኔ ሽብር ቡድን አባላት እንዳሉና ጥቃት እንደሚፈፅሙ ስለሚታሰብ ነው። እንደሚታወቀው ቱሪዝም ምንም አይነት “ኮሽታ” የማይፈልግና ፍፁማዊ ሰላምን የ ሚፈልግ ነው። በመሆኑም የቱሪዝም መዳረሻ ልማቱን በውቡ መስህብ ወንጪ ላይ መስራትና መመረቅ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን ማስፈን ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን ከፍተኛ የአገር ሃብት ወጥቶበት አልቆ በሰላም እጦት ምክንያት ጎብኚዎች እንዳሻቸው ገብተው የማይወጡ ከሆነ ከንቱ ልፋት ይሆናል። በመሆኑም ማህበረሰቡን በማወያየት፣ ከፍተኛ የፀጥታ ሥራ በመስራትና ጎብኚዎች ስጋት እንደማይገባቸው ማረጋገጫ በመስጠት የታሰበውን ታላቅ አገራዊ አላማ ማሳካት ይገባል እንላለን።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ ሚያዝያ 2 ቀን 2014 ዓ.ም